ቱርክ ለሞሳድ መረጃ አሳልፈው ሰጥተዋል የተባሉ ሰዎችን አሰረች

የቱርክ የፀጥታ ኃይሎች ለእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ መረጃ አሳልፈው ሲሰጡ ነበሩ ያሏቸውን ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተነገረ።

ሰባቱ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የቱርክ የደኅንነት ኤጀንሲ የሆነው ኤምአይቲ በኢስታንቡልና ኢዝሚር በተባሉት ከተሞች ውስጥ ድንገተኛ ዘመቻዎችን ካደረገ በኋላ ነው።

ቱርክ ከአንድ ወር በፊት ከሞሳድ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን 34 ሰዎች በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር አውላ ነበር።

የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን እስራኤል የሐማስ አባላትን ቱርክ ውስጥ ዒላማ ብታደርግ “ከፍተኛ መዘዝ” እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀው ነበር።

ከመስከረም ማብቂያ ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የገባውን ሐማስን በርካታ ምዕራባውያን እና አረብ ሀገራት አሸባሪ ቡድነት ቢፈርጁትም፣ ቱርክ ግን እዚህ ውሳኔ ውስጥ የለችበትም።

ከሞሳድ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ሰዎች የቱርክ መንግሥት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ ባያወጣም፤ የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ግን ሞሳድ የግል መርማሪዎችን ተጠቅሞ የሐማስ ቡድን አባላትን እንቅስቃሴ እንዲከታተሉና ፎቶግራፍ እንዲያነሱ ስለማድረጉ የሀገሪቱ የደኅንነት ተቋም ደርሶበታል ብለዋል።

ከአንድ ወር በፊት በቁጥጥር የዋሉት 34 ሰዎች “ፖለቲካና ወታደራዊ” ዓላማን ለማሳካት ለእስራኤል የደኅንነት ተቋም ስለላ በማድረግ ክስ እንደተመሠረተባቸው የቱርክ የፍትሕ ሚኒስትር ይለማዝ ቱነከ ተናግረው ነበር።

ሞሳድ የስለላ ተግባሩን እንዲፈጽሙለት በቱርክ ነዋሪ የሆኑ ፍልስጤማውያን እና ሶሪያውያን ሳይቀጥር እንደማይቀር ይገመታል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።

ኤርዶዋን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁን የጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ “ዘር ማጥፋት” ብለው ከመግለጻቸውም በላይ ኔታኒያሁን ከናዚ ጀርመን መሪው ሂትለር ጋር አነጻጽረዋል።

እስራኤል በበኩሏ ከጋዛ በተጨማሪ በሊባኖስ፣ ኳታር እና ቱርክ የሚገኙ የሐማስ አባላትን ዒላማ እንደምታደርግ ስትዝት ቆይታለች።

መስከረም ወር 2016 ዓ.ም. የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል። እስራኤል ለሐማስ ጥቃት እያካሄደችው ባለው የአጸፋ ምላሽ በርካታ ሰዎች መገደላቻውንና በጋዛ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ውድመት ማጋጠሙን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር                                           

Recommended For You