የአካል ጉዳተኞች ድምጽ

አንዳንድ ቅን ሰዎች አሉ፤ እነርሱ ያሳለፉትን ችግር ሌሎች እንዳይገጥማቸው ሲሉ ልምዳቸውን በተለያየ መንገድ የሚያካፍሉ። በዚህ ሥራቸው እነርሱ በርትተው ሌላውን ያበረታታሉ። ጠንክረው ላልጠነከሩት ብርታት እና አርአያ መሆን ይቻላቸዋል። «አይቻልም» ብለው ተስፋ ለቆረጡትም የ«ይቻላል!!!» መንፈስን በማጋባት የፅናት ምሳሌ እስከመሆን ይደርሳሉ።

ነገሩን ከአካል ጉዳተኞች ጋር ስናያይዘው ደግሞ በርካቶቹ እንደ ጉዳት ዓይነታቸው የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው እሙን ነው። ከመረጃ እጦት እና ከአመለካከት ጋር የተያያዘ ችግር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ፈታኝ ሲያደርግባቸው ይስተዋላል። ይህን ችግራቸውን ከግንዛቤ በማስገባት ክፍተቶቻቸውን ለማጥበብ የራሳቸውን ልምድ እና ሌሎች መረጃዎችን በማሰባሰብ የሚሠሩ ግን ጥቂቶች ናቸው።

ኤደን እቋር ትባላለች። ጋዜጠኛ፣ ገጣሚ እና በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ፈጠራ እና መብት ላይ በስፋት ትሠራለች። «ልሳን ለአካል ጉዳተኞች» (Lesan For Disability Organization) የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ስትሆን «አካል ጉዳተኝነት እና እርግዝና» የተሰኘ መጽሐፍም ለንባብ አብቅታለች።

ኤደን መጽሐፉን ለመጻፍ ምክንያት የሆናት አካል ጉዳተኞች በመረጃ እጦት በርካታ ችግሮች እንደሚገጥማቸው በማሰብ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው። በተለይም አካል ጉዳተኛ ሴቶች በእርግዝና፣ በወሊድና በአራስነት ወቅት የሚያጋጥሙ አብዛኞቹ ችግሮች ቀድመው ቢታወቁ በቀላሉ መታለፍ የሚችሉ መሆናቸውን ከራሷ ልምድ በመነሳት ሌሎች ያለጭንቀት እንዲያልፉት ለማድረግ የድርሻዋን አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ኤደን መረጃዎችን ቀድማ አግኝታ ቢሆን ኖሮ ሊያጋጥሟት የሚችሉትን ነገሮች ቀድሞ ለመረዳት እንደሚያስችላት በመግለጽ፤ በተለይም ለሌሎች አካል ጉዳተኛ እህቶቿ ይህንን መጽሐፍ በሚገባ ቀድመው ተረድተው እንዲዘጋጁበት ያግዛል ትላለች። በተጨማሪም ብዙ አካል ጉዳተኛ እናቶች ካላስፈላጊ የሥነ ልቦና እና ተጨማሪ የአካል ጉዳት ሊጠበቁ ይችላሉ ብሎ በማሰብ በጋዜጠኝነት ሙያዋ ስትሠራ ብዙ አካል ጉዳተኞች ከወሊድ ጋር ተያይዞ የገጠማቸውን ችግሮች ጠንቅቃ ታውቃለችና እውቀቷን እና ልምዷን ለማካፈል፤ እንዲሁም ያለውን የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍ በሚልም መጽሐፉን እንደፃፈችው ታስረዳለች።

ድርጅቱም ዲጂታል ተደራሽነትን እውን ለማድረግ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ ከሚያሠራቸው እና ሊሠራቸው ካሰባቸው መካከል መረጃዎችን በስፋት ማዳረስ አንዱ ሲሆን፤ መጽሐፉም http://www.lesanfordisability.org ድረ ገፅ ላይ ይገኛል። አካል ጉዳተኞች የተለያዩ መረጃዎችን እና መጽሐፉን ከድረ-ገጹ በቀላሉ አውርደው ማንበብ እንደሚችሉ ትገልጻለች።

ኤደን እንደምትገልጸው ከሆነ፣ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ በሚሠራው ሥራ ያለው መተባበር ሰፊ ክፍተት የሚታይበት ነው። ይህንን ለመቅረፍ ሲባል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፤ በተለይ በድረ-ገጹ አማካኝነት በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ ተብለው ይጠበቃል።

ሌላው ደግሞ አካል ጉዳተኞች ቢቻል ችግር እንዳይገጥማቸው ማድረግ፤ ካልሆነ ግን ችግራቸውን ማቅለል ይገባል። ለዚህ ደግሞ በተቻለ መጠን የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ እና መፍትሔ ላይ በማተኮር የተሻለ ነገር መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የምታስረዳው። መጽሐፉ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ቅርንጫፍ፤ እንዲሁም ካዛንቺስ በሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ የሚገኝ ሲሆን፤ ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ እስከ አራስነት የሚገጥሙ ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ቢታወቁ፣ ቅድመ ዝግጅት ቢደረግባቸው መልካም መሆኑን በመግለፅ ሌሎች አካል ጉዳተኞች እንዲጠቀሙበት መጽሐፉን ከማሳተም በተጨማሪ በነፃ እንዲዳረስ አድርጋለች።

በሕክምናም ይሁኑ ሌሎች ተቋማት ላይ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። መስማት ለተሳናቸው እና ማየት ለሚቸገሩ ሰዎች የምልክት ቋንቋ የሚችሉ ባለሙያዎች በመቅጠር እንዳይጉላሉ እና እንዳይጨናነቁ ማድረግ ይገባል። እርሷም ሁሉንም መረጃ እና አገልግሎት በተቻለ መጠን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እና አካታች ሆኖ ማየት ምኞቷ እንደሆነ ትናገራለች። በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት እቅዶች እንዳሏት የምትናገረው ኤደን፤ በተለይም ከዲጂታል ተደራሽነት እና አካል ጉዳተኞችን በጋዜጠኝነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ከማብቃት፣ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በኢኮኖሚ አቅማቸውን ከፍ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራዎች ለመሥራት እቅዱ እንዳላት ታስረዳለች።

አካል ጉዳተኞች በእያንዳንዱ አገልግሎት በሚባል ደረጃ በርካታ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። በትራንስፖርት፣ በመንገድ አመቺ አለመሆን፣ የሕንፃ ግንባታዎች ምቹ አለመሆንን ጨምሮ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው ይታወቃል። ኤደን እነዚህን ችግሮች ከመዘርዘር እና ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በተቻለ መጠን መፍትሔ ላይ አተኩሮ የተሻለ ነገር መሥራት ይገባል ባይ ነች። ለዚያም ነው ዛሬ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራች ያለችው። ሌሎችም ይህንን ሥራዋን እንድትገፋበት እያበረታቷት ይገኛሉ። እርሷም በሥራዋ ተማምነው ድጋፍ ለሚያደርጉላት እና ለሚያበረታቷት ሁሉ ምስጋናዋን ታቀርባለች።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 23/2016

Recommended For You