የኤኮ ቱሪዝም ጽንሰ ሀሰብ ለኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ መሆኑ ይገለጻል፤ እንዲያም ሆኖ ግን ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አድናቆት የተቸራቸው የኢኮቱሪዝም መንደሮች እንዳሏት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) አነሳሽነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው የወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም መንደር ተመርቋል፡፡
በኤኮ ቱሪዝም ልማት ተዋናይ መሆን ካለባቸው መካከል ልማቱ የሚካሄድበት የአካባቢ ማህበረሰብ አንዱ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ከዚህ የቱሪዝም ዘርፍ ከሚገኘው ሀብት ተቋዳሽ እንዲሆን መደረግ ይኖርበታል፤ ራሱም ለቱሪስቶች አገልግሎቶችን በመስጠት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
በወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም መንደር ግንባታ ወቅትም ይሄው ተጠቃሚነት መታየት ጀምሯል፡፡ የኤኮ ቱሪዝም መንደሩ የተለያዩ ግዙፍ መሰረተ ልማቶች የተገነባለት ሲሆን፣ ለበርካታ የአካባቢው አርሶ አደሮች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች ተካሂደዋል፡፡
የኤኮ ቱሪዝም መንደሩን የተመለከቱ መረጃዎች እንደጠቆሙት፤ በወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም መንደር ግንባታ ወቅት የአካባቢው ወጣቶች ታላላቅ የልማት ስራዎች ይዘው የሚመጡትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማጣጣም ጀምረዋል፤ በግንባታው ወቅት ከስምንት ሺ እስከ 12 ሺ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል አስገኝቷል። ሰፊው የአካባቢው ማህበረሰብም አሁን የላቀ ተጠቃሚነት እድል ማግኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ማስታወቃቸውን መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው አመልክተዋል፡፡
መንደሩ ከተገነቡለት መሰረተ ልማቶች መካከልም 43 ኪሎ ሜትር መንገዶች፣ 35 ኪሎ ሜትር የመንገድ መብራትና የኃይል አቅርቦት፣ 72 ሜትር ድልድይ እና የትምህርት ቤት ግንባታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የቴሌኮምና የንጹህ መጠጥ ውሃ መሰረተ ልማትም ተገንብተውለታል፡፡
የኤኮ ቱሪዝም መንደሩን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) የወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ባለሀብቶች በቀጣይ ለሚሰሩት ሥራ የተመቻቸ ሁኔታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ጅምር ሥራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ ትልቅ ሥራ ይጠብቀናል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ባለሀብቶች በወንጪ ደንዲ አካባቢ በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፤ የአካባቢው ማህበረሰብም የአካባቢውን ተፈጥሮ ጠብቆ ያቆየበትን ሁኔታ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት የወንጪ ደንዲ የኤኮ ቱሪዝም መንደር የኢትዮጵያን ኤኮ ቱሪዝም ከማሳደግ ባለፈ የአፍሪካ ኤኮ ቱሪዝም እንዲያድግ በር ይከፍታል ሲሉ ተናግረዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲለማና እንዲያድግ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ነው ያስታወቁት፡፡
በወንጪ ደንዲ ኤኮ ቱሪዝም፣ እንደ ሀገር ባለው የኤኮ ቱሪዝም ሀብትና በተያዘው የኢኮ ቱሪዝም ልማት ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህር አቶ በቀለ ኡማ፣ በትምህርት ክፍሉ በቱሪዝም ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን፣ የምርምርና ጥናት እንዲሁም የማማከር ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ በግሉ ዘርፍም በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ላይ ድርጅት ከፍተው እየሰሩም ናቸው። በቱር ኦፕሬሽን ቢዝነስ እንዲሁም በቱሪዝም ላይ በሚዘጋጁ ሁነቶች ዝግጅት ላይም ይሰራሉ፡፡
