አሰገደች መኩሪያ የአንድ ልጅ እናት ናት፡፡ የ10 ዓመቱ ወንድ ልጇ እንደ እኩዮቹ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፤ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት መሄድ አይቻለውም። የአእምሮ እድገት ውስንነት አለበት፡፡ እናቱ በሄደችበት ቦታ ሁሉ እርሱን አዝላ የመሄድ ግዴታ አለባት፡፡ ብቸኛዋ እናት እዚህ ቦታ አስቀም ሥራ ልሥራ (በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ልሳተፍ) እንዳትል ልጇን የምትሰጠው፣ የእኔ የምትለው የቅርብ ሰው የላትም፡፡ ኑሮዋን ለመግፋት ደጋፊ አካል አስፈልጓታል፡፡ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ቀለብ ሰፍረውላት ነው ኑሮዋን የምትመራው።
አሰገደች ወጣት እንደመሆኗ ሠርታ ራሷን መቻል ትፈልጋለች፡፡ ልጇም ትምህርት ቤት ቢገባ ደስ ይላታል። ይህን ፍላጎቷን የሚያውቅ አንድ ሰው ልጇን ወደ ትምህርት ቤት እንድታስገባው ይጠቁማታል፡፡ እርሷም ሂደቱን ጀመረችው፡፡ እንዳሰበችው ግን ቀላል አልነበረም። ከሆስፒታል ወደ ወረዳ፤ ከወረዳ ልጇን ወደሚቀበላት ትምህርት ቤት ፍለጋ ብዙ ምልልሶችን አድርጋለች፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ልጇ ትምህርት እንዲጀምር ተደረገ። ዛሬ በትንሹም ቢሆን እፎይ ብላለች፡፡ ልጇ ላይ ጥሩ የሚባል ለውጥ እያየችበት ነው፡፡ እርሷም ልጇ ትምህርት ቤት በሚውልበት ሰዓት ሰፌድ፣ መሶብ፤ እንዲሁም የጉልበት ሥራዎችን እየሠራች ኑሮዋን ለማቅናት ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች፡፡
እንደ አሰገደች ልዩ ፍላጎት ያሏቸው ወላጆች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ብዙ መሰናክሎች ያጋጥማቸዋል። ከስነ ልቦና ተፅዕኖ ባሻገር በኢኮኖሚዊ እና በማህበራዊ ሕይወታቸው እጅጉን እንደሚፈተኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች በአካላዊ፣ የነርቭ፣ አዕምሯዊ ወይም የስሜት ህዋሳት ጉዳቶች (ውስንነት) እና በተለያዩ ተጽዕኖዎች የተነሳ ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በእኩል ደረጃ እንዳይሳተፉ ያስገድዳቸዋል፡፡ በትምህርት አሰጣጡ ውስጥም ጉዳታቸውን ያገናዘበ የትምህርት አሰጣጥ መተግበር እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡
እኛም የትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች ምን ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠይቀናል፡፡
ወይዘሮ መሠረት በቀለ በትምህርት ሚኒስቴር የአርብቶ አደርና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ወይም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፏቸው ሲታይ ‹‹በጣም ዝቅተኛ›› የሚባል ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት የመምጣታቸውም ነገር አናሳ ነው፡፡
ለዚህም ሁለት ምክንያቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ‹‹አካል ጉዳተኛ (ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያለው) ተማሪ ምንም ሊያመጣ ወይም ሊለውጥ አይችልም›› የሚል አስተሳሰብ በብዙ ወላጆች ዘንድ በመኖሩ ወደ ትምህርት ቤት የመላክ ፍላጎት አለመኖሩ ይጠቀሳል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የማህበረሰቡን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡ ተማሪዎች፤ ትምህርት ቤቶች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ሳይቻላቸው ሲቀር ሌሎች ተማሪዎች የሚያገኙት የትምህርት ዕድል እንዳያገኙ ያስገድዳቸዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና የተሻለ የትምህርት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር እንደ አንድ መንገድ ያየዘው የአካቶ ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ማቋቋም እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ መሠረት፤ የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኛው ምቹ እንዲሆኑ ይደረጋል ይላሉ።
ከስድስት ዓመታት በፊት ትምህርት ቤቶች ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች ከአንድ እስከ አራት በመቶ የሚሆን ተጨማሪ በጀት ይመድቡ ነበር፡፡ የበጀት አጠቃቀሙ የተለያየ መሆን ብዙ ለውጥ እንዲታይ አላደረገም። በአሁኑ ወቅት ግን የተለያየ በጀት ከመመደብ ይልቅ የአካቶ ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከላት በማቋቋም ልዩ ፍላጎት ላላቸው እና አካል ጉዳተኛውን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራበት ይገኛል፡፡
በዘርፉ የሰለጠኑ መምህራንም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲቀጠሩ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥርዓቱን በማስቀጠል ላይ ሲሆኑ፤ በተጨማሪም የትምህርት ቤት ምቹነትን ከመፍጠር አኳያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ከዓለም ባንክ በተገኘው በጀት ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተቋቋሙ ያሉት የአካቶ ትምህርት የድጋፍ መስጫ ማዕከላት አንዱ መሆናቸውን ኃላፊዋ ያነሳሉ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከባንኩ ባገኘው ድጋፍ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማቋቋም ላይ ሲሆን፤ እስከ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ 1ሺህ 353 የሚሆኑ የድጋፍ መስጫ ማዕከላት ለማቋቋም ተችሏል፡፡ እነዚህ ማዕከላት አገልግሎታቸው በዙሪያቸው ለሚገኙ አጋር (satellite) ትምህርት ቤቶች ጭምር እንደሆነ በማንሳት፤ ይህም ማለት የድጋፍ መስጫ ማዕከላት ቢያንስ በዙሪያቸው ላሉ አምስት አጋር ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡
የድጋፍ መስጫ ማዕከላቱ ላይ ያሉትን መሻሻሎች ለማየት በየጊዜው ክትትል እና ድጋፍ ይደረግባቸዋል። እንዲሁም በየጊዜው ከክልሎች ጋር የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት ሥራዎች እንደሚሠሩ የሚገልጹት የአርብቶ አደሮች እና የልዩ ፍላጎት ዴስክ ኃላፊዋ፤ በዚህም መሠረት መሥራት የሚጠበቅባቸውን የድጋፍ ማዕከላት መሥፈርቱን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል፡፡ ዕቅዶችም የት ደረሱ? በማለት ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያነሳሉ፡፡
እንደ ዴስክ ኃላፊዋ ማብራሪያ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ባላቸው ልጆች ላይ በማህበረሰቡ እና በሌሎች በኩል የሚታይ የአመለካከት ችግር አለ፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ትምህርትን ለሁሉም ዜጋ መስጠት ግዴታው አለበት፡፡ ችግሩ በትምህርት ማህበረሰቡ ልጆች ተቀብሎ ላለማስተማር፣ በወላጅም በኩል ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያለውን ልጁን ደብቆ የማስቀመጥ ነገር በስፋት መታየቱ ነው፡፡
በመሆኑም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ማህበረሰቡን ለማንቃት የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ችግሩ ሙሉ በሙሉ አያጋጥምም፤ ሁሉም ሰው ለአካል ጉዳተኞች ጥሩ አመለካከት አለው ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም የሚሉት የዴስክ ኃላፊዋ፤ የግንዛቤ ችግሩ እዚህም እዛም ያለ እንደሆነም ይታወቃልና ሁሉም በጋራ መሥራት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም