በቦስተን የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች የበላይነቱን ለመቀዳጀት ይሮጣሉ

በዓለም አትሌቲክስ መሪነት በተለያዩ ዓለማት የቤት ውስጥ ቱር ውድድሮች እየተካሄዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከወር በኋላ በግላስኮ ከሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አስቀድሞ የሚደረገው ቱር የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፤ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው መካከል የሆነው የቦስተን ኒው ባላንስ ግራንድ ፕሪክስ ከነገ በስቲያ ይደረጋል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይም ኢትዮጵያዊያኑን ጨምሮ በርካታ ስመጥር አትሌቶች ተካፋይ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

እአአ ከ1996 አንስቶ ይህንን ውድድር በማካሄድ ላይ የሚገኘው ቦስተን ጠንካራ አትሌቶችን በማፎካከር የሚታወቅ ሲሆን፤ በርካታ የዓለም ክብረወሰኖች በተለያዩ ርቀቶች የተሰበሩበት ስፍራም ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች መሰረት ደፋር እና ጥሩበሽ ዲባባ (ለሁለት ጊዜ) ይገኙበታል፡፡ ከነገ በስቲያ በሚደረገው በዘንድሮው ውድድር ላይም በሴቶች የ5ሺህ ሜትር እንዲሁም በ3ሺህ ሜትር የወንዶች የዓለም ክብረወሰን ባለቤቶቹ ጉዳፍ ጸጋይ እና ለሜቻ ግርማ ተሳትፏቸውን ማረጋገጣቸውን ተከትሎ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

የመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌቷ ጉዳፍ ጸጋይ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሩጫዋን በካዛኪስታን እንደምታደርግ ቢጠበቅም ከሳምንታት በፊት መሰረዟን አስታውቃ ነበር፡፡ አትሌቷ ባራዘመችው የውድድር መርሃ ግብሯ መሰረትም ከነገ በስቲያ ቦስተን ላይ የተለመደ አስደማሚ ብቃቷን ለማሳየት ተዘጋጅታለች፡፡ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናን ጨምሮ በኦሊምፒክ፣ በዓለም ቻምፒዮና፣ በዳይመንድ ሊግ፤ እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች ኢትዮጵያን ያስጠራቸው የ5ሺህ ሜትር ንግስቷ ጉዳፍ ከሃገሯ ልጆች ጋር በመሆን በ1ሺህ 500 ሜትር ትሮጣለች፡፡

ባለፈው የውድድር ዓመት ድንቅ ብቃቷን ያስመሰከረችው አትሌቷ ከቡዳፔስቱ ስኬታማ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መልስ በዳይመንድ ሊግ የ5ሺህ ሜትር ክብረወሰን መስበሯ የሚታወስ ነው፡፡ በብቃቷ ጫፍ ላይ የምትገኘውን ምርጧን አትሌት በቤት ውስጥ ውድድርም ስኬታማ ስትሆን፤ እአአ 2016 በፖርትላንድ ሃገሯን በመወከል የነሃስ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ኢትዮጵያ ከዓለም አንደኛ ደረጃን ይዛ ባጠናቀቀችበትና ከሁለት ዓመት በፊት ቤልግሬድ ላይ በተደረገው ቻምፒዮና ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ነበር ያስመዘገበችው፡፡ የአትሌቲክስ አፍቃሪያን በፓሪሱ ኦሊምፒክ ላይ ሊመለከታት የሚጓጓላት ጉዳፍ ባለችበት ወቅታዊ አቋም በቱር ውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ሀገሯን ለምትወክልበት ቻምፒዮና በቀጥታ ከመሳተፍ ባለፈ በ1ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን የመጨበጥ እድሏ ከፍተኛ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

ልምድ ያላት ጉዳፍ ከወጣቶቹ አትሌቶች አያል ዳኛቸው እና ብርቄ ኃየሎም ጋር ውድድሩ ላይ የምትሳተፍ ሲሆን፤ ሌሎች ተፎካካሪዎች ፈተና መሆናቸው አያጠያይቅም። ምክንያቱ ደግሞ በዓለም የወጣቶች ቻምፒዮና የ800 እና 1ሺህ 500 ሜትር አሸናፊዎች የሆኑት አያል እና ብርቄ ጠንካራ ተፎካካሪና ለአሸናፊነትም ተጠባቂ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚሁ ርቀት በወንዶች በኩል አትሌት ዮናስ አስማረ እና ሳሙኤል ዘለቀም ተካፋይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ሌላኛው የቻምፒዮናው ተጠባቂ ውድድር በወንዶች 3ሺህ ሜትር ሲሆን፤ ውድድሩን ከሚያደምቁ አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ለሜቻ ግርማ ነው፡፡

በዓለም ቻምፒዮና የሶስት ጊዜ እንዲሁም በኦሊምፒክ አንድ ጊዜ የብር ሜዳሊያ ያገኘው ወጣቱ አትሌት ኢትዮጵያን በ3ሺህ ሜትር መሰናክል ካስጠሩ ጥቂት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ቤልግሬድ ላይ በነበረው ቻምፒዮናም በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያውን መውሰድ ችሎ ነበር፡፡ አትሌቱ ባለፈው ዓመት ሌቪን ላይ በተደረገው የቤት ውስጥ ቱር ውድድር ርቀቱን 7:23.81፣ ከቤት ውጪ ደግሞ 7:52.11 በሆነ ሰዓት በመሸፈን ሁለቱንም ክብረወሰኖች ከእጁ ማስገባቱም አይዘነጋም፡፡ ይህም ውድድሩን አጓጊ የሚያደርገው ሲሆን፤ ተፎካካሪዎቹን በአሳማኝ ብቃት በመርታት ግላስኮ ላይ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ያደርጋታል በሚልም ይጠበቃል፡፡

በዚህ ውድድር ከለሜቻ ባሻገር ወንድሙ ድሪባ ግርማ እና ሳሙኤል ፍሬው ለአሸናፊነት የሚፋለሙ አትሌቶች ናቸው፡፡ በርቀቱ በሴቶች በኩል ደግሞ አትሌት መዲና ኢሳ፣ መልክናት ውዱ፣ ፈንታዬ በላይነህ፣ ሰናይት ጌታቸው እንዲሁም አይናዲስ መብራቱ ይሮጣሉ፡፡ በየውድድሩ ተግባራዊ በማድረግ በሚታወቁበት ቅንጅት የሚሮጡት ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ለተፎካካሪዎቻቸው ስጋት በመሆን የበላይነቱን እንደሚወስዱም ይገመታል፡፡

እያንዳንዱ የቱር ውድድር አትሌቶች በሚኖራቸው ተሳትፎ የሚያስመዘግቡት ነጥብ ተደምሮ ከሚያገኙት ከፍተኛ መጠን ያለው ሽልማት ባለፈ በዓለም አቀፉ ቻምፒዮና በቀጥታ ሃገራቸውን ወክለው የሚሳተፉበትን እድል ሊያስገኝላቸው ይችላል፡፡ የዘንድሮው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በእንግሊዟ ግላስኮ አዘጋጅነት ለ19ኛ ጊዜ ይደረጋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You