አቶ በቀለ የወንጪ ደንዲ ኤኮ ቱሪዝም መንደርን ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ፣ ምርጥ ምሳሌ፣መንግሥት የወሰደው ምርጥ እርምጃ ሊባል የሚችል ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ የወሰደው እርምጃ ትክክለኛና ወቅታዊ የቱሪዝም አቅጣጫን የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ምክንያቱም በግሉ ዘርፍ የማይሰራውን መንግሥት ከሠራ፣ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ማድረግ ያለበትን ካደረገ ሀገሪቱና የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሁሉም እንደ ድርሻው ከቱሪዝሙ የሚቋደስበት ሁኔታ ይፈጠራል›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሌሎች የኤኮ ቱሪዝም መንደሮች በአርሲ፣ በአማራ ክልል በደቡብ ክልል አሉ። የወንጪ ደንዲ ኤኮ ቱሪዝም መንደር አሁን ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታ መሆን ችሏል፡፡ በዚህ ልማት የተከናወነውን ምርጥ ሥራ ወደ ሁሉም ክልሎች ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
በሀገሪቱ ለኤኮ ቱሪዝም አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ በጥናት የተለዩም ያልተለዩም ቦታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ላይ ምርጥ የኤኮ ቱሪዝም ስፍራዎችን መገንባት ከተቻለ ኢትዮጵያ ወደፊት ከቱሪዝም ዘርፉ የምትጠቀመው፣ ቱሪዘም የሚያመጣው አዎንታዊ ገጸ በረከት ብዙ ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
ኤኮ ቱሪዝም ለአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑንም መምህሩ ጠቁመው፣ ‹‹ኤኮ ቱሪዝምን ማነው እንዲያለማ የሚጠበቀው፤ መንግሥት ደንዲ ወንጪ ላይ ገንብቷል፤ በቀጣይስ ይህን የመሰለ መሰረተ ልማት ያለው የኤኮ ቱሪዝም መንደር ማነው የሚያለማው?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ቱሪዝም የእያንዳንዱን ተዋናይ እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራትን እንደሚጠይቅ አስታውቀው፣ ይህ ሥራ በአንድ አካል ብቻ የሚሰራ ከሆነ ስራው ጊዜያዊ ይሆናል፤ ዘላቂ የቱሪዝም ልማት ጥቅምን ሊያመጣ አይችልም ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በግሉ ዘርፍ የማይደፈሩ፣ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ የሚበዛባቸውና የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው ልማቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ መሰረተ ልማት መዘርጋት በግሉ ዘርፍ ብቻ አይሰራም። መንግሥት ከደንዲ ወይም ከጊንጪ እስከ ወንጪ ድረስ የአስፋልት መንገድ ሠርቷል፡፡ ይህንን በግሉ ዘርፍ መስራት አይቻልም፤ ወጪው በጣም ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት ይገባበታል፡፡ ይህ አሁን በወንጪ ደንዲ የተጀመረው የኤኮ ቱሪዝም ልማት በጣም ጥሩ ስትራቴጂ ነው የሚሉት መምህሩ፣ የኢትዮጵያን ቱሪዝም አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያስፈነጥረውም አስታውቀዋል፡፡
ሀገሪቱ ከእነዚህ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ የምትሆነው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) አንድ ላይ ተቀናጅተው ሲሰሩ ብቻ ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡
መንግሥት በወንጪ ደንዲ መሰረተ ልማት ዘርግቷል፤ የግሉ ዘርፍ ደግሞ ሆቴሎችን፣ ሎጂዎችንና ሪዞርቶችን መገንባት ይኖርበታል ያሉት አቶ በቀለ፣ ማህበረሰቡን ከልማቱ ተጠቃሚ የምታደርገው ከሆነ መሰረተ ልማቱን፣ መንደሩን በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ይህ ሲሆን ማህበረሰቡ ለሆቴሎቹም፣ ለሎጆቹም፣ ለመንገዱም፣ ወዘተ ጥበቃ ያደርጋል ብለዋል፡፡
‹‹ይሄ ሆቴል፣ ሎጅና ሪዞርት ቢበላሽ በቀጥታም በተዘዋዋሪም መንገድ የምጎዳው እኔ ነኝ›› የሚል አመለካከት እንዲይዝ፣ ‹‹ጉዳት ቢደርስበት ገጸታው የሚባለሸው የእኔም ነው›› ብሎ እንዲያስብ ማድረግ ላይ መሰራት እንዳለበትም ያመለክታሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከተሰራ በቱሪዝም ልማቱ በጣም ብዙ የሚያራምድ፣ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን የሚያመጣ ከልማቱም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹ኤኮ ቱሪዝም ማለት ማህበረሰቡን ያማከለ ቱሪዝም ማለት ነው›› ያሉት አቶ በቀለ፣ ‹‹እንደ እኔ አባባል ኤኮ ቱሪዝም ማለት የማህበረሰቡን ለማህበረሰቡ ማለት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ኤኮ ቱሪዝም ባለቤትነቱ የማህበረሰቡ ነው፤ የአንድ ሰው የሁለት ሰዎች አይደለም ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ለኤኮ ቱሪዝም መንደርነት ሊውሉ ለሚችሉ አካባቢዎች መሰረተ ልማት ከተሟላ ማህበረሰቡ የቱሪዝም ምርቶችን፣ ቡና፣ ምግብ፣ ወተት፣ ባህላዊ መጠጦችና የመሳሰሉትን በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ ጎብኚዎችም ይህን እንደሚወዱት ይገልጻሉ፡፡
የኤኮ ቱሪዝም አካባቢ ማህበረሰብ ወደ ከተማ ወስዶ የሚሸጣቸው ለምግብነት የሚውሉ እንደ እህል፣ አይብ፣ ወዘተ ያሉ ምርቶች እንዳሉት ጠቅሰው፣ የቱሪዝም መንደሩ በአካባቢው ከተመሰረተ እነዚህን ምርቶች እዚያው አካባቢ ላይ ለጎብኚዎች ሊሸጥ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡
ከዘላቂ ቱሪዝም ልማት ሀገሪቱም ማህበረሰቡም በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተፈለገ መንግሥትና የግሉ ዘርፍም ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ ይህ ካልሆነ የምናልመውና የምናቅደው ቦታ መድረስ አንችልም የሚል እምነት ነው ያለኝ ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ በእያንዳንዱ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራ የመንግሥትና የግል አጋርነት መኖር ግዴታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የግሉ ዘርፍም ኢንዱስትሪው ውስጥ በመግባት መንግሥት ያመቻቸለትን ሁኔታ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበው፣ መንግሥት እንድ እርምጃ ወደፊት ከሄደ የግሉ ዘርፍ ይህን ተቀብሎ ኢንዱስትሪውን የማስቀጠል ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ኤኮ ቱሪዝም በዓለም ደረጃ ከተጀመረ ቆይቷል፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው በቅርቡ ነው ያሉት አቶ በቀለ፣ በተለይ ማህበረሰብ ተኮር ኤኮ ቱሪዘም ያላቸው ሀገሮች ብዙ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በኤኮ ቱሪዝም ላይ እየሰሩ ካሉ የእስያ ሀገሮች ህንድና ኢንዶኔዢያን ጠቅሰው፣ የእነዚህ ሀገሮች ማህበረሰቦች በዚህ የቱሪዝም አይነት ገፅታቸውን ይገነቡበታል፤ ባህላቸውን ይሸጡበታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በአፍሪካም እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ባሉት ሀገሮች እንደሚሰራበት አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሥራት ጀምሯል፤ በዚህ ላይ የግሉ ዘርፍም ሊሳተፍበት ይገባል፤ ሀገሪቱ ጥሩ ጥሩ የኢኮ ቱሪዝም ቦታዎችን ማልማት ትችላለች፤ ይህም ሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ከሚያመጣቸው አዎንታዊ ጥቆሞች እንድታገኝም ያስችላል፡፡
ማህበረሰብ ባለበት ቦታ ሁሌም ኤኮ ቱሪዝም አለ፤ በተለይ ከከተማ ራቅ ብለው የሚኖሩ ማህበረሰቦች ባሉባቸው አካባቢዎች እምቅ አቅሙ ይኖራል፤ በዚህም ላይ ትንሽ ሀብት በማውጣት አካባቢውን መዳረሻ በማድረግ፣ በዚህም በርካታ ቱሪስቶችን በማሰብ የአካባቢውን ማህበረሰብም ሀገርንም ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡
ለኤኮ ቱሪዝም በሚሆን አካባቢ ላይ ብዙ ወጪ ማድረግ አያስፈልግም፤ ማህበረሰቡም መስህቡም እዚያው ያሉ ናቸው ያሉት መምህሩ፣ ማህበረሰቡም መስህቡም ከየትም አልመጡም፤ እዚያ የሚደረስበት፣ በዚያ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ብቻ ነው የተፈጠረው ብለዋል። ለምሳሌ ወንጪ ስምንት ቁጥሩ /ሀይቁ/ እዚያው የነበረና ያለ ነው፤ ማህበረሰቡም እዚያ ያለ ነው፤ በፈረስ መጓዝና የመሳሰሉትም እዚያው ያሉ ናቸው፡፡ የተሰራው ይህን ትንሽ ከፍ ማድረግ ላይ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የቱሪስቶችን ምቾት ከመጠበቅና ከመሳሰሉት አኳያ ሆቴሎችን፣ ሪዞርቶችን ፣ ሎጆችን፣ የመንገድ፣ የውሃ የቴሎኮምና በመሳሰሉት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ነው የሚያስፈልገው ብለዋል፡፡
መምህሩ ሌላው ለዘርፉ አስፈላጊ ብለው የጠቀሱት ሰላምና ደህንነት ነው፡፡ እንደ አሳቸው ማብራሪያ፤ ቱሪዝም ሲታሰብ በቅድሚያ ወደ አእምሮ የሚመጣው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ነው፤ ቱሪዝም ማለት የሰዎች ጉዞ፣ እንቅስቃሴ ነው፤ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሱበታል፡፡ ስለቱሪዝም ሲወራ ስለሰዎች እንቅስቃሴ ነው የሚወራው፡፡
ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በቅድሚያ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ብርና ጊዜ ያላቸው መሆኑ ብቻ አይደለም ሲሉም ጠቅሰው፤ በቅድሚያ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው የአካባቢው ደህንነትና ጸጥታ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ለእዚህም የአካባቢ ደህንነትና ጸጥታ በደንብ መጠበቅ ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ እሱ በመንግሥትም በግሉ ዘርፍም መሰራት እንዳለበት ጠቁመው፤ በተለይ በኛ ሀገር በትናንሽ ነገሮች የሚነሱ ችግሮችን መፍታት ከቻልን በቱሪዝም ዘርፉ ጥሩ መስራት እንችላለን ብዬ አስባለሁ ብለዋል፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም