‹‹ካባ›› ቀደም ሲል የክብር መገለጫ፣ በንጉሣውያን ቤተሰብ የሚዘወተር፣ የሀብት መገለጫም ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚለበስም አይደለም፤ የሚለብሱት ቢኖሩም በየቀኑ የሚለበስ አይደለም።
አሁን አሁን ከባሕላችን አንዱ በሆነው የሠርግ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ለመለስ ሙሽሪት እና ሙሽራው በሚለብሱት የሀገር ባሕል ልብስ ላይ ካባ ይደርባሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ የመስቀል ምስል ያረፈበትን ካባ እና ተመሳሳይ የሆነውን በአናት ላይ የሚጠለቅ አክሊል አድርገው የጋብቻ ሥርዓታቸውን ያከናውናሉ።
በተለያዩ ሁነቶች፣ የምስጋና እና የሽልማት ፕሮግራሞች፣ በሥራቸው ከበሬታን ላተረፉ ሰዎች ካባ በሽልማትና የክብር መገለጫነት ይበረከትላቸዋል። በትዳራቸው በርካታ ዓመታትን በአብሮነት ያሳለፉ ጥንዶችም እንዲሁ በትዳር የቆዩበትን የብር፣ የወርቅ እዮቤልዩ በዓል ሲያከብሩ ካባ ይደርባሉ። ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ሰዎች የልደት በዓላቸውን ለማክበር የሚደርቡትም ነው።
በሌሎች አገራት ኢትዮጵያን ወክለው የሚሠሩ አምባሳደሮችም ሀገራቸውን ያስተዋውቁበታል። ከዚህም ባሻገር ለሌላ ሀገር ዜጋ እና ለኢትዮጵያ በጎ ነገር ላበረከቱ የሥራ ኃላፊዎችም ያላቸውን ክብርና ምስጋና ካባ በመስጠት እና በማልበስ ይገልጻሉ።
ይህ ካባ አሁንም ተወዳጅነቱ እና ተፈላጊነቱ ቀጥሏል። አቶ ዓለምሰገድ አሰፋ የዚህ በጥቂት ሰዎች እጅ ላይ ብቻ የሚገኝ ካባ ሙያ ባለቤት ነው። በዚህ ሥራም ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል። በሚኖርበት አካባቢ ይህንን ሙያ የሚያወቁ ሰዎች በመኖራቸው ወደሥራ ቦታቸው በመሄድ ሙያውን ተምሮ አሁንም ድረስ የገቢ ምንጩ አድርጎት እየሠራ ይገኛል።
በሙያው የ15 ዓመት ልምድ ያለው ዓለምሰገድ፤ የካባ ሥራ ቀላል የማይባል ጊዜ እና ጉልበት እንደሚጠይቅ ይናገራል። ዓለምሰገድ እንደሚለው፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ካባ ሲባል የተለመደው ጥቁር ከፋይ ጨርቅ ላይ ከላይ እስከታች ለየት ባለመልኩ ወርቃማ በሆነ የክር ቀለም የተጠለፈ ሲለበስም የተለየ ውበትን የሚያጎናጽፍ ነው። ካባ አሁን በተለያዩ የቀለም አማራጮችና ዲዛይኖች እየተሠራ ነው።
በገበያው ላይ እንደ መግባቢያ ‹‹የሙካሽ ካባ›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ መነሻውም ካባ ለመሥራት እንደ ግብዓት የሚያገለግለው ‹‹ሙካሽ›› የሚባል ክር በካባው ላይ ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ ነው። ካባ ምንም እንኳን በኛ ሀገር ብቻ የሚታወቅ የክብር ልብስ ቢሆንም፣ ዓለምሰገድ በቆየባቸው የሥራ ዓመታት ካባ ለመሥራት የሚጠቀምባቸው የከፋይ ጨርቅና ሙካሽ ግን ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ናቸው።
‹‹ ዋናው ግብዓት ሙካሽ ሲሆን ሌሎች እቃዎችን ሰዎች ሲያመጡ እግረ መንገዳቸውን እንዲያመጡልን እናደርጋለን›› የሚለው ዓለምሰገድ፤ ቋሚ የሆኑ አስመጪዎች ባለመኖራቸው ካባ ሳይሠሩ የሚቆዩባቸው ጊዜያት መኖራቸውን ይናገራል። ግብዓቱ ከተለያዩ ሀገሮች ይመጣል፤ የህንድ ሙካሽ፣ የግሪክ ሙካሽ እየተባለ ይጠራል። ሕንዳውያን ይህንን ሙካሽ ለጌጣጌጥ መሥሪያነት ይጠቀሙበታል።
አንድ ካባ ተሠርቶ ለደንበኞች ሲቀርብ ለሠርግ ከሆነ ለሙሽሮች አንድ ላይ ጥንድ ካባ ይዘጋጃል። ዓለምሰገድ አንድ ካባ ብቻውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ 15 ቀናት እንደሚወስድ ጠቅሶ፣ ካባው በስድስት ባለሙያዎች ከተሠራ ደግሞ አንድ ሳምንት ይወስዳል ።
