የውሃ ማቆር ሥራ – ለአርብቶ አደሩ ዋስትና

ከዓለም ሕዝብ ከፊሉ ሕይወቱን የመሰረተበትና በኢኮኖሚ ውስጥም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የግብርናው ዘርፍ አንዱ ክንፍ አርብቶ አደርነት ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከዓለም ሕዝብ ከ350 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕይወቱን በአርብቶ አደርነት ይመራል፡፡ ከዓለም 25 በመቶ የሚሆነው ሞቆታማና ደረቃማ መልክዓ ምድርም የአርብቶ አደሮች መኖሪያ ነው፡፡

በኢትዮጵያም ከሀገሪቱ ቆዳ ስፋት ከ52 እስከ 61 በመቶው የአርብቶ አደር አካባቢ ሲሆን፣ የዚህ አካባቢ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሕዝብም ኑሮውን በእዚሁ በአርብቶ አደርነት ያረገ ነው፡፡ አርብቶ አደሮቹ የሚገኙት በአብዛኛው በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ነው፡፡

ይህ የአርብቶ አደሩ አካባቢ በከብት፣ በውሃና በሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ታድሏል፤ ይሁንና አካባቢው ቆላማና ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ተከትሎ ይህ አርብቶ አደር ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለመሳሰሉት አደጋዎች ሲጋለጥ ቆይቷል። የሕልውናው መሰረት የሆኑት እንስሳት በእነዚህ አደጋዎች ሳቢያ ሲያልቁበት እንደመኖሩ ለክፉ ቀን የሚለው የበቃ ጥሪት ሳይኖረው ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻልና ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ አወንታዊ ሚና ይጫወት ዘንድ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በየሁለት ዓመቱ በሚከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን አማካኝነት የማኅበረሰቡ ችግር ጎልቶ እንዲታይና እንዲፈታ አቅጣጫ ለመጠቆም ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ መንግስት እያከናወነ ካለው ተግባር በተጨማሪ የዓለም ባንክ፣ የአሜሪካ ልማት ድርጅት፣ አውሮፓ ሕብረት፣ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክን የመሳሳሉት ድርጅቶች የማህበረሰቡን ሕይወት ለመታደግና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን እያከናወኑ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ አርብቶ አደሮች በብዛት ከሚኖሩባቸው ክልሎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ የክልሉ መንግስትም እንዲሁ የክልሉን አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ኑሮ ለመለወጥ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ሥራዎች መካከል አንዱ የአርብቶ አደር በዓል በየዓመቱ እያከበረ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ በዚህም ለአርብቶ አደሩ እውቅና ከመስጠት ባለፈ የዘርፉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው፡፡

ዘንድሮም በኦሮሚያ መስኖ ልማትና አርብቶ አደር ቢሮ አዘጋጅነት 19ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን በክልል ደረጃ ‹‹የአርብቶ አደር ልማት ለጋራ ብልጽግና›› በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ ተከብሯል። በወቅቱ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ቦኩ ተጬ፤ አርብቶ አደርነት ለኦሮሞ ሕዝብ እንደ ኢኮኖሚ ምንጭ ብቻ ሳይሆን እንደ ባህላዊ መገለጫም ተደርጎ የሚታይ የረዥም ዘመን ታሪክ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በኦሮሚያ ክልል በ10 ዞኖች 45 የአርብቶ አደር ቀጠናዎችና 746 ቀበሌዎች ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት በቆላማ፤ 15 በመቶዎቹ ተራራማና ሜዳማ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው፡፡ በክልሉ አርብቶ አደሮች የሚገኙባቸው አካባቢዎች አማካይ የሙቀት መጠን ከ25 እስከ 35 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው፤ አካባቢዎቹ ከመሬት ጠለል በላይ ከ400 እስከ አንድ ሺ 600 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ከ400 እስከ 700 ሚሊ ሜትር ዓመታዊ የዝናብ መጠንም አላቸው፡፡

አርብቶ አደርነት ረዥም እድሜን ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ ማነቆዎች ምክንያት ወደ ሚፈለገው ደረጃ መሸጋገር አልቻለም ያሉት ዶክተር ቦኩ፤ ስለአርብቶ አደሩ የሚሰነዘሩ ኋላቀር አስተሳሰቦች፣ ግልጽ የሆነ ፍኖቶ ካርታ አለመኖር፣ የድንበር ላይ ግጭቶች፣ የመሬት አጠቃቀም ችግር፣ የውሃ እጥረትና ድርቅ የዘርፉ ዋና ዋና ፈተናዎች እንደነበሩ ያመለክታሉ፡፡

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱራህማን አብደላ በበኩላቸው፤ አርብቶ አደሩ በእንስሳት ሀብት ወጪ ንግድ 90 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይገልፃሉ፡፡ ዘርፉ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ባሻገር የሰላም፣ የባሕልና የማኅበራዊ መስተጋብር መገለጫ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ‹‹በክልሉ የሚገኙ አብዛኛዎቹ አርብቶ አደሮች በድንበር አካባቢ የሚኖሩ እንደመሆናቸው ለሀገሪቱ ዳር ድንበር መከበርም ጭምር የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ›› ይላሉ፡፡

አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ማዕድናት የሚገኙትም በእነዚሁ አርብቶ አደሩ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በመሆኑ አርብቶ አደሩ አካባቢ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ድል እየፈጠረና እንደሀገር ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹የኦሮሞ ባሕል ሳይጠፋ ከዚያኛው ትውልድ ወደዚህኛው ትውልድ እንዲሸጋገር ካደረጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አርብቶ አደሮች ተጠቃሽ ናቸው›› ያሉት አቶ አብዱራህማን፤ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ከማስቻል አንጻር የአርብቶ አደሩ ባሕል ጠባቂነት አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ ነው ያነሱት፡፡

አርብቶ አደሩ ለክልሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ቢታመንም፤ ለዘመናት ትኩረት ተነፍጎት ነው የኖረው ሲሉም ይናገራሉ፡፡ ከለውጡ ወዲህ ግን መንግሥት ዘርፉን የሚያነቃቁ ርምጃዎችን መውሰዱን ተከትሎ መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በክልሉም የአርብቶ አደሩን ሕይወት መቀየር የሚያስችሉ የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅዶች ታቅደው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የአርብቶ አደሩ ትልቁ ችግር የውሃ እጥረት ነው፤ ክልሉ 73 የሚሆኑ የውሃ ማቆሪያ ግድቦችን ለመሥራት አቅዶ፤ በፊና ፕሮጀክት አማካኝነት በ10 ቢሊዮን ብር ወጪ ለመጠጥ፣ ለእንስሳትና ለመስኖ ልማት የሚውሉ 35 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ተሠርተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም የአርብቶ አደሩን የጤና፣ የትምህርት፣ የገበያ ትስስር፣ የመንገድ ችግሮችን የሚፈቱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ጥራት ያላቸውን የከብት ዝርያዎችን በማርባትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የበለጠ ውጤታማ የሚሆንባቸውን መንገዶች እንዲከተል እገዛ እየተደረገለት ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ድርቅ በዘላቂነት ለመከላከል የተፋሰስ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራና የእርከን ሥራዎች በልዩ ትኩረት መሰራታቸውን ይናገራሉ፡፡ አርብቶ አደሮች መሬታቸውን በኃላፊነት እንዲያስተዳድሩ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እየተሠራ ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ከዚሁ ጎን ለጎን አርብቶ አደሩ መሬቱን በአግባቡ ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን እንዲያሳድግ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የአፈር ምርምርና ጥናት እያደረገ ይገኛል›› ይላሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል መስኖ ልማትና አርብቶ አደር ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ፤ የክልሉ አርብቶ አደሮች እንደሀገር ባለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በእንስሳት አቅርቦት ብቻ ከ12 እስከ 16 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ጎን ለጎንም በሚሠራው የእርሻ ሥራ 40 በመቶ የሚሆነው ምርት የሚገኘው ከዚሁ አካባቢ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ አርብቶ አደርነት ለኦሮሞ ሕዝብ ማንነቱ፣ ሕይወቱ፣ ኢኮኖሚው፣ ሰላሙ፣ ባሕሉና ውበቱ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

