“ የዩኒየኖች እና የኅብረት ሥራ ማህበራት አመራሮች በኢንስፔክሽን ግኝቱ መሠረት ቢፈተሹ አንዳቸውም ከተጠያቂነት አይተርፉም”ልዕልቲ ግደይ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር

በከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ ቁጥር ተቋቁመው ለህዝብ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የአዲስ አበባ የህብረት ስራ ኮሚሽን ነው:: ዋና ዓላማውም የህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፎችን ለማድረግ ነው::

ማህበራቱ ዋና አላማቸው ይህ ይሁን እንጂ በተጨባጭ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በብዙ የተለየ እንደሆነ በስፋት ይነገራል ፣ በተለያዩ ከአሰራር መዛነፎች፤ ከሙስናና ከብልሹ አሰራሮች ጋር በተያያዘ ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ይነሳባቸዋል:: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባስጠናው ጥናትም የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ከፍተኛ የአሰራር ብልሽት እንዳለበት አመላክቷል::

የኢፕድ መልካም አስተዳደርና ስነ ምግባር ዝግጅት ክፍል የኮሚሽኑ የአሰራር ስርዓት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፤ማህበራት ከተቋቋሙበት አላማ አንጻር ለምን ውጤታማ እንዳልሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት መቀነስ ለምን ተሳናቸው በሚሉትና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ልዕልቲ ግደይ ጋር ቆይታ አድርጓል:: መልካም ምንባብ!::

 አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ የህብረት ሥራ ኤጀንሲ ወደ ኮሚሽን የመለወጡ ፋይዳ ምንድን ነው? ከስም ባሻገር በተግባር ምን ለመስራት ታስቧል?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ተቋሙ የስም ለውጥ ብቻ አይደለም ያደረገው፤ ዓላማውም የስም ለውጥ ማድረግ አይደለም:: ከዚህ በፊት ኤጀንሲ ሆኖ ሲሰራ በነበረበት ወቅት ተጠሪነቱ ለንግድ ቢሮ ነበር:: በዚህ ወቅት ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን አንጻር በስትራቴጂ እየተመራ አልነበርም:: ማህበረሰቡ ተቋሙን የሚያውቀው በአንዷ የስራ ዘርፍ በሸማቾች ማህበራት ብቻ ነው:: ስራው ግን ከዚህ የተሻገረ ነው ። ወደ ስምንት ሺ የሚደርሱ ማህበራት በውስጡ የያዘ ነው:: ከነዚህ ውስጥ 154ቱ የሸማች ማህበራት ብቻ ንግድ ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ነው::

ማህበራት እንደየተደራጁበት ዓላማ ትኩረት ይፍልጋሉ:: ለንግድ ቢሮ ተጠሪ ሆኖ እያለ ትኩረት የሚደረግበት ግብይት የሚያከናውኑት ሸማች ማህበር ብቻ ነው:: በመሆኑም ማህበራት መለወጥ ባለባቸው ልክ እንዳይለወጡ እና እንዲዘነጉ አድርጓቸዋል:: በዚህም በርካታ ማህበራት ለሀብት ብክነትና ለብልሹ አሰራር ተዳርገዋል:: የስም ለውጡ ከስያሜ ባሻገር ከዚህ በፊት በተለያዩ አካላት የሚነሱ ቅሬታዎችን እና ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው:: ከተጠሪነት ወጥቶ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮና ስልጣን ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ማድረግ ያስችለዋል በሚል ነው ።

ንግድ ቢሮ ትርፍን መሰረት አድርጎ የሚሰራ ነው:: ህብረት ስራ ማህበራት ደግሞ ከትርፍ ይልቅ አገልግሎትን የሚያስቅድሙ ተቋማት በመሆናቸው በንግድ ህጉ አይተዳደሩም:: በመሆኑም ንግድ ቢሮ ሸማቾችን የሚመራበት ህግና ሌሎች የንግድ ሥራዎችን የሚመራበት ህግ አንድ አይደለም:: በዚህ ሳቢያ ሸማች ማህበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማህበራት ማገልገል የሚለውን ሀሳብ በመርሳት የነጋዴነት ባህሪ እየያዙ መጥተዋል:: እነዚህን እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት በመሳብ የተቋሙን ስያሜ እና አሰራር እንዲቀየር የከተማዋ ካቢኔ ካጸደቀው በኋላ ለከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ቀርቦ ተጠሪነቱ ለከንቲባ በመሆን ስያሜው ኮሚሽን እንዲሆን ተወስኗል::

