ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለኢንዱስትሪዎቿ የሚያስፈልጋትን የድንጋይ ከሰል ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ በመመደብ ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች። ይህ ደግሞ ሲሆን የኖረው ሀገሪቱ በቂ የድንጋይ ከሰል ጥሬ እቃ ክምችት እያላት ነው፡፡ መንግስት ለማእድን ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረቱ ስራ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቶበታል፤ እየሰራበትም ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎም ባለፈው ዓመት ሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ፍላጎቷን ማሟላት የቻለችው በሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርት ለመተካቱ ስራ መንግስት አሁንም ትኩረት ሰጥቶታል። የማዕድን ሚኒስቴር በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ከሲሚንቶ እና ከድንጋይ ከሰል አምራች ኩባንያዎች ጋር ውይይት ባካሄደበት ወቅት የተጠቆመውም ይሄው ነው። በድንጋይ ከሰል ምርት ዕቅድ ላይ ሚኒስቴሩ ከአምራቾቹ ጋር ባደረገው ውይይት ወቅትም በዋናነት ሲጠቀስ የነበረው ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ጉዳይ ነበር፡፡
በሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ሀብት በስፋት በሚገኝባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የድንጋይ ከሰል ልማት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የድንጋይ ከሰል ሀብት፤ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የዳውሮ ዞን ይጠቀሳል፡፡ የዚህን ሀብት መኖር ተከትሎ በዞኑ በታርጫ ዙሪያ ወረዳ የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን፣ በዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ይህን የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካ በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡ ፋብሪካውን እያስገነባ ያለው የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የተባለው ኩባንያ ሲሆን፣ ግንባታውም ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቅቋል፤ በቅርቡ ይመረቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ከውጭ አገር የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት አገሪቱ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ስታስመጣ የምታወጣን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት አኳያ የፋብሪካው ሚና የጎላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በመጠቀም ረገድም ሆነ በአካባቢው ለሚገኙ የስራ እድልን በመፍጠር በኩል የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካው ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡
የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር በላይ አሰፋ ፋብሪካው ግንባታው ተጠናቅቆ ወደስራ ሲገባ በሰዓት 150 ቶን የድንጋይ ከሰል ማጠብ እና ማበልጸግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ በቀን 24 ሰዓት ከሰራ ደግሞ ሶስት ሺ 600 ቶን ማምረት እንደሚችል ገልጸዋል። ይህ አቅሙ በዓመት ሲሰላ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የማጠብና የማበልጸግ አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ፤ አትዮጵያ ለድንጋይ ከሰል ከ350 እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ወጪ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል ፍጆታ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፋብሪካው ይህን የሀገሪቱን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ያሟላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ማለት በአገር ውስጥ ትልቅ ፍላጎት እንዳለ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
