ቱሪዝምና ስፖርት የተሳሰሩበት የወንጪ ደንዲ ሩጫ

በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገችው ኢትዮጵያ በምቹ የአየር ንብረቷና ማራኪ መልከዓ ምድር አቀማመጧ የተለየች ሀገር ነች። ምቹ የአየር ንብረቷ አትሌቲክስን በመሰሉ ስፖርቶች ውጤታማ እንድትሆንም አስችሏታል። እነዚህን ገፀ በረከቶቿ ዘመኑን እንዲዋጁ በማድረግ የስፖርት ቱሪዝምን ለማሳደግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሀገር ውስጥ እንዲካሄዱ ማድረግ ያስችላል።

በቅርቡ በዘመናዊ መልኩ ተገንብተው ለጎብኚዎች እንዲሁም ለስፖርተኞች ግልጋሎት ላይ ከዋሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዱ የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ነው፡፡

የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም መንፈስን ሀሴት የሚሞላ ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኝና ነፋሻማ አየር ያለው ከመሆኑ ባለፈ አትሌቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተገንብቶ በቅርቡ መመረቁ ይታወቃል። ይህን ትልቅ የቱሪዝም እሴት ከስፖርት ቱሪዝም ጋር ለማስተሳሰር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ በኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ፣ በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች አዘጋጅነት ታላቁ የወንጪ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ተካሂዷል፡፡

በውድድሩ በወንዶች የሸገር ከተማው አትሌት አዲሱ ነጋሽ አሸናፊ ሲሆን፣ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ሞገስ ጥኡማይ እና የጥሩነሽ ዲባባው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አትሌት ኤሊያስ ጫኔ ተከታትለው በመግባት፤ ከወርቅ እስከ ነሐስ ያሉትን ሜዳሊያዎች አጥልቀዋል። ሦስቱ አትሌቶች እንደየደረጃቸውም የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በሴቶች የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ አትሌቶቹ ጌጤ አለማየሁ እና ኑሪት አህመድ አንደኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የወርቅና የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት ፎቴን ተስፋዬ ደግሞ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች። ውድድሩን ተከትሎም የመካከለኛ ርቀት አትሌቷ ፎቴን፤ ሩጫው ዳገታማ በሆነ ቦታ በንፋሳማ አየር ታጅቦ የተካሄደ ቢሆንም ለአትሌቶች ተፈላጊ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ለስፖርቱ ምቹ የሆነውን ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመመልከቷ ባለፈ ፈታኝ በነበረው ሩጫ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቋም መደሰቷን ገልፃለች።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ በነበረው ጦርነት ለ3 ዓመት ከስፖርቱ ርቃ የቆየችው አትሌት ፎቴን ወደ ቀደመ ብቃቷ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡ በወንጪ ያደረገችው ልዩ ውድድርም ዝግጅቷን የለካችበት ሆኗል። በተያዘው የውድድር ዓመትም ጠንክራ በመሥራት ከወራት በኋላ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ሀገሯን ወክላ ለመሳተፍ ጥረት እያደረገች መሆኑንም ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ ውድድሩ የተካሄደበት የወንጪ አካባቢ ከፍተኛ ስፍራ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ እንደሆነ ይናገራል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይህንን በመሰሉ ከፍተኛ ቦታዎች ልምምድ በመሥራት በውጭ ሀገራት ዝቅተኛ ስፍራዎች በሚደረጉ ውድድሮች ላይ መሳተፋቸው ውጤታማ ያደርጋቸዋልም ይላል፡፡ በመሆኑም ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ነዋሪና ለቱሪስቶች ብቻም ሳይሆን አትሌቶችን ጨምሮ ለስፖርተኞች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ያስረዳል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ የክልል ፌዴሬሽኖች ስፍራው ላይ የአትሌቶች ማረፊያ መገንባት ቢቻል ልምምድ በመስራት ስፖርቱንም ቱሪዝሙንም ማሳደግ እንደሚቻል ያለውን እምነት ገልጿል።

የቀድሞው የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የማራቶን ባለድል ‹‹በውጭ ሀገራት ይህንን በመሰሉ ቦታዎች ስንወዳደር የምንመኛቸው ቦታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን አብዛኛዎቻችን አናውቅም። በመሆኑም እኔን ጨምሮ አብዛኛዎቻችን አትሌቶች የተሰማራነው በሆቴል ሥራ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የመሰሉ ሥራዎች በማከናወን የሀገራችንን ቱሪዝም ከፍ ከማድረግ ባለፈ አትሌቲክስን የሚያሳድግም ነው›› በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።

በውድድሩ ላይ ተገኝተው ለአትሌቶች ሽልማት ያበረከቱት የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስትርና የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ ፕሮጀክቱ ለቱሪዝምና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሆኖ መገንባቱን ጠቁመዋል፡፡ አካባቢው ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ባለው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አትሌቶች ልምምዳቸውን እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እየተገነቡ የሚገኙት ሀገራዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ስፖርትን ታሳቢ አድርገው የተገነቡ በመሆኑ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም ለውድድር ምቹ ናቸው፡፡ ይህ ውድድር የተካሄደበት የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ለጎዳና ሩጫ አመቺ ከሆነው ስፍራ ባለፈ ሁለቱን ሐይቆች የሚያገናኝ የ21 ኪሎ ሜትር (ግማሽ ማራቶን) መም ተሠርቷል፡፡ በስፍራው ከዚህ ቀደም የፈረስ ግልቢያና ጉግስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፤ የሩጫ ውድድሩም በየዓመቱ የሚካሄድ ቀጣይነት ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ የብስክሌት ውድድር ለማዘጋጀት እየተሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ብርሃን ፈይሳ  

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You