የባሕር በር ስምምነቱ – ለጋራ ተጠቃሚነት

ከወራት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን ስለ ቀይ ባሕርም ሆነ የባሕር በር ጉዳይ ላይ ዝምታን ከመምረጥ ይልቅ መወያየቱ እና እርስ በእርስ መነጋገሩ አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸው ይታወቃል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ይህን ያሉትም ለፓርላማ አባላት ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ መወያየት የሚፈራበት ዘመን ማብቃት እንዳለበት አክለው መግለጻቸው ይታወሳል:: በተለይም ለአባላቱ በሰጡት ማብራሪያቸው ላይ አያይዘው እንደገለጹት ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ የመኖር አሊያም የአለመኖር ጉዳይ እንደሆነም ጭምር ነው::

ስለ ባሕር በር ጉዳይ በንግግር ደረጃ እንኳ በኢትዮጵያ መንግሥት መነሳቱ ያስበረገጋቸው አካላትም ሆኑ ሀገራት፤ አፍታም ሳይቆዩ በወቅቱ መያዣ መጨበጫው የጠፋው አይነት ሐሳብ ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል:: በተለይም ስለ ባሕር በር ጉዳይ በኢትዮጵያውያን መነሳቱና የኢፌዴሪ መንግሥትን ጽኑ መሻት ያጤኑ አካላት ከወዲህ ወዲያ መናወጣቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው::

በብዙዎች ዘንድ እንደሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ናቸው:: ይሁንና ይህንን በተፈጥሮ የተቸሩትን ሀብት በጋራ ከመጠቀም ይልቅ እንደ ስጋት ቆጥረው አይነኬ ሆኖ እንዲቀመጥ ይሻሉ:: የንግድና ቀጣናዊ ትስስርን እንደመፍጠር እርስ በእርስ በስጋት ይተያያሉ::

ይሁንና ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ፣ በመልማትና በጋራ ማደግ ላይ የምታምን በመሆኗ ከወር በፊት ስለ ባሕር በር ጉዳይ ከውይይትና ከንግግር በዘለለ ከራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም በቅታለች:: ስለ ባሕር በር በተለይም ስለ ቀይ ባሕር እንዴት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይነሳል በሚል ሲብከነከኑ ከነበሩ መካከል ‹‹ሱማሌላንድ ዛሬም ቢሆን የእኔ ናት›› ከምትለዋ ሱማሊያ ጀምሮ አንዳንድ ሀገራት በማያገባቸው ገብተው ሁኔታውን ለማባባስ ሲጥሩ ተስተውለዋል::

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ አብሮ የመልማት አካሄድን በመከተል የምሥራቅ አፍሪካ አካሄድ በጋራ እንዲያድጉና የተጠናከረ ትስስር እንዲኖራቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች:: ሆኖም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

በጉዳዩ ዙሪያ ካነጋገርናቸው ምሑራን አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፒ.ኤች.ዲ ተማሪ የሆኑት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ሽመልስ ኃይሉ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት፤ የባሕር በር ማለት አንድ ሀገር ያለ ሌላ አገር ጣልቃ ገብነት ከዓለም ጋር የምትገናኝበት መንገድ ነው:: ለአንድ አገር ሉዓላዊነት፣ ደህንነት እና ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ የሆነ ነው::

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ላለችበት አካባቢ፤ የባሕር በር በጣም ወሳኝ የሆነ ነው:: አካባቢው ቀይ ባሕር፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤ እና የሕንድ ውቅያኖስ ያለበት እንደመሆኑ፤ የዓለም ኢኮኖሚ፣ ደህንነት እና የፖለቲካ እንቅስቃሴም ጭምር የሚወስን ኮሪደር ነው::

ስለዚህ በዚህ የጂኦፖለቲካ አካባቢ የባሕር በርን ማጣት ማለት ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል እንደማለት ነው:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን ስለምታውቅ ጥያቄዋን በማቅረብ በሰነድ ላይ እንዲሰፍር አድርጋለች::

