ብዙዎች ስኬት ‹‹በራስ የተቀመጠ ግብ ላይ በጥረት መድረስ›› መሆኑን በመግለፅ ለቃሉ የተብራራ ትርጉም ያስቀምጡለታል። መሻታቸው ከልብ ሲደርስ፤ ያሰቡትን ኢላማ ሲመቱ፣ እቅድና ፍላጎታቸው መሬት መርገጡን ሲገነዘቡ፤ በትግልና በትዕግስት ያገኙትን ድል ያጣጥሙታል። ይህ ስኬታቸው ለነገ ሌላኛው ታላቅ ሕልማቸው መሰረት ከመሆኑ በላይ ለብዙሀኑ ደግሞ አርዓያና መነሳሳትን የሚፈጥር ይሆናል።
የዛሬ እንግዳችንም ለዚህ ተምሳሌት ነች። ከልጅነት ህልሟ ጋር የተገናኘች፤ አሁን ላለችበት ደረጃ ሙሉ አቅሟንና እውቀቷን የሰጠች የፋሽን ዲዛይነር ነች። ሙያው ከልጅነት ጀምሮ ልትደርስበት የምትፈልገው ሕልሟ ነበር። ዛሬ ላይ ራሷን ከማብቃት አልፋ ብዙኃን ሕልማቸው ዳር እንዲደርስ ምክንያት እየሆነች ነው።
የፋሽን ዲዛይነር ሰናይት ጥበቡ ትባላለች። የፋብሪክ ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት ባለቤት ናት። ተወልዳ ያደገችው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የደብረብርሀን ከተማ ነው። በልጅነቷ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ ያስጠራው አትሌቲክስ (ሩጫ) ወዳጅ ነበረች። ትምህርት ቤቷን በመወከል በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። የፋሽን ዲዛይን ሙያ ቀዳሚ ምርጫዋ ባይሆን ኖሮ ዛሬ ሰናይትን በስፖርት መድረኮች ላይ ልናያት እንችል እንደነበር ፈገግ እያለች ትናገራለች።
ሰናይት ከቤተሰቦቿ ሳትርቅ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን በደብረብርሃን ከተማ ተከታትላች። በቀለም ትምህርት አቀባበሏ ጎበዝ ስለነበረች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል የግድ የትውልድ መንደሯን ትታ የካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት ወደሚገኝበት ዱራሜ ማቅናት ነበረባት። ይህ የቤተሰቡ ውሳኔ የሰናይትን የሕይወት አቅጣጫ ያስቀየረና ለዛሬ እሷነቷ መሰረት የጣለ ጭምር ሆነ።
ዱራሜ- የአዳሪ ትምህርት
ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆነችው ዲዛይነር ሰናይት የዱራሜ የካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በምትከታተልበት ወቅት ቀደም ሲል ከነበራት ስፖርታዊ ፍቅር ባሻገር ተሰጥዖ እንድታገኝ የሚያስችላት አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። በጊዜው የአዳሪ ትምህርት ቤቱ በግቢው የጥልፍና ስፌት ትምህርት ቤት ነበረው። በመምህራኑ በኩል ተማሪዎች በቀለም ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ ግፊት ቢኖርም ለሙያው ፍላጎት የነበራቸውን ተማሪዎች ያለምንም ጫና እውቀቱን እንዲያገኙ እድሉ ይፈጥርላቸው ነበር። ሰናይት ወደ ዱራሜ ከመምጣቷ በፊት በአንድ የካቶሊክ ሲስተሮች ቤት አዳነች ወልደሰንበት በምትባል ሲስተር አማካኝነት የሹራብ መስሪያ ማሽን የማየት አጋጣሚውን አገኘች፡፡ ወደ ስልጠናው ለመግባትም ልዩ ፍላጎት አደረባት።
