ሴቶች ከቤት ውጪ በሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴያቸው ቦርሳ አይለያቸውም። ከቤት ለመውጣት ሲያስቡም እንደ ዋዛ ያላቸውን ቦርሳ ያዝ አድርገው አይወጡም። ከልብሳቸው እና ከሚገኙበት ሁነት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ቦርሳ ይመርጣሉ። የቦርሳቸው አገልግሎት እቃዎችን ከመያዝ ያለፋል። ለሥራ ፣ ለጉዞ ፣ ለተለየዩ ፕሮግራሞች የሚመረጡ ከመሆናቸውም በላይ በአይነትም ይለያያሉ፡፡
‹‹ቦርሳ ለሴት ልጅ በጣም ወሳኝ ነው፤ እኔም ቦርሳ በጣም እወዳለሁ ›› የምትለው ዲዛይነር ረድኤት እጅጉ፣ ከቤት ውጪ በሚኖራት እንቅስቃሴዋ ሁሉ ቦርሳ ከእጇ እንደማይጠፋ ትናገራለች። ዲዛይነሯ ቦርሳ ትሠራለች። ከምትሠራቸው ቦርሳዎች መካከል በሴቶች ትእዛዝ የምትሠራቸው ቦርሳዎች ይገኙበታል።
‹‹ዱዋላ ሌዘር ›› በተሰኘው ድርጅቷ ከቆዳ የሚሠሩ ቦርሳዎችን በደንበኞቿ ምርጫና ፍላጎት እንደምትሥራ ተናግራ፣ ለድርጅቷ ‹‹ዱዋላ ሌዘር›› የሚለውን ስያሜ የሰጠችበት ምክንያትም፤ ቃሉ ከቤንች ቋንቋ የተወሰደና ትርጉሙም በልዩነት አንድነት የሚል መሆኑን ገልጻለች። ‹‹ዱዋላ ሌዘር›› ከተመሠረተ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። በሰዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት መልካም ነው።
የቆዳ ቦርሳዎችን በሰዎች ምርጫ በትእዛዝ መሥራት በኢትዮጵያ ብዙም አልተለመደም ያለችው ረድኤት ፣ ቦርሳዎችን በትእዛዝ ብቻ አትሠራም። ያረጁ እና አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ቦርሳዎችን በተለየ መንገድ በማደስ በድጋሚ አገልግሎት እንዲሰጡም ታደርጋለች።
ወደ እዚህ ሥራ ልትገባ የቻለችው አባቷ በመኖሪያ ቤታቸው የቆዳ ጃኬቶችን ሲሠሩ በትኩረት ትመለከት ስለነበር ነው፤ በዚህም ሙያውን በሚገባ መማር ችላለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ቦርሳ መሥራት ብዙም ያልተለመደ መሆኑን በማሰብ ‹‹ቦርሳዎችን በሰዎች ፍላጎት ዲዛይን አድርጌ ለምን አልሠራም የሚል ሃሳብ መጣልኝ›› ትላለች። የእጅ ሙያ ረድኤት ባደገችበት ቤተሰብ ውስጥ የሚበረታታ እና የሚደገፍ መሆኑም ወደ ቦርሳ ሥራው እንድትሳብ ያደረጋት ምክንያት ነው። ወደ እዚህ ሥራ ስትገባ ከወላጆቿ ጥሩ ድጋፍን ማግኘቷም በሥራው ውጤታማ እንድትሆን እንደረዳት ገልጻለች።
ረድኤት አሁን በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመያዝ እየተማረች ትገኛለች። ወደዚህ ሥራ ለመግባት ያሰበችው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና ወስዳ እረፍት ላይ በነበረችበት ወቅት ነው። የፈተና ውጤቷን እየጠበቀች ባለችበት ወቅት በእረፍት ጊዜዬ ምን ልሥራ በሚል ሃሳብ ሰዎች በፈለጉት ዲዛይን ማለትም በደንበኞች ፍላጎት መሠረት ‹‹ custom made ›› የሴት ቦርሳ ለመሥራት መወሰኗን ገልጻለች።
‹‹የተመደብኩት ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ነበር። በወቅቱ የነበረው የጸጥታ ሁኔታ ከባድ ስለነበር እዚሁ በኮሜርስ የማታ እየተማርኩ ቀን ቀን ስራዬን ለመሥራት ወሰንኩ›› የምትለው ረድኤት፤ ከዚያም ሙሉ ጊዜዋን ለእዚህ መስጠቷን ትገልጻለች።
‹‹ቦርሳ እንደ ፋሽን በሀገራችን ገና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ነው›› የምትለው ረድኤት፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ቤተሰቦቿ ጋ ሆና እየተከታለች ቢዝነሷን ለማስኬድ ወስና እየሠራች ትገኛለች። ቀጥላም ያደረገችው የወሰደችውን የአጭር ጊዜ ሥልጠና እንዲያጠናክርላት በቤቷ ሆና ቦርሳ መሥራቱን መሞከር እና በቅርቧ ላሉ ሰዎች ማስተዋወቅ ነበር።
ሥራውን ስትጀምረው ደንበኛ ማግኘትና ሰዎችን ማሳመን በጣም ከብዷት ነበር፤ በሂደት ግን ቦርሳዎችን ለመሥራት በቅታለች። ሥራዋን በጀመረችበት ወቅት የቅርቤ የምትላቸው ሰዎች እና ቤተሰቦቿ እሷን ለማበረታት ብለው ቦርሳ እንድትሠራላቸው ያደርጉ እንደነበርም ታስታውሳለች።
ሥራው ፈታኝ እንደሆነም ጠቁማለች። ከቆዳ የሚሠሩ ቦርሳዎችን በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ ዋናው ግብዓት የሆነው ያለቀለት ቆዳ፣ ዚፕ ፣ ማንጠልጠያ ፣ ቁልፎች እና ማስዋቢያ ጌጣጌጦች በአብዛኛው ከውጭ ሀገር የሚመጡ እንደሚመጡ ጠቅሳ፣ ‹‹እነዚህን ግብዓቶች ማግኘት በጣም ይከብዳል፤ ዋጋቸውም በጣም ውድ ነው›› ትላለች፡፡
ረድኤት የቦርሳ ሥራዋ አነስተኛና በራሷ የምታንቀሳቅሰው ቢዝነስ መሆኑን አመልክታ፣ የምትጠቀማቸውን ግብዓቶችም በአነስተኛ ዋጋ ከሚያቀርቡ አከፋፋዮች ነው የምትገዛው።
ግብዓቶቹን በማታገኝበት ጊዜ ደንበኞቿን ሌላ አማራጭ እንዳለ ትነግራቸዋለች፤ ምክንያቱም ደግሞ እሷ የምትሠራው ሰዎች በሚፈልጉት የቆዳ ቀለም ያዘዙትን የቦርሳ አይነት በመሆኑ ነው ትላለች።
ሰዎች በፎቶ አይተው የወደዱትን ማንኛውንም እቃ በአካል ሲመለከቱት የሚኖራቸው ምላሽ ተመሳሳይ አይሆንም። በፎቶ ያዩትን ልክ ሆኖ ሲያገኙት በእርግጥም በሀገር ውስጥ የተሠራ ነውን ሲሉ በጥርጣሬ እንደሚጠይቁ ገልጻለች።
የምትሠራቸውን ቦርሳዎች የተመለከቱ ሰዎች የተለያዩ ዓለምአቀፍ ብራንድ የሆኑ እና የታወቁ የቦርሳ ዲዛይኖችን በማሳየት ቦርሳውን በሀገር ውስጥ እንድትሠራላቸው እንደሚፈልጉ ጠቅሳ፣ ‹‹ብዙ ሰዎች ደውለው በትክክል ይመጣል ወይ ብለው እንደሚጠይቋት ትናገራለች። ‹‹እኔ ግን ትክክለኛውን ዲዛይን ለማምጣት በቅድሚያ በቆዳ ላይ ከመሥራቴ በፊት በሴንቴቲክ ላይ በተደጋጋሚ እሞክረዋል፤ ሰርቼ ስጨርስ ካልወደዱት ደግሞ መልሼ አስተካክለዋለሁ ›› በማለት ታብራራለች።
‹‹ደንበኞቼ መጀመሪያ የሚፈልጉትን አይነት የቦርሳ ዲዛይን ፎቶ ይልኩልኛል። እኔም ለቦርሳው የሚሆነውን የቆዳ አይነት አማራጭ አሳያቸዋለሁ። የሚፈልጉትን ከመረጡ በኋላ የሚያስፈልጉኝን እቃዎች አሟላለሁ ›› የምትለው ረድኤት፤ ሥራውም ከ10 እስከ 15 ቀናትን እንደሚፈጅ አስረድታለች።
ረድኤት ቦርሳዎችን በአካባቢዋ ለምታውቃቸው ሰዎች በመሥራት እና በማስተዋወቅ ስትሠራ ቆይታለች፤ በቅርቡ ደግሞ የራሷን የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከፍታ ምርቶቿን በማስተዋወቅ ጥሩ ደንበኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማፍራት መቻሏንም ገልጻለች። ለዚህም ፈጣሪዋን እና በሥራዋ የደገፏትን ወላጆቿን አመስግና፣ በቅርቡም የራሷን ዲዛይኖች ይዛ አንድ መድረክ ላይ እንደምትቀርብ ጠቁማለች።
ቦርሳ ዲዛይን ማድረግ ልምድ እንደሚጠይቅ ጠቅሳ፣ አሁን ሰዎች ያሳዩዋትን ዲዛይን መሠረት አድርጋ ቦርሳዎችን እያመረተች ሲሆን፣ ወደፊት የራሷ ዲዛይን እንዲኖራት ለማድረግም አቅዳለች።
ረድኤት በቀጣይ ደግሞ በሀገሪቱ ብዙም ትኩረት ያልተደረገባቸውን ሰፌድን እና ቆዳን ከሀገሪቱ ጥለቶች ጋር በማጣመር ከቀርከሃ የሚሠሩ ቦርሳዎችን ለመሥራት ሃሳቡ አላት። ቦርሳ የሚያስውቡ ጌጣጌጦች ከውጭ የሚመጡ እና ውድ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ እነዚህን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ከሚሠሩ ጎበዝ ባለሙያዎች ጋር ለመሥራት ማሰቧንም ገልጻለች። ወጣቷ ዲዛይነር ረድኤት በቅርቡም በሰዎች ምርጫ ጫማዎችን መሥራት እንደምትጀምር ጠቁማለች።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም