ብዙዎች በህይወት ዘመናቸው ሁሉ እጅግ የተደሰቱበትን ቀን አስታውሱ ቢባሉ የሠርግ ቀናቸውን እንደሚያነሱ ይገለጻል። ወላጆችም ቢሆኑ ልጅ ከወለዱበት ቀን ያልተናነሰና እጥፍ ድርብ የሆነ ደስታን የሚጎናጸፉት ልጆቻቸውን አሳድገው አስተምረውና ለቁምነገር ከማድረስ ባለፈ በወግ በማዕረግ ኩለው ሲድሩ ነው፡፡
ሠርግ ለተጋቢዎቹና ለዘመድ አዝማዱ ከሚሰጠው ደስታ ባለፈ ማስጨነቁ እና ማሳሰቡ አይቀርም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚገኝ ክስተት በመሆኑ ነው፡፡ ከአልባሳት ጀምሮ ቦታው፣ መስተንግዶውና አጠቃላይ ስነ-ስርዓቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ትልቅ ጉዳይ እንደመሆኑ ሠርጉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሙሽሮቹንና የቤተሰቡን ከፍተኛ ክትትልና ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
አጠቃላይ የሠርግ ስነ-ስርዓት የሙሽሮቹንና የቤተሰቡን ከፍተኛ ትኩረት የሚጠይቅ ቢሆንም ከተጋቢዎቹ መካከል ደግሞ እጅግ የሚጓጉት ሴቶች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ‹‹ሴቶች ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምረው ስለ ሠርግ ቀናቸው አብዝተው ይጨነቃሉ›› ሲባልም ይደመጣል፡፡ በተለይም ሙሽሪት በሠርጓ ቀን ስለምትለብሰው የሙሽራ ልብስ (ቬሎ) ስለ መጫሚያዋና መዋቢያዋ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ አብዝታ ትጨነቃለች፡፡
አመጣጡ ከታላቋ ብሪታኒያ እንደሆነ የሚነገርለት ሙሽሪት በሠርጓ ዕለት የምትለብሰው ነጭ ልብስ /በተለምዶው ‹‹ቬሎ›› ተብሎ የሚጠራው/ነው፡፡ ይህ ነጭ የሠርግ አልባስ በሀር መሳይ ጨርቅ የተሰራ፣ አብረቅራቂ ጌጣጌጦች ያሉትና በተለያየ መልኩ የተጌጠ ሲሆን፤ ዘመናትን አልፎ አሁንም ድረስ የሴቶች የሠርግ ልብስ ምርጫ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በኢትዮጵያም ያለው ልምድ ይሄው በመሆኑ ሀጫ በረዶ የመሰለውንና ውብ ጸአዳ የሆነውን ቬሎ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው ለገበያ የሚያቀርቡ፣ የሚያከራዩ እንዲሁም የሚያስውቡ ባለሙያዎች በሥራው ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል ቹቹ አበራ አንዷ ናት፡፡ ቹቹ፤ በሠርግ ወቅት የሚለበሱ የተለያዩ አልባሳትን በተለያዩ አማራጮች ታቀርባለች፡፡ በርካታ ደንበኞችንም አፍርታለች፡፡ በቦሌ ሞርኒንግ ስታር ህንጻ ላይ አሞሬ የሙሽራ ቀሚስ የሚል ስያሜ ያለው ድርጅት አላት፡፡ ሶስት ዓመታትን በዚህ ሥራ ላይ የቆየችው ቹቹ ወርሃ ጥር እና ሚያዝያ ሠርግ የሚበዛበት ወቅት እንደሆነ ጠቅሳ፤ ‹‹በሁሉም እምነት ተከታዮች ዘንድ ወቅቱ የጾም ወቅት ከሆነ ለሠርግ የማይመረጥ ነው›› ትላለች፡፡
በተለይም በወርሃ ጥርና ሚያዚያ በርካታ ሠርጎች የሚከናወኑበት እንደመሆኑ ቬሎ ፈልገው የሚመጡ በርካታ ደንበኞች እንዳሏት የገለጸችው ቹቹ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን በቬሎ ሲያዩ የሚያለቅሱ ሴቶች እንዳሉና ይህም እጅግ የተለየ ስሜት የሚፈጥር እንደሆነ አጫውታናለች፡፡
አሁን ያለው የሠርግ አልባሳት ፋሽን እየተቀየረ መሆኑን ጠቅሳ፤ የአሁኖቹ ቬሎዎች ከተለመደው ነጭ ቀለም ወጣ ያሉና የተለያየ ቀለም ያላቸው እንደሆኑ ገልጻለች፤ እነዚህን የተለያየ ቀለም ያላቸው ቬሎዎች ሙሽሮች በአብዛኛው በሠርጋቸው ዕለት የፎቶ ስነ-ስርዓት ያከናውኑበታል፡፡ በቀደመው ጊዜ ቁመታቸው አጠር ያሉ ቬሎዎች ይዘወተሩ ነበር፤ ከዚያም ረጅምና ከሙሽሪት ጋር ተመጣጣኝ ቅርጽና ቁመት አልፈው መሬት ላይ የሚጎተቱ ቬሎዎች ተመራጭ እንደሆኑ አስረድታለች፡፡
በተለምዶ ‹‹ ስፓጌቲ ›› የሚባለው የቬሎ አይነት በሙሽሪት አንገት ላይ እንደ ክርክር ቀጭን ዲዛይን ያለው ሙሉ የደረት ክፍልን የማይሸፍን ነው፣ ቲሸርት የዲዛይን አይነት ትከሻን ሙሉ ለሙሉ ሸፍኖ ከትከሻ በታች ያለውን እጅም ይሸፍናል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሙሉ ለሙሉ እጅን የሚሸፍነው ‹‹መርሜድ›› ዲዛይን የሚባለው ሴቶች ያላቸውን የሰውነት ቅርጽ ይዞ የሚወርድ የቬሎ አይነት ነው፡፡
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተመራጭ የሆነው ደግሞ አንገት ድረስ የሚሸፍነው ‹‹መስከሪና ›› የሚባለው ዲዛይን መሆኑን ጠቅሳ፤ አብዛኛዎች ደንበኞች ተሰቅሎ ከሚያዩት ይልቅ በሰው ላይ ሲያዩት አይናቸው ውስጥ እንደሚገባና ራሳቸው ሲለብሱት ይበልጥ እንደሚማርካቸው ትናገራለች ፡፡
አልባሳቱን ከአገረ ቻይና በራሷ ዲዛይን በትዕዛዝ የምታስመጣ መሆኑን የገለጸችው ቹቹ፤ አልባሳቱ ደንበኞች በሚፈልጉት አይነት እንዲመቻቸው ተደርጎ የሚስተካከል መሆኑንም ገልጻለች፡፡ ቬሎን ከሌላው አልባሳት ጎላ ብሎ እንዲታይና እንዲያምር የሚያደርገው ከልብሱ ውስጥ የሚደረገው መወጠርያ መሆኑን ጠቅሳ፣ ይህም ቬሎው ይበልጥ ውበት እንዲኖረው የሚያደርግና ሙሽሮችም የሚፈልጉት እንደሆነ ነው ያስረዳችው፡፡
‹‹ቬሎ ለገበያ የሚቀርበው በኪራይ ነው›› የምትለው ቹቹ፤ ሰዎች ከሠርግ ቀናቸው ሶስትና አራት ወራት አስቀድመው መምረጥና ቀጠሮ መያዝ እንዳለባቸው ጠቅሳለች፡፡ በተለያየ አማራጭ የሚቀርብ መሆኑንም ገልጻለች፡፡ ከቬሎ በተጨማሪ በተናጠል በሠርጋቸው እለት ብቻ የሚለብሷቸው እንዲሁም ለፎቶ ፕሮግራም ብቻ የሚፈለጉ አልባሳት በጥቅል መልክ እንደሚዘጋጁም ተናግራለች፡፡
ቬሎው ለኪራይ የሚቀርብበት ዋጋን አስመልክታም፤ እንደ ቬሎው አዲስነት የሚወሰን መሆኑን ነው የገለጸችው፤ ዋጋቸው ከሚሸጥበት ሱቅ፣ ቬሎው ከሚመጣበት ቦታና በቆይታ ጊዜው ጭምር የሚከራይበትን ዋጋ እንደሚወስኑት አስታውሳለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ በተናጠል አንድ ቬሎ ከ15 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 45 ሺህ ብር ድረስ አሁናዊ ገበያው ነው። በአሞሬ የሙሽራ ልብስ ዲዛይን ለተጠቃሚዎች የቀረበው አማራጭ የሙሽራ ልብስ ጥቅል ሶስት ቬሎዎችን በአንድ የያዘ ለመስክና ለስቱዲዮ ፎቶ ፕሮግራም የሚውለው ነው። ሙሽሮች ለሰርጋቸው ቀን የሚለብሱት አንድ ላይ ነው፤ ይህም ከ65 ሺህ ብር እስከ 95 ሺህ ብር ድረስ ለኪራይ ይቀርባል፡፡
ቬሎ በባህሪው ትልቅና ነጭ በመሆኑ ደንበኞች ሲወስዱት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል የምትለው ቹቹ ልብሱን ከመውሰዳቸው በፊት ግማሽ ክፍያ ፈጽመው እና ተጨማሪ ገንዘብ አስይዘው ነው ትላለች፡፡ አከራይ ባለሱቆች ደግሞ በምትካቸው የማረጋገጫ ደረሰኝ፣ ልብሱ ላይ ሊደረግ የሚገባን ጥንቃቄ ከውል ጋር አስፍረው ያከራያሉ፡፡
ልብሱ ቢቀደድ፣ የማይለቅ መጠጥ ቢፈስበት፣ ተመልሶ ሊስተካከል የማይችልበት እንከን ቢኖረው እንዲሁም በተስማሙበት ቀን ካልተመለሰ እንደማስያዣ የተቀመጠው ገንዘብ ተመላሽ አይደረግም፡፡ ደንበኞች ልብሶቹን ተጠቅመው ሲመልሱም ቀላል እጥበት ተደርጎላቸው ለሌላ ደንበኛ ይዘጋጃሉ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ የሙሽራ ልብሶች ከሚዜ ልብሶች ጋር አንድ ላይ የሚቀርቡ ሲሆን፣ የሙሽራ ልብስን ብቻ የሚያቀርቡም እንዳሉ በገበያው ላይ ይስተዋላል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ጥር 27/2016 ዓ.ም