ሁለት እጥፋት አንድም ከጋዜጠኝነት አንድም ከቴሌቪዥን መስኮት፤ ከመዝናኛው ቤት ሞት ጭካኔው ከፋ፡፡ ሞት ሆይ ስለምንስ አንዣበብክ አይባልም፤ ምክንያቱም መወለድ ካለ ሁሌም ሞት አለና፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን አያያዝና አወሳሰዱ ሲታይ `ሞት ምነው? አሁንስ መካሪ አጣህሳ` ያስብላል፡፡ ልክ እንደዚህ በአንድ ጀንበር እንደሱናሚ ሲያናውጽ። በዚሁ በያዝነው የወርሀ ጥር ላይ ከሀገራችን ዝነኞች የሕይወት ጓዳ የደገሰው ድግስ መልካም አልነበረም። ሁለት ብርቱዎች፤ በሁለት እጥፋት አንድ ሞት ይዟቸው ነጎደ፡፡
ባጋመስነው የጥር ወር ሀዘን በፊታችን ጥላውን አጥልቶ ልባችንን በመጥፎ የትውስታ ድባቴ ከወቁን ነገሮች አንደኛው የአስፋው መሸሻ የሞት ዜና ነበር። ሞት አይቀሬው፤ ሽምጥ የጋለበ ዕለት ማን ችሎ ማንስ ደፍሮ ይመልሰዋል፡፡ ደግነቱ የወሰደውን ሰው ሥራና ትዝታ ከትውስታ ማህደራችን የመፋቅ አቅም የለውም። ከሬዲዮ ጣቢያ የሰማነው ያ የሚያስገመግም ድምጽ፤ ከቴሌቪዥን መስኮት አፍ ከፍተን የተመለከትነው ጨዋታና እስከ ዕለተ ሞቱ ያልተለየውን ውብ ፈገግታው፤ ከፊታችን ድቅን እያለ በሀዘን ልብን ማስቆዘሙ አይቀርም፡፡ አስፋው መሸሻን የወለደችው አዲስ አበባ ብትሆንም ያሳደገው ግን ብዙ ነው፡፡ ሐምሌ 19 ቀን 1959 ዓ.ም በአዲስ አበባ፤ ዶሮ ማነቂያ መንደር ውስጥ ነበር የተወለደው፡፡ የኋላ ላይ ትንሽ ልጅ ሳለ፤ ከአዲስ አበባ ለቆ በሐረር ከተማ ውስጥ ባለ ትምህርት ቤት የተማረበት አጋጣሚም አለ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ግን ባህር ተሻግሮ፤ ድንበር ዘሎ ከሀገር ወጣ፡፡ ብቻውን አልነበረም፤ ከቤተሰቡ ጋር እንጂ፡፡ አባቱ መሻሻ የታወቁ እንደራሴ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ያገለግሉ በነበረበት የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ምክንያትም 1972 ዓ.ም ወደ ታንዛኒያ በመዘዋወራቸው አስፋውን ጨምሮ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደዚያው አቀኑ፡፡ አስፋውም `ኑሮ በታንዛኒያ` ብሎ የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የኮሌጅ ትምህርቱን በማጠናቀቅ የመጀመሪያ ዲግሪውም በኮምፒውተር ሳይንስ ላይ አረፈ፡፡ በኋላም ከቤተሰቡ ጋር ከታንዛኒያ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በማምራት ለጥቂት ዓመታት ያህል ከዚያ ቆይቶ በ1984 ዓ.ም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ያቆማትን የሐረር ኑሮ ጀመረ፡፡