በዚህ አጋጣሚ ነው በዱራሜ አዳሪ ትምህርት ቤት ሰናይት ሲስተር ማርያ ሮዛ ከምትባል ጣሊያናዊት ልዩ ድጋፍና ክትትል አግኝታ የጥልፍ፣ ዲዛይንና፣ ስፌት ሙያን ክረምት ላይ መማር የጀመረችው። በዚያን ጊዜ የሙያው ፍቅር እና የወደፊት ህልሟም አብሮ ተወለደ።
ከሕንድ፣ ከጣሊያንና ከተለያዩ አገራት የመጡ መምህራን በፍጥነት በምታሳየው ለውጥና በስራዋ ብቃት ይደሰቱና ያበረታቷት እንደነበር ታስታውሳለች። የትምህርት ቤቱን የፀሎት ቤት ዲኮር ስታደርግና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲኖሩ ለስራው ሰናይት ተመራጭ ሆነች። የቀለም ትምህርቷን ሳይነካ የፋሽን ዲዛይኒንግ ፅንሰ ሀሳብን መማሯ ይበልጥ ወደ ዘርፉ እንድትሳብና ፍቅሩ እንዲያድርባት አደረጋት።
የፋሽን ዲዛይነሯ ሰናይት ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በዱራሜ ካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት የቀለም ትምህርቷን ተማረች። ከዋናው ትምህርቷ ውጪም የዲዛይንና ፋሽን ሙያ ፍቅር እንዲኖራት ትምህርት ቤቱ ምክንያት ሆነላት። በዚህ ሁኔታ ላይ ነበር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የተፈተነችው። በወቅቱ ውጤት አምጥታ የቀድሞው ናዝሬት ቴክኒካል ኮሌጅ የአሁኑ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ተመደበች። ይሁን እንጂ የደረሳት የትምህርት ክፍል ሰናይትን ከሕልሟ የሚያደርስ አልሆነም። ነገር ግን በኮሎጁ ቆይታ አድርጋ በኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ ሙያ ትምህርቷን ተከታተለች።
የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን ሰናይት የዲዛይን እና ፋሽን ፍቅር ቢያሸንፋትም ለቀለም ትምህርት እጅ የምትሰጥም አልነበረችም። የመጀመሪያ ድግሪዋን ያዘች፤ ይህን ይዛ ስራ ወደመፈለግ ግን አልገባችም። ይልቁኑ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ከተመረጡ ከ5 የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራ ወደነበረው ‹‹Africa Virtual University›› በኮምፒውተር ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ በመማር ኢንተርናሽናል አድቫንስ ዲፕሎማ መያዝ ቻለች። በዚህም ሙያ ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ የኮምፒውተር መለዋወጫ ሱቅና ኢንተርኔት ቤት ከፍቶ መስራትን ምርጫዋ አደረገች።
በካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት በጥብቅ ስነ ምግባር እና የስራ ጥንካሬ ነበር ታንፃ የተማረችው። ወደ ስራው ዓለም ስትገባም ይህ ተፅዕኖ አድርጎባት በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ የከፈተችው ሱቅ ለደንበኞች በሚማርክና መንፈስን በሚያድስ የዲዛይን ውጤት የተከፈተ ነበር። በአካባቢው ተመራጭና ብዙዎች የሚያዘወትሩት የኢንተርኔት እና የንባብ ክፍልም ነበረው። የንግድ ዓለሙን ስትቀላቀል ንፅህና፣ ማራኪ ገፅታ፣ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳብ የሰናይት መርሆች ሆነው የሕይወት መንገዷን ተቀላቀሏት።
ቤተሰብና ንግድ
‹‹በስራው ትንሽ እንደቆየሁ ቤተሰብ መስርቼ ልጆች ወለድኩ›› የምትለው የፋሽን ዲዛይነሯ፣ በአዲስ አበባ ኑሮዋን ብታደርግም በባለቤቷ ስራ ምክንያት ወደ ትውልድ አካባቢዋ ደብረብርሀን ከተማ ለመመለስ ተገደደች። ወደ ደብረብርሃን የመመለሷ ዋና ሀሳብ ባለቤቷ በከፈተው ትምህርት ቤት በመስራት ድጋፍ ማድረግ ቢሆንም እንዳሰበችው ግን እቅዷን ሳታሳካ ቀረች። ይህን ጊዜ በራሷ የንግድና የፋሽን ዲዛይን ሀሳብ ተጠመደች።
የሰናይት የልጅነት ሕልሟ የዲዛይንና ፋሽን ሙያ ለዓመታት በቤት ውስጥ ብቻ ተገድቦ ቆየ። ልጆቿንና ቤቷን በፈጠራ ስራዎቿ ማስዋብ ብትችልም ወደ አደባባይ ወጥታ ሙያዋን ለማሳደግ ግን ሁኔታዎች አልፈቀዱላትም ነበር። ወደ ሕልሟ ለመቅረብ ግን ጥረቷን አላቆመችም። እዚያው ደብረብርሃን እያለች የሴቶች አልባሳት መሸጫ ቤት የመክፈት ሀሳብ ይመጣላታል። ወዲያው ተግባራዊ ታደርገዋለች። በጊዜው ሴቶች ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርግ ቡቲክ ቤት ስላልነበር የንግድ ሀሳቧ ወዲያው ተቀባይነት አገኘ።
በሳምንት ሁለት ሶስት ጊዜ ወደ መርካቶ በመምጣት ተወዳጅነት ያላቸው አልባሳትን መርጣ በማቅረብ ገበያውን መቆጣጠር ቻለች። ከቀድሞ ስራዋ አንፃርም ልብስ ቤቱ ለፋሽንና ዲዛይን ፍቅሯ የቀረበ በመሆኑ በፍላጎት ነበር የምትሰራው። በዚህ ሁኔታ በደብረብርሃን ለአራት ዓመታት ስትሰራ ቆየች። በትውልድ ከተማዋ የጀመረችው ንግድ ግን ሊዘልቅ አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ ለልጆች የተሻለ ትምህርት ፍለጋ በቋሚነት አዲስ አበባ መመለስ ነበረባት።
ወደ አዲስ አበባ
ዲዛይነር ሰናይት ቤተሰቧንም ንግዱንም ወደ አዲስ አበባ በቋሚነት ይዛ መጣች። በወቅቱ የባለቤቷ ስራ ደብረብርሃን የሚያመላልስ በመሆኑ ልጆቻቸውን የመንከባከብ ተደራቢ ኃላፊነት ነበረባት። ለጫናው ሳትበገር ስራዋን ቀጠለች። በተጨማሪም ለፋሽን ዲዛይኒንግ ሙያዋ የሚያግዛትን ትምህርት ከአልባሳት ንግዱ ጎን ለጎን መማር ጀመረች።
አጫጭር ስልጠናዎችን በተለያዩ የፋሽን ዲዛይኒንግ ትምህርት ቤት ወሰደች። በዚህ ሳታበቃ አራኬል በሚባል ኮሌጅ በጀርመኖች ስፖንሰር አድራጊነት የሚሰጥ ስልጠናን ተከታተለች። ቀድሞ የነበራት ልምድና ተሰጥዖ ስላገዛት አራት ዓመት የሚወስደውን ስልጠና በአንድ ዓመት ውስጥ በብቃት ልታጠናቅቅ ቻለች። ከዚህ በኋላ ነበር ሰናይትና የፋሽን ዲዛይን ሙያ በሙሉ ጊዜ የተገናኙት።
ስልጠናዎቹን እንዳጠናቀቀች ባለቤቷ በስጦታ በገዛላት ልብስ መስፊያ ማሽን (ሲንጀር) በቤት ውስጥ የፈጠራ ውጤቶቿ የሆኑ አልባሳት መስራት ጀመረች። የትዳር አጋሯ ድጋፍና ማበረታታት ወደ ስኬት ይገፋት ጀመር። ጓደኞቿ፣ በማኅበራዊ ድረ ገፅ የምታገኛቸው ደንበኞች ጭምር ምርጫቸው አደረጓት። በዚህ ጊዜም ከሙያዋ ጋር የተያያዙ የፈጠራ ውጤቶቿ ሕይወት መዝራት የጀመሩ።
ኮቪድ-አዲስ የፈጠራ መንገድ
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ መከሰት ሰናይትና ባለቤቷ የጀመሩትን ንግድ ክፉኛ ጎዳው። ትምህርት ቤቱንም አልባሳት መሸጫውንም ለመዝጋት አስገደዳቸው። ሰናይት ግን ዓለም አቀፍ ፈተናን በደቀነው ወረርሽኝ ምክንያት እጅ ለመስጠት አልፈቀደችም። ይልቁኑ በቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቀመጧ ለአዲስ የፋሽን ዲዛይኒንግ ፈጠራ ሀሳብ ረድቷታል። በብዛት የሰራቻቸውን አልባሳት ለማስተዋወቅና የሙያ ደረጃዋን ለማሳደግ የጎዳና ላይ ፋሽን ትርዒት የማዘጋጀት ሀሳብ የመጣላትም በዚያው ጊዜ ነበር። በማኅበራዊ ሚዲያ ስራዎቿን ማስተዋወቅም ቻለች።
‹‹በኮቪድ ጊዜ በርካታ ልብሶችን ዲዛይን ማድረግ ቻልኩ። ኢትዮጵያዊ ባሕልን የሚወክሉ፣ ዘመናዊና ለተለያየ የአየር ፀባይ ወቅቶች የሚለበሱ ነበሩ›› የምትለው ዲዛይነር ሰናይት፤ በቀላል ወጪና በአገር ውስጥ በሚገኙ ጨርቆች አስውባ እንደሰራቻቸው ትናገራለች። እነዚህን ልብሶች የምታስተዋውቅበት አጋጣሚ ስታስብ ነበር ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያልተለመደውን ‹‹የጎዳና ላይ የፋሽን ትርዒት›› ለማዘጋጀት የወሰነችው።
የጎዳና ላይ የፋሽን ትርዒት
የሰራቻቸው አልባሳት ለእይታ እንዲበቁና እንዲተዋወቁ እውቅ ሞዴሎችን ተጠቅማ የፋሽን ትርዒት ለማዘጋጀት ወሰነች። ሂደቱ ግን ቀላል አልነበረም። ሕዝብ የሚበዛበት አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎች በር ላይ ፍቃድ ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጋለች። ተባባሪ አካላትን በሚፈለገው መንገድ አለማግኘት፣ የፋይናንስ እጥረትና አንዳንድ አካላት ለዘርፉ ትክክለኛ ግንዛቤ አለመያዛቸው ቢፈትናትም እጅ እንዳልሰጠች ትናገራለች።
የጎዳና ላይ ፋሽን ትርዒቱን ለማድረግ ያሰበችበት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያዊ ምርት፣ ቀለምና ባሕል ያለውና ዘመናዊ ልብስ በቀላል ዋጋ ሊሰራ እንደሚችል ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር። ይህንን ሀሳቧን ይዛ አልባሳቱን ዲዛይን አድርጋ እና ሞዴሎቿን መርጣ አጠናቀቀች።
ከብዙ ጥረት በኋላ የጎዳና ላይ የፋሽን ትርዒቱንም በገርጂ አልፎዝ ህንፃ ስር ለብዙ ሺ ሕዝብ በነፃ አሳየች። ወቅቱን መለስ ብላ ስታስበው ‹‹ፈተናዎች የነበሩት ቢሆንም እጅግ ስኬታማና ለዛሬ የፋብሪከ ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት መፀነስ መሰረት ነበር›› ትላለች።
ፋብሪክ- የዲዛይንና ፋሽን ማሰልጠኛ
ዲዛይነር ሰናይት የመጀመሪያውን የጎዳና ላይ ፋሽን ትርዒት ካደረገች በኋላ ስራዎቿ በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት አገኙ። በሙያው የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲኖራት የሚገፋፏት በዙ። በርካታ ደንበኞችን አፈራች። ከዚህ በኋላ ነበር ለበለጠ ራዕይ መትጋት የጀመረችው። እርሷ የመጣችበትን መንገድ ለማቅለልና በሙያው ብዙሃንን ለማፍራት በማሰብ የዲዛይኒንግ ትምህርት ቤት ለመክፈት ወሰነች። በዚህ ጊዜም የባለቤቷ ድጋፍ አልተለያትም። እቅዷን በአምስት ዓመት ውስጥ ለማሳካት አስባ የነበረ ቢሆንም፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ተግባራዊ አደረገችው። ፋብሪክ የዲዛይኒንግ ትምህርት ቤት በተለምዶ ፊጋ ፍየል ቤት በሚባለው አካባቢ በሰናይት ራዕይ ከስምንት ወር በፊት ተመሰረተ።
የሰናይት የዲዛይኒንግና ፋሽን ሙያ ከንግድና ከጎዳና ፋሽን ትርኢት አልፎ የዘርፉ የልህቀት ማእከል ለመሆን እየተንደረደረ ይገኛል። በመጀመሪያው ዙር ከ90 በላይ ተማሪዎች ሙያውን ተምረዋል። መምህራንን ጨምሮ ስምንት ሰራተኞችን ቀጥራ እያሰራች ትገኛለች። የጎዳና ላይ የፋሽን ትርዒቱንም ለሁለተኛ ገዜ በራሷ ዲዛይንና ሞዴሎች ለእይታ አብቅታለች።
‹‹ተማሪዎቼ ሕልማቸውን እንዲከተሉ አበረታታለሁ። ያለኝን እውቀት ሳልሰስት ልክ እንደቤተሰብ አጋራለሁ›› የምትለው ሰናይት፤ ማኅበራዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት ሙያውን መማር ፈልገው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የነፃ የትምህርት እድል እንደምትሰጥም ትናገራለች። አጠቃላይ ተማሪዎቿ ቤተሰባዊ ስሜት እንዲያድርባቸው ከማድረግ ባሻገር የሚማሩበት ከባቢ ምቹና ንፁህ እንዲሆን እንደምትተጋ ትገልፃለች። ሕሊና እረፍት አግኝቶ የፈጠራ ስራም የሚበረታታው ምቹ ከባቢ ሲኖር እንደሆነ ስለምታምን ትምህርት ቤቷም በዚያ የተቃኘ ነው።
የዲዛይነሯ ራዕይ
ዲዛይነር ሰናይት ፋብሪክ በፋሽን ኢንዱስትሪው ተፅእኖ የሚፈጥሩ ባለሙያዎችን እያፈራ እንደሚቀጥል ትናገራለች። ቅርንጫፎችን አስፍታ ዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ መድረስ ቀጣይ ሕልሟ ነው። ኢትዮጵያዊ ቀለምና የባሕል ተፅእኖ ያረፈባቸውን አልባሳት በጋርመንት (ኢንዱስትሪ ደረጃ) ለማቅረብ እንደምትተጋም አልሸሸገችም።
ሌላው የዲዛይነር ሰናይት እቅድ ለሁለት ጊዜ ያካሄደችውን የጎዳና ላይ የፋሽን ትርዒት ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በኢትዮጵያ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች ማቅረብ እንደሆነ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራት ቆይታ አጫውታናለች። እኛም የልብ መሻቷ እንዲደርስ እየተመኘን ለዛሬው አበቃን!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም