ውሃ እና ግጦሽ ፍለጋ ከብቶቹን ይዞ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው አርብቶ አደር ዛሬም በአየር መዛባት ምክንያት ከሚያጋጥመው ድርቅ እንስሳቱን ለመታደግ ቀዬውን ለቆ ይሄዳል። በአካባቢ ላይ የሚከሰቱ ግጭቶችም የአርብቶ አደሩ ሌላው ፈተና ነው። እንስሳቱን ወደ ኢኮኖሚ ጥቅም በማዋል በኩልም ክፍተቶች ይስተዋላሉ። እንዲህ ያለው ችግር ሶማሊያ፣ ኬኒያ በመሳሰሉ ጎረቤት ሀገሮች ውስጥም ተመሳሳይ ችግሮች ያጋጥማሉ።
በተፈጥሮ መዛባት እያጋጠመ ያለው የዝናብ እጥረት፣ የድርቅ መደጋገም በተለይ ለአርብቶ አደሩ ማሕበረሰብ የእለት ተእለት ኑሮ የከፋ እያደረገው በመምጣቱ ቀጠናውን ያስተሳሰረ መፍትሄ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህም በባሕል፣ በታሪካና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የማይነጣጠለውን በጋራ መድረክ በማገናኘት የመፍትሄ ጥረቱ ተጀምሯል።
ለዚህም አንዱ ማሳያ በየዓመቱ የሚካሄደው አርብቶ አደሮችን መሠረት ያደረገ ሲፖዚየም ነው። ሰሞኑንም 19ኛው የአርብቶ አደሮች ቀን ‹‹አርብቶ አደርነት የምሥራቅ አፍሪካ ሕብረ ቀለም›› በሚል መሪ ቃል በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ተከፍቷል። ጥረቱ ግን ከዚህም በላይ መሆን እንዳለበት ይጠበቃል።
የአፋር ክልል ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት ውስጥ በአማካሪነት እየሰሩ የሚገኙት አቶ አህመድ ያሲን ዊሊሳ፤ እንደሚያስረዱት አርብቶ አደሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ በሚያጋጥሙት ችግሮች በአንድ ቦታ ተረጋግቶ እንዳይኖር አድርጎታል። በተለይ ደግሞ ከራሱ በላይ ለእንስሳቱ ቅድሚያ ስለሚሰጥ ለእንስሳቱ መኖ እና ውሃ ፍለጋ ቀዬውን ለቆ ይሄዳል። በዚህ የተነሳም የልማት ተጠቃሚ ሳይሆን ኑሮውም ሳይቀየር ዘመናት ተቆጥረዋል። ትኩረት የሰጠው ባለመኖሩ ኑሮው በየዘመናቱ ተመሳሳይ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአርብቶ አደሩ መንደሮች ለውጦች እየታዩ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ የከብት ጭራ ተከትሎ የሚሄድ አርብቶ አደር መባል እየቀረ መሆኑንም የአፋር ክልልን ተሞክሮን ለአብነት ጠቅሰዋል። ዳመናን ተከትሎ መሄድ ሳይሆን፤ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ ዘመናዊ የእንስሳት አረባብ ዘዴን እየተለማመደ መሆኑንና በአካባቢው ላይ የከብት መኖ እያዘጋጀ እንስሳቱን መመገብ መጀመሩን አስረድተዋል።
አርብቶ አደር የሚባለው ማሕበረሰብ አሁን ከፊል አርሶ አደር እየሆነ መሆኑንም ገልጸዋል። ‹‹በፀይ መውጫ ምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ ሲፖዚየም መዘጋጀቱ ለአርብቶ አደሩ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል። የአንዱ ችግር የሌላውም ጭምር ነው። መተባበር አለብን›› በማለት ይገልጻሉ።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ፤ በአፋር ክልል ከዚህ ቀደም ያልተለመደ የልማት ሥራ እየታየ ነው። አፋር በእርሻው በቆሎ፣ ሰሊጥ ካልሆነ በእንስሳቱ ነው በስፋት የሚታወቀው፣ አሁን ላይ በአፋር ክልል የግብርና ሥራ የለም የሚለው ብሂል ታሪክ ሊሆን እየተቃረበ ነው።
ስምጥ ሸለቆን ተከትሎ እንደ ሀገር እየተከናወነ ባለው የበጋ መስኖ ልማት አፋር ክልል ውስጥ የስንዴ ልማት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል ልማቶች መልማት ጀምረዋል። በዚህ መልኩ እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ ለክልሉም ለሌላው ተአምር እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።
አቶ አህመድ እንዳብራሩት፤ ክልሉ ቅድሚያ እየሰጠ ያለው ከእርዳታ እራስን ለማውጣት በምግብ እህል እራስን መቻል ላይ ነው። በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት አለመረጋጋት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ልማቱን ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስረድተዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ በይነመንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) አርብቶ አደሮችና የእንስሳት የቆላማ አካቢዎች ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ደረጀ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ የኢጋድ ሀገራት 70 በመቶ የሚሆነው፤ ቆላማና በዝናብ ለሚከናወን እርሻ ምቹ ያልሆነ ነው። ከዚህ ይልቅ አካባቢው ለእንስሳት እርባታ በጣም ምቹ ነው። በዚህ የተነሳም በቀጠናው ክልል ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ይገኛል።
ይህን ከፍተኛ ሀብት ይዘው የሚገኙት የአርብቶ አደር ማህበረሰቦች ደግሞ በስፋት የሚገኙት በድንበር አካባቢ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ ሀገሮች መካከል ላይ የምትገኝ በመሆኗ ብዙ ሀገሮችን ታዋስናለች። በሚያዋስኗት ሀገሮች አብዛኛው በሚባል ደረጃ ተመሳሳይ የሆነ ቋንቋ፣ ባሕል፣ የኑሮ ዘይቤ ያላቸው ናቸው። ይህ አይነቱ ተመሳሳይነት ደግሞ የቀረበ ዝምድናን ፈጥሯል።
እንዲህ ያለው ነገር ደግሞ ለልማት፣ የአካባቢ ሰላምን ለማስፈን፣ በአጠቃላይ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንድነትን ለመፍጠር ምቹ ሆኖ ይገኛል። እንዲህ ያለው ምቹ ሁኔታ ያለው በአርብቶ አደሩ ማሕበረሰብ ውስጥ ነው።
አርብቶ አደሩ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚገደደው ለእንስሳቱ መኖና የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ነው። አርብቶ አደሩ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ባለው የተፈጥሮ ሁኔታ ታስቦበት ከብት መኖ ስለማይመረት ብዙ አርብቶ አደሮች አቋርጠው ለመሄድ ይገደዳሉ። ድንበር አቋርጠው ሲሄዱ ትብብርና ድጋፍ የሚያገኙትን ያህል ግጭትም ይገጥማቸዋል። እንስሳቶቻቸውም ለተላላፊ በሽታ ይጋለጣሉ። ስለዚህም አርብቶ አደሩ ተረጋግቶ ሕይወቱን እዲመራ ለእንስሳት መኖ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
ሌላው የአርብቶ አደሩ ችግር በእንስሳቶታቸው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ተግዳሮት ከሆነባቸው አንዱ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ነው። ወደ ማዕከል ገበያ ለማምጣት የመንገድ ችግር ያጋጥማቸዋል። በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የገበያ ትስስር ችግር አለባቸው።
ገበያ ተኮር የሆነ የአመለካከት ክፍተትም ሌላው ተግዳሮት ነው። ሸጦ ለውጦ ሕይወትን ለመለወጥ የሚደረገው አናሳ ነው። አብዛኞቹ የእንስሳት ሀብት ባለቤት መሆናቸውን ብቻ ነው የሚያስደስታቸው። ስለዚህም አርብቶ አደሩ በዘመናዊ ግብይት ላይ በቂ ስልጠና እና ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ ነው።
የአየር መዛባትና ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርቅ በተደጋጋሚ መከሰቱ አርብቶ አደሩን ለኢኮኖሚ ችግር እየዳረገው ነው። ለተከታታይ ዓመታት በሚከሰት ድርቅ አንድ ቤተሰብ እስከ ሶስት መቶ እንስሳቱን ያጣበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
አንድ ቤተሰብ እስከ ሶስት መቶ ድረስ እንስሳት ካለው፤ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል። ይህን ሁሉ የእንስሳት ሀብት ይዞ መቀመጥ ለሁሉም አደጋ አለው፤ የአርብቶ አደሩንም ሆነ፣ የሀገር ተጠቃሚነትን በማሳጣት፣መሬትን በማራቆት ነው ጉዳቱ የሚገለፀው። እንስሳቱ ወደ ገበያ ሲወጡ ግን ቀሪ እንስሳት መኖ ሣር ለማግኘት ነፃ መሬት እንዲኖር ያስችላል። ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም ከፍ ይላል።
እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት፣ የአርብቶ አደሩን የእንስሳት ሀብት ወደ ኢኮኖሚ በመለወጥ እነርሱም ሀገርም ተጠቃሚ እንዲሆን ሥራዎች መሰራት አለባቸው። ኢጋድም አርብቶ አደሩ በእንስሳቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ነው ግፊት እያደረገ የሚገኘው። ለዚህም እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች ለፖሊሲ አቅጣጫና ድጋፍ የሚሆኑ ተግባራት ይጠቀሳሉ።
ለአብነትም አርሶ አደሩ ለእንስሳቱ የሚሆን መኖ ከገበያ ላይ መግዛት ቢፈልግ አቅርቦቱ የለም። በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ ስትራቴጂክ የሆነ የመኖ ክምችት ያስፈልጋል። በአርብቶ አደሩ አካባቢ ከእንስሳት ሀብት በተጨማሪ ወደ ሀብትነት ሊቀየሩ የሚችሉ ሌሎች የሀብት ክምችቶች ይገኛሉ። ማር፣ ለሳሙና እና ለተለያዩ ግብአቶች የሚውሉ እጽዋትን እንዲሁም እጣን አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ይቻላል።