አስፋውንና አዲስ አበባን ዳግም ያገናኘው ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራበት “ፕሬስ ዳይጀስት” የተሰኘው መጽሔት ነበር፡፡ ከተወሰነ የመጽሔት ቆይታው በኋላ በ1992 ዓ.ም ወደ ሌላኛው አዲስ መንደር ተሸጋገረ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ኤፍ ኤም 97.1 የሬዲዮ ጣቢያ ስርጭቱን የጀመረው በዚሁ ዓመት ነበርና አስፋውም የሙያ ችሎታውን ይዞ ተቀላቀለ። በዚህም፤ ከቅርብ ጓደኛው ዳንኤል ግዛው ጋር በመሆን “አይሬ” የተሰኘ የመዝናኛ ዝግጅት ማቅረብ ጀመሩ። ዝግጅቱም ሆነ ሁለቱ አቅራቢዎች በአድማጩ ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትና ታዋቂነትን ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር፡፡ አስፋው፤ በሬዲዮ ጣቢያው የአይሬ መዝናኛ ለስድስት ዓመታት ያህል ከዘለቀ በኋላ፤ ጣቢያውን ለቆ ወደ ዛሚ ሬዲዮ አመራ። ቀጣዮቹንም የሕይወቱን ጥቂት ዓመታት በዚያው አደረገ፡፡ አስፋው መሸሻ ኑሮውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የዛሬ 14 ዓመታት ገደማ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ቀድሞም የነበረውን የዝነኝነት ካባ ደርቦ ለመልበስ የቻለው፡፡ እውቁን ስሙንና አስገምጋሚውን የሬዲዮ ድምጹን ባይረሱትም፤ ብዙዎች በደንብ የተዋወቁት ግን በኢቢኤስ የቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲል ነበር፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያው ሲቋቋም፤ መርቀው ከከፈቱ ነባር የሚዲያ ሰዎች አንደኛው አስፋው ነው። በወቅቱ በነበረው የሥራ ድርሻ፤ ኢትዮጵያዊያን በስደት፤ በሀገረ አሜሪካ የሚደርስባቸውን የሕይወት ውጣውረድና ስኬት የሚዳስሰው “ኑሮ በአሜሪካ” የተሰኘውን ዝግጅት በማቅረብ ለዓመታት ቆይታ አደረገ፡፡ የአዲስ አበባ የናፍቆት አባዜ አይለቀውምና ተመልሶም ወደ ሀገሩ መጣ፡፡ አሁን ደግሞ ይበልጥ ፍካቱ ጨመረ፡፡ “እሁድን በኢቢኤስ” በተሰኘው የእሁድ የመዝናኛ ዝግጅት ላይ ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን፤ በአስተዋዋቂነት “ሞቅ! ደመቅ! ሸብረቅ!” እያለ በመሪነት ከተፍ አለ፡፡ ከቃላቱ ጋር ስሜት እየፈነጠቁ፤ በአዝናኖት ማሞቅ ማሸብረቁ እንደሆን የእርሱ የራሱ የግሉ ንብረት ነውና በዝነኝነቱ ላይ ፍቅርና ክብርን ደረበበት፡፡ 14 ዓመታት በኢቢኤስ፤ 27 ዓመታት በመዝናኛ ዝግጅት ስሙን ሰቀለበት፡፡
አስፋው “መሸሻ ይሙት!” ካለ በቃ እውነቱን ነው፤ በዚህ መሀላ እውነት ከፍቅር ጋር ቆመው ምስክርነትን ይሰጣሉ፡፡ አባቱን ሲወድ መቼም አይጣል ነው፤ መሸሻ የሚለውን ስም ሳይጠራ ውሎ አያድርም፡፡ “በመሸሻ ሞት!” ካለም በቃ አስፋው በነገሩ በጣሙን ተገርሟል፤ አሊያም ግራ ተጋብቷል ማለት ነው፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል፤ የሚወደውን አባቱን ከሚወዳት ባለቤቱ ጋር በአንድ ቀን በአንድ ጀንበር በመኪና አደጋ አጣቸው፡፡ ከዚህ በላይ እጥፋት፤ ከዚህ በላይ ስብራት ምን አለ? በሕይወቱ እጥፋት ላይ መቼም ከአይንና ከልብ የማይጠፋ ጥቁር ነጥብ ያረፈበት የእርሱ መጥፎው ጊዜ ይሄው ነበር፡፡ ሳይደግስ አይጣላምና በሞት ካጣት ባለቤቱ ሱዛን ባገኘው አንዲያ ልጁ በሳምሶን አስፋው (ጃፒ) ለመጽናናት እየሞከረ ኖረ። አስፋው መሸሻ ደግነቱ ወሰን አልባ ልቡ የቅንነት አርማ ነበር፡፡ ከህልፈቱ በኋላ ዕውቁ ተዋናይ ሰለሞን ቦጋለ በአንድ የቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ “አስፋው የተለየ ፍጡር ነው፡፡ የአባቱ ስጦታ የሆነውና የሚወደውን መኪና ለልብ ህሙማን ህጻናት ለሚሰራው ሆስፒታል በእርዳታ ሰጥቷል። ለመስጠት እንደሚፈልግ ከነገረኝ በኋላ መኪናዋ እድሳት ተደርጎላት በጨረታ እንድትሸጥ ወስነን ነበር፡፡ በጽኑ ከመታመሙ ቀደም ብሎ፤ አንድ ቀን ምሽት ላይ ደወለልኝ፡፡ እናም `እባክህን እሺ በለኝና የመኪናውን ሊብሬ ላስረክብህ፤ የሚሆነው አይታወቅምና በቶሎ ከእጄ ቢወጣ ይሻላል` ሲል ለዚህ ሆስፒታል ምን ያህል ጉጉት እንዳደረበት በደግነቱ ውስጥ አሳይቶኛል። ሆስፒታሉ ስራው ተጀምሮ ሲጠናቀቅ ውለታውን አንረሳምና ስሙን በትልቁ የምናኖርበት ይሆናል” በማለት በቅርብ የሚያውቀውን ወዳጁን ቸርነት መስክሯል፡፡ በዚህ ብቻም ሳይሆን ካለው ሁሌም ቢሆን ከመስጠት በረከት አይጎድልም፡፡ የነበረበት የጭንቅላት ካንሰር የሕይወቱን ጫፍ ለማጠፍ በአልጋ ላይ ባዋለው ጊዜ እርሱን ለማዳን ያልተሯሯጠ አልነበረም። ብዙ ደጋግ ኢትዮጵያዊያን፤ ሕይወቱን ለማትረፍ ከውስጥና ከውጭ በገንዘብ እርዳታ ቢረባረቡለትም በሞት የተጠቀለለውን የሕይወት እጥፋት ለመመለስ ግን ሳይቻል ቀረ፡፡ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም አጥቢያ እስትንፋሱ ተቋረጠ፡፡ ሥራውን ከእጹብ ማንነቱ ጋር ጥሎ፤ የሞትን እጥፋት ተከትሎ ሄደ፡፡
ሁለተኛው እጥፋት፤ ሁለተኛው ጥቁር ነጥብ በወርሀ ጥር፤ በሌላኛው የስፖርት ጋዜጠኛ ላይ ያረፈ ነበር፡፡ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ስምና ምግባር ልክክ ብለው ሲገጣጠሙ የመጀመሪያው ባይሆንም የመጨረሻውን ደረጃ ግን አሳይቷል፡፡ ልክ እንደ ስሙ ሁሉ ለራሱም ለሀገሩም ጀግና የነበረ ብርቱ የስፖርት ጋዜጠኛና ስፖርተኛ ለመሆን በ1955 ዓ.ም የመጋቢት ወር ላይ በይርጋለም ከተማ ተወለደ፡፡ የእርሱ የጋዜጠኝነት ሕይወት እንደ ዘንባባ ለምለምና ውብ ነበር አለማለት፤ ንፉግነት ነው፡፡ ምክንያቱም የእርሱ የጋዜጠኝነት ሕይወት የጀመረው አውቆና ተረድቶ በወጣትነት ሳይሆን፤ ምኑንም ከምኑ ለመለየት ከሚያዳግትበት ገና ከልጅነቱ ነበር፡፡ በለጋ ዕድሜው ስፖርትና የስፖርት ጋዜጠኝነት አብረው በፍቅር ጣሉት፡፡ ይህም ፍቅር ከተወለደባት ይርጋለም እስከ ሻሸመኔ፤ ከሻሸመኔ እስከ አዲስ አበባና ምሥራቅ አፍሪካ በጎዳናዎቻቸው ሁሉ ስሙን እየተከለ በክብር አልፏል፡፡
ገና ታዳጊ የነበረው ገነነ፤ የስፖርት ጋዜጠኝነት ፍቅሩ ሲያናውዘው እንዲህ ነበር፡፡ ነጋዴው አባቱ መኩሪያ፤ በቁጥርና ፊደላት ያጨቁትን የሂሳብ መዝገባቸውን እያነሳ እርሱ ደግሞ በጽሑፍና ፎቶ ግራፍ ላይና ታቹን ያደማምቀዋል፡፡ ጋዜጦችን እያየ የራሱን ጋዜጣ እየሰራ መሆኑ ነው፡፡ ጋዜጣ በተለይ ደግሞ የስፖርት ጋዜጣ አያመልጠውም፤ እያደነ ከእጁ ያስገባቸዋል፡፡ ከዚያም በጋዜጣው ላይ ያሉትን ምስሎች ቀዶ እያወጣ ባዘጋጀው ወረቀት ላይ ይለጥፋቸዋል፡፡ የጋዜጦቹን ዜና እያነበበም በተረዳው መጠን የራሱን ዜና ይጽፍበታል፡፡ ቅሉ እርሱ ስም ባይሰጠውም `ገነነ ጋዜጣ` እንደማለት ነው፡፡ ይህን ጋዜጣ ከቤቱ ቁጭ አያደርገውም፤ እየወሰደ ለሠፈሩ ልጆች ግማሽ ገጽ ላነበበ የቁልፍ አዝራር፤ ሙሉውን ላነበበ ደግሞ አምስት ሳንቲም እያስከፈለ ያስነብባል፡፡
ሊብሮ የስፖርት ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚያ ቀድሞ ራሱ ጎበዝ ስፖርተኛ ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ይቺ ድቡልቡሏ ኳስ ለእርሱ ድቡልቡል ዓለሙ ናት። ኳሱን በእግሮቹ ባንቀሳቀሰ ቁጥር እሷኑ መሳይ የሆነችውን ይህቺን ድቡልቡል ዓለም፤ ከእግሮቹ በታች ያደረገ ያህል መስሎ ይሰማዋል፡፡ ምን አይነት ጸጋ ነው፤ምን አይነት መታደል እንዲሉ ከመኩሪያ ልጆች አምስቱ የእግር ኳስ ተጫዋች ነበሩ፡፡ ያውም በአንድ ቡድን ውስጥ፡፡ ታዳጊው ገነነና አራቱ ወንድሞቹ የሁሉንም ቀልብ የሳቡ ነበሩ፡፡ በአንድ ቤተሰብ የታጨቀውን የእግር ኳስ ቡድን የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች “የቡድኑ ስያሜ ተቀይሮ ለምን መኩሪያ ቡድን አይባልም” ይሉ እንደነበረ ገነነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያወሳዋል፡፡ በእግር ኳስ ሕይወቱ ከትንሿ የመንደር ጨዋታ ተነስቶ የኢትዮ ኤሌክትሪክና ሜታ ቢራን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ቡድኖችን ለመቀላቀል የቻለ ጀግና ነው፡፡ እንዲህ `ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም` የሚባለው ይሄው አይደል፡፡ “ሊብሮ” የሚለው የስሙ ስያሜም የፈለቀው ከዚሁ ነበር።
ከዕለታት በአንደኛው ቀን ይህ ሆነ፡፡ በጊዜው ገነነ(ሊብሮ) የሜታ ቢራ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች፤ ጓደኛው ኃይሌ ካሴ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች። ሁለቱም ቡድናቸውን ወክለው ወደሜዳ ሊገቡ የቀራቸው ጊዜ ከአንድ ሰዓት ያነሰ ነበር፡፡ እናም ሁለቱ ጓደኛሞች በመጨዋወት ላይ ሳሉ ገነነ መኩሪያ ሊብሮ ስለሚባል የእግር ኳስ ጥበብ ትንተና እየሰጠ ለወዳጁ ያጫውተዋል፡፡ ከዚያም ከወዳጅነቱ የአፍታ ጨዋታ፤ ሽሚያ ወደበዛበት ለእግር ኳስ ጨዋታ ወደ ሜዳው ገቡ፡፡ ጨዋታው ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ ቅድም ለጓደኛው ያጫወተው የሊብሮ ጥበብ ትዝ ቢለው፤ ከተከላካይ ስፍራ ላይ የነበረው ገነነ ለብቻው ኳሱን እየነዳ ከተቃራኒው የግብ ክልል ደረሰ፡፡ ከመድረሱም ከመረቡ ወዝውዞ ግሩም ግብ አስቆጠረ፡፡ ጓደኛውም አሁን በደንብ ሳይገባው አልቀረም፡፡ ገነነ ከጨዋታው መልስ “ሊብሮ” የሚል ቅጽል ስያሜ ተሰጠው። በዚህ ስም ከመታወቁም በላይ የኋላ በጋዜጠኝነቱ ወቅት ያዘጋጀው የነበረው የስፖርት ጋዜጣ ስምም ሆነ። ጋዜጣውም ለ13 ዓመታት ያህል ለመዝለቅ ችሏል። የግሉ ከነበረው ሊብሮ ባሻገርም ማራካኛ፣ ፉት ቦል፣ ሻምፒዮንና በሌሎች የስፖርት ጋዜጦች ላይም ሠርቷል፡፡
ከእግር ኳሱ ጉዳቶችና ድካም በኋላ ያመራው ወደየትም አልነበረም፤ ይልቅስ የልጅነት ህልሙ ወደነበረውና ወደጓጓለት የስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ ነበር፡፡ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ሳይቀር፤ ስፖርትን በጋዜጠኝነት ሙዳይ ውስጥ እንደያዘ 30 ዓመታትን ቆይቷል፡፡ በቅርቡም በአሻም የቴሊቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ ስፖርቱን በመተንተን ላይ ነበር፡፡ ገነነ መኩሪያ ኳስን በእግር ማንጠባጠቡንና መተንተኑን ብቻም ሳይሆን፤ ብዕርን ከእጁ ማጥበቁንም ያውቅበታል። በእግር እየኮመኩ፤ በአፍ እየተነተኑ፤ በእጅ መከተቡ የእርሱ ናት፡፡ ስምንት መጽሐፍትን ጽፎ ለስፖርት አፍቃሪ አንባቢያንና ለሀገሩ አበርክቷል፡፡ ከጻፋቸው መጽሐፍት መካከል ኢህአፓ እና ስፖርት፣ ፍትሐዊ የጠጅ ክፍፍል እና መኩሪያ የተሰኙት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በርካቶች እንዲህ ሲሉ ነበር የሚጠሩት “ተንቀሳቃሹ ቤተ መጽሐፍት” በእርግጥም ነበረ። ሁለተኛው እጥፋትም እዚህ ጋር ነበር ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም፡፡ በህመም ተይዞ ጉልበቱ ዛለና ሕክምና ሲደረግለት ቢቆይም፤ ከዚህች ቀን ንጋት ለማለፍ ግን ለማለፍ ሳይችል ቀረ፡፡ የዕድሜው ዘመን የተጻፈባት ያቺ ጦማር እጥፍ አለች፡፡ የሞት መልአክ ጦማሩን አጣጥፎ በቃህ አለው፡፡ ለሠራ ሰው ሞት ግዱም አይደል፤ ምክንያቱም ከሞት በላይ የሆነውን ሥራ ሰርቷልና። በእጥፋቱ ላይ፤ ሀገሩን እስቲ አንዲት ቃል ጻፊበት ብትባል፤ “ኮራሁብህ!” አሊያም “አመሰግንሀለሁ!” ነበር ሊሆን የሚችለው፡፡ ታዲያ ይህን ሰው እንዴትስ ሞተ ለማለት ይቻላል? ገነነ መኩሪያ ዕድሜ ዘመኑን ሙሉ ከስፖርት ጋር ኖሮ፤ ቢደክመው ጊዜ፤ በስፖርት ጥላ ስር አርፏል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን (ካፍ) ይህንን ውለታውን አልዘነጋውም፡፡ የክብር ሜዳይ ከአንገቱ አጥልቆለታል፡፡ ለዚህ ሽልማት ከበቁትም፤ ለአፍሪካ ስድስተኛው፤ ለምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ብቸኛው ሰው አድርጎታል፡፡ ኮምኮ ለግብ፤ ከትቦ ለንባብ…አይ ገነነ …!!
እንግዲህ በወርሀ ጥር፤ ያውም በሳምንት ልዩነት እነዚህ ሁለት እንቁ ጋዜጠኞች የሕይወት ጦማራቸውን አስቀምጠውልን ሄደዋል፡፡ የወር ክፉ የለውምና `አንተ ክፉ` አይባልም፡፡ የቀንም ጎዶሎ የለምና `ጎዶሎ ቀን` አይባልም፡፡ የዕድሜ ውሃ-ልክ ሕይወትን አጣጥፎ፤ ሞትም መንገዱን እየጠቀለለ በማይፈታ እጥፋት ቢመጣ ነው፡፡ ነፍሳችሁን በአጸደ-ገነት ያኑረው ከማለት በስተቀር ምንስ ለማለት ይቻላል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም