ለስድስት ወራት የሚካሄዱት የ2016 የበጋ ወራት ውድድሮች ሰላሳ የሚጠጉ የሠራተኛ ስፖርት ማሕበራትን በማሳተፍ ባለፈው እሁድ “የሠራተኛው ስፖርት ለሰላም፣ ለጤናና ለምርታማነት” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በደማቅ የመክፈቻ ስነስርዓት ተጀምሯዋል።
በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አዘጋጅነት የቤት ውስጥ ውድድሮችን ጨምሮ በ10 የስፖርት አይነቶች ፉክክር በሚደረግበት የበጋ ወራት ውድድር በሁለቱም ፆታ በአትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቮሊቮል፣ ዳማ፣ ቼስ፣ ገበጣ፣ ገመድ ጉተታና ሌሎችም የስፖርት አይነቶች ከ1ሺህ 500 በላይ ሠራተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ።
በእግር ኳስና አትሌቲክስ፣ እንዲሁም በሌሎች አዝናኝ ውድድሮች በደመቀው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አሕመድ፣ የሠራተኞች ስፖርታዊ ተሳትፎ የሚሰሩበትን ተቋም ከማስተዋወቅና የቤተሰባዊ ባለድርሻነት ስሜትን ከማዳበር ባለፈ ጤናማ፣ ንቁና ምርታማ እንደሚያደርጋቸው ጠቅሰዋል።
“ስፖርታዊ ተሳትፎ ለማንኛውም የልማት ተቋም ቢሆን አትራፊ እንጂ አክሳሪ አይሆንም።” ያሉት አቶ አያሌው፣ ኢሠማኮ እስከ ዛሬም ድረስ ከራሱ ከሚመድበው በጀትና ቀና የስራ ኃላፊዎች፤ እንዲሁም ባለሀብቶች በሚያደርጉለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በየዓመቱ የበጋና የክረምት ስፖርት ቻምፒዮናዎችን የሚያዘጋጀው አካላዊና ሕሊናዊ ብቃቱ የዳበረና ምርታማ ሠራተኛ ለማፍራት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢሠማኮ አሰሪና ሠራተኞችን ለማግባባት፣ የልማት ተቋማትን ገፅታ ለመገንባትና የሠራተኞችን አንድነት ለማጠናከር ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚገነዘብም ውድድሮችን ለበርካታ ዓመታት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
“ስፖርት አገራዊ አንድነትና ሰላምን ለማጠናከር እንዲሁም ዓለማቀፋዊ ቅርርቦሽን ለማስፈን ጭምር የሚያስችል ኃይል ያለው ‘ሰላማዊ’ መድረክ ነው” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ እንዲህ አይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ አካላዊ ደህንነትን ከማላቁ ባሻገር ለአእምሮና ለስሜት ደህንነት አስተዋፅኦው ቀላል እንዳልሆነ፤ ለስራው የበለጠ ተነሳሽነትና እርካታ ያለው የሰው ኃይል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
አሰሪዎችም ይህን ለስፖርት የሚያውሉትን ሀብት እንደወጪ ብቻ ሳይሆን ለስራ ኃይላቸው ደህንነትና የእርስበርስ ቅርርብ መዋዕለ ንዋይ እንዳፈሰሱ ሊቆጥሩት ይገባል ብለዋል። ከእንዲህ አይነት ተነሳሽነቶች የሚገኙ ጥቅሞች ለአዎንታዊና ለበለፀገ የስራ ከባቢ አስተዋፅኦው ትልቅ መሆኑንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን ሕጋዊ እውቅና ካገኘበት ከሚያዝያ 01-1955 ዓ.ም ጀምሮ ሠራተኛው ከደመወዙ ላይ ለስፖርት አገልግሎት የሚውል የተለየ መዋጮ እንዲያዋጣ በማድረግና በጀት በመመደብ ለሠራተኞች አንድነት ማጠናከሪያና ለአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት መሻሻል ሲጠቀምበት ቆይቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን ካለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት በላይ የሠራተኛው የስፖርት መድረክ ለአገራዊ ስፖርት እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መካሄዱን ቀጥሏል።
እነዚህ ውድድሮች ሠራተኞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን ለማፍራት፣ የሠራተኞችን አንድነት ለማጠናከር፣ የልማት ተቋሞቻቸውን ማስተዋወቀና የባለቤትነት ስሜታቸው እንዲጠናከር ዓላማ በማድረግ የሚከናወኑ ናቸው። በኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ የስፖርት መድረኮች አንዱ የሆነው ይህ የሠራተኞች ውድድር በዚህ ዘመን ሠራተኛው በስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ ለሚሠራበት ድርጅት ውጤታማነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ስፖርቱ የሠራተኛውን አንድነትና ለጋራ ጉዳይ አብሮ የመቆም ባሕሉን አጠናክሮበታል።
በአገሪቱ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ እየተሳተፉ ጤናማ፣ ንቁና አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ውድድሮችን ማሰናዳት ውጤታማ ሠራተኛ ለማፍራት የሚያበረክቱት ሚናም ቀላል አይደለም።
በአሠሪና ሠራተኛው መካከልም ጥሩ ግንኙነት እንዲዳብር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ለኢንዱስትሪ ሰላም መስፈን የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውም ባለፉት በርካታ ዓመታት በተካሄዱ ውድድሮች ለመታዘብ ተችሏል።
በነዚህ ውድድሮች ላይ ተቋሞቻቸውን ወክለው በሚካፈሉ ተወዳዳሪዎች መካከል ከተቋም ጋር ያለውን መቀራረብ፣ ልምድ ማካፈል እንዲሁም ለተለያዩ ክለቦች ግብዓት የሚሆኑ ስፖርተኞች ማፍራት የቻለ ውድድር መሆኑንም በሠራተኛው ስፖርት ውስጥ ረጅም ዓመታትን ያሳለፉ ሰዎች ይመሰክራሉ። በውድድሩ በሚካፈሉ ተቋማት መካከል በሚፈጠረው ፉክክር ምክንያትም ሠራተኛው የተሻለ ውጤት ይዞ ለመምጣት ሲሽቀዳደምና ለዓመታዊ ውድድሩ ዝግጅት ሲያደርግ መመልከት የተለመደ መሆኑንም ያስረዳሉ።
የሰራተኛው የስፖርት መድረክ እንደ አገር በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ቢሆንም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እየተካሄደ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከነዚህ ፈተናዎች አንዱ የተሳታፊ ማሕበራት ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ ነው። የተሳታፊ ማሕበራትን ቁጥር ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጥረት ማድረጉን እንደቀጠለ የሚናገሩት የኢሠማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ፣ “እኛ በርካታ ማሕበራት እንዲሳተፉ ጥያቄ እናቀርባለን የሚመጡት ግን በሚፈለገው ልክ አይደለም፣ ይህ ከበጀትና አሰሪዎች ለስፖርት ካላቸው አመለካከት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፣ ለስፖርቱ ግንዛቤና ጥሩ አመለካከት ያላቸው አሰሪዎች ሰራተኞችን የማሳተፋቸውን ያህል የሌላቸውም አሉ።” በማለት ምክንያቱን ያስረዳሉ።
አዳዲስ ማሕበራት ወደ ስፖርቱ የመምጣታቸውን ያህል በተለያዩ ምክንያቶች ነባር የነበሩ የሚቀሩበትም ሁኔታ አለ። አብዛኛው የእነዚህ ማሕበራት ችግር የበጀት ነው። ይሄ ሲስተካከል ግን ወደ ስፖርቱ ለመመለስ ፍላጎት አላቸው።
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለፃ፣ የሰራተኛውን ስፖርት የሚያካሂድበት የራሱ የማዘውተሪያ ስፍራ አለመኖር ሁሌም የስፖርቱ ትልቅ ችግር ነው። ኢሰማኮ ሰራተኛው ስፖርታዊ ውድድሮቹን የሚያደርግበት የራሱ ማዘውተሪያ ስፍራ ባለቤት እንዲሆን ባለፉት ዓመታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም