ቀጣናዊ ትስስር – ለአርብቶ አደሩ የላቀ ተጠቃሚነት

በቆላማ አካባቢዎች ኑሮውን ያደረገው የኢትዮጵያ አርብቶ አደር የኑሮ መሠረቱ ለሆኑት እንስሳት ግጦሽና ውሃ ፍለጋ ብርድና ቁሩ፤ ሐሩሩና ፀሐዩ ሳይበግረው ዘወትር ይማስናል።ለራሱ ይሄነው የሚለው ጥሪት ሳይቀረው ከልጆቹ ለማይለያቸው ከብቶቹ፤ በጎቹ፤ ፍየልና ግመሎቹ ሲል ነጋ ጠባ ይጓዛል፤ በየደረሰበት ጎጆውን ይቀልሳል፤ ደግሞ አፍርሶ ይጓዛል።

አልፎ ተርፎም ጎረቤት ሃገራት እየገባ የእንስሳቱን ቀለብ ይፈልጋል፤ የንግድ ልውውጥ ያደርጋል።እንደእሱ በእንስሳት እርባታ ላይ ከተሠማሩ ጎረቤት አርብቶ አደሮች ጋር ወዳጅነት መሥርቶ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይፈጥራል።አልፎ አልፎም የጥቅም ግጭት እያጋጠመው ለጉዳት ሲዳረግ ይስተዋላል ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማጎልበት ረገድ ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ የልማት ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሠራ ይገኛል።በተለይም በየሁለት ዓመቱ በሚከበረው የአርብቶ አደሮች ቀን አማካኝነት የማኅበረሰቡ ችግር ጎልቶ እንዲታይ፤ ብሎም የሚፈታበትን አቅጣጫ ለመጠቆም ጥረት አድርጓል፤ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ዘንድሮም ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ በዓል በባሕል፤ በቋንቋና አኗኗር ዘይቤው ከጎረቤት ሀገራት አርብቶ አደሮች ጋር ያለው ማኅበራዊ መስተጋብር ይበልጥ ሊጠናከር በሚችልበት መልኩ እየተከበረ ነው።በበዓሉ ላይም ከሱዳን በስተቀር የሁሉም ምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት አርብቶአደር ተወካዮች የታደሙ ሲሆን የየሀገራቸውን የአርብቶ አደሮች ሕይወትና ስለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሚያሳዩ መሰናዶ ይዘው ቀርበዋል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ (ዶክተር) ሰሞኑን ከ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የዘንድሮው የአርብቶ አደሮች በዓል የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራትን ባሳተፈ መልኩ እንዲካሄድ የተደረገበት ዓላማና ፋይዳውን ሲያብራሩ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር የቆየውን የአርብቶ አደሮች ቀን በዓል ዘንድሮ በተለየ መልኩ ጎረቤት ሃገራትን በማሳተፍ ማክበር ያስፈለገው ቀጣናዊ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር በማለም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹አርብቶ አደርነት የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረ-ቀለም›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ የሚገኘው ይኸው በዓል፣ በዋናነት አርብቶ አደርነት የሁሉንም ሀገራት ሕዝቦች የሚያዋሕድና ኅብረቀለም የሚፈጥር መሆኑን ለማሳየት ታሳቢ ተደርጎ መቀረፁን ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዳሉ።በበዓሉ የሚታደሙት አርብቶ አደሮች ባሕላዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ከማጠናከር ጎን ለጎን የጋራ በሆኑ እንደ ድርቅ፤ የጎርፍ አደጋ እንዲሁም ኮንትሮባንድ ንግድ የመሰሉ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም በልማት አማራጮች ላይ ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሠሩ ምቹ እድል ይፈጥራል ተብሎ መታመኑን ያመለክታሉ፡፡

በበዓሉ የአፋር አርብቶአደሮች ከጅቡቲ፤ የሱማሌ ክልል አርብቶ አደር ከሱማሌ ላንድና ከሶማሊያ፤ በኦሮሚያና ደቡብ ያሉት ከኬንያ፤ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉት ከደቡብ ሱዳን አርብቶ አደሮች ጋር የባሕል፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚና የገበያ ትስስራቸውን ይበልጥ ስለሚያጠናክሩበት መንገድ የሚወያዩበት እድል እንደተፈጠረላቸው ይጠቁማሉ።

የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማሳየት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው፣ ‹‹የቀጣናው አርብቶ አደሮች ልምድና ተሞክሮቻቸውን በመለዋወጥ የንግድ ትስስራቸውን ይበልጥ እንዲያሳልጡ፤ ብሎም ለሚያገጥሟቸው የጋራ ችግሮች በጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ ነው›› ይላሉ።

ተክለዮሐንስ ብርሃኑ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ናቸው። እንደእሳቸው ገለፃ፤ እንደ ሃገር የአርብቶ አደሮች ቀን መከበሩን ለአርብቶ አደሩ እውቅና ከመስጠት፤ በአካባቢው ያሉ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታትና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ የማይናቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል።በየአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ለመጠቀም አወንታዊ ሚና ተጫውቷል።

ዘንድሮ ደግሞ ከሀገር በላቀ ቀጣናዊ ትስስር እንዲፈጥር ታሳቢ ተደርጎ መከበሩ ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።በተለይም በሁሉም ሃገራት ያለው አርብቶ አደር አካባቢ በመሠረተ ልማት የተጎዳ፤ በልማትም ወደኋላ የቀረ ከመሆኑ አንፃር መድረኩ ስለችግሮቻቸው በመወያየት፤ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ የሚያግዝ እንደሆነ ያስረዳሉ።በፖሊሲ ማዕቀፍ ተደግፈውም በጋራ ፕሮጀክቶች ነድፈው የልማት ሥራዎችን እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

መድረኩ በተለይም ሀገራቱ ድርቅን ለመከላከልና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ ምርምሮች፤ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችንና ልምዶችን እርስበርስ ለመለዋወጥ የሚያግዝ መሆኑን ያነሳሉ።አንዱ ሀገር ከሌላው ተሞክሮ ከመቅሰም ባሻገር በጋራ በሆኑ ችግሮች ላይ በጋራ ምርምርና ጥናት በማድረግ መፍትሔ እንዲያመጡ ያደርጋልም የሚል እምነት አላቸው።

በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃውን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሀገራቱ በተናጠል በሚያደርጉት እሳት የማጥፋት ዘመቻ ብቻ ውጤት ሊመጣ አይችልም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜያት እቅዶችን በማውጣት በጋራ ሆነው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና የአርብቶ አደሩን ድርቅ የመቋቋም አቅም ማጎልበት እንዲቻል ተቀናጅተው ሊሠሩ ይገባል።ከዚህ በተጨማሪም የየሀገሩቱ ተመራማሪዎችና የግብርና ባለሙያዎች በመተባበር የግጦሽ መሬትና የመኖ አቅርቦትን በማሻሻል እና በመስኖ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የእንስሳት ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳንኤል ተመስገን(ዶ/ር) ደግሞ እንደሚሉት፤ በመድረኩ የሀገር መሪዎችና የእርዳታ ተቋማትም የሚሳተፉ መሆኑ በአካባቢው ያሉ ችግሮች፤ የኅብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎችና ያሉ ምቹ እድሎች በተጨባጭ እንዲገነዘቡ ያደርጋል።ከዚህም ባሻገር የፖሊሲ ትኩረት እንዲያገኝና በቂ የፋይናንስና ቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያገኙም የላቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።በአካባቢው በየራሳቸው መንገድ የሚሠሩ የልማት ድርጅቶችም ተናበው በቅንጅት እንዲሠሩ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።

በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) የቆላማ አካባቢዎችና የእንስሳት ልማት ዳይሬክተር ደረጀ ዋቅጅራ (ዶ/ር)በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የኢጋድ የእንስሳት ልማት ማዕከል በዋናነት በአባል ሀገራቱ ያለውን የእንስሳት ሃብት እንዲሁም በቆላማ አካባቢዎች ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በጋራ አልምተው እንዲጠቀሙ ይሠራል።የስምንቱ የኢጋድ ሀገራት 70 በመቶ የሚሆነው መሬት ቆላማ ነው።በእነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ሰብል ማምረት የማይቻል በመሆኑ ኅብረተሰቡ የሚተዳደረው በአርብቶ አደርነት ነው።ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ ሀገራት ጋር በአርብቶ አደሮች አማካኝነት ትተሳሰራለች።አርብቶ አደሩ ዝናብና ግጦሽ ፍለጋ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው በመሄድ ከሌላ ሀገር አርብቶአደር ማኅበረሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥሯል።

