አባባ ማሙሽ እና እማማ ሚጡ

የምንኖርባት ዓለም በየቀኑ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸውን አዳዲስ የሚወለዱ ሕፃናትን ታስተናግዳለች። በዚህም የህዝብ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን ይጨምራል። ሀገራት የሚኖራቸው የህዝብ ቁጥር መጨመር ደግሞ በተለምዶው በ“ሶስተኛው ዓለም” ወይም በታዳጊ ሀገራት ላይ በስፋት ይስተዋላል፡፡

ይህ ትዝብቴ ግን በእናታቸው ማህጸን ዘጠኝ ወራትን ቆይተው ስለሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ሳይሆን፣ በምድር ቆይታቸው በሥራና ኃላፊነታቸው “አንቱ” ወይም፣ “አዋቂ” የሚሰኙ፤ በተግባራቸው ግን ማሙሽና አቡሽ ስለሆኑ ሰዎች ነው፡፡ በዚች አጭር ጽሑፍ የትኛውን አንስቼ የትኛውን እንደምተወው ባላውቅም፤ በየዘርፉ “ትልልቅ” የሚባሉ ሰዎች በእድሜ የማይመጥናቸውን ሥራ ሲሠሩ ይስተዋላል፡፡ ‹‹ምነው ትልቅ ሰው አይደለህ/ሽ፣ ፊደል አልቆጠርክም/ሽም›› የሚሉ ቃላትም ትልቅ ከምንላቸው/ከምናከብራቸው ሰዎች ያልተለመደ ተግባር ስናይ የምንጠቀማቸው ቃላት ናቸው፡፡ አባባ ማሙሾች እንዴት ያሉት እንደሆኑ እና እነማን እንደሆኑ አንድ ሁለት ብዬ አስታውሳችኋለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ አንባቢያን ታውቋቸዋላችሁ፡፡

አባባ ማሙሾች ከቤታችን ውጪ የምንጠቀምባቸው የህዝብ መገልገያዎችን በኃላፊነት የማይጠቀሙ ናቸው፡፡ እስኪ ስንቶቻችን ነን የመስሪያ ቤቶቻችን መጸዳጃ ቤት ውስጥ የምናያቸው ግድ የለሽ አጠቃቀሞች፤ በእውኑ እዚህ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሕፃናት ናቸው ወይስ በእውነት አብረውን የሚውሉት ባለሱፍና ባለ ክራቫቶቹ የቢሮ ሰራተኞች ናቸው የሚገለገሉበት? የምንለው። በመጸዳጃ ቤቱ ውስጥ ውሃ ቢኖርም የተጠቀሙበትን ለማጽዳት እጃቸው የማይዘረጋ፣ በመጸዳጃ ቤቱ በር ላይ የተለጠፉ መመሪያና ማስጠንቀቂያዎችን ችላ የሚሉ እና ለጽዳት ሰራተኞች ጉልበት ቦታ ባለ መስጠት ጥፋትን ይሰራሉ፡፡ ጽዳትን ከድመት እንኳን የማይማሩ ከውጪ አንቱ የሚባሉ፤ ሰው በማያያቸው ቦታና ሰአት ነውርን እና ጥፋትን የሚፈፅሙ ናቸው፡፡

ሌላኛዎቹ አባባ ማሙሾች እና ሚጡዎች ደግሞ ከትዳራቸው ውጪ የሚወሰልቱ ሴቶችና ወንዶች፣ በእድሜ ከሚያንሷቸው ጋር የሚወሰልቱ ባለትዳር ወንዶች ናቸው፡፡ ባለቤቱ በማን እንደሆነ ባይታወቅም እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ‹‹ወመሽ›› (ወጣት መሳይ ሽማግሌ) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተቀባይነትንም አግኝቶ መታወቂያቸው ሆኗል።

ከነሱ እድሜ ያነሱ፣ በወጣትነት እድሜ ላይ የሚገኙ ከስነ-ምግባር ታርቀው ራሳቸውን በጤነኛ ግንኙነት ውስጥ አድርገው ህይወታቸውን ይመራሉ። ሰዎችን ከትምህርት ቤት ባሻገር እድሜና ህይወት ይበልጥ ያስተምራል ሲባል ብንሰማም እነዚህ ሰዎች ግን በዚህ አጸያፊ ተግባር ላይ ተሰማርተው የመገኘታቸው ምክንያት መለከፍ (ልክፍት) እንጂ ሌላ ምን ምክንያት ሊገኝለት አይችልም፡፡

ሌላው አባባ ማሙሽ ደግሞ በትዳር ውስጥ ሁሉንም የቤት ውስጥ ኃላፊነቶች ሚስት እንድትወስድ የሚፈልግ ነው፡፡ ትዳር በሁለት ሰዎች ጥምረት የሚመሰረት ተቋም ሲሆን ቤቱን የማቅናት ኃላፊነትም የሁለቱ ሰዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ሚስት ማለት ሞግዚት የምትመስላቸውና ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይቅርና ከወለዷቸው ልጆች እኩል ትኩረትና እንክብካቤን የሚሹ፤ “የሚበላ በጊዜ አልቀረበልኝም፤ ልብሴ ታጥቦ አልተተኮሰም፤ ጫማዬ የታለ?” የሚሉ ጥያቄዎችን በማግተልተል ሌላ ሸክም ይሆናሉ፡፡

ሚስት እንክብካቤን የምትሻ፤ ተፈጥሮ በራሱ ብዙ ሸክሞችን ያሸከማት በመሆኗ እነዛን ሸክሞች ደግሞ አብራው እንድትኖር ከመረጠችው አጋሯ በተሻለ ሌላ ማንም ሊካፈላት የማይችል በመሆኑ አባባ ማሙሾች የትዳር አጋሮቻቸውን የመርዳትም የመረዳትም ኃላፊነታቸውን ማስታወስ ይገባቸዋል።

እነዚህ የልጅነት ባህሪ የሚያጠቃቸው ሰዎች አንዳንዴ ደግሞ ታክሲ ላይ ያጋጥማሉ፡፡ የጫኑት የሰው ህይወት የማይመስላቸው ለራሳቸውም ለተሳፋሪዎቻቸውም ግድ የሌላቸው እና እንደ ልጅነት ጊዜያቸው በጓደኞቻቸው ላለመቀደም በውድድር የተጠመዱ ናቸው፡፡ የያዙት የህዝብ መጓጓዣ ሳይሆን የስፖርት ውድድር መኪና የሚመስላቸው። ‹‹ኧረ ቀስ ብለህ ንዳ፤ የምን መንቀዥቀዥ ነው›› ለሚለው አስተያየት ቦታ የሌላቸው። ፈጣሪን የማይፈሩ፣ ኃላፊነት የጎደላቸውና በልጅነታቸው የተጫወቱትን የሽቅድድም ውድድር ዛሬ ላይም በሰው ህይወት ሊያስቀጥሉ የሚዳዳቸው ናቸው፡፡

ድሮ ድሮ አስታውሳለሁ “እከሌ እከሌን ትችለዋለህ?” እንዴታ፣ አናፍጠዋለሁ። ሌላኛውን ወገን ደግሞ “አንተስ? እሱ አናፍጠዋለሁ እያለ ነው”፤ “አይ እኔ ድብድብ አልወድም፤ እናቴ ትቆጣኛለች” ሲል ዛሬ ተደባድበህ እራስህን አታስከብርም፤ ፈሪ” ይለዋል አንድ የቦክስ ዳኛ የሆነ የሚመስለው እና ሰውን ከሰው በማፋጀት መከባበር ያሰፈነ የሚመስለው የጸብ ጫሪነት ጂኒ ያለበት ሕፃን፡፡

ልጆቹም ፈሪ ላለመባልና ሁሌ ሲሰደቡ ላለመኖር በማሰብ ጸብ ይጀምራሉ፡፡ አንዱ ይመታል፤ ሌላው ደግሞ ተመቶ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ ነገር ግን፣ ዛሬ ይመታ እንጂ ነገ ተደራጅቶ ወይም ተዘጋጅቶ ብድሩን ይመልሳል፡፡ ይሄ ነገር አዙሪት ስለሚሆን መቼም የማይቆምን ጠብ ይወልዳል፡፡

ታዲያ ይህ አይነቱ በልጅነት የሚጠናወት ጂኒ ባህር ማዶ ድረስ ተከትሎ ይሄድና በሰላም አብሮ ሲኖር የቆየን ማህበረሰብና ህዝብ ማባላት ይጀምራል። እሱ ልጆቹን የሞቀ ፍራሽ ላይ እያስተኛ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለጎዳና እንዲዳረጉ ያደርጋል፡፡ ያኔስ አለማወቅ ነው፤ ልጅነት ይሆናል ተብሎ የሚታለፈው ስህተት ዛሬ ላይ ስህተት ብቻ ነው ለማለት አያስደፍርም፤ እጅግ አረመኔያዊ ተግባር ነው፡፡

እንደዚሁ ሁሉ እነእማማ ሚጡም አሉ፡፡ የእናት አባቶቻቸው ትከሻ ላይ ተቀምጠው ለቤተሰቦቻቸው ሸክም የሚሆኑ፤ በውበታቸው ተመክተው ከወንድ ወንድ እያቀያየሩ የሰዎችን ትዳር የሚያፈርሱ፤ የሴቶች እኩልነት ማለት ምን እንደሆነ በትክክል ያልተረዱ፡፡

እንደልጅነታቸው ካልታዘልን፤ እንኮኮ ካልተባልን የሚሉና ዛሬም ራሳቸውን ላለመቻል እንቶፈንቶ ምክንያትን እየደረደሩ ሰው ላይ ሸክም የሚሆኑ እና በስሌት በመኖሪያቸው ሰአት በስሜት የሚኖሩ እማማ ሚጡዎች አሉ፡፡ ልክ ልጅ የቤተሰቦቹን ኪስ እንደማይረዳ ሁሉ የባሎቻውን የኪስ ሁኔታ ከመረዳት ይልቅ እራሳቸውን ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር እያወዳደሩ ያላቸውን ሳይሆን የሌላቸውን በመቁጠር የትዳራቸውን ሰላም የሚያደፈርሱ፤ የያዙት ህይወት እና ኑሮ መሆኑን ረስተው በፉክክር መድረኮቻቸውን ጎልተው ለመታየት ባሎቻቸውን ጎል የሚከቱ ናቸው፡፡

በዚህ ነገር ስንቱ ባል እንደተፈተነ ቤት ይቁጠረው። “እኔ አልሰርቅም፤ ህዝቤን አልበድልም፤ አደራ አላጎድልም” ሲል በሴቶች የነገር መርፌ ጠቅ ተደርገው ወደ ወንጀል እና ሙስና የገቡት። እንደዚህ አይነት አባዜ ያለባችሁ ሴቶች እባካቹ አድቡ፡፡ ቁመት መለካካት በልጅነታችን የቀረና ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም የሚልን አስተሳሰብ ከጭንቅላታሁ አስገብታችሁ ባላችሁ ነገር መደሰት ባትችሉ እንኳን ሰላማችሁን ለማስጠበቅ ስሩ የሚለው የበርካቶች ምክር ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

የአሜሪካ የውጭ መሥሪያ ቤት አራት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 31 ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች)፣ ሚሳኤሎች እና ሌሎች ወታደራዊ ቁሶች ለሕንድ በሽያጭ እንዲተላለፉ አጸደቀ።

ኤምኪው-9ቢ ፕሪዴተር የተባለው ድሮን ለሕንድ በሽያጭ እንደሚተላለፍ ይፋ የተደረገው የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ባለፈው ዓመት ሰኔ በአሜሪካ ጉብኝት ባደረጉ ወቅት ነበር።

ይሁን እንጂ ኅዳር 2016 ዓ.ም. በአሜሪካ ምድር የሕንድ ዝርያ ባለው ግለሰብ ላይ ግድያ ለመፈጸም የሕንድ መንግሥት አሲሯል መባሉን ተከትሎ ምርመራ እንዲደረግ ከተወሰ በኋላ የሽያጭ ስምምነቱ እንዲዘገይ ተደርጎ ነበር።

ስምምነቱ በኮንግረሱ ከጸደቀ በኋላ የጦር መሳሪዎቹ ለሕንድ በሽያጭ ይተላለፋሉ ተብሏል።

ይህ ስምምነት 31 ኤምኪው-9ቢ ስካይጋርዲያን ድሮኖች፣ 170 ኤጂኤም-114አር ሄልፋየር ሚሳኤል እና የተለያዩ ዓይነት ቦምቦች፣ የግንኙነት እና የስለላ መሳሪዎችን እንደሚያካትት የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን አስታውቋል።

የሕንድ መንግሥት ተሳታፊ ሳይሆን አይቀርበትም የተባለውን የግድያ ሴራን ሲመረምሩ የነበሩት የሴኔት ኮሚቴ አባሉ ሴናተር ቤን ካርዲን፣ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩ ላይ ዝርዝር ምርመራ ለማድረግ ከተስማማ በኋላ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ መስማማታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የባይደን አስተዳደር ምርመራ አድርጎ ተጠያቂነትን እንደሚያረጋግጥ ተስማምቷል ያሉት ሴናተር ካርዲን፤ መሰል እንቅስቃሴዎች የሕንድ መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ዋሽንግተን አሜሪካዊ ዜግነት ያለው እና ከሕንድ ተገንጥላ ካሃሊስታን የተባለች ሉዓላዊት ሀገር ለመመሥረት የሚንቀሳቀስ ሕንዳዊ የዘር ግንድ ያለውን ግለሰብ አሜሪካ ምድር ላይ ለመግደል ዴልሂ አሲራለች ብላ ነበር።

የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን የሀገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ምንም ተሳትፎ እንደሌለው ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጨምሮም ከአሜሪካ ዘንድ የቀረበውን ክስ እና የደኅንነት ስጋት የሚያጣራ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያሉበት ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል።

ሐሙስ ዕለት ፔንታገን ወታደራዊ ቁሶቹ ለሕንድ በሽያጭ መተላለፋቸው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን ከመደገፉ በላይ የአሜሪካ-ሕንድ ስትራቴጂካዊ ግንኙነትን ያጠናክራል ብሏል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You