የዳውሮ ዞን በማዕድን ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ የበለጸገ ቦታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት እንዳለው በመታወቁ ነው የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር በቢሊዮን ብር ኢንቨስት እያደረገ የሚገኘው፡፡
የአክሲዮን ማህበሩ ተወካይ አቶ ወንድሙ ምትኩ ለኢፕድ እንዳሉት፤ ኢቲ በማዕድን ሚኒስቴር በ2014 ዓ.ም ከተመረጡ ስምንት ኩባንዎች አንዱ ነው፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ በዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ በ2014 ዓ.ም በወቅቱ የማዕድን ሚኒስትር የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሲሆን፣ በወቅቱ ኢስት አፍሪካ የሚባለው ኩባንያ ለሚገነባው ተመሳሳይ ፋብሪካም በዚሁ በዳውሮ ዞን የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ነበር። ይሁንና ኢስት አፍሪካ ኩባንያ እስካሁን ግንባታውን አልጀመረም፡፡
የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካው የሚገኘው በዳውሮ ዞን፣ በተርጫ ዙሪያ ወረዳ፣ ላላ ገንጃ ቀበሌ ነው፡፡ ኩባንያው ወደስራ የገባው አጠቃላይ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ ነው፡፡ ፋብሪካው ለግብዓት ምልልስ ያመቸው ዘንድ መንገድ ጭምር ገንብቷል፡፡ በእስካሁኑም ሒደት ለግንባታው ወደ አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ወጪ ወጥቷል ሲሉ ተወካዩ ተናግረዋል፡፡
የኩባንያው ትልቁ ድርሻ የታጠበ የድንጋይ ከሰል ማቅረብ ነው የሚሉት የአክሲዮን ማህበሩ ተወካይ አቶ ወንድሙ፣ ይህ ፋብሪካ የተገነባውም ከውጭ አገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት ለማስቀረት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ወደስራ የተገባውም ከውጭ አገር ከሚመጣው የድንጋይ ከሰል 75 በመቶውን ኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር ኩባንያ ይሸፍናል ተብሎ ነው ብለዋል፡፡
በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ እንደሚችል ጠቅሰው፣ ፋብሪካውን የመገንባት ስራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል። የቀረው የኢንስታሊሽን ስራ ደግሞ ተጠናቅቆ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለምረቃ እንደሚበቃ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ወንድሙ እንደሚሉት፤ በአካባቢው የድንጋይ ከሰል ክምችት መኖር ባለሀብቱን ወደስፍራው እንዲሳብ አድርጓል፡፡ የባለሀብቶች ወደ አካባቢው መሳብ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብዙ እድሎችን ይዞ መጥቷል፡፡ ለአብነትም ፋብሪካው ለላላ ገንጂ ቀበሌ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ወደ 900 የሚደርሱ ተማሪዎች ደብተርና እስክሪብቶ ልገሳ አደርጓል፡፡ ይህም በብር ሲታሰብ አንድ ሚሊዮን 330 ሺ ብር ነው፡፡ በተጨማሪ በሸባ ዮኒ ቀበሌ አንድ ጤና ኬላ ሰርቶ አስረክቧል፡፡ በተመሳሳይ ላላ ገንጂ ቀበሌ ላይ የጤና ኬላ ግንባታ ተጀምሯል፡፡
ሌላኛው ስራ ደግሞ የዳውሮ ዞን ሕዝብ ለሚጠቀምበት ሆስፒታል መድኃኒት ማስቀመጫ እና መሸጫ ለመገንባት ፋብሪካው እቃ እያስገባ ይገኛል፡፡ የግንባታው የቅየሳ ስራ እያለቀ ሲሆን፣ ግንባታው ወደ ስድስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ በሌላ በኩል ተጨማሪ የመማሪያ ክፍል እጥረት ያለበት ትምህርት ቤት በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጥያቄ ቀርቦ ባለ አምስት የመማሪያ ክፍል ትምህርት ቤት ለመገንባት ቦታ ተረክቧል፤ እቃ ግዥ እያካሄደ ነው፡፡
ፋብሪካው ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የድርሻውን እየተወጣ ሲሆን፣ አንዳንዴ ስራው ከፍ ሲል እስከ 420 ሰራተኞችን ያሰማራል፤ ይህ አሀዝ የስራው ሁኔታ በቀዘቀዘ ጊዜ ደግሞ ወደ 187 አካባቢ ይወረዳል፡፡ ቋሚ ሰራተኞችን መቅጠር ገና እንዳልተጀመረም አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው የአካባቢ ብክለት እንዳያደርስ የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግም ተወካዩ አስታውቀዋል። ፋብሪካው በአካባቢው ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንዳይኖረው ዘመናዊ የተረፈ ምርት መልሶ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ፋብሪካ ልዩ የሚያደርገውም አካባቢውን የማይበክል እና ራሱ የሚያወጣውን ተረፈ ምርት መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
ፋብሪካው በጣም ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተሰራ እንደሆነም ጠቅሰው፣ ፋብሪካውን የሰሩ ቱርካውያን ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አንድ ዓመት ድረስ ራሳቸውን ከስራው ጋር በአግባቡ እስከሚያለማምዱ አብረው ሲሰሩ እንደሚቆዩም ጠቅሰዋል።
የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካውን የተከለው የቱርኩ ቡካ ማሽነሪ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እና ንግድ ኩባንያ ባለቤት ሊትፉ ዑዘር እንዳሉት፤ በዚህ ፋብሪካ ገጠማ ላይ ከ24 ዓመት በላይ ልምድ አላቸው፡፡ ያንን ልምድ በመያዛቸውም ወደ ተለያዩ አገራት በመሄድ ፋብሪካዎችን ይገጥማሉ፤ የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ማሽኑ የተገጠመው ከዚህ ጥሬ የድንጋይ ከሰል ተወስዶ በድንጋይ ከሰሉ ይዘት መሰረት ነው፡፡
ይህ በዳውሮ ዞን የተገጠመው ማሽን በተፈለገው አቅም ልክ እንዲሰራ ተደርጎ ነው፡፡ ከዚህ ማሽን ገጠማ 95 በመቶውን ያካሄዱት እሳቸው በራሳቸው ዎርክሾፕ ውስጥ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ማሽን በሚገጠምበትም ወቅት የፋብሪካው ባለቤት ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸው የገጠማቸው ችግር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ የፋብሪካው ባለቤት እና ስራ አስኪያጆች ስራው እንዲቀላጠፍ በማድረጋቸውም ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም አስችለውናል ብለዋል፡፡
እርሳቸው በሩሲያና ዮርዳኖስ በዚህ ማሽን ገጠማ ስራ ተሰማርተው ሰርተዋል፡፡ በቱርክም በተለያየ ቦታ ማሽኖቹን ገጥመዋል፡፡ በአፍሪካ ይህን ማሽን ሲገጥሙ ይህ የኢትዮጵያው የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ‹‹እዚህ መጥተን ስለሰራን በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ኢትዮጵያም ካሰብኳት በላይ ሆና አግኝቻታለሁ›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግርን አስመልክተን ላነሳንላቸው ጥያቄ ፋብሪካውን የገጣጠመው ኩባንያ ባለቤት በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ አሁን ባለው ሁኔታ ከቴክኒሺያኖቼ ጋር ያሉ ልጆች አምስት ያህል ናቸው። እነርሱም በደንብ እየለመዱ ነው፡፡ የሚሰሩትን ሁሉ እያዩ እና አብረውን እየሰሩም በመሆኑ ልምድ እየቀሰሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች ስራውን አልቆ ሲወጡ በፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ይሆናሉ፡፡
እንዲያም ሆኖ ማሽኑን ለተወሰኑ ጊዜ የሚያስቀጥሉ ሰዎች ከውጭ ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ማሽኑ ላይ ለሚሰሩ አካላት ስልጠና የሚሰጡ ናቸው፡፡ ለስራው የሚያስፈልገው የሰው ኃይል የሚወሰነው እዚህ ቴክኖሎጂውን እየተከታተሉ በሚገኙት ሰዎች አቅም ላይ ነው፡፡ ከእኛ ጋር እየሰሩ ያሉ ሰራተኞች የመስራት ፍላጎታቸው ከፍተኛና ስራውን በአግባቡም የሚከታተሉ ናቸው፡፡ ማስተማር ያለብንን በሙሉ እያስተማርናቸው ነው፡፡ ፋብሪካው ከአንድ ወር በኋላ ወደሙከራ ስራ ይገባል፡፡
ፋብሪካውን የገጣጠመው ኩባንያ ባለቤት ሊትፉ ዑዘር ‹‹እኛ፣ የብረት ማበልጸጊያ፣ የብርና የወርቅ ማበልጸጊያ ማሽኖችንም እንሰራለን፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የማይገኝ ላቦራቶሪም ገጥመናል፡፡ ይህ ላቦራቶሪ ከድንጋይ ከሰል ውጪ ያሉ ማእድናትን ለመፈተሽ አገልግሎትም ሊውል ይችላል›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ስንታየሁ መኩሪያ ጂኢሎጂስትና የኢቲ ማዕድን ልማት የላቦራቶሪ ባለሙያ ናቸው፡፡ በላቦራቶሪው ለአገልግሎት የተዘጋጁት እቃዎች ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመቱ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በሌሎች ፋብሪካዎች ያሉ ላቦራቶሪዎች ከሰሉ ከተቃጠለ በኋላ “ይህን ያህል ካሎሪ አለው” የሚለውን ብቻ የሚለዩ ናቸው፤ እንደ ኢቲ ማዕድን ልማት ላቦራቶሪ አይነት የድንጋይ ከሰሉን ጥራት አረጋግጦ የሚሰጥ ማሽን በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የለም ሲሉም ያብራራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢቲ ማዕድን ልማት፣ የድንጋይ ከሰሉን የካሎሪ መጠኑን፣ የአሽ ቫሊዩን ይለካል፣ መለካት ያለበትን ሁሉ መለካት ይችላል፡፡ መረጃ የምንሰጠውም እያንዳንዱን መለካት ያለበትን ለክተን ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡
የላቦራቶሪ ባለሙያዋ ስንታየሁ የማዕድን ከፍተኛ ባለሙያ እና የስራ አስኪያጁ አማካሪም ጭምር ሲሆኑ፣ ላቦራቶሪው ገና የድንጋይ ከሰል ጥሬ እቃውን ሲቀበልም ሆነ ጥሬ እቃው ፋብሪካ ገብቶ ከወጣም በኋላ በላቦራቶሪው ፍተሻ እንደሚደረግበት ይናገራሉ፡፡ በተለይም ከሰሉ ከታጠበ በኋላ ውጤቱ ምን አይነት ደረጃ ላይ ደረሰ የሚለውን እና ምን ያህል እሴት ጨመረ የሚለውም እንደሚፈተሽ አስታውቀዋል፡፡
ላቦራቶሪው ዘመናዊ መሆኑን የገለጹት ባለሙያዋ፤ በአሁኑ ወቅት ለተቋቋመለት ፋብሪካ ይስራ እንጂ ለሌሎችም መስራት የሚያስችለው አቅም እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሱት የተሰራበት ሌላው ጉዳይ አንዱ ገበያ ማስገኛም ጭምር ስለሆነ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ፋብሪካው በሳምንት ውስጥ የሚፈትሽው የድንጋይ ከሰል መጠን አንድ መቶ ሺ ቶን ይሁን እንጂ ላቦራቶሪው ግን የሚፈትሽው የድንጋይ ከሰልን ብቻ አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፣ የአፈር ምርመራን ማድረግ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ላቦራቶሪ ማለት ለዚህ ለድንጋይ ከሰል ፋብሪካው ዋና ጉዳዩ ነው፡፡ እንዲያውም ፋብሪካው የሚመራው በላቦራቶሪው ነው ማለት ይቻላል፡፡ የትኛውን የድንጋይ ከሰል ማስገባት እንዳለበትና የትኛውን ከሰል ማውጣት እንዳለበት ሙሉ ለሙሉ የሚያስተካክለው ላቦራቶሪው ነው ሲሉም ያብራራሉ፡፡
መንግሥት በየዓመቱ የድንጋይ ከሰል ከውጭ አገር ለማስገባት የሚያወጣው ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ በ2014 ዓ.ም ከማድዕን ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህንንም የድንጋይ ከሰል የሚያስገባው ከተለያዩ አገራት እንደሆነም መረጃው ያመለክታል፡፡ ይህን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረትና ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ለማስቀረት የተለያዩ ውሳኔዎች ላይ ተደርሶ ወደ ትግበራ መገባቱ ይታወሳል፡፡
በዳውሮ ዞን እየተገነባ ያለው የድንጋይ ከሰል ማበልጸጊያ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ ሲገባ ለብረት፣ ወረቀት፣ ሲሚንቶ፣ ሴራሚክ እና ሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ማቅረብ ይችላል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2016