መምህር ሽመልስ እንደሚሉት፤ አንዳንድ የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያን ጠንቅቀው ያውቃሉ:: ሀገሪቱ ቀደም ሲልም የነበራት ማንነት ከባሕር በር ማግኘት ጋር ተዳምሮ እንደፈለጉ ሊያዟት እንደማይችሉም የተገነዘቡ ይመስላል:: በእርግጥ ኢትዮጵያን እንደፈለጉ ማዘዝ የሚቻለው የባሕር በር ስታጣ ነው:: ስለዚህ ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት የትኛውም አካል እንደሚፈልገው ሊያዛት አይችልም:: የባሕር በር የማግኘቱ ጉዳይ ለኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር የሕልውና ጉዳይ ነው ያሉትም ለዚያም ነው::

በሰላሌ ዩኒቨርስቲ በሕግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ፒ.ኤች.ዲ በመማር ላይ የሚገኙት የሕግ መምህሩ ዘላለም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ እና በራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት አሳሪ አይደለም ብለዋል:: ሆኖም ግን ከስምምነቱ በኋላ ብዙ ጥያቄዎችና ውዥንብሮች መነሳታቸውን ተጠባቂ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል::

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የሆነ ነገር ላይ ይረባረባሉ:: አንዳንዶች እኤአ በ1960ዎቹ ከአፍሪካ ብዙ ሀገራት ነፃ ስለወጡ ቅኝ አገዛዝ የቆመ መስሏቸዋል፤ ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ያውም በ21ኛ ክፍለ ዘመን የቅኝ ግዥ አስተሳሰብ ቀጥሏል:: ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝ ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለሚያውቁ በብዙዎች ዘንድ ስጋት መፈጠሩ የሚያስደንቅ አይደለም:: ስለዚህም ኢትዮጵያ መትጋት ያለባት ትግሉ ከውሃም ያለፈ በመሆኑም ጭምር ነው:: ምክንያቱም ጉዳዩ ከቅኝ ግዛት ጋርም የተያያዘ ነውና ነው::

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር ስምምነት የኢኮኖሚ አማራጭን መሠረት አድርጋ ነው የሚሉት መምህር ሽመልስ ደግሞ ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘንድ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን እንፍጠር፤ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ጎላ እናድርግ ከሚለው በጎ አመለካከት የመነጨ ነው ይላሉ:: ኢትዮጵያና ራስ ገዟ ሱማሌላንድ የተፈራረሙት ሰነድ ዓላማው በጋራ ለመሥራትና አብሮ ለማደግ እስከሆነ ድረስ መልካም የሆነ ሐሳብ ነው ሲሉ ይናገራሉ::

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ገና ያልለማ እና እንዲሁ ቁጭ ያለ መሬት አላቸው:: የባሕር በርም አላቸው፤ ስለዚህ ያላቸውን ሀብት በአግባቡ እየተጠቀሙ ካለመሆናቸው የተነሳ በጋራ በመልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንሁን በሚል ኢትዮጵያ ስምምነቱን ማድረጓ ተገቢነት ያለው ነው:: ለዚህ ደግሞ የንግድ ልውውጥ ማድረግም ተገቢ በመሆኑ ውይይት ወሳኝ ነው:: ከሱማሌ ላንድ ጋር የተደረገውም ስምምነት ከዚያ ውስጥ አንዱ ነው::

እኔ እንደማምነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግዙፍ ነው:: የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ኢኮኖሚ ከመሆኑም በተጨማሪ እያደገ ያለ ነው:: የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያድጋል:: ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አንድ ወይም ሁለት ብቻ ወደብ ሳይሆን ብዙዎቹን መጠቀም ትሻለች:: ስለዚህ ለጊዜው የተጀመረው ከሱማሌ ላንድ ጋር ይሁን እንጂ ጉዳዩ ከሁሉም ጋር በመስማማት የሚካሄድ ነው ብለዋል::

ስምምነቱ የመግባቢያ ሰነድ ነው:: ይህ የመግባቢያ ሰነድ ለኢትዮጵያ አንድ ጥሩ እፎይታ ነው:: ወደጥሩ ነገርም የሚወስድ ነው:: አማራጮችን ስናይ ከደቡብ ሱዳን እና ከኢትዮጵያ ውጭ ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሱማሊያ፣ ጅቡቲ ኤርትራም የባሕር በር አላቸው:: የኤርትራን ወደብ ብንመለከት ለኢትዮጵያ በጣም አዋጭ የሆነ ወደብ ነው:: ሰሜን ምዕራቡም እንዲሁ ነው:: ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሐሳብ ከሁሉም ጋር መነጋገር የሚያስችልና በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ የሆነም ጭምር ነው:: የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደግሞ ከሁሉም ጋር መሥራት የሚያስችል ነው:: ጥሩው ነገር የአፍሪካ ቀንድ የንግድ ስምምነት በማድረግ በኢኮኖሚ ማስተሳሰር ነው::

መምህር ሽመልስ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ አንድ ወደብ ላይ ብቻ መቀመጥ አትፈልግም:: በየአካባቢው ካሉ ጋር የኢኮኖሚ አዋጭነት ስላለ በጋራ ማደግና መሥራትን ትፈልጋለች፤ ይህ ደግሞ እነሱንም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ብቻ ለብቻ የሚያድጉ ከሆነ አፍሪካ ቀንድ ላይ ችግር አይፈታም:: ስለዚህ አብሮ በመልማት ውስጥ የኢኮኖሚ ፍትሐዊነትና መስተጋብርን ስለሚፈጠር ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሐሳብ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሱማሌላንድ ቀዳሚ ሆናለች:: የላሙ ወደብም የኬንያ በሂደት ያለ ነው:: የሱዳንም ተጀምሮ ወደ መግባባት ላይ ሲደረስ በአገሪቱ በተነሳው ቀውስ ሳቢያ ገታ የተደረገ ነው:: በዚህ መልክ ሲታይ አማራጮቹ ብዙ ናቸው:: ኢትዮጵያ ደግሞ ያለውን አማራጭ ሁሉ መጠቀም ትፈልጋለች::

እርስ በእርስ ተደጋግፎ ለማደግ የሚከለክላቸው ሕግ አለ ወይ የሚለው ነገር አከራካሪ ነው የሚሉት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰሩ ዘላለም ናቸው:: ስምምነቱን በተመለከተ በትንሹ ሦስት ጎራዎች አሉ ይላሉ:: አንደኛው ጎራ ስምምነቱ የሱማሊያን ሉዓላዊነት የጣሰ ነው፤ ስለዚህ የአፍሪካ ኅብረት መርሕ የሚያሳየው አንድን ድንበር አንዴ ከተመሠረተ በኋላ ሀገራት ሌላ አይነት መፍጠር የለባቸው:: ስለሆነም ማክበር አለባቸው የሚል ነው:: ሁለተኛው ደግሞ አዳዲስ ሀገራትም ተፈጥረዋል:: ወደፊትም ይፈጠራሉ:: ይህም እንደዚያ አይነት ሒደት ስለሆነ ሕገ ወጥ አይደለም የሚሉ አሉ:: ከዚህ የተነሳ ሱማሌላንድ የራሷ መንግሥት፣ መሬት፣ ሕዝብና ሀብት አላት:: ከሱማሊያም ምናልባትም ከአንዳንድ ጎረቤት ሀገራት በተሻለ መልኩ ምርጫ ታካሒዳለች:: ከዚህ የተነሳ ዴሞክራቲክ የሆነች ራስ ገዝ ናት:: የቀራት ነገር ቢኖር የዓለም አቀፍ እውቅና ነው በሚል ክርክር ያነሳሉ:: ሦስተኛው መንገድ ደግሞ አብሮ ለማደግ እስከሆነ ድረስ ይቻላል የሚል አተያይ ያለው ሲሆን፣ ለምሳሌ የተለያዩ ሀገሮች ከሱማሌላንድ ጋር በቢዝነስ፣ በሠላም ዙሪያ፣ በንግድም ሀገር ናት ብለው ሳይሆን አብሮ ለመሥራት ሞክረዋል፤ አድርገዋልም:: ኢትዮጵያም እየገባችበት ያለው ሦስተኛውን አማራጭ ለመጠቀም ነው:: ይህ ሦስተኛው አማራጭ አብሮ መሥራት እስከሆነ ድረስ ይቻላል ሲሉ የመምህር ሽመልስን ሐሳብ አጠናክረዋል::

የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን አቅም የሚለውጥ ነው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሽመልስ፣ እንዲያ ይሁን እንጂ ሁሉም አካል ስምምነቱን በበጎ ያየዋል ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል:: ይሁን እንጂ ጫጫታው ሁሉ ኢትዮጵያ እንዳትሠራ ይገድባታል ማለት አይደለም ብለዋል::

ለአብነትም ሲጠቅሱ እንደተናገሩት፤ ምሳሌ የዛሬ አምስት ወር አካባቢ ስለባሕር በር ጉዳይ ቢያንስ መነጋገር አለብን፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልጋታል ሲባል፤ ይህማ ወረራ ነው ተብሎ ነበር:: ዛሬ ላይ ግን ከአምስት ወራት በኋላ የዓለም ሀገራት ሁሉ የባሕር በር ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የምታገኘው እንዴት ነው ወደሚለው ሐሳብ መምጣት ችሏል:: ስለዚህ ቢያንስ ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቷል ማለት ነው:: ቀጣዩ ደግሞ እንዴት እንደምታገኝም ማስረዳት የሚፈልግ ይመስለኛል::

ነገር ግን ጫጫታው የመጣው ከየት ነው? ምንስ አይነት አንድምታ አለው? የሚለውን በአግባቡ መፈተሽ አስፈላጊ ነው:: በእኔ እምነት ይህን ከሦስት ከፍዬ አየዋለሁ:: አንደኛው ኢትዮጵያ የባሕር በርን ካገኘች የእኛ ኢኮኖሚ ይጎዳል፤ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ ሀገራት ጥቅማችን ይጎዳል ብለው ያስባሉ:: ይሁንና የባሕር በር ጥያቄን ኢትዮጵያ ስታነሳ ይህ አይነቱ ንትርክ እንደሚኖር ሳታውቅ ቀርታ አይደለም:: ይህን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መጋፈጥ ግን ብልህነት ነው ብለዋል::

ሁለተኛ ነጥብ ያሉትን ሲያስረዱ እንዳሉት፤ አሁን ያለው የዓለም አቀፍ ሁኔታን መሠረት አድርጎ በቀናነት የሚያነሱ አሉ:: ለምሳሌ ብዙዎቹን መግለጫዎች ካያችኋቸው ከሁለት ሦስት ሀገራት ውጭ ይህን ነገር እርስ በእርስ ብትነጋገሩበት ጥሩ ነው የሚል ሐሳብ የተሰነዘረባቸው ናቸው:: በተለይም ሱማሊያና ኢትዮጵያ መሐል ችግር መፈጠር ስለሌለበት ብትነጋገሩ መልካም ነው ያሉት:: ምክንያቱም ዓለም ያለችበት ሁኔታ ጦርነት ነው:: ራሽያ ከዩክሬን እንዲሁም እስራኤል ከሐማስ ጦርነት እየተካሔደ ነው:: ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ቀንድ ሲመጣ ሱዳንም አጣብቂኝ ውስጥ ያለች ሀገር ናትና እዚህ ላይ ሌላ ጦርነት የሚጀመር ከሆነ ዓለም ወደአላስፈለጊ ነገር ትሔዳለች:: ስለዚህ በሚያግባባ መልኩ ተነጋገሩበት እንጂ የጭቅጭቅ መንስዔ አይሁን የሚል ሐሳብ ነው:: ይህን ሐሳብ ደግሞ ማንኛውም አካልም ሆነ መንግሥት የሚቀበለው ነው:: ኢትዮጵያም ከዚህ አኳያ እያየች ነው:: ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው የማንንም ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነገር አይደለም:: የምታደርጋቸው ስምምነቶች በመግባባት ነው::

ሦስተኛው ጉዳይ ያሉት፤ ስምምነቱን በሀገር ውስጥ ያለውም አካል ከስምምነቱ በተቃራኒ መቆሙን የሚያሳይ ነው:: ይህ የሚያመላክተው ብሔራዊ ጥቅምን በአግባቡ ካለመረዳት ነው::

ይሁንና ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው አብረን እንደግ ስለሆነ ብዙም የሚያሰጋ አይደለም፤ ነገር ግን ዲፕሎማሲው ላይ በደንብ መሥራት የግድ ነው:: ኢትዮጵያ የወደብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የባሕር በር ማግኘት ይኖርባታል:: የባሕር በር ደግሞ ይዞ የሚመጣው በርካታ ትሩፋት አለ:: አንደኛው የባሕር ኃይል እንዲኖር ማድረጉ ነው:: በባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ እቃዎችን ለመቆጣጠር የሚያግዝም ይሆናል:: ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለውም ወደውጭ የምትወጣበትን የባሕር በር የማግኘት እድልን ነው:: ምክንያቱም የባሕር በር ማለት በራስ ማዘዝ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው::

በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ሠላማዊ መንገድ የሚከተሉ ሀገራት አሉ፡ ኢትዮጵያ አንዷ ናት የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ ለማደግ ስትታትር አንዳንድ አካላት መርዝ ሲረጩባት ይስተዋላል:: እሷ ግን ያንን መርዝ የሚያመክን ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ መከተል አለባት ይላሉ:: ይህ አዋጭ ነው:: ምክንያቱም አፍሪካ ነፃ ሀገር ሆና እንድትፈጠር ያደረገችና የአፍሪካ አንድነት የመሠረተች ሀገር በተለይ ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ሱማሊያን ወረረች ቢባል ከባድ ነው:: የባሕር በር ለማግኘት ሲባል የቆመችበትን መልሕቅ ማጥፋት የለባትም:: ወንድማማችነት ላይ መመሥረት አለባት:: በዚህም ማደግ ይቻላል::

እነርሱ ወደጦርነት እንድትገባና ጡንቻ እንድታሳይ ያደርጋሉ:: እርሷ ግን ያንን መከተል አለባትም:: ወደጦርነት በመግባት የሞራል ልዕልና ማጣት የለባትም። እነርሱ ፍላጎታቸው ኢትዮጵያ ጦርነት ገብታ እንድትከስር ነው:: ገብታ ብታሸነፍም ባትሸነፍም መጨረሻዋ የሞራል ውድቀት ስለሆነ እነርሱ ፍልሚያውን የጦርነት ሲያደርጉ እርሷ ግን የልማት ማድረግ አለባት ብለዋል፡

መምህር ሽመልስ እንደሚሉት፤ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ያላቸውን ሀብት ከሠሩበት ራሳቸውን የሚችሉ ይሆናሉ:: ያለውን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር ይቻላል:: ለዚህ ግን ትብብር አስፈላጊ ነው:: ኢትዮጵያ ውጪዋ ጥንካሬ እንዳለ ሁሉ ውስጣዊ ጥንካሬም ሊኖራት ይገባል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መግባባት ካለ ውጪያዊ ጉዳይ ላይ በጎ ተፅዕኖን መፍጠር ይቻላል:: ቢያንስ ቢያንስ የሀገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል::

ምሑራኑ እንደሚናገሩት ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ያቀደችው ዓላማ ስኬታማ መሆን የሚችለውና አብሮ ማደግ የሚቻለው ዲፕሎማሲው ላይ መሥራት ስትችል ነው:: በጋራ ማደግ የሚቻለው በጠብመንጃ አሊያም አሳሪ የሆነ ሕግ በመደንገግ አይደለም:: አብሮ በጋራ ለማደግ የሚያስችል የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ነው:: በተለይም በቀጣናው ያሉ ሀገራት በኢኮኖሚ ማደግ የሚቻል መሆኑን የማሳመን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያ የተያያዘችው መንገድ ዓላማው አብሮ የማደግ እንጂ ማንንም የማጥቃት አይደለም:: ይህን ለማሳመን ግን አሁንም ቢሆን ሰፊ የዲፕሎማ ሥራ የሚጠይቅ ነው:: ይህንን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ሰፊ ሥራ መሥራት የግድ ነው:: ሥራው አምስትም አስርም ዓመት የሚወስድ ሊሆን ይችላል:: ይህንን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መሥራት የግድ ነው::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You