በአምስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

– 150 ቶን ከሰል በሰዓት የማምረት አቅም አለው

– የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን 75 በመቶ የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ያሟላል

ታርጫ፡- በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት አለ፡፡ በተለይ የከሰል ማዕድን ክምችት በከፍተኛ መጠን ይገኛል፡፡ ይህንን የከሰል ማዕድን አልምቶ ሀገርን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ መጥቀም ያስፈልጋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ፋብሪካው በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል እየተገነባ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለፃ፤ ፋብሪካው በተለይ ከውጭ የሚገቡ የታጠበ የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትን ለመቅረፍም የራሱ አስተዋፅዖ አለው። የታጠበ የድንጋይ ከሰል ከውጪ በከፍተኛ ምንዛሪ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ፋብሪካው እስካሁን አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል ብለዋል።

የከሰል ማዕድን አምራቹ ኢቲ ማይኒንግ ፋብሪካ እንደሚሰኝ የተናገሩት ኃላፊው፤ ፋብሪካው ወደ ሙከራ ትግበራ እየገባ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል። የኢቲ ማይኒንግ ድርጅት ተወካይ ወንድሙ ምትኩ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፋብሪካው የመጨረሻ አስፈላጊ የሚባሉት ነገሮች እየተገጠሙለት ይገኛል። በመገባደድ ላይም ነው።

እንደ አቶ ወንድሙ ገለፃ፤ ፋብሪካው ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረ ነው። በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ሥራው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በፋብሪካው የሚሠሩ ቋሚ ሠራተኞች ሥልጠና እየተሰጠ ነው። የሙከራ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተመርቆ ሥራ ይጀምራል።

ኢትዮጵያ በቂ የከሰል ማዕድን እያላት ከደቡብ አፍሪካ በውጭ ምንዛሪ የታጠበ ከሰል ገዝታ እንደምታስገባ የገለፁት አቶ ወንድሙ፤ በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዚህ ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገዋል ብለዋል። ይህ ፋብሪካ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የታጠበ ከሰል ፍላጎትን 75 በመቶ የመሸፈን አቅም ያለው ነውም ብለዋል።

ፋብሪካው በሰዓት 150 ቶን የታጠበ ከሰል የማምረት አቅም እንዳለውም ነው የገለፁት። የፋብሪካው ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር በላይ አሰፋ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የታጠበ ከሰል ፍላጎት ሀገሪቱ በዓመት በአማካይ 400 ሚሊዮን ዶላር እያሳጣት ነው። ኢቲ ማይንግ ፋብሪካ ሲጠናቀቅ ይህን ወጪ ማዳን ያስችላል ብለዋል።

ፋብሪካው 3 ሺህ 600 ቶን የታጠበ ከሰል በቀን የማምረት አቅም አለው ያሉት ኢንጅነር በላይ፤ በጥቂት የውጪ ሀገር እና በሀገር ውስጥ ሠራተኞች እየተገነባ መሆኑ ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ልምድ መካበት የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለዋል።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን ጥር 21/2016

Recommended For You