ካባው ላይ ያሉት ዲዛይኖች ይህ ነው የሚባል ስም እንደሌላቸው የሚያነሳው ዓለምሰገድ፤ ጠላፊው በጊዜ ሂደት እና በሥራ ልምድ ቆይታው የራሱን ፈጠራ በማከል እንደሚሠራው ይገልጻል።
ደንበኞችም ዓይናቸው ያረፈበትን አንዳንዴም ደግሞ ታዋቂ ሰዎች ላይ የተመለከቱትን ዲዛይን እንደሚመርጡ ገልጾ፤ የአሠራር ሂደቱ የሚጀምረው ደንበኞች በመረጡት የከፋይ ቀለም ተለክቶ ከተቆረጠ በኋላ ነው፤ ከዚያም በአቡጀዲ ጨርቅ ላይ ተወጥሮ በስፌት ክሮች ዲዛይን ከወጣለት በኋላ በክሩ በመመራት በሙካሽ ይጠለፋል ሲል ያብራራል።
‹‹አንድ ሰው የካባ ሥራ ለመልመድና በሥራው ባለሙያ ለመባል ዓመታትን ይወስድበታል›› የሚለው ዓለምሰገድ፤ በሙያው ብቁ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለ ይናገራል። ለዚህም ምክንያቱ ሙያውን ለመልመድ የሚያስችል ትምህርት ቤት በሀገሪቱ ባለመኖሩም መሆኑን ገልጿል። በሀገራችን በልምድ እየተላለፉ ከመጡ የሙያ ዓይነቶች እንደ ሽመና እና የካባ ሥራን ጨምሮ ሰዎች በፍላጎት ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ተጠግተው የሚማሩበት ሁኔታ ብዙም እንዳልሆነም ተናግሯል።
አብዛኛዎቹ ካባ ማሠራት የሚፈልጉ ሰዎች በማሽን የሚሠራ እንጂ በሰዎች እጅ የሚጠለፍ እንደማይመስላቸው ጠቅሶ፣ በቶሎ እንዲደርስላቸው እንደሚፈልጉም ዓለምሰገድ ይገልጻል፤ ሥራው ጊዜ የሚወስድና ጥንቃቄ የሚፈልግ መሆኑንም ይናገራል። ለተለያዩ ፕሮግራሞች ካባ ሲሠራ ጊዜ የመውሰዱን ያህል ሲለበስም እንዲሁ ጥንቃቄን እንደሚፈልግ ነው የተናገረው።
ዓለም ሰገድ እንደሚለው፤ ለካባ የሚደረገው ጥንቃቄ ከአቀማመጥ ይጀምራል። ሙካሹ የሽቦ ባሕሪ ያለው በመሆኑ በጊዜ ሂደት እንዳይደበዝዝ አየር ማግኘት ይኖርበታል፤ እንደ ሽቶ ያሉ ነገሮች ባይደረጉበት ይመረጣል። ማጽዳት ከተፈለገም ተሠርቶ በተጠናቀቀበት ወቅት ወጥ ሆኖ እንዲቆይ ማድረቂያ የሚቀባ ሲሆን፣ ውሃ ከነካው ስለሚለቅ ውበቱ ይቀንሰዋል። በመሆኑም ማፅዳት በተፈለገበት ወቅት የእጥበት አገልግሎት በሚሰጡ ባለሙያዎች ደረቅ እጥበት ይደረግለታል ።
ዓለምሰገድ ካባን ለመሥራት እንደ ግብዓት የሚያገ ለግለውን ከፋይ ጨርቅ በሜትር፤ ሙካሽ ደግሞ በኪሎ ገዝቶ ይሠራል። ‹‹የካባ ሥራን የሚያስውበው ሙካሽ ሲሆን፣ ዋጋው እንደምንጠቀመው የሙካሽ ብዛት ይወሰናል›› የሚለው ዓለምሰገድ፤ ካባው ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ለገበያ የሚቀርብበት ዋጋ እንደ ሠሪው እንደሚወሰን ይናገራል። አንድ ባለሙያም ካባው ላይ የሚጠቀመውን ሙካሽ ሳይሰስት ጥንቅቅ አድርጎ የሠራው እንደሆነ ዋጋው ከፍ ያለ እንደሚሆንም ጠቅሶ፤ ተጨማሪ ግብዓቶቹን የሚገዛበት ዋጋ ካባው በሚሸጥበት ዋጋ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣም አመላክቷል ።
ከዚህ ቀደም አንድ ሜትር የከፋይ ጨርቅ ከ50 እስከ 80 ብር፣ ሙካሽ ደግሞ ከአንድ ኪሎ እስከ አንድ ኪሎ ከግማሽ ሙካሽ የሚፈጅ ሲሆን አንዱ ኪሎ በ80 ብር ይሸጥ ነበር። ካባው ተሠርቶ ሲሸጥም ሁለት ሺ ብር ያወጣ ነበር። አሁን ላይ ግን አንድ ሜትር ከፋይ ጨርቅ አንድ ሺ ብር፣ አንድ ኪሎ ሙካሽ ደግሞ አምስት ሺህ ብር ለገበያ የቀረበበት ዋጋ ነው። ታዲያም ጥራት ያለው ጥንድ ካባ 20 ሺህ ብር እና ከዛም በላይ ለገበያ ይቀርባል። ለገበያ በሚቀርብበት ጊዜም ለሚፈልጉት ሁነት የሚገዙም፣ ተከራይተው የሚጠቀሙም አሉ ሲል ዓለምሰገድ አስታውቋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም