
ስምንተኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤል እና ኢራን ግጭት “መስፋፋት ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል እሳት ሊያቀጣጥል ይችላል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳሰቡ። ዋና ጸሐፊው በሀገራቱ መካከል ያለው ግጭት መቀጠል ዓለምን ወደ ቀውስ የሚከት ነው ብለዋል።
ጉቴሬዝ የግጭቱ ማዕከል “የኒውክሌር ጥያቄ” ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ ተናግራለች። ነገር ግን ማወቅ ያለብን የመተማመን ክፍተት እንዳለ ነው” ብለዋል። “ጦርነቱ እንዲቆም እና ወደ ድርድር እንዲመለሱ እማጸናለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
እስራኤልና ኢራን በሰማይ ላይ የሚያደርጉት ግጭት ስምንተኛ ቀኑን ይዟል። የእስራኤል ጦር፣ የኢራን የኒውክሌር ምርምር ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ ከ60 በላይ የሚሆኑ ይዞታዎችን በቴህራን እና በሌሎች ስፍራዎች ላይ ማጥቃቱን አስታውቋል።
የኢራን ሚሳኤል በደቡባዊ እስራኤል ቤርሼባ ከተማ የሚገኝ የቴክኖሎጂ ፓርክ መምታቱን ተከትሎ በርካታ ሕንጻዎች ወድመዋል። ሞት ባይከሰትም ሰባት ሰዎች ግን በደረሰባቸው ጉዳት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የጀርመን እና የፈረንሳይ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺን ጋር በጄኔቫ ይገናኛሉ። ስምንት ቀናት ባስቆጠረው ግጭት ኢራን ከምዕራባውያኑ ጋር ፊት ለፊት ስትወያይ የመጀመሪያዋ ነው። የጄኔቫ ውይይቶች እንደታቀደው የሚቀጥል ከሆነ በእዚህ ቀውስ ውስጥ ትልቁን የአውሮፓ ተሳትፎ እንደሚያመለክት ተጠቁሟል፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እስራኤል ጥቃቷን እስካላቆመች ድረስ ሀገራቸው ከአሜሪካ እንደማትደራደር መናገራቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የባህል፣ ሚዲያ እና ስፖርት ሚኒስትር ሊሳ ናንዲይ የኢራን እና እስራኤልን ግጭት ለማስቆም ብቸኛው አማራጭ ዲፕሎማሲ ነው አሉ። ሚኒስትሯ ይህን ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሀገራቸው በሁለቱ ሀገራት ግጭት የሚኖራት ተሳትፎ ላይ ለመወሰን የሁለት ሳምንት ቀነ ገደብ ባስቀመጡበት ወቅት ነው። አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም እስራኤልን ከተቀላቀለች ዩኬ ርምጃዋን ልትከተል ትችላለች ወይ ተብለው የተጠየቁት ሚኒስትሯ፣ “ ወሳኙ ነገር ግጭቱ እንዳይባባስ ማድረግ እንደሆነ” አፅንኦት ሰጥተዋል።
በመከላከያ እና በደኅንነት ዙሪያ ብቸኛዋ የቅርብ አጋራችን ከሆነችው አሜሪካ ጋር በቅርበት እየሠራን ቢሆንም ካለው ሁኔታ የሚያወጣን “ግጭቱ እንዳይባባስ ማድረግ እና ዲፕሎማሲ ነው” ብለዋል። ሚኒስትሯ ጨምረውም በኢራን ያለውን “ያልተረጋጋ መንግሥት” እና “በጋዛ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ቀውስ” በመጥቀስ በሕይወት ዘመናቸው መካከለኛው ምሥራቅ እንዲህ ዓይነት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅ ተናግረዋል።
“በጣም በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙን ነው። የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና ሰዎችን ለመደገፍ የሚረዳው መንገድ አንድ ነው – እርሱም ዲፕሎማሲ ነው።” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ለሚካሄደው የሰላም ድርድር የሁለት ሳምንት ጊዜ ቢሰጡም በሁለቱ ሀገራት መካከል ግን ሚሳኤሎች መወንጨፋቸውን አላቋረጡም። የእስራኤል ጦር በኢራን አየር ክልል ላይ ወደ 60 የሚጠጉ የእስራኤል ጄቶች በዋና ከተማዋ ቴህራን ዙሪያ እና ከኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር በተያያዙ ቦታዎች ላይ ዒላማዎች መደብደባቸውን አስታውቋል። የእስራኤል መከላከያ የኢራን የኒውክሌር ምርምር ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት ተመትቷል ሲል አስታውቋል። በተጨማሪም በርካታ የኢራን ሚሳኤል ማምረቻ፣ ማስ ወንጨፊያ ስፍራዎችን ማውደሟን ገልጻለች።
በምላሹ ኢራን ከትናንት በስቲያ ጥቃት በፈጸመችበት በደቡባዊ እስራኤል ከተማ ቤርሳቤህ ድብደባ አካሂዳለች። ዒላማው የቴክኖሎጂ ፓርክ ሲሆን፤ ትናንት ጥቃት ከደረሰበት ሆስፒታል አቅራቢያ የሚገኝ ነው። ኢራን አሁንም የእስራኤልን የአየር መከላከያ አይረን ዶም በማለፍ ረገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነች ያሳያል። በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከበፊቱ በተሻለ ፀጥ ያለ ሌሊት ነበር። ከትናንት በስቲያ ምሽት በኢየሩሳሌምም ሆነ በቴልአቪቭ ምንም የአደጋ ጊዜ ደወል አልተሰማም ሲል የዘገበው ቢቢሲና የኢራን መገናኛ ብዙኃን ናቸው።
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም