ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ47 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፡- ከውጭ ሀገር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ47 ሚሊዮን 514ሺ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሽያጭና ገቢዎች አስተዳደር ኃላፊ ሚኒሊክ ጌታሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት የኤሌክትሪክ ሽያጭን ያከናውናል።

በግማሽ አመቱም ከውጭ የኤሌክትሪክ ሽያጭ 66 ሚሊዮን 274 ሺ 260 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 47 ሚሊዮን 514 ሺ 16 ዶላር ለማግኘት መቻሉንና ይህም አፈጻጸሙ 72 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ አፈጻጸም ተቋሙ ባቀደው ልክ ላለመሳካቱ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ኃይል ከሚላክላት ሀገር አንዷ የሆነችው ሱዳን ባለባት የጸጥታ ችግር ሳቢያ የተላለፈላትን ኃይል ክፍያ በአግባቡና በወቅቱ እየከፈለች አለመሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በመንግሥት ደረጃ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ የሚቀርብላቸው የኃይል መጠን 50 በመቶ እንዲቀነስ የተደረገ ቢሆንም ኢትዮጵያ የምታገኘውም ገቢ እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

አቶ ሚኒሊክ በዘንድሮው በጀት አመት ለሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንም ዓይነት ገቢ አለመሰብሰቡና በጥቅሉም የ 70 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንዳለባት ገልጸዋል።

ጅቡቲንና ኬንያን በሚመለከትም ይወስዳሉ ተብሎ ከታሰበው የኃይል መጠን ፍላጎታቸው የቀነሰ ሲሆን ይህም በተወሰነ ተጽእኖ ማሳደሩና የግማሽ አመቱ ክንውን ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

ኃላፊው እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም የውጭ የኃይል አቅርቦት ላይ ከአምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲወዳደር 15 በመቶ ከፍ ማለቱን አብራርተዋል።

ተቋሙ ከውጭና ከሀገር ውስጥ ከኤሌክትሪክ ሽያጭ 13 ቢሊዮን 433 ሚሊዮን 246 ሺ 943 ብር ለማግኘት አቅዶ የነበረ ሲሆን ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭም 10 ቢሊዮን 234 ሚሊዮን 869 ሺ 88 ብር ማግኘቱንና በጥቅሉም 12 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ለሽያጭ የሚቀርበው የኃይል መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲወዳደር 16 በመቶ ያህል ጭማሪ ያለው ሲሆን ገቢውን በሚመለከት 19 ነጥብ 6 በመቶ ያህል ጭማሪ አለው ብለዋል።

አቶ ሚኒሊክ በዘንድሮው ግማሽ አመት 8 ሚሊዮን 505 ሺ 725 ነጥብ 416 ሜጋዋት ኃይል መጠን ለመሸጥ ታቅዶ 8 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ኃይል መጠን መሸጥ መቻሉን አብራርተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You