ከታኅሣሥ ወር አንስቶ በጥር፣ በሚያዚያ እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ መኸር በተሰበሰበበት ሜዳ የተለያዩ ጨዋታዎችንና የእርስ በእርስ ፉክክር ማድረግ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የተለመደ ነው:: እነዚህ ጨዋታዎች ዛሬ ላይ ለሚዘወተሩት ዘመናዊ ስፖርቶች መሠረት ቢሆኑም፤ ከዘመኑ ጋር እየተበረዘ፣ በወጣቱ ዘንድ ያለው ተዘውታሪነትም እየቀነሰ መምጣቱ እርግጥ ነው:: በመሆኑም ትውልዱን ወደ ማንነቱ ለመመለስ ወቅቱን ጠብቆ ባሕላዊ የስፖርት ውድድሮችን በክልሎች፤ እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጃ ማካሄድ የተለመደ ነው::
ከባሕላዊ ውድድሮች ጎን ለጎንም የባሕል ፌስቲቫል በማዘጋጀትም እሴቱን ከማሳደግ ባለፈ ከትውልዱ ጋር የማስተዋወቅ ሥራም ይሠራል:: 20ኛው የመላው የኦሮሚያ ባሕል ስፖርት ሻምፒዮና እንዲሁም 16ኛው የባሕል ስፖርት ፌስቲቫልም ይህንኑ መሠረት በማድረግ በአምቦ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል:: ለቀናት በሚዘልቀው በዚህ ሻምፒዮና ላይም 20 ዞኖችና 13 ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮቻቸውን እያፎካከሩ ይገኛሉ:: 1ሺህ 80 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በባሕል ጨዋታዎቹ ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፤ 3ሺህ 800 የሚሆኑት ደግሞ በባሕል ፌስቲቫሉ ላይ ተካፋይ ናቸው::
ውድድሩም በሃገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካገኙ የባሕል ጨዋታዎች መካከል በ10ሩ ይካሄዳል:: በፌስቲቫሉ ደግሞ በባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጣቸው አምረው የተገኙት ተሳታፊዎች የጭፈራ እና የአመጋገብ ሥርዓታቸውን በማሳየት እርስ በእርሳቸው ይፎካከራሉ:: ዘንድሮ ለ21ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ሻምፒዮና ላይ ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ የባሕል ስፖርት ተወዳዳሪዎችን መምረጥ የሻምፒዮናው ቀዳሚ ዓላማ ነው:: ሕዝቡ የራሱን ባሕል መግለጽ እንዲችል፤ እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ዞኖች ትውፊታቸውን ለሌላኛው ዞን በማስተዋወቅ እርስ በእርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግም ጠቃሚ ነው:: በሌላ በኩል ከሥልጣኔና ዘመናዊነት ጋር በተያያዘ ስለ ባሕሉ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን ትውልድ ማንነቱን እንዲያውቅና ባሕሉን እንዲያሳድግ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው::
እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ የኦሮሚያ ክልልም በተለያዩ ባሕላዊ እሴቶች የበለጸገ መሆኑ ይታወቃል:: ነገር ግን ከዚህ ቀደም በዘርፉ የነበረው ሁኔታ ወደ ኋላ የመቅረት አዝማሚያ የታየበት እንደነበረ የሚያስታውሱት፤ በኦሮሚያ ክልል የባሕል ስፖርት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ ኢራሱ ናቸው:: በመሰል ውድድሮች ላይም በባሕል ልብስ ተውቦ መገኘት ያልተለመደ ነበር:: ፌዴሬሽኑም ይህንን በመገንዘብ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የውድድር ተወዳዳሪዎች ወደ ሜዳ ሲገቡ ባሕላቸውን በሚያንጸባርቅ አልባሳት መቅረብ እንዳለባቸው በመደንገጉ፤ እንዲሁም ፌስቲቫሉም እንዲካሄድ በመደረጉ አስደናቂ ለውጦች ታይተዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስፖርቱን የሚመራው የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ትኩረት በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ የባሕል ስፖርት ጽሕፈት ቤት እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ አድርጓል:: በዚህም የተሳታፊ ዞኖችን፣ እንዲሁም ተወዳዳሪዎችን ቁጥር በማሳደግ የመላ ኦሮሚያ ሻምፒዮና ሊሆን ችሏል::
በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ሻምፒዮና ላይም ክልሉ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆኑ ከደረጃ ወርዶ እንደማያውቅ ኃላፊው ይጠቁማሉ:: በቅርቡ የሚካሄደውን ሻምፒዮናም በበላይነት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል:: ክልሉ በተለይ ከሚታወቅባቸው የባሕል ስፖርቶች መካከል አንዱ የፈረስ ስፖርት ነው:: ይህን የፈረስ ሃብት በትልቅ ደረጃ ለማስተዋወቅና ስፖርቱን ለማሳደግ የተጀመረ ፕሮጀክት ነበር:: ይኸውም የተለያዩ ማኅበራትን በማቋቋም በሰባቱ የፈረስ ስፖርቶች በየዓመቱ ውድድር እንዲካሄድ እየተደረገ መሆኑንም አቶ በቀለ ያብራራሉ:: አሁን ካለበት በይበልጥ እንዲያድግና ስፖርቱ እንዲስፋፋም እንደ ክልል አቅጣጫ የተያዘ ሲሆን፤ በቀጣይም ማኅበራትን በማደራጀት ይሠራል::
ነገር ግን የማንነት መገለጫ የሆነው ይህ ስፖርት አሁንም በይበልጥ እየተዝወተረ የሚገኘው በገጠራማ አካባቢዎች ነው:: በከተማ አካባቢዎች ያለው እንቅስቃሴ ደካማ የሚባል ነው:: በእርግጥ ቀድሞ ተሳታፊ ያልነበሩ ክልሎች በቅርቡ ተወዳዳሪዎችን መላክ ስለጀመሩ ጥቂት ለውጥ መጥቷል ማለት ቢቻልም፤ በታዳጊዎች ዘንድ ግን ምንም አልተሠራም በሚያስብል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው አልሸሸጉም:: በመሆኑም የባሕል ስፖርትና ፌስቲቫልን በክልል ደረጃ ከማካሄድ ባለፈ በየዞኑና በወረዳ እንዲካሄድ በማድረግ ኅብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው:: በዚህም ስፖርቱን ማሳደግና ወጣቱም ባሕሉን እንዲያውቅ ለማድረግ እንደሚቻልም ተስፋ ተደርጓል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም