መጪውን ጊዜ ለቴክኖሎጂ

ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ትምህርቱስ? ጥናት እንዴት ነው? በጣም ጥሩ እንደሚሆንላችሁ እተማመናለሁ፡፡ እንደምታውቁት ወይም እንደሰማችሁት በአሁኑ ወቅት ዓለማችን የቴክሎጂ ውጤቶችን በስፋት እየጠቀመች ትገኛለች፡፡ መጪዎቹ ዓመታትም ከዚህ ሊበልጡ እንጂ ሊቀንሱ ይችላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ታዲያ ልጆችዬ እናንተስ ከቴክኖለጂው ጋር ለመተዋወቅ እና እንዴት መጠቀም እንዳለባችሁ ለመረዳት እየሞከራችሁ ነው? መልሳችሁ ‹‹አዎ›› እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህም ልጆችዬ ዛሬ የምናቀርብላችሁ ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል ቻይና በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ተሳትፎ ስላደረገው የኢትዮ ሮቦቲክስ ቡድን ይሆናል፡፡ ቡድኑ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ በውድድሩ 21 ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች የተወዳደሩ ሲሆን፤ በ“ቤስት ኦርጋናይዜሽን አዋርድ”፣ በ“ቤስት ቲም አዋርድ” እና በ“ሞስት ዲቨሎፕመንት አዋርድ” ለሽልማት በቅተዋል፡፡ የተወሰኑ ተሸላሚዎችን አነጋግረናል፤ ልምዳቸውን እና ተሞክሯቸውን እንደሚከተለው እንካፍላችኋለን፡፡

ተማሪ ኪሩብ ወንዱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በቻይና ሀገር ሄደው ከተወዳደሩት ታዳጊዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በውድድሩ የእርሱ ድርሻም ሮቦቶችን ኮድ ማድረግ ነበር፡፡ ከተወዳደሩት 27 ሀገራት መካከል 3ተኛ በመውጣታቸው ደስታውን ይገልፃል፡፡

ተማሪ ኪሩብ ሀገራችን፣ ከቻይና እና ከሌች ሀገራት ጋር ስትወዳደር ገና በማደግ ላይ ያለች ሀገር እንደሆነች ከውድድሩ ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ ሀገራችን ጠንክራ መሥራት እንዳለባት ይመክራል፡ ፡ ልጆችዬ፣ ኪሩብ ወደ ፊት የሶፍትዌር ዲዛይነር መሆን ይፈልጋል፡፡ ለዚህ እንዲረዳውም ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሮቦቲክስ ትምህርትን በመከታተል ላይ ነው፡፡

ለወደ ፊት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አትሪፊሻል ኢንተለጀንስ)ን የመጠቀሙ ነገር እንደሚስፋፋ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እናም ኪሩብ ሀገራችን ቴክሎጂን የመጠቀሙ ነገር በሥፋት ከተጠቀምችብት ካደጉት ሀገራት እኩል ለመሄድ እንደሚያግዛት ይናገራል፡፡ ስለዚህም፣ ልጆች ከቴክኖሊጂ ጋር ከተያየዙ ጉዳዮች ጋር ቅርርብናተገቢው እውቀት እንዲኖራቸው፤ የተለያዩ ስልጠናዎፐችንም እንዲወስዱ እመክራለሁ ብሏል፡፡

ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን፣ ለልጆች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። መንግስትም ሮቦት እና ተያያዥ ትምህርቶችን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ቢሰጡ ጥሩ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተማሪ ኪሩብ ይመክራል፡፡ የሂሳብ፣ ሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ እና መሰል ትምህርቶችን በመሠረታዊ ኮርስነት ቢሰጡ ሀገራችንን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚረዳ ታዳጊው ይናገራል፡፡

ወደ ሌላኛው ተሳታፊ እና የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ወደ ተሰጠው ተማሪ እንለፍ፡፡ ተማሪ አህመድ አቡበከር ይባላል፡፡ የ12ተኛ ክፍል የተፈጠሮ ሳይንስ ተማሪ ነው፡፡ ለወደፊት መካኒካል ኢኒጂነር የመሆን ፍላጎት አለው፡፡ አሁን የሚማረው የሮቦቲክስ ትምህርት ትልቅ እገዛ እንደሚደርግለት በመተማመን ከትምህርቱ ጎን ለጎን ስልጠናውን በመውሰድ ቻይና ሀገር ሄዶ ለመወዳደር በቅቷል፡ ፡ ለወደ ፊት በትምህርቱ ጠንክሮ በመማር ሀገሩን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡

ቻይና ሀገር ሄደው ከመወዳደራቸው ባሻገር ብዙ ልምድ እንደቀሰመ የሚናገረው ተማሪ አህመድ፣ ከሶፍትዌር እና ሮቦቶችን ኮድ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ብዙ ልምዶችን ማግኘቱንም ይገልጻል፡፡ ልጆችዬ፣ ተወዳዳሪው ተማሪ ለልጆች እና ለታዳጊዎች ምክር አለኝ ይላል፡፡ መጪውን ጊዜ በማሰብ ልጆች ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ ሳይንስ፣ ሂሳብ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢንጂነሪንግን መማር አለባቸው የሚል ምክር ነው ያለው፡፡

ተማሪ ሄራኒ ፍቅሩን እናስተዋውቃችሁ። የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ቻይና ሀገር ኢትዮጵያን ወክለው ከሄዱት መካከል አንዷ ናት። ለወደ ፊት ኢንጂነር የመሆን ፍላጎት ያላት ሲሆን፤ በርትታ ተምራ ሀገሯን የማስጠራት ፍላጎት እንዳለት ትናገራለች፡፡ ልጆች ከቴክኖሊጂ ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንዴት መማር እና ማወቅ፤ የወላጅ እገዛ መጠየቅ እንዳለባቸውም ትመክራለች ፡፡

አቶ ሰናይ መኮንን የኢትዮ ሮቦቲክስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እርሳቸውም የአርቴፊሻል አስተውሎት (ኤአይ) ዓለምን እየተቆጣጠረ ያለ ቴክኖሎጂ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለልጆች ሮቦት እንዴት እንደሚሠራ በማሰልጠን ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ልጆቻችን ዲዛይነሮች፣ ፕሮግራመሮች፣ እንዲሆኑ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው›› ያሉ ሲሆን፤ ማዕከሉ በአሁን ሰዓት ከሁለት መቶ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ ቴክሎጂ መር የሆነበት፤ ቴክኖሎጂ እየመራ ያለበት ዘመን ላይ ስለተደረሰ ህጻናት እና ታዳጊዎች ኢንጂነሮች፣ ዲዛይነሮች መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ሠናይ፣ በቅርቡ በየካቲት ወር፣ በአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ሻምፒዮን ይካሄዳል፡፡ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች የሚመጡ ታዳጊዎች በዚህ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ፡፡

አቶ ወንድሙ ሴታ የከተማ እና መሰረት ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ እንዳሉት፤ ዓለም በቴክሎጂው ዘርፍ በፍጥነት እየሄደ ነው፡፡ ዓለም ላይ ለመድረስ ደግሞ ልጆች እና ታዳጊዎች የቴክኖሎጂ፣ ሂሳብ፣ ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ ግንዛቤ ሊያገኙ ይገባል፡፡ መንግሥትም ለልጆች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሠራ እንደሆነ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

ልጆችዬ፣ እነ ሄራኒ ጎበዞች ናቸው አይደል? እናንተም ጎበዞች ናችሁ። ስልክ ከመነካካት ይልቅ እንዴት ጌሞች እንደሚሠሩ እና መሰል ነገሮችን ለማወቅ መጓጓት ይኖርባችኋል፡፡ በሉ እንግዲህ ልጆችዬ፣ መሰነባበቻችን ደረሰ፡፡ በሌላ ቀን፣ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስከምንገናኝ ቻው ቻው፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You