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ኤጀንሲ በነበረበት ወቅት ከተጠሪነቱ ባሻገር የአሰራር ከፍተቶች አልነበሩበትም?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡– ከአሰራርና ከአደረጃጀት አንጻር ክፍተት ነበር:: አሰራሮች ይጣሳሉ፤ ሸማቾችና ዩኔኖች ላይ ህገ ወጥ ግብይቶች ይከናወናሉ:: ይህም ከመመሪያ ጥሰት፤ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር ጋር ከፍተኛ ችግር ነበር:: ለምን ተደረገ? ተብለው ሲጠየቁም “ከንግድ ቢሮ ታዘን ነው” የሚል ምላሽ የሚሰጡ አካላት ነበሩ:: አዛዦች መብዛትም ለመልካም አስተዳደርና ለብልሹ አሰራር ዳርጓቸው ቆይቷል:: ሸማቾች ነጻ ማህበሮች ናቸው:: አሰራር ከተዘረጋላቸው በኋላ ነጻ ሆነው የመሸጥ መብት አላቸው:: ክትትልና ቁጥጥሩ ህግ መጣሳቸውን አለመጣሳቸውን ማየት ነው:: ለንግድ ቢሮ ተጠሪ ሆነው በቆዩበት ጊዜ ግን ለብልሹ ለአሰራር በር ከፍቶ ነበር::

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽን ከሆነ በኋላ ቀደም ሲል የነበሩ ጣልቃ ገብነቶችና ብልሹ አሰራሮች እየተቀረፉ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር አለ ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡– ኮሚሽን ከሆነ በኋላ አሰራሮች ተጠብቀው የአመራር ቅንጅቱም ወጥ ነው:: አማረም ከፋም ሰበብ የሚደረግበት ነገር አይኖርም:: የነበሩ ብልሽቶችን በተገቢው መንገድ ለመቆጣጠር የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን ሁሉንም ማህበራት በእኩል ሚዛን በመገምገም አመራር እየተሰጡ ክፍተቶችን እያረሙ ለመስራት ሰፊ እድል ፈጥሯል::

ከዚህ ቀደም ማህበራትም ከይዞታ አንጻር የመብት ጥያቄ ነበራቸው:: ነገር ግን ጥያቄአቸው በቀጥታ ለተገቢው አካል ይደረስ ስላልነበር ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም ነበር :: አሁን ላይ ቀጥታ ለኮሚሽኑ ተጠየቂ በመሆናቸው ከይዞታ እና መስል ጉዳዮች ጋር የተያዙ ጥያቄዎች ለከንቲባዋ በማቅረብ ምላሽ እንዲገኝበት ተደርጓል::

ይህም ወደ ከሚሽን ማደጉ ከስም ለውጥ ባሻገር አሰራሮችን በማስጠበቅ ጥራት ያለውና ወቅቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ፣ሸማቾችም የተሻለ ግብይት እንዲፈጥሩ ዕድል ፈጥሯል:: ወደ ከንቲባዋ የምንቀርበው በሦስተኛ ወገን ሳይሆን ቀጥታ ስለሆነ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ሪፎርሙ በማህበራቱ ላይ የሚነሱ የአደረጃጀትና የመዋቅር ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ነው?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ኤጀንሲው ኮሚሽን ከሆነ ስድስት ወሩ ነው:: ላለፉት ስድስት ወራት በጥናት ላይ የተመሰረተ የሪፎርም ስራዎን ሲሰራ ቆይቷል:: ሪፎርሙ ከማህበራት ጀምሮ እስከ ታች ያሉትን ሸማች ማህበራት ያካተተ ነው :: ከብልሽት የጸዳ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ማህበረሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ በሚያነሳባቸው ጉዳዮች ላይ መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው:: ጥናቱ ከላይ እስከ ታች ድረስ በሰው ኃይልና በአደረጃጀት መልስ ሊሰጥ በሚችል ሁኔታ ሪፎርም እየተደረገ ነው:: በዚህም ተገቢውን ግብዓት በማሟላት እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ አንድ ሺ 437 የሚሆኑ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓል::

ሪፎርሙ ማዕከል የሚያደርገው ይህን ብቻ አይደለም:: ዘጠኝ የሚደርሱ አገልግሎቶች እንዲዘምኑ ለማድረግ በጥናቱ ተለይተው እየተሰራባቸው ነው:: የግብይት ስርዓት፤ የማህበር ቤት አደረጃጀትና አያያዝ፤ የመዝናኛ ማዕከላት አያያዝ በህግና በአሰራር ማድረግ ይገኝበታል:: የመዝናኛ ማዕከላት በህግና በአሰራር የተደገፉ አልነበሩም:: ገቢ የሚደረጉ ሂሳባቸው በተቀናጀ መንገድ እየተያዘ አይደለም:: የተቋሙን የሰው ኃይል መልሶ ከተደራጀ ፣ 154ቱ ሸማች ማኅበራት የሰው ኃይላቸውን እንዲያደራጁ ከተደረገ በኋላ መዝናኛ ማዕከላት በአንድ የአመራርና የአሰራር ስርዓት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል:: የቤት ማህበራት አደረጃጀት ሲታይም ከተደራጁ በኋላ እንዴት እንደሚመሩ መመሪያ የለውም:: በዚህ ሳቢያ በየቦታው ከፍተኛ ቅሬታ አለ:: ይህን መመለስ የሚያስችል መመሪያና ተግባራዊ ይደረጋል::

አዲስ ዘመን፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ የከተማዋን ነዋሪ እየተፈታተነ ነው:: ይሁን እንጂ ማህበራትም ገበያውን በማረጋጋት በኩል ሚናቸው ዝቅተኛ ነው የሚል ቅሬታ ይነሳል:: ይህን እንዴት ይገመግሙታል?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- የሸማች ማህበራት በመደበኛው ስራቸው ለማህበረሰቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ አስፈላጊውን ምርት ማቅረብ ነው:: ከዚህ አኳያ ከአዲስ ዓመት ጀምሮ በሸማች የህብረት ስራ ማህበራት በቂ ምርት አቅርቦት እንዲቀርቡ ተደርጓል:: ከሁሉም ክልሎች ጋር በተለይ ከኦሮሚያ፤ አማራና ደቡብ ክልል ከሚገኙ ዩኒየኖች ጋር ምን አይነት ምርት እንደሚያቀርቡና ውጤታማ የምርት አቅርቦት ትስስር እንዲኖር ተደርጓል::

አቅርቦቱ በዓልን መሰረት ያደረገ ሳይሆን በየጊዜው ሸማች አለ፤ በየሳምንቱ የእሁድ ገበያ ስላለ ምርት ያለምንም እጥረት ይዘው እንዲቀርቡ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል:: ስጋ ቤቶች ከዚህ በፊት የነበራቸው የዋጋ ተመን ወጥ ስላልነበር ከስድስት መቶ እስከ አንድ ሺ ብር ድረስ የሚሸጡበት ሁኔታ ነበር:: ዝቅተኛ ገቢን ማዕከል አድርጎ ለመስራት አዲስ ዓመት ሳይገባ ጥናት በማካሄድ አንድ ኪሎ ስጋ ከ400 እስከ 460 ብር ድረስ እንዲሸጡ ተድርጓል:: ከዚህ በላይ መሸጥ አይችሉም::

አዲስ ዘመን፡- በኮሚሽኑ ከተቀመጠው ዋጋ በላይ ሲሸጡ በተገኙ ስጋ አቅራቢዎች ላይ የተወሰደ እርምጃ አለ ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ከተቀመጠው ዋጋ በላይ የሚሸጥ የሸማች ስጋ ቤት እርምጃ ይወሰድበታል:: በአዲስ ዓመት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከተቀመጠው ዋጋ በላይ ሲሸጥ ተገኝቶ እርምጃ ተወስዶበታል:: በሌሎች ላይም ክትትል ይደረጋል:: በገና በዓልም ከላይ የተጠቀሰውን ዋጋ እንዲያስቀጥሉ ተደርጓል::

ይህ ሲሆን ግን የእርድ ከብት ዋጋ ስለሚጨምር ይቸገራሉ:: በከፍተኛ ዋጋ በሬ ገዝተው በ400 እና በ460 ብር ኪሎ ስጋ መሸጥ አያዋጣም የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ:: ለዚህ እንደ መፍትሔ የቀረበው የአንድ ወር የቤት ኪራ እንዳይከፍሉ ነው:: ለምሳሌ የሱቁ ኪራይ ከ10 ሺ እስከ 20 ሺ ከሆነ ሸማቾች እንዳይቀበሉ ይደረጋል::

አዲስ ዘመን፡- በእሁድ ገበያ ላይ ሸማቾች ማህበራት ተገደው በጫና ኪሰራ ውስጥ ገብተው እየሸጡ እንደሆነ ቅሬታ ይነሳል:: በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ይከስራሉ የሚለውን መውሰድ አልችልም:: ትርፍን ብቻ ታሳቢ አድርገው አይሰሩም:: ትርፍን መሰረት አድርገው እንዳይሰሩ ጫና ይደረጋል:: መጫን ብቻ ሳይሆን ከተማ አስተዳደሩ አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ድጎማ አድርጎላቸዋል:: ድጎማውን ወለድ አይከፍሉበትም፤ በነጻ ተጠቅመው የተሰጣቸውን ብር ብቻ ነው የሚመልሱት::

ለምሳሌ ለአንድ ዩኒየን መቶ ሚሊዮን ብር ተሰጥቶ ከሆነ መጨረሻ መመለስ የሚጠበቅበት መቶ ሚሊዮን ብሩን ብቻ ነው:: ብሩ በልዩ ሁኔታ ድጎማ የሚደረግላቸው በቀላሉ ሳይቸገሩ ምርት ገዝተው ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ነው:: ሲሸጡ ግን እንደ ማንኛውም የግል ነጋዴ ትርፍን ብቻ ታሳቢ አድርገው አይደለም:: በዓል ሲመጣ አልፎ አልፎም ትርፍን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ እንዲሸጡ የሚደረግበት ሁኔታ አለ:: እንደ እቁላልና ዶሮ ሳያተርፉም ሳይከስሩም እንዲሸጡ ይደረጋል:: ስለዚህ የራሳቸው የአያያዝ ስርዓት ካልሆነ በስተቀር ከኮሚሽኑ የሚመነጭ ሸማቾችን እንዲከስሩ የሚያደርግ አሰራሩም አይፈቅድም፤ አይደረግም::

አዲስ ዘመን፡- በከተማ አስተዳደሩ ለህብረት ስራ ማህበራት የተመደበውን የተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ለታለመለት አላማ እየዋለ አይደለም ይባላል:: እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

 ወይዘሮ ልዕልቲ፡- በከተማ አስተዳደሩ የተዘዋዋሪ ፈንድ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር መድቧል:: ከዚህ በፊት የተዘዋዋሪ ፈንድ ብር ለዩኒየኖች ሲሰጥ የአሰራር መመሪያ አልነበረውም:: ለአንድ ዩኒየን እስከ መቶ ሚሊዮን ብር ይሰጣል:: ነገር ግን አጠቃቀሙ ላይ ሰፊ ክፍተት ነበር:: አንዳንድ ዩኔኖች በወለድ ጭምር ብሩን ያበድሩ ነበር:: ከዓላማ ውጭ በሆነ መንገድ ህንጻ ገዝተው ይሸጡበት ነበር:: ሌላ አካውንት በማስቀመጥ ወለድ ለማግኘት ተጠቅመውበታል::

የብሩ ዓላማ ዩኒየኖች ምርት እንዲገዙበትና ለመሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ማቅረበ ነው:: ሪፎርሙ ካስተካከላቸው አሰራሮች የተዘዋዋሪ ብድር ብር ማን ምን ስለሰራ እንዴት ይሰጠዋል? የሚለው አንደኛው ነው :: የብር አሰጣጥና አመላለስ መመሪያ እንዲኖረው መመሪያው ለፍትህ ቢሮ ተሰትቷል:: ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል ማን መውሰድ እንዳበትና እንዴት መመለስ እንደሚገባው ቸግር አይሆንም:: መመሪያው ስራ ላይ እስከሚውል ድረስ ግን የተዘዋዋሪ ፈንዱን በተመለከተ ኦዲት ተሰርቶ ዩኔኖች የተዘዋዋሪ ብርና መደበኛ ብራቸውን የሚያስቀምጡበት አካውንት ኦዲት ተደርጓል:: ተዘዋዋሪ ፈንዱ ምን ላይ እደዋለ በቦታው በመሄድ በትክክልም ለተገቢው ምርት ግዥ መዋሉን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው::

አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ተዘዋዋሪ ብድሩ በትክክል ሥራ ላይ እንዲውል ምን እየተሰራ ነው፤ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ካልዋለስ ምን እርምጃ ይወሰዳል?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- የተዘዋዋሪ ብድር ገንዘብ የሚወስዱ ዩኒየኑ እንደ ጤፍ፤ ዱቄት፤ ፓስታና መኮረኒ ምርቶ እንዲገዙበትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማች ማህበራት እንዲያሰራጩ ለማድረግ ነው:: በከማው 11 ዩኒየኖችና 154 ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አሉ፤ ተዘዋዋሪ ፈንዱን በአግባቡ ያልተጠቀሙ ዩኔኖች በኢንስፔክሽን ከተገኙ አመራሮች ከሥራ ማገድ እስከ ህግ መጠየቅ ድረስ የሚደርስ እርምጃ ይወሰድባቸዋል:: በትክክል በመጠቀም ምንም አይነት የኦዲት ችግር ያልተገኘበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ዩኔን ነው::

አዲስ ዘመን፤- የከተማ አስተዳደሩ ጸረ ሙስና ኮሚሽን በኮሚሽኑ አሰራሮች ላይ ያስጠናው ጥናት በርካታ ክፍተቶቸን ያመላከተ ነበር:: ጥናቱን ምን ያህል ተቀበሉታላችሁ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡– እውነት ለመናገር በኮሚሽኑ የተጠናው ጥናት የተቋሙን ችግሮች የሚገልጽ ነው:: ጥናቱ ቀርቦ የጋራ ሲደረግ ግን በጥናቱ የቀረቡ ችግሮች በአጋጣሚ በሪፎርሙ ተለይተው ለማስተካከል እየተሰሩ ያሉ ናቸው:: ሌብነትና የተዘዋዋሪ ብድር ላይ ብልሽቶችች ስለመኖራቸው ፣ በየቀበሌው የገቢ ማስገኛ የሆኑ የቀበሌ መዝናኛ፤ ሻውር ቤቶች፤ ካራንቡላ ቤቶችና መሰል የገቢ ማስገኛ ተቋማት ገቢያቸው እንዴት ይሰበሰባል? የሰው ኃይላቸው እንዴት እንደሚቀጥሩ መመሪያ ስለመኖሩ፤ በዚህ ሳቢያም የግለሰቦች መጠቀሚያ መሆናቸውን ያመላከተ ነው።

አንድ የመዝናኛ ማዕከል የሰው ኃይል ሲቀጥር በምን አግባብ እንደሚቀጥር፤ ገንዘቡ እንዴት እንደሚመራ፤ በሸማች ስር ሆነው ገንዘቡ ግን በተለየ አካውንት እንደሚገባ ኮሚሽኑ አረጋግጧል:: ስለዚህ ይህን ስርዓት ለማስያዝ በመመሪያ ሊመራ እንደሚገባ ታምኖበት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ::

አዲስ ዘመን፡- ያለመመሪያ የባከነው የህዝብ ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ኮሚሽኑ የሚያውቀው ነገር አለ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- በዚያ ልክ የለየነው የለም:: ሸማች ማህበራት ከተቋቋሙ ብዙ አስርት ዓመታትን ያሳለፉ ናቸው:: ስርዓት ሳይበጅላቸው ኪሳራ እና ምዝበራ ቢደርስባቸው አያስደንቅም:: አሰራር ሳይበጅላቸው ስለኪሳራቸው ለማውራት መሰረት የለውም:: አሰራር ባለመኖሩ በርካታ ሀብት እንዲባክን ሆኗል:: ሲጠቀምባቸው የነበረው አባሉ ሳይሆን ግለሰቦ ናቸው:: አንድ ሸማች ማህበር በስሩ ስጋ ቤቶች፤ መዝናኛ ማዕከላት፤ ሻውር ቤት፤ ክሊኒክ፤ ትህርት ቤት ይኖሩታል:: ይህ ቢኖም አባላቱ ምን የተጠቀሙት ነገር የለም :: ኪሳራ ጭምር የሚከፋፈሉ አሉ::

አዲስ ዘመን ፡- ኮሚሽኑ ወጥ የሆነ መመሪያ በማዘጋጀት እስከመቼ ወደ ሥራ ይገባል?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡– እውነት ለመናገር ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ቀጠሮ የሚሰጠቀው ጉዳይ አይደለም:: የዚህ ዓመት ስራችን ነው:: ፍትህ ቢሮ መመሪያውን አጽድቆ ሲሰጠን እኛ ወደ ሥራ እንገባለን::

አዲስ ዘመን ፡- የከተማዋ ከፍተኛው ችግር ቤት መሆኑ ይታወቃል:: ከቤት ማህበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በመፍታት የቤት ችግር ለማቃለል የሚያስችል በተጨባጭ በሪፎርሙ ምን ተሰርቷል?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ለማህበራት ህጋዊ ሰውነት ከመስጠት አንጻር በሪፎርማችን መመሪያ አውጥተናል:: ከዚህ በፊት ግን ይህ አልነበረም:: ከተማ አስተዳደሩ ሲጠቀም የነበረው የፌዴራልን መንግሥቱን ነበር። ምክንያቱም የፌዴራል መመሪያ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስለሚሰራ::

በፌዴራል መመሪያ በቤት ማህበራት መደራጀት የሚፈልጉትን ህጋዊ ሰውነት መስጠት ይቻላል:: ነገር ግን እንደከተማዋ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ የራሳችንን መመሪያ አውጥትን በኮሚሽኑ መመሪያ መመራት አለብን ብለን መመሪያ አውጥተናል:: በመመሪያው አንድ ሰው በቤት ማህበራት ለመደራጀት ምን ምን ማሟላት ይጠበቅብታል የሚለው ተካቷል::

አዲስ ዘመን ፡- በሸማቾች ስር ጤና ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ:: እየተመሩ ያሉት እንዴት ነው ? ትምህርት ቤቶችን በስርዓት ለመምራት ከትምህርት ቢሮ ጋር ተቀናጅቶ ከመስራት አንጻር ውስንነት የለም? ያለው ሁኔታ ምን መስላል ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- በእኛ ማህበራት የሚተዳደሩ 19 ትምህርት ቤቶች አሉ:: እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ ነበር። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ለትምህርት ክፍያ ይከፍላሉ:: ነገር ግን የሚከፍሉት ክፍያ የግል ትምህርት ቤቶች ከሚከፈሉት ክፍያ በጣም ያነሰ ነው:: ነገር ግን ወቅቱ ከሚጠብቀው አንጻር ትምህርት ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎት በቂ ነው? ከተባለ መልሱ በቂ አይደለም ነው::

አዲስ ዘመን ፡- በሸማች ስር የሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ሆን ተብሎ ከደረጃ በተቻ እንዲሆኑ በማድረግ እየተዘጉ ወደ መጠጥ ቤት ሲቀየሩ ይስተዋላል:: ይህን እንዴት ያዩታል?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡– ሆን ተብሎ ሲባል ማህበራት ይህ ትምህርት እንዲዘጋ እንፈልጋልን ይላሉ ማለት አይደለም:: ነገር ግን አፈጻጸማቸው ይዘጋ ወደሚለው ውሳኔ የሚያመጣ ሆኖ ይገኛል:: የተዘጉም ይኖራሉ:: ትምህርት ቤቶች ለህብረተሰብ አገልግሎት እና ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆናቸውን ተረድቶ እንዲሻሻሉ የሚሰሩ የትምህርት ቤት አመራሮች አሉ:: በአንጻሩ ለግል ጥቅማቸው ብቻ ብለው የሚሰሩ አሉ:: በእነዚህ ማህበራት ስር ያሉ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም:: በዚህም ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ በማድረግ ትምህርት አላዋጣንም መጠጥ ቤት ይሁኑ የሚሉ ማህበራት በተጨባጭ አግኝተናል:: ስለሆነም የተነሳው ቅሬታ በተግባር የሚታይ ነው:: ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል:: ከተዘጉ በኋላ ደግሞ ዘርፍ ቀይረው መጠጥ ቤት ሆነው የሚታዩ አሉ::

አዲስ ዘመን ፡- ትምህርት ቤቶችን ሸማቾች እንዲያስተዳድሩት የሚፈቀድ መመሪያ አለ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ትምህርት ቤቶች ለሸማች ማህበራት ሲሰጡ እና የሸማች ማህበራት እንዲያስተዳድሯቸው ሲደረግ በመመሪያ ሳይሆን በአደራ መልክ ተሰጥተው ነው:: ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን መዝናኛ ማዕከላትም በአደራ ነው የተሰጡት:: ትምህርት ቤቶች በአደራ የተሰጡትም በካቢኔ ውሳኔ ነው::

በአደራ የተሰጡት ተቋማት ውጤታማ ናቸው ወይ ? ከተባለ ውጤታማ የሆኑም አሉ ፤ ውጤት ማምጣት ያልቻሉም አሉ:: ውጤታማ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ወደ ተጠያቂነት እንዳንሄድ ደግሞ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት የለም:: በሪፎርሙ ከለየው አንዱ ችግር በአደራ የተሰጠው አካል አደራውን ቢያጎድል እንዲጠየቅ የሚያደርግ ነው:: በዚህም መመሪያ ተዘጋጅቶ ለፍትህ ቢሮ ተሰጥቷል::

አዲስ ዘመን ፡- ያልተገባ አሰራር በሚሰሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ክፍተቶች እንደነበሩበት የከተማ አስተዳደሩ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባጠናው ጥናት ተመላክቶ ነበር:: ከሪፎርሙ በኋላ ባሉት ስድስት ወራቶች ምን አይነት ተጨባጭ እርምጃዎች ተወሰዱ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- ከተጠያቂነት አንጻር እንደኮሚሽን ከተሰጠን ስልጣን አንጻር እኛ ልንትገብረው የምንችለው ነገር አለ:: ከኮሚሽኑ በላይ ከሆነ ደግሞ ወደ ክስ የሚሄድበት አግባብ አለ:: ሪፎርሙ ከተጀመረ ጀምሮ ባልተለመደ መልኩ በከፍተኛ ፍጥነት እና ጫና የተሰሩ ስራዎች አሉ:: ከእነዚህም መካከል ሸማቾችን እና ዩኒየኖችን ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ማድረግ ነው:: ምክንያቱም ዝም ብሎ ተጠያቂ አይደረግም:: ኢንስፔክሽን አድርጎ የሚገኝ ግኝት አለ:: በዚህ በመነሳት በገንዘብም እና በማቴሪያል የሚታያዩ ብክነቶች እና ብልሽቶች ይኖራሉ:: እሱን መነሻ በማድረግ የወሰድናቸው እርምጃዎች አሉ::

ለምሳሌ በቂርቆስ ከፍለ ከተማ የፖለቲካ አመራሮች እና የህብረት ሥራ ጽህፍት ቤት አሰራሩ ከሚፈቅደው ውጪ በመንቀሳቀስ ግብይት ፈጽመዋል:: ይህም በብዙ ሚሊዮን ብር ነው:: ይህንን ግብይት የሚፈጽሙት ከዩኒየን አመራር ጋር በመተባባር ነው:: ይህንን በኢንስፔክሽን ካረጋገጥን በኋላ ወዲያውኑ የኢንስፔክሽን ግኝቱን የማህበሩ ጉባዔተኛ ተጠርቶ ለጉባዔው ቀርቧል:: በዚህም የቦርድ አመራሩና ዩኒየን አመራሮች ሙሉ በሙሉ እንዲታገዱ ተደርጎ ሌላ አዲስ አመራር ተተክቷል:: ነገር ግን የቦርድ አመራሮች ማንሳት ብቻ ግብ አይደለም :: በገንዘብ የሚቀጣው ገንዘብ እንዲቀጣ፤ በህግ መጠየቅ ያለበትም በህግ እንዲጠየቅ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው::

ሁለተኛው የኢንስፔክሽን ግኝት የተገኘበት ጉለሌ ነው:: በኢንስፔክሽኑ ግኝት መሰረት ሙሉ በሙሉ አመራር ተቀይሯል:: መቀየር ብቻ ሳይሆን እንደጥፋታቸው መጠን በገንዘብ እና በህግ እንዲጠየቁ አድርገናል:: በጉለሌ የቦርድ አመራሩ ዩኒየኑ ከሚያተርፈው ትርፍ ሁለት በመቶ ለመውሰድ የውስጥ ደንብ አውጥተው ሲካፈሉ ነበር:: በእነዚህም ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ በህግ እየታየ ነው::

