ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ´ዚህ ከባድና ውስብስብ ርእስ ተገባ። እየከበደ በሄደ ቁጥር እልህ እየፈጠረ በመምጣቱ ምክንያት ላለመፋታት ውሳኔ ላይ ተደረሰ። እነሆም በሚከተለው መልክ ይቀርብ ዘንድም ፍቃድ ሆነ።
ለነገሩ፣ የተፈጥሮን አንድ በመቶ (100%) እንኳን ገና ላላወቀው ሰው ስለ “ሰው እና ተፈጥሮም ይሁን “ተፈጥሮና ሰው ለመጻፍ ቀርቶ ለአፍታ እንኳን ለመናገር ቢከብድና ቢቸግረው ምንም የሚደንቅ ነገር የለውም። ምክንያቱ ደግሞ ስለማያውቁት ነገር ለመጻፍ መሞከር በራሱ አለማወቅ ነውና ነው።
ነገር ግን፣ ሰው የተፈጥሮን አንድ በመቶ እንኳን ገና አላወቀም ማለት ሰው ከተፈጥሮ ውጪ ነው ማለት ባለ መሆኑ፤ ተፈጥሮና ሰው ገና በቅጡ አልተዋወቁም ማለት ተፈጥሮ ለሰው ልጅ ያበረከተችው፣ እያበረከተች ያለችውንና ልታበረክት የምትችለውን አለማወቅ ማለት ባለ መሆኑ፤ ሰው ስለ ተፈጥሮ ምንም አላወቀም ማለት ከተፈጥሮ ጋር እየተጣላ አይደለም ማለት ባለመሆኑ፤ ሰው “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር ለማዋል ባለው መሰረት የለሽ ቅዥትና ከጣራ በላይ ፍላጎት በራሱ ላይ ቅጣትን እያወረደ አይደለም ማለት ስላልሆነ ወዘተ ስለ ተፈጥሮ እና ሰው ለመጻፍ ሙከራ ማድረግ ባያሸልም እንኳን አያስጠይቅምና (አንባቢ እያነበበ እንዳለው) እየሞከርን እንገኛለን።
በነገራችን ላይ፣ ሰው እና ∙ ∙ ∙፤ ሰው እና ∙ ∙ ∙፤ ∙ ∙ ∙ እና ሰው፤ ሰው እና ∙ ∙ ∙፤ እየተባለ ብዙ ሲነገር (ለምሳሌ“ሰውና እግዚአብሔር፣ “ሰውና መላእክት ∙ ∙ ∙)፤ ብዙም ሲጻፍ ይታያል። እነዚህ ሁሉ በሚባሉበት ወቅት ከበስተ ጀርባቸው ያለው ምንድን ነው? ሰው ከተፈጥሮ ተነጥሏል ማለት ነው፣ ሰውና ተፈጥሮ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው/አይደሉም ለማለት ነው? ሰውና ተፈጥሮ በትክክል ተገናኙ የሚባለው መቼና ምን ሲሆን ነው? ሰው የአምላኩን ትእዛዝ እየፈፀመ ነው? ሰው ከፈጣሪው ጭምር እየተጣላ ነው? ሰው ከራሱ ከሰው ጋር እየተጣላ ነው? የምሁራንን ማብራሪያ ይጠይቃል።
ለምሳሌ ያ ሰውዬ “ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው አለ ተብሎ ሲነገር ስለ መኖሩ ሁላችንንም ዋቢ አድርጎ አደባባይ የሚወጣ ካለ ያዋጣዋል። ያኛው ደግሞ “ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው አለ ተብሎ በተገኘ መድረክ ሁሉ በጆሯችን ሲንቆረቆር ስለ መኖሩ አሁንም ምስክሮቹ እኛው ነን። ሀበሻ በቀበሮ አሳብቦ “ለሰው ሞት አነሰው ማለቱን እዚህ ላይ ላስታወስ ጉዳዩ እንቆቅልሽ እየሆነበት እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውምና እንዳላነሳነው ተቆጥሮ ማለፉ የተሻለ ይሆናል። “እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ ተፀፀተ የሚለውንም እንደዛው።
“ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ለእግዚአብሔር ክብር የተፈጠረ ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ፤ በራሱ ነፃ ምርጫ የሚንቀሳቀስ ህያው ፍጥረት ነው፡፡ የሚለው ኃይማኖት ነክ ብያኔ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለውና እድሜ ጠገብ አተያይና ግንዛቤ ነው። እንዲሁም፡-
ሰው ዓለም ሳይፈጠር በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የነበረ እና በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ለእርሱ ክብር የተፈጠረ ነው (ኤፌ 14፡11-12፤ ዘፍ 1፡1 – 25 ኢሳ 43፡7)፤ ሰው እንደ እንስሳ በደመነፍስ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ክፉንና ደጉን የሚለይ ግብረገባዊ ፍጡር መሆኑ (ዘፍ 2፡ 15 – 17)፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሰው የሚያስፈልገውን ሁሉ ካዘጋጀ በኋላ ሰውን በመልኩና ባምሳሉ ፈጠረው፤ ሰው የእግዚአብሔር ተወካይ ወይም እንደራሴ በመሆን ምድርን የሚያስተዳድር ችሎታ ያለው (ዘፍ 2፡15 – 17) ነው የሚለው ገዥ ቃል ስለ ሰው በተነሳ ቁጥር ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። በሌሎች ኃይማኖቶችም ተመሳሳይ ባይሆን እንኳን የተራራቀ እንደማይሆን ተስፋ አለ።
ተፈጥሮና ፍጥረታትን በተመለከተ ደግሞ፤
እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረው ሰውንና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ሲሆን የተቀሩትን ፍጥረታት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግብ ስጋ፣ ለምግብ ነፍስ ነው። (መዝ.148፣1-3፤ ራዕ4፣11፤ የሐ.ሥራ14፣17፤ ሮሜ.1፣20)፤ ሰው ከፍጥረታት ሁሉ የከበረ ነው፡፡ (መዝ.48፣12)፤ በመሆኑም፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ ገዥ፣ አዛዥ ሊሆን ችሏል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ፈለገው በተፈጥሮ ዘና ይል ዘንድ ተፈቅዶለታል ማለት ነው – “በአግባቡ ከሚለው ራሱን ነጠለ እንጂ።
እዚህ ላይ፣ “ሰውን በተመለከተ አንድ ማጠናከሪያ ሀሳብ ይሆነን ዘንድ ወንጌል የተባሉ ሰው በአንድ ጽሑፍ መግቢያቸው ላይ “ሰው ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ ያለጥርጥር እጅግ መሠረታዊ የሆነ የፍልስፍናና የሥነ-መለኮት ተግባራዊ ጥያቄ ነው። ሰዎች መጀመሪያ ከየት መጣን? ለምንስ መጣን? መሄጃችንስ ወዴት ይሆናል? የሚሉና ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይሆናሉ። ፍልስፍና እዚህን ጥያቄዎች ለማጥናትና መልስ ለማግኘት በየዘመናቱ በተነሱ ፈላስፋዎቹ አማካይነት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጓል። የብዙዎቹን ፍልስፍናዎች የአጠናን ዘዴና መልሶቻቸውን ስናይ፣ ሰዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች እርግጠኛ መልስ ለማግኘት አለመቻላቸውን እንረዳለን። ያሉትን አስፍረን ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንመለስ።
ስለ “ሰውም ሆነ “ተፈጥሮ ያልተባለ የለም እና ታሪካዊውን ሀቲት (ኦሪጅን) እዚሁ ላይ ገታ እንድናደርግ እና ወደ ምድራዊው እውነታ እንመለስ።
በሚገባ እንደሚታወቀው፣ ከላይም እንደጠቃቀስነው፣ ሰው ተፈጥሮን የመጠቀም ልዩ እድልን ይዞ ነው ወደዚህ ምድር ዱብ ያለው። በመሆኑም፣ ጥያቄው “ለምን ተጠቀመ?″ ሳይሆን “እንዴት ነው እየተጠቀመ ያለው?″ የሚለው ነውና እሱን ማየቱ ይበጃል።
አሁን ያለንበት ዘመን በግልፅ እንደሚያሳየው ሰውና ተፈጥሮ ከምር የተጣሉበት ጊዜ ነው ያለው። ወቅቱ ተፈጥሮ አምርራ ከመቀየሟ የተነሳ የሰው ልጅ ላይ ፊቷን ያዞረችበት ከባድ ወቅት ስላለመሆኑ መከራከሪያ ነጥብ የለም። ለዚህ ቀዳሚ ማስረጃና መረጃው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ሲሆን፣ መገለጫውም እየደረሰ ያለው አደጋ፤ እየወደመ ያለው ሀብትና ንብረት፤ እየተራቆተ ያለው አረንጓዴና ለምለምና ለም መሬት፤ እንደ ባለሙያዎች አስተያየት የዚህ ሁሉ ውድመት ተጠያቂው ሰው ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮና ሰው የከረረ ግጭትና እንደ ቅድመ 1800 ዘመናት እጅ ለእጅ ተያይዞ መሄድ አለመቻል ነው።
“የተፈጥሮ እና ሰው መጋጨት ሲባል ምን ማለት ነው? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። “የተፈጥሮና ሰው መጋጨት ማለት የሰው ልጅ በተሰጠው ነፃ ፍቃድ አማካኝነት ተፈጥሮን በአግባቡ መጠቀም ሳይችል ሲቀር፤ ወይንም፣ የአጠቃቀም ጉድለት መታየት ነው ተብሎም ሊመለስ ይቻላል። “ውጤቱስ? ከተባለ ከስነ-ምህዳር ጀምሮ መዛነፍን ማስከተሉ መልስ ሆኖ ቢመጣ፤ ወይም የሰው ልጅ ተፈጥሮን ከመጠቀም ወደ መበዝበዝ (አቢዩዝ፣ ኤክስፕሎይት ማድረግ) መሸጋገሩ ነው ቢባል፤ “ይህ ብቻ አይደለም ካልተባለ በስተቀር “ስህተት የሚል አይኖርም።
ደን “ከምድር መሬት ውስጥ 30 በመቶውን የሚሸፍን እና 80 ከመቶው ብዝሃ-ሕይወቷን የያዘ የሕይወት ድጋፍ ስርዓት“ ነው የሚለው የባለሙያዎችና ጥናቶቻቸው ድምዳሜ ላይ ተግባብቶም ተጨባጩን ዓለም እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
ድሮ፣ “ተፈጥሮ ሁል ጊዜ የሰዎች መኖ ነች፣ እኛ በሕይወት ለመትረፍ በእሱ ላይ እንመካለን። ሰውና ተፈጥሮ ስምሙ እንደ ነበሩ የማይናገሩ የታሪክ ድርሳናት የሉም – በተለይ ከ1800ዎቹ አስቀድሞ ፍቅራቸው ልዩ ነበር ነው የተባለው። የሁለቱ ፍቅር፤ የሁለቱ ተደጋጋፊነት፤ የሁለቱ ተመጋጋቢነት፤ ለዚህች ውብ ዓለም የሁለቱ አስፈላጊነት እንደ ብርቅ የሚታይበት ዘመን ነበር አሉ። “ዘንድሮስ? ጥያቄው ይሄ ነው።
የደን አያያዝ ልምዶች የምስክር ወረቀትን ለማስተዋወቅ፣ ሕገ-ወጥ የደን ስራዎችን ለመዋጋት፣ የንግድ ፖሊሲዎችን ለማሻሻል፣ የደን አካባቢዎችን ለመጠበቅ እና ሌሎችም ከመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ኩባንያዎች፣ ማሕበረሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ከሚሰራው፤ አምራቾች በዚህ አቅጣጫ ጥረታቸውን እንዲያረጋግጡ ለመደገፍ የደን ጥበቃ የምስክር ወረቀት አገልግሎት ከሚሰጠው፣ ከ“የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ (WWF) የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የሰው ልጅ መጥፊያውን የተያያዘው ሲሆን፣ ለዚህም የሚከተሉት ማስረጃዎች ናቸው።
• ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ወደ 17 ከመቶው የአማዞን ደኖች ጠፍተዋል፤
• በተደረገው ስሌት መሠረት እ.ኤ.አ. በ 2019 ወደ 30 የሚጠጉ የእግር ኳስ ሜዳዎችን የሚያክል ሞቃታማ የደን አካባቢ በየደቂቃው ይጠፋል፤
• ባለፉት 25 ዓመታት ከደቡብ አፍሪቃ ከሚበልጠው አካባቢ ደኖች ቀንሰዋል፤
• በየዓመቱ ስዊዘርላንድ የሚያህል አካባቢ በደን መጨፍጨፍ ይደመሰሳል።