ይህም ከቦታ ቦታ የመኖር ዘይቤ አሉታዊ ጎን እንዳለው ይናገራሉ።‹‹አርብቶ አደሮቹ ከአንዱ ወደ አንዱ ሃገር ሲንቀሳቀሱ የተለያዩ ችግሮች ይፈጠራሉ፤ በዋናነትም የእንስሳት በሽታና ግጭት ተጠቃሽ ነው›› ይላሉ።እያንዳንዱ ሃገር የራሱን በሽታ ካልተቆጣጠረ በሽታው ወደ ሌላ ሀገር ይዛመታል።ግጭቱን መከላከል ካልቻለ ትልቅ ቀውስ ያስከትላል ሲሉ ያስረዳሉ።በመሆኑም ተቋማቸው በዋናነት የእንስሳት በሽታዎችም ሆነ ግጭቶቹ እንዳይስፋፉ በጋራ የመቆጣጠር ሥርዓት እንዲዘረጋ ኃላፊነቱን ወስዶ እያሠራ ስለመሆኑ ያብራራሉ።

በሌላ በኩል በድንበር አካባቢዎች ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሃብት ሃገሮች የተሻለ ገበያ እንዲያመቻቹ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠቅሳሉ።በተለይም በዓረብ ሃገራት ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ፍላጎት ስላለ በጋራ እንዲነግዱ የሚደረግ መሆኑን ይጠቁማሉ።ከዚሁ ጎን ለጎንም እንደመንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶች ሃገራቱ በጋራ ተቀናጅተው እንዲያለሙ በማድረግ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን፤ ንግዱም እንዲሳለጥ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹እኛ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው አካባቢውን በመቀየር የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግና ቀጣናውን በልማት ማስተሳሰር ላይ ነው፤ ይህም በአሁኑ ወቅት ትልቅ ተቀባይነት እያገኘ ነው›› የሚሉት ደረጀ(ዶ/ር)፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ‹‹ሆርንኦፍ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ›› የተሰኘ ፕሮግራም በዓለም ባንክ፤ በአፍሪካ ልማት ባንክ፤ በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ተግባራዊ መደረጉን ነው ያመለከቱት።

የኅብረተሰብ መሪ የሆኑ ሰዎች በመድረኩ መሳተፋቸው፤ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ወክለው የመጡትንም ማኅበረሰብ የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ።በግጦሽም ሆነ በተለያየ ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱም ያደርጋልም ይላሉ።ተቋማቸው መሰል የሠላምና የውይይት መድረኮች ማጠናከር ሥራን እየሠራ መሆኑን አንስተው፤ ‹‹በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር ባሉ አርብቶአደሮች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የሃገር ሽማግሌዎችን በማወያየት አለመግባባቶች እንዲፈቱ፤ ሕገወጥ ንግድንም በጋራ መከላከል እንዲቻል ጥረት ያደርጋል›› ሲሉ በአብነት ይጠቅሳሉ።በተጨማሪም የውሃ መሠረተ ልማቶችም በቅንጅት በማልማት የሁለቱም ሃገራት አርብቶአደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

በቀጣናው ያለው ሰፊ ሃብት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግም ሆነ አካባቢውን ከድርቅ ነፃ ማድረግ የረጅም ጊዜ ሥራ መሆኑን ደረጀ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል።በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ማኅበረሰብ ለመፍጠር አርብቶ አደሩን በቴክኖሎጂ፤ በምርምርና በፋይናንስ የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑን ያመለክታሉ።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራቱ በበዓሉ ላይ መታደማቸው ትስስራቸው ምን ያህል የጠነከረ መሆኑንና አርብቶአደር አጥር፤ ድንበር የሌለው መሆኑንም በተጨባጭ አመላክቷል የሚል እምነት አላቸው።‹‹ኢትዮጵያ በዚህ ዝምድና ታምናለች፤ ደግሞም የቀጣናው አሰባሳቢ ሃገር እንደመሆኗ ይህንን ትልቅ አካባቢ /ስቴት/ ይዘን የቀጣናችን ትስስር በማጠናከር አብሮ መበልፀግ ነው የምትፈልገው›› ይላሉ፡፡

‹‹ስንደመር ውበት እንጨምራለን፤ ስንደመር ኃይላችን ይበረታል›› የሚሉት አፈጉባኤው፤ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሀገራት ምንም እንኳን የተለያዩ ማኅበራዊ፤ ባሕላዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ- ምሕዳራዊ ባሕሪያት ቢኖራቸውም፤ ሀገራቱ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን በታሪካቸው እና በሥነ-ሕዝባዊ ባሕሪያቸው ያላቸውን የቅርብ ዝምድና አቅም አድርገን ወደ ብልፅግና ፈጥነው መራመድ እንደሚገባቸው ያስገነዝባሉ።

እንደአፈ ጉባኤው ማብራሪያ፤ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በተፈጥሮም የሚጋሯቸው በርካታ ሃብቶች አሉ። በዋናነትም ለልማት ምቹ በሆኑ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ሰፊ መሬቶች፣ እጅግ የበለፀጉ ማዕድናት ባለቤቶች ናቸው።ይሁንና አካባቢዎቹ ከዚህ ሀብት ይልቅ ገዝፈው የሚታዩት የከፋ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ስደትና ግጭቶች ናቸው።ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅና የምግብ ዋስትና እጦትም የእነዚህ አካባቢዎች መለያ ሆነዋል።

‹‹‘ይህ ለምን ሆነ?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል›› የሚሉት አቶ ታገሰ፤ ማኅበረሰቡ በተሰጠው ፀጋ መበልፀግ ሲችል በድህነትና ረሀብ የሚሰቃይበትን ምክንያት የየሃገራቱ መንግሥታትና ፖሊሲ አውጪዎች ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል የሚል እምነት አላቸው።ሀገራቱ ከምንጊዜውም በላይ ቀጣናዊ ትስስራቸውን ማጥበቅ ቀዳሚ ጉዳያቸው አድርገው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም ነው አስገንዝበዋል።

እንደአፈጉባኤው ማብራሪያ፤ የአፍሪካ ብሎም የቀጣናው አካባቢዎች የሚራቡት፣ የሚጠሙትና የሚሰደዱት ለመበልፀግ የሚችሉበት ሃብት ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም።ለአብነት እንኳ አርብቶአደሮች ያላቸው ሰፊ የእንስሳት ሃብት የእነርሱን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ሕይወት መቀየር ትልቅ አቅም ይሆናል።ነገር ግን የሚታየው በተቃራኒው መሆኑ ሁሉንም ሀገራት ሊያስቆጭ ይገባል።የቀጣናው የድህነት ታሪክ ወደፊትም እንዳይቀጥል የምሥራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ አርብቶ አደሮችና መንግሥታት ኃላፊነት ነው።

‹‹የባሕልና የደም ትስስራቸውን ወደ ኢኮኖሚ ትስስር ፈጥኖ መቀየር ለነገ የምንለው የቤት ሥራ አይደለም›› የሚሉት አቶ ታገሰ፤ ለዚህም ቀጣናዊ ትስስሩን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ የኢትዮጵያ የምንጊዜም እምነት እንደሆነ ይገልጻሉ።ትስስሩን በኢኮኖሚ ገመድ በማጥበቅ የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈንም የሀገሪቱ የምንግዜም ፍላጎትና ጥረት መሆኑንም አስታውቀዋል።‹‹ኢትዮጵያ ምንጊዜም ትስስርን ታስቀድማለች።ሌላው ቀርቶ የምትገነባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶቿ ጎረቤቶቿም እንዲጠቅሙ፣ ከበረከቱም አብረው እንዲቋደሱ የማድረግ የቁርጠኝነቷ ማሳያ ናቸው›› ይላሉ፡፡

በመሆኑም በዚህ ደረጃ የተጀመረው የትስስር መንፈስ ተጠናክሮ አካባቢው የተቸረውን ውድ የተፈጥሮ ስጦታ በጋራ በማልማትና በመጠቀም፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገርም በቀጣናው ሰላምን እያሰፈኑ መጓዝ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።እንዲህ ያሉ መድረኮች ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህ መድረክ ቀጣይነት እንዲኖረው መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ማሕሌት አብዱል

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You