ሌላው የኢንስፔክሽን ግኝት የተገኘበት ደግሞ የምዕራብ ዩኒየን ኮልፌ ላይ ነው:: በዚህ ዩኔን ከአባሉ በተለየ አመራሩ አምስት በመቶ ትርፍ እንዲከፋፈል የራሳቸውን የውስጥ ደንብ አውጥተው ሲካፈፈሉ ተደርሶባቸዋል:: አምስት በመቶ ማለት ቀላለ ብር አይደለም:: በእነዚህ አካላትም ላይ ህጋዊ አርምጃ እርምጃ ወስደናል:: ነገር ግን ዩኒየኖች እና የህብረት ስራ ማህበራት አመራሮች በኢንስፔክሽን ግኝት መሰረት ቢፈተሹ አንዳቸውም ከተጠያቂነት አይተርፉም:: ቢያንስ የችግራችንን መጠን እንተው ብለን ነው ኢንስፔክሽን ሥራ ያስጀመርነው::

እውነት ለመናገር የዩኒየኖች እና ህብረት ሥራ ማህበራቱን ኢንስፔክሽን አሰርተን ስናየው ያስደነግጣል:: በኢንስፔክሽኑ መሰረት ተጠያቂ እናድርግ ቢባል ከተጠያቂነት የሚተርፍ ሰው አይኖርም:: ስለሆነም ይህን የኢንስፔክሽን ግኝት ቢያንስ ለሪፎርም ስራችን መጠቀም አለብን በሚል ለሪፎርም ስራችን እንደ ግብዓት እየተጠቀምን ነው:: የከፋ ችግር ባለባቸው በቀጣይ ሪፎርም ስራችን አባሉ እንዲያውቀው ተደርጎ እንዳይቀጥሉ ይደረጋል:: አዲስ የሚመረጠውም አመራር መጠየቅ እንዳለ እንዲያውቅ የሚያደርግ ነው:: አሁን አሁን በተለይ ግዥ ላይ ዩኒየኖች ትንሽ እጃቸውን ሰብሰብ አድርገዋል:: መጠየቅን እንዳለ እየተገነዘቡ መጥተዋል:: በፊት ግን ትጠየቃላችሁ የሚላቸው ሰው አልነበረም::

አዲስ ዘመን ፡- ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አንጻር የነበራችሁ ልምድ ምን ይመስላል? ወደፊትስ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የማህበራቱን አሰራር ከማዘመን አንጻር ምን እየተሰራ ነው ?

ወይዘሮ ልዕልቲ፡– በሪፎርማችን ከለየናቸው ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ አገልግሎቶች መካከል ህብረት ሥራ ማህበራቱ በቴክኖሎጂ ተደግፈው መስራት እንዳለባቸው ነው :: ምክንያቱም ማህበራቱ የተበታኑ ስለሆኑ በቀላሉ መቆጣጠር አይቻልም:: በቴክኖሎጂ መደገፍ አለበት ብልን የለየነው አገልግሎት መካከል የግብይት ስርዓታችንን ነው:: ዩኔኖች ምን ገዙ ፣ መጋዘናቸው ውስጥ ምን ገባ ፣ምን ሸጡ የሚለውን በሲስተም ማዕከል ላይ ሆነን እግር ለእግር ሄደን መቆጣጠር ካልቻልን ከብልሹ አሰራር መውጣት አይቻልም:: ለህብረተሰቡም በተፈለገው ልክ ማገልግል አይቻልም::

የኢንስፔክሽን ስራችን በቴክኖሎጂ ቢሆን ብለን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ኢንስፔክሽን ለማካሄድ እየሰራን ነው:: ዘጠኝ ለሚደርሱ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መደገፍ አለባቸው ብለን ለይተን ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ እንዲያለማ ሰጥተናል:: በአዋጅ ስልጣን የተሰጠው ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ስለሆነ በጨረታ ወደ ውጪ ለማውጣት አልፈልግንም::

ከዘጠኝ ዓመት በፊት ተቋሙን በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ስራ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ ተጅምሮ ነበር:: ነገር ግን ስራው በተግባር ሳይታይ የወጣው ገንዘብ ለብልሽት ተዳርጓል:: አሁን ለተጀመረው የቴክኖሎጂ ማስጀመሪያ 40 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተመድቧል:: በዚህ ዓመት በቴክኖሎጂ የማስተሳሰር ሥራ አልቆ ሥራ እንጀምራለን::

አዲስ ዘመን፡- ለነበርን ቆይታ እናመሰግናለን::

ወይዘሮ ልዕልቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ::

ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You