እንደ ዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ መሠረት ከሆነ ደኖች የምድር ገጽን ከ30 በመቶ በላይ የሚሸፍኑ ሲሆን፣ እነዚህ የደን አካባቢዎች ከአንድ ቢሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች በቀጥታ ምግብ፣ መድኃኒት እና ነዳጅ በቋሚነት ይሰጣሉ፡፡ ይህ ማለት የአንድ ቢሊዮኖች ሕይወት ሙሉ ለሙሉ የተንጠለጠለው በደን ላይ ሲሆን፣ ደን ጠፋ ማለት የእነዚህ ሕይወት አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ይሆናል።
ለእናት ተፈጥሮ ተገቢውን ትርጉም ይሰጥ ዘንድ የሚጠበቀው የሰው ልጅ ተፈጥሮን ሲዋጋ እና ሲያወድም የሳተላይት የመሬት ቁጥጥር ስርዓቶች (አገራት ለደን መሬት አጠቃቀሞች እና ለውጦች እና የደን ተግባራት የእንቅስቃሴ መረጃን ለመለየት እና ለመሰብሰብ የሚያግዙት) እንኳን ሊያስታግሱት አልቻሉም፤ ብሔራዊ የደን ፖሊሲዎችን በማቀድ፣ በዘላቂ ልማት ላይ አስተማማኝ የደን ሀብት መረጃን ማዳበርን የሚደግፈው፤ በደን ላይ ጥራት ያለውና አስተማማኝ መረጃን ለማመንጨት የሚተጋው የዓለም እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ሀይ ሊለው አልተቻለውም።
ምን ይሄ ብቻ፣ ሰውን የደን ልማት ስትራቴጂ እና የደን ተግባር ዕቅዶች ደንን ከማውደም ሊመልሱት አልቻሉም። ሰው ለደን ደህንነት ሲባል እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች (ለምሳሌ በwww.forestprotection.net ላይ የሚለቀቁ) ሊያስተምሩት፤ ወይም፣ የባህርይ ለውጥ ያመጣ ዘንድ ሊያግዙት አልተቻላቸውም። አይሰማም። እራሱ ካልጠፋ በስተቀር ከጥፋት የሚመለስ ሁሉ አይመስልም። በሌሎች ፍጡራን የማይታየው እራስ በራስ መገዳደል በሰው ልጅ ዘንድ የእለት ተእለት ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል። ለራሱም አልተመለሰ እየተባለ ነው።
ይህ እራስን ማጥፋት ከመምጣቱ በፊት፣ ከላይ በጠቀስነው የመረጃ ምንጭ መሰረት፣ ቀጣይነት ያለው የሰው ልጅ የቀድሞ ዘመን የሰውና የእናት ተፈጥሮ ግንኙነት መመለስ አለበት፤ ማለትም የነበረውንና የተቋረጠውን ግንኙነት ሊያድስ፤ ወደ ቅድመ 1800ዎቹ ክፍለ ዘመናት ሊመለስ ሁኔታዎች እያስገደዱት ይገኛሉ።
እንደ ደን ተንከባካቢ ምክር ቤት (FPC) ጥናት (ሪፖርት) ከግማሽ በላይ የሚሆነው የምድር ምድራዊ ብዝሃ ሕይወት በደን ውስጥ ነው፡፡ ሞቃታማ ደኖች በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ወደ 90 በመቶ የሚጠጉ ዝርያዎችን ይይዛሉ፡፡ ይህ ማለት ደን ማልት ምን ማለት እንደ ሆነ በራሱ ይናገራልና የሰው ልጅ የደን አያያዝ ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባል።
የተደረጉ ጥናቶች ሁሉ እንደሚስማሙበት፣ እንደ የእፅዋት እድገት፣ የካርቦን ቅደም ተከተል፣ የአበባ ዱቄት፣ የዘር መበታተን እና አልሚ ንጥረ ነገሮችን መልሶ መጠቀም እና የመሳሰሉት የስነምህዳር ሂደቶች ለምግብ ደህንነት እና ለምግብነት አስፈላጊ በሆነው ብዝሃ-ሕይወት ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡ ስለሆነም የደን ሥነ-ምህዳሮችን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊና ለሰው ልጅ ሰው ሆኖ መቀጠል ወሳኝ እርምጃ ነው።
እንደ የአየር ንብረት ለውጥ እና ከባዮኢነርጂው ዘርፍ የእንጨት ፍላጎት መጨመር በመሳሰሉ ስነምህዳራዊ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ እድገቶች በርካታ ችግሮች እየገጠሙት ያለው የተፈጥሮ ሀብት (ደንና ሌሎችም) ኃላፊነት በጎደለው አጠቃቀም ምክንያት ብዝሃ ሕይወት እየቀነሰ ነው፡፡ በጫካዎች ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ፣ ሥነ-ምህዳሩን ወደ ነበረበት መመለስ እና ባዮሎጂካዊ ሀብቶችን በዘላቂነት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየደረሰ ያለው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ ተደጋጋሚና የተራዘመ ድርቅ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ እሱን ተከትሎ የሚመጣው ጎርፍ ወዘተ ሁሉ ምክንያትና መነሻቸው የዓለማችን የደን መራቆት ሲሆን፣ ከ1800ዎቹ ወዲህ ለመራቆቱ ዋናው ምክንያት የሰው ልጅ መሆኑ ተረጋግጧል። ዓለማችን በአንታርክቲክ አካባቢ ብቻ 1.75 ሚሊዮን ስኴር ኪሎ ሜትር የውቅያኖስ አካባኒ ግግር በረዶ አጥታለች፤ ይህ ከ1981-2010 ባለው ጊዜ ውስጥ ከተከሰተው በአማካኝ ያህሉን ሲሆን፤ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ሰው እንጂ ሌላ አይደለም።
የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግጭት በዚሁ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በ2050 የዓለም የሙቀት መጠን 1∙5 ዲግሪ ሴልሺየስ (2.7° ዲግሪ ፋራናይት)፤ በ2100 ደግሞ ከ2 – 4 ዲግሪ ሴልሺየስ (2.7° ዲግሪ ፋራናይት) ይደርሳል ተብሎ ተተንብዮአል (ተፈርቷል)። ይህ እንዳይሆን፣ ጦሱም ለፕላኔቶች ሁሉ እንዳይተርፍ ሰው ኃላፊነቱን ወስዶ ከወዲሁ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። (“ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አለበለዚያ ∙ ∙ ∙ የሚለውም እዚህ ጋ ይሰራል።)
በ17ኛ ክፍለ ዘመን የ“ተግባራዊ እውቀት ፈልሳፊ፣ እንግሊዛዊው ፍራንሲስ ቤከን እንዳለው ከሆነ፣ እንደ አስፈላጊነቱ ለተፈጥሮ ትርጉም የሚሰጠው ሰው ከተፈጥሮ በጣም ተለያይቷል። እናም በሕይወት ውስጥ በማንኛውም መንገድ መሳተፍን ማሰብ አይችልም። በሁለቱ መካከል ያለው ጤናማ መስተጋብር በጣም እየቀነሰ ነው። (እዚህ ላይ የ17ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዓያቆብ ስለ ሰውና ተፈጥሮ በ“ሀተታው ያለውን መመልከት ጉዳዩን ከፍ ከማደረጉም በላይ በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያ ለዓለሙ ያደረገችውን አስተዋፅኦ ለመረዳት እንደሚያግዝ ሳንናገር ብናልፍ ንፍገት ይሆናልና ስንጠቅሰው “በኩራት!!! ነው።)
በአቶሚ ላይ ሰፍሮ እንደሚነበበው “አካባቢያዊ ችግሮችን በተመለከተ ፈላስፋዎችና ፕሮፌሰሮች የመጨረሻውን ፍርድ ሰጥተዋል – አንድ ሰው ከተፈጥሮ ባህሪው (እና እራሱን፤ እንደዚሁም ለውጦቹን) ይቀይራል፤ ወይንም ደግሞ ከምድር ፊት ይጠፋል። (ለበለጠ መረጃ am.atomiyme.comን ይጎብኙ) ከሁለት ዓመት በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳለው ከሆነም የሰው ልጅ (በተለይም መሪዎች) ባስቸኳይ እናት ተፈጥሮ መልሳ ታገግም፤ ወደ ነበረችበትም ትመለስ ዘንድ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ካልቻሉ የሰው ልጅ ወደ እማይቀለበስ ቀውስ ውስጥ ይገባል።
ሰው ሆይ ስማ
ስማ ∙ ∙ ∙ ሲል ያዘመው ማን ነበር??
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም