አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የኢንቨስትመንት ዘርፉን የማሳደግ ጥረት

የሲዳማ ክልል በሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ነው። ክልሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆኑ ምርቶች መገኛ ነው። በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በቡና አብቃይነታቸው ይታወቃሉ። ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችም ይመረቱበታል።

ክልሉ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከግብርናው በተጨማሪ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እድል የሚፈጥር ነው። በክልሉ ከ17 በላይ የማዕድን ዓይነቶች፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስዕቦች ያሉ መሆናቸውም ክልሉን በማዕድን እና በሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንቶች ተመራጭ ያደርጉታል።

ክልሉ የእምቅ ሀብት ባለቤት ከመሆኑ በተጨማሪ፤ በርካታ ስራ ፈላጊ ወጣት የሰው ኃይል መኖሩ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ናይሮቢ የሚዘልቀው መንገድ የክልሉን ዋና ከተማ ሐዋሳን አቋርጦ ማለፉ እና ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት መኖሩ በኢንቨስተሮች ተመራጭ እንዲሆን የሚያስችሉት መልካም አጋጣሚዎች ናቸው።

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የይርጋዓለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና የመሳሰሉት ትላልቅ የኢንቨስትመንት ተቋማት ያሉት እንደመሆኑም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶች የሚመረቱበት፣ ለኢንዱስትሪ ተቋማቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለሚያቀርቡ አርሶ አደሮች አቅራቢዎችም ምቹ ገበያ ያለበት ነው።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በ2016 የበጀት ዓመት በክልሉ ለ12 የግብርና፣ ለ34 የኢንዱስትሪ፣ ለ20 የአገልግሎት እና ለ44 የኮንስትራክሽን ዘርፍ ፕሮጀክቶች፣ በአጠቃላይ ለ110 ባለሃብቶች፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ያስመዘግቡታል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል መጠን ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው።

በክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ ፈቃድና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ሮባ እንደሚገልፁት፣ በስድስት ወራት ውስጥ አምስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 36 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። ፈቃድ የወሰዱት ባለሃብቶች በግብርና፣ በማምረቻ፣ በግንባታና በአገልግሎት ዘርፎች የሚሰማሩ ሲሆን፣ ለሁለት ሺ 265 ዜጎች ቋሚ ስራ እድሎችን ፈጥረዋል። ፈቃድ ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል በሴራሚክ ምርት ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ የወሰደ አንድ ኩባንያ ይገኝበታል፤ የኩባንያው አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገበ ነው።

አቶ ታሪኩ እንደሚናገሩት፣ በበጀት ዓመቱ ለግብርና ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠት የተጀመረው በሁለተኛው ሩብ ዓመት ነው። ‹‹በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለግብርና ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አልተሰጠም። አዲስ ፈቃድ ከመስጠት በፊት የቀድሞዎቹን የአፈፃፀም ደረጃ መገምገም አስፈላጊ በመሆኑ በዘርፉ ፈቃድ የወሰዱ ፕሮጀክቶች ኦዲት ተደርገዋል። በግብርና ዘርፍ በገቡት ውል መሰረት ስራ ያልጀመሩና አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፕሮጀክቶችን የመለየት ስራ ተሰርቷል›› ይላሉ።

በሲዳማ ክልል በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የሚሳተፉ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አቶ ታሪኩ ይናገራሉ። ባለፈው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች (99) መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች መሆናቸውን አስታውሰው፣ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥም በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለመሰማራት ጥያቄ አቅርበው ፈቃድ ከተሰጣቸው አልሚዎች መካከል አብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንደሆኑ ይገልፃሉ።

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ የኦንላይን (Online) እና የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰራሮች ተግባራዊ ተደርገዋል። እነዚህ አሰራሮች ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙና ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ የተሻለ እድል ፈጥረዋል። ይህም በአጠቃላይ የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ አፈፃፀም ላይ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።

ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት፣ የክልሉን ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ሀብት በጥናት መለየት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን የሚጨምሩ ጠንካራና ተከታታይ የፕሮሞሽን ስራዎችን መስራት እና ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ በበጀት ዓመቱ በላቀ ትኩረት እየተከናወኑ የሚገኙ ዋና ዋና ተግባራት ናቸው።

አቶ ታሪኩ በክልሉ ሦስት የኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል። እነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች የኢንቨስትመንት አቅም ጥናትና የመሬት ዝግጅት፣ ፕሮሞሽን እና ፈቃድና ክትትል መሆናቸውን አንስተው፣ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ረገድ ከማምረቻ ዘርፍ በተጨማሪ ክልሉ በአገልግሎት ዘርፍም በሐዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ትልልቅ ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን በመገንባት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ ደግሞ፣ አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ አብቃዮች በመሆናቸው በእነዚህ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ለክልሉ ኢንቨስትመንት፣ በተለይም ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች፣ እድገት ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ እድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱ ከሐዋሳ ከተማ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሆነ አቶ ታሪኩ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት ከ25 በላይ አልሚዎች ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ፈፅመው በተለያየ የትግበራ/ስራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ኩባንያዎቹ በመደበኛ ምርት፣ በሙከራ ምርት እንዲሁም በማሽን ተከላ ላይ ይገኛሉ። ኩባንያዎቹ በአቮካዶ፣ በማንጎ፣ በእንጆሪ፣ በቡና፣ በማር፣ በወተት፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአኩሪ አተርና በሌሎች ምርቶች ማቀነባበር ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው። በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ ከሚገኙት ኩባንያዎች፤ የአቮካዶ ዘይት በማቀነባበር ለውጭ ገበያ፣ ወተት እና የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲሁም የማር ምርትን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡት አምራቾች ይጠቀሳሉ። ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ወደ ውጭ ለመላክ በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት ተገኝቷል።

የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለምርት የሚያገለግለውን የጥሬ እቃ አቅርቦቱን የሚያገኘው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ነው። የአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል። አርሶ አደሮቹ የፓርኩ መጋቢ በሆኑ ሦስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት (በንሳ ዳዬ፣ አለታ ወንዶ እና ሞሮቾ አካባቢዎች የሚገኙ) እና በኅብረት ስራ ማኅበራት በኩል የአቮካዶ፣ የማር፣ የወተት፣ የቡናና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በፓርኩ ውስጥ ለተሰማሩ ለአልሚዎች እያቀረቡ ነው።

የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማር እንዲሁም የወተት ምርት የሚያቀርቡ ማኅበራት ግብዓቶችን የሚሰበስቡት በገጠር የሽግግር ማዕከላቱ በኩል ነው። ፓርኩ ግብዓቶችን በማቅረብ የገበያ ትስስርና የገቢ ምንጭ ከተፈጠረላቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ በየዓመቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል። ይህ ተግባር የሥራ እድል የመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የማስቀረትና ገቢ ምርትን የመተካት ድርብርብ ዓላማዎች አሉት።

ከሦስት ዓመታት በፊት ትልቅ ገበያ ያልነበረው የአቮካዶ ምርት በአሁኑ ወቅት ደረጃ ወጥቶለት አርሶ አደሩ በስፋት ምርቱን እያቀረበ፣ ገቢ እያገኘና አዳዲስ ዝርያዎችን እያለማ ነው። ፓርኩ አርሶ አደሩ ጥሬ እቃን በብዛትና በጥራት እንዲያቀርብ እድል እየፈጠረ ነው። ይህም የግብርና ምርታማነት እንዲጨምርና የአርሶ አደሩ ሕይወት እንዲሻሻል እያደረገ ነው።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው። በዚህ ረገድ በሲዳማ ክልል የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ሕብረተሰብ በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙ አቶ ታሪኩ ይገልፃሉ።

ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ሲሰማሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከሚያደርጉባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሥራ እድል ፈጠራ ነው። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የስራ እድል ፈጥረዋል። ከስራ እድል በተጨማሪ የክልሉ ሕዝብ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድልም ተጠቃሚ ሆኗል።

እንደ አቶ ታሪኩ ገለፃ፣ በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 207 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። አርሶ አደሮቹ የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ከሆኑባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ግብርና ነው። በግብርና ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የምርት ዘዴዎችንና ግብዓቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። ለአብነት ያህል በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አርሶ አደሮች ዘመናዊ የዶሮ እርባታ ስልት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸው እንዲሁም በንብ እርባታ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮች በነፃ ማቅረባቸውና ስለአጠቃቀሙም ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረጋቸው የዚህ ተሳትፎ ማሳያ ተደርገው የሚጠቀሱ ናቸው።

ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ስራዎቻቸውን በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራትን ስለሚያከናውኑ በዚህ ተግባር በኩል በርካታ የክልሉ ሕዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኗል። በክልሉ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና የትምህርት ግብዓቶችን በማቅረብ ለአገልግሎት አብቅተዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ አለመሆን፣ የብድር አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመመቻቸት እንዲሁም በመስመር ዝርጋታ እና በትራንስፎርመር እጥረት ምክንያት የሚፈጠር የኃይል አቅርቦት እጥረት በክልሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የተጋረጡ መሰናክሎች እንደሆኑ አቶ ታሪኩ ይናገራሉ። ለኢንቨስትመንት የተዘጋጀ መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ያለመሆን፣ ባለሀብቶች በገቡት ውል መሰረት ያለማልማት፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ያለመደገፍ ችግር እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ክፍተቶች በበጀት ዓመቱ እቅድ አፈፃፀም ላይ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብለው ከተለዩት ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

አቶ ታሪኩ ‹‹ከዘርፉ መሰናክሎች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት ችግር (የኃይል አቅም ማነስና መቆራረጥ) ነው። የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶችም ቅሬታ የሚያቀርቡበት የመሰረተ ልማት ዘርፍ ነው። በተለይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የኃይል አቅርቦት እንዲስተካከልላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። በፋይናንስ አቅርቦት ረገድም የኢንቨስትመንት ፕሮፖዛሎችን ገምግሞ ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት ችግር ይስተዋላል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ችግሮቹን ለማቃለል ጥረት እያደረግን ነው። ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ መፍታት ባይቻልም እንዲቃለሉ ተደርጓል›› ይላሉ።

አንተነህ ቸሬ

 አዲስ ዘመን ጥር 23/2016

Recommended For You