ቶዮታ 50 ሺህ በአሜሪካ የሚገኙ ተሽከርካሪዎቹ እንዳይነዱ አስጠነቀቀ

የተሠሩ የአደጋ መከላከያ ከረጢቶች (ኤር ባግ) ፈንድተው ሊገድሏቸው ስለሚችሉ በአሜሪካ የሚገኙ 50 ሺህ የአሮጌ ተሽከርካሪ ባለቤቶች አፋጣኝ ጥገና እንዲያደርጉ ቶዮታ አሳስቧል። “እንዳይነዳ” የሚለው ማሳሰቢያ ከ2003 እስከ 2005 የተሠሩትን አንዳንድ የመኪና ሞዴሎችን ያካትታል።

እአአ ከ2009 ወዲህ በታካታ በተመረተው የአደጋ መከላከያ ከረጢት ምክንያት ከ30 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። “ከረጢቱ ከተዘረጋ በውስጡ ያለው ክፍል ፈንድቶ ስለታማ የብረት ቁርጥራጮችን የመተኮስ ዕድሉ ከፍተኛ ነው” ሲል ቶዮታ ገልጿል።

ይህ ችግር የገጠማቸው ተሽከርካሪዎች የ2003-2004 ሞዴል ኮሮላ፣ 2003-2004 ኮሮላ ማትሪክስ እና 2004-2005 ራቭ4 ናቸው። በታካታ የአደጋ መከላከያ ከረጢቶች ችግር ምክንያት ከ100 ሚሊዮን በላይ መኪናዎች እና ከ20 በላይ መኪና አምራቾች ተሽከርካሪዎቻቸውን ለጥገና እንዲጠሩ አስገድዷቸዋል።

ከአስር ዓመት ተኩል በላይ በውጣ ውረድ እና አሜሪካ ውስጥ በወንጀል ምርመራ ያሳለፈው ታካታ በ2017 ኪሳራ እንደገጠመው አሳውቋል። ንብረቶቹም በቻይናዊ ባለቤትነት ለተያዘው ኪይ ሴፍቲ ሲስተምስ በ1.6 ቢሊዮን ዶላር ሸጧል። ቶዮታ ባለፉት ወራት የገጠመው ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም። በዚህ ሳምንት የጃፓኑ ግዙፍ መኪና አምራች ቶዮታ በናፍታ ሞተሮች ላይ በተደረገው የማረጋገጫ ሙከራ ስህተት ምክንያት የአንዳንድ ተሽከርካሪዎችን ማስረከብ አቁሟል።

በተደረገው ምርመራ የቶዮታ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች የፈረስ ጉልበት ሙከራዎችን ውጤት አሳስተዋል። ችግር የገጠማቸው ሞተሮች ሂስ ቫን እና ላንድክሩዘር ስፖርት መኪናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሸጡ 10 የመኪና ሞዴሎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ሲል ቶዮታ ተናግሯል።

ቶዮታ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ የቆዩ የደህንነት ሙከራዎችን ማጭበርበሩን ካመነ በኋላ በዳይሃትሱ ላይ የደረሰውን የሥነምግባር ጉድለት ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ የዳይሃትሱ ዋና መሥሪያ ቤት በጃፓን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ምርመራ የተከናወነበት ሲሆን የተሽከርካሪዎቹን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አቋርጧል። መንግሥት የሦስት የዳይሃትሱ ሞዴሎችን የምስክር ወረቀት ሰርዟል።

በቶዮታ ቅርንጫፎች ውስጥ ስላሉት ችግሮች የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ ኮጂ ሳቶ ሠራተኞቹ በጣም ፉክክር ባለበት ኢንዱስትሪ ውስጥ በፍጥነት ለመሥራት ግፊት እንደነበረባቸው አምነዋል። “በጥራት ማረጋገጫ ቦታ ላይ ያሉ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ አመራሮቹም ስለጥራት ማረጋገጫ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳልነበራቸው እንገነዘባለን” ማለታቸው ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You