እንደእሳቸው ገለፃ፤ የክልሉ አርብቶ አደሮች በአመዛኙ በከርሰ-ምድርና በገጸ-ምድር ውሃ ይጠቀማሉ፡፡ እንደ አዋሽ፣ ዋቤ ሸበሌና ገናሌ ዳዋን የመሳሰሉ ወንዞች የክልሉ አርብቶ አደሮች ከሚጠቀሙባቸው ታላላቅ ወንዞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በዝናብ እጥረት፣ በጎርፍና በድርቅ ምክንያት እንስሳት ግጦሽ ሳር ማግኘት ባለመቻላቸው የአርብቶ አደሩ ሕይወት ክፉኛ ሲፈተን ቆይቷል፡፡ በተለይም የውሃ ችግርን ለማስወገድ የክልሉ መስኖ ልማትና አርብቶ አደር ቢሮ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡

በመርሃ-ግብሩ አርብቶ አደሮች በብዛት ከሚገኙባቸው ዘጠኝ ዞኖች መካከል የውሃ ማቆር (የፊና ፕሮጀክቶችን) በመጠቀም በመስኖ ልማትና በሳር ልማት የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ሞዴል አርብቶ አደሮችና የልማት ሠራተኞች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚሁ መሰረት የቦረና፣ የምስራቅ ባሌና የምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ያለውን ቦታ ይዘዋል፡፡ በወረዳ ደረጃ ከምስራቅ ባሌ ዞን የሳዊና ወረዳ፣ ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን የማዩ ሙሉቄ ወረዳ እንዲሁም ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን የቡረቃ ኢኒቱ ወረዳ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱሰላም ዋሪዮ ዞኑ ካሉት የአርብቶ አደር ዞኖች መካከል የተሻለ አፈጻጸም ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የቦረና ዞን አርብቶ አደሮች ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በነበረው የዝናብ እጥረት ምክንያት ለከፍተኛ ድርቅ ተጋልጠው ነበር፤ ይህን ችግር በኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብርና በክልሉ መንግሥት ጥረት መሻገር ተችሏል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተለይም የውሃ ጉድጓዶችን የመቆፈር እና የውሃ ማቆሪያ ግድቦችን የመሥራት ሥራዎች ተከናውነዋል›› ይላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በእቅድ ከተያዙት ግማሽ ያህሉ ተሠርተው ለእንስሳት፣ ለሰዎችና ለመስኖ ልማት ትልቅ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ይገልፃሉ፡፡ የውሃ ማቆሪያ ግድቦቹ ለአርብቶ አደሮቹና ለእንስሳት ብቻ ሳይሆን የዱር እንስሳትንም ሕይወት መታደግ ያስቻሉ ስለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊት በአካባቢው ያልተለመዱ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለመትከልና የበጋ ስንዴን ለማልማትም አስችለዋል። በዚህም ከ350ሺ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል ይላሉ፡፡

የቦረና ዞን ከክልሎች አንደኛ ሆኖ መሸለሙና አርብቶ አደሩ ድርቅን ተቋቁሞ ለዚህ ደረጃ መብቃቱ የሚያኮራና በቀጣይ ተግቶ ለመሥራት የሚያነቃቃ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ‹‹ሽልማቱ በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካል ለተሻለ ተልዕኮ እንዲነሳሳ የቤት ሥራ የሰጠ ነው›› በማለት ያመለክታሉ፡፡

የቦረና ዞን መስኖና አርብቶ አደር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታዲ ገርብቻ ለአርብቶ አደሩ ማኅብረሰብ ትልቁ ሀብቱ እንስሳት እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ በዞኑ ለተከታታይ ዓመታት የተከሰተው የዝናብ እጥረት ለድርቅ መከሰት ምክንያት እንደነበር አስታውሰውም፣ እንስሳት እንዳይጎዱና አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብም በኢኮኖሚ እንዳያሽቆለቁል የክልሉ መንግሥት የውሃ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና በዚህም አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

በቦረና ዞን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ 14 የውሃ ማቆሪያ ግድቦችን ለመሥራት እቅድ እንደተያዘ አቶ ታዲ ገልጸው፤ እስከ አሁንም ስምንቱ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም አበረታች ውጤት እንደተገኘ ነው ያመለከቱት፡፡

በቦረና ዞን፤ ያበሎ ወረዳ፤ ዲድ ያበሎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሌላዋ ሞዴል ተሸላሚ ወይዘሮ ኤሌማ ቡሌም በአርብቶ አደር ሕይወት ስኬት ካስመዘገቡና እውቅና ከተሰጣቸው መካከል አንዷ ናቸው፡፡ ግለሰቧ ከ7 ነጥብ 5ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበዋል። አርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ክልሉ እያደረገ ያለው ልዩ ድጋፍ ለውጤታማነታቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ይገልጻሉ፡፡ ፍየሎችን፣ የቀንድ ከብቶችንና ግመሎችን በማርባት ባገኙት ገንዘብ በአካባቢያቸው በሚገኝ አነስተኛ ከተማ ቤት ሠርተው በማከራየት ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በቦረና ዞን የውሃ ችግር እንደሚስተዋል የገለጹት ወይዘሮ ኤሌማ፤ የክልሉ መንግሥት ውሃ ማቆሪያ ግድቦችን እየሠራ መሆኑ ለከብቶች መኖና ለመጠጥነት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ከዚህ በፊት እርሻ በማይታወቅባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የበጋ ስንዴን ለማምረት አስችሏል ይላሉ፡፡ የምርጥ እንስሳት ዝርያዎችንና እንስሶቻቸው የጤና ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉ ለውጤታማነታቸው አስተዋጽኦ እንዳደረጉላቸው ያስረዳሉ፡፡

በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ የሙዲ አምቦ አርብቶ አደሮች መንደር ነዋሪና ሞዴል አርብቶ አደር ጎዳና ቦሩ ደግሞ አርብቶ አደርነት ከቤተሰቦቻቸው የወረሱትና መተዳዳሪያቸው መሆኑን ይናገራሉ። እርሳቸውም በአርብቶ አደርነት ረዥም እድሜን አሳልፈዋል፡፡ ቀደም ሲል ለአርብቶ አደሩ እንደ አሁኑ ትኩረት የሚሰጥ አካል ባለመኖሩና በማኅበረሰቡም ዘንድ ግንዛቤ ባለመኖሩ ከእንስሳት የሚያገኘው ጥቅም አነስተኛ እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ አርብቶ አደሩ፣ በእንስሳት ምርጥ ዘር አቅርቦትና በሕክምና፣ በብድር እና በተለያዩ ጉዳዮች ድጋፍ ስለሚደረግለት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል ይላሉ፡፡

አቶ ጎዳና እንደሚሉት፤ እሳቸው የቀንድ ከብቶችን፣ ግመል፣ ፍየልና በጎችን በማርባት አጠቃላይ ካፒታላቸው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ለሽልማት እንዲመረጡ ያስቻላቸው ዋናው ጉዳይ ግን በአካባቢያቸው ተገድቦ የተያዘውን ውሃ ተጠቅመው የተለያዩ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን ማምረት በመቻላቸው ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአካባቢው የማይመረቱትን እንደ ጎመን፣ ቡና፣ ብርቱካን የመሳሰሉትን በማምረት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምሳሌ ሆነዋል፡፡ ተረፈ ምርቱንም ለከብቶቻቸው መኖ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ መንግሥት የሚሠራቸው የውሃ ማቆሪያ ግድቦች የአርብቶ አደሩን መሰረታዊ የውሃ ችግር ከመቅረፍም ባሻገር አርብቶ አደሩ ጎን ለጎን የእርሻ ሥራዎችን እንዲሠራና አዲስ የሥራ ባሕል እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡

 ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ጥር 27/2016  ዓ.ም

Recommended For You