እነዚህ ሀብቶችን በአግባቡ በመምራት ተጨማሪ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ በአካባቢው ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ያለውን ዛፍ ቆርጦ ለከሰል በማዋል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ጉዳት የማድረስ ችግር ነው የሚስተዋለው። ለችግሮች መፍትሄ ሰጥቶ ውጤታማ ለመሆን ክልሎችን ማስተሳሰር ያስፈልጋል።
በአርብቶ አደሮች ቀን፣ ቢያንስ ስድስት ሀገራት ተሳትፈዋል። በሚካሄደው ሲምፖዚየምም ለአርብቶ አደሩ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ምክክሮች ይካሄዳሉ። ውይይቱ ጥልቅ እውቀት ካላቸው ባለሙያዎች ጋር የሚካሄድ በመሆኑ፣ አርብቶ አደሩን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ጠቃሚ ነገሮችና ምክረሀሳቦች ይነሳሉ።
እንዲህ ባለው መንገድ የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር የመንግሥታት ቁርጠኝነትና በፖሊሲ ዙሪያም ያለውን ሁኔታ በተመለከተም ዶክተር ደረጀ እንዳብራሩት፤ ሂደቱ ረጅም ቢሆንም ጅማሮዎች አሉ።
በቆላማ አካባቢ የሚኖሩ የአርብቶ አደር ማሕበረሰቦች ለምን በድርቅ ይጎዳሉ?፣ ከእርዳታም እንዲወጡ ሥራዎች ለምንስ አይሰሩም ? በሚል ቁጭት እኤአ 2011 ትልቅ የውይይት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር።
በዚህ ፕሮግራም መነሻ በኢጋድ በኩል ብዙ ሥራ ተሰርቷል። የገበያ ዕድልም ተፈጥሯል። የእንስሳት ሕክምና ተቋማትም ተከፍተዋል። በዚህ ወቅት የተፈጠሩ መነሳሳቶች ናቸው ከኬኒያ ተነስቶ ሞያሌ ለመግባት ሰሶት ቀናትን ይወስድ የነበረውን ጊዜ በአንድ ቀን ማሳጠር የተቻለው።
ኢትዮጵያም እስከ ሞያሌ ድረስ አስፓልት ለማድረግ የተነሳሳችው የጋራ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ነው። የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ከዩጋንዳ ወደ ከረሞጃ የሚባል አካባቢ ለመሄድ ሁለት ቀናት ጊዜ ይወስድ ነበር። በዚያ ላይ እስከ ሕይወት ማጣት የሚያደርስ ስጋትም ነበር። በመንግሥት በተደረገ ርብርብ መሠረተልማት በመዘርጋቱ ስጋቶች ተቀርፈዋል። ይህን ተከትሎም ለእንስሳት ንግድ ምቹ ሆኗል።
‹‹እኔ እኤአ በ2015 ደቡብ ኦሞ አካባቢ እንስሳትን በበቆሎ ነበር አርብቶ አደሩ ቀይሮ የሚጠቀመው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው ትብብር በተለያዩ ቦታዎች ገበያዎችን በማቋቋም ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ጥረት አድርጓል›› ሲሉም ዶክተር ደረጀ የመንግስትን ጥረት አድንቀዋል።
አርብቶ አደሩ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ካላቸው የመሬት ስፋት አንጻር በልማት ለማዳረስ ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ደረጀ፤ በመንግሥት በኩል ፍላጎቱ መኖሩን ግን አረጋግጠዋል። ወደፊት፣ ወደኋላ የሚሉ ነገሮች እንዳይኖሩ፤ የምሥራቅ አፍሪካ የእንስሳት ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረጉን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ይላሉ።
የተጀመረውን ሥራ ወደፊት ለማራመድና በፖሊሲም እንዲደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢጋድ ክፍተት በሚስተዋልባቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን የጥናት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ደረጀ፤ ‹‹ለአብነትም እንስሳት ከምግብነት ባለፈ ለማዳበሪያ፣ የእርሻ መሳሪያም ሆኖ በማገልገል ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለውም ከፍ ያለ ግንዛቤ ባለመያዙ በሁሉም ሀገራት ዘንድ ለእንስሳት ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንት አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የተሰጠው ትኩረት መልካም በሚባል ሁኔታ ላይ እንዳለና ተጠናክሮ ከቀጠለም ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ነው ከአስተያየት ሰጪዎቹ መረዳት የሚቻለው። በተለይም ቀጠናውን ያስተሳሰረ እንቅስቃሴ ለውጤት እንደሚያበቃም ነው የገለጹት።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም