ያስጠጉትን ማጥቃት ከጥፋት ሁሉ የላቀ ጥፋት

አስገድዶ መድፈር የፆታዊ ጥቃት ዓይነት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ከሌላ ሰው ፈቃድ ውጪ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን የሚያካትት ነው። አስገድዶ መድፈር የሚፈጽሙ ሰዎች የተጎጂውን አቅም ማጣት (የንቃተ ኅሊና ማጣት፣ ከፍተኛ የአልኮል ስካር፣ የአእምሮ ሕመም)፣ አካላዊ ጥቃትን ወይም የአጠቃቀሙን ስጋት፣ የሥነ-ልቦና ጫና፣ የተጎጂውን ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ ወይም ሌላ ጥገኝነት ይጠቀማሉ።

አስገድዶ መድፈር ከፆታዊ ወንጀሎች አንዱ ነው። ትክክለኛው ፍቺው በተለያዩ ግዛቶች ሕግ ይለያያል… «ብዙ ደፋሪዎች አይደፈሩም» ምክንያቱም ጉዳት ለማድረስ ስለሚፈልጉ በቀላሉ እሷን/እሱን እንደ ህያው ሰው አይገነዘቡም ወይም አይቆጥሩም። ስለ አስገድዶ ደፋሪዎች ለምን ተነሳ ቢባል በየጊዜው የምንሰማቸው ነገሮች በጣም አሳዛኝ ነገሮች በመሆናቸው ነው። ድርጊቱ ብዙዎችን የሚያሳዝን የሚያስቆጣ ከባህላዊ እሴታችን ጋር የማይሄድ ማኅበረሰባዊ ሕግና ሥርዓትን የጣሰ ነውር ነው።

ከዚሁ ኀዘንና ቁጣ በመነሳት አንዳንድ ሰዎች መደረግ ያለበትን እርምጃዎች ይጠቅሳሉ። በሕግ የተቀመጠው ቅጣት አነስተኛ ነው። ወደ ሞት መቀየር አለበት የሚሉ ሃሳቦች ይሰማሉ። እንዲህ ዓይነት ወንጀል የሠሩ ሰዎች ስማቸው፣ አድራሻቸውና እንቅስቃሴያቸው ሊመዘገብና ለሕዝብ ይፋ መሆን አለበት የሚሉ ሃሳቦች ይሰማሉ። የወንጀል ቅጣትን ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው ቅጣትን በመጨመር ብቻ አይደለም። የመያዝና የመቀጣት ዕድሉን በመጨመር፣ ፈጣን የፍትህ ሂደት እንዲኖር በማድረግና በመሳሰሉትም ነው። ከሁሉም በላይ ግን ለወሲባዊ ነፃነት ያለንን ማኅበራዊ እይታ በመፈተሽ ነው።

በአንዳንድ ሀገራት የወሲብ ጥቃት ፈፃሚዎች ስም፣ አድራሻ፣ እንቅስቃሴ እንዲመዘገብና ይፋ እንዲሆን ያደርጋሉ። ጥያቄው ምን ዓይነት ውጤት አለው? ከድርጊታቸው መውጫ ቀዳዳውን በማጥበብ በዚያው እንዲወሰኑ የሚያደርግ ስለሆነ። ፍትህ የራሱን ወሳኔ ቢሰጥም ቅሉ እንደ አንድ ማኅበረሰብ የችግሩን ስፋት በመመልከት መሻሻል ቢኖር የሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሃሳብም እንዳይዘነጋ በማለት ነው ይህን ሃሳብ ያነሳነው። ከላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ ልንል የወደድነው ለዛሬ ከአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ያገኘነውን የወንጀል ታሪክ ልናካፍላችሁ ስለሆነ ነው። መልካም ቆይታ።

ወጣትዋ ማስተዋል

ማስተዋል አይቸው ትባላለች። ከተወለደችበት ቀዬ የዋጣችው የዕድሜዋን መጨመር የተመለከቱ ልጅነቷ እልፎ ወደ ወጣትነት መሸጋገሯን የተመለከቱ የአካባቢው ጎረምሶች ከዓላማዋ እንዳያሰናክሏት በሚል ነበር። ልጅቷ ጎንታይዋ ሲበዛ የሩቅ ዘመድ የተባሉ ሰዎች ተፈለገው እነሱ ጋር ተጠግታ እንደትማር በሚል ነበር የሞቀ የእናቷን ቤት ጥላ የወጣችው። እንደመጣች ትምህርት ቤት በመግባቷ እጅግ በጣም ነበር የተደሰተችው። ከተወለደችባት ቀዬ የወጣቸው በ15 አመቷ ነበር። ልጅነትና ጉርምስና መካከል የምትዋዥቀው ቆንጆ ቀን ትምህርት ቤት ውላ ከትምህርት ቤት መልስ አሳዳሪዎቿን በሥራ በማገዝ ለማስደሰት ትጥር ጀመር።

ከትምህርትና ከቤት ውስጥ ሥራ የተረፋትን ጊዜ ዓላማዬ ነው ላለችው ከትውልድ ቀዬዋ ላስወጣት ትምህርቷ ስኬት እንቅልፍ ራሱ ገፍቶ እስኪጥላት ድረስ ታነባለች። ከዚያ ደግሞ ማልዳ ተነስታ አስፈላጊውን የቤት ውስጥ ሥራ ከውና ወደ ትምህርት ቤት ትሮጣለች። እንዲህ እንዲህ እያለች ለሦስት አመታት የቀጠለችው ልጅ ዕድሜዋ ሲጨምር ውበቷ ጎልቶ መታየት ጀመረ። ሸሽታ ያመለጠችው የመሰላት ጉንተላም እዚህ ድረስ ተከትሏት መጣ።

የውጪውን ጫና እንደምንም ተቋቁማ ትምህርቷን ዳር ለማድረስ መትጋት ጀመረች። ከቤት ውጭ ያለውን ታግላ ልታሸንፍ ብትታትርም የሩቅ ዘመድ ነው እሱ ጋር ተጠግተሽ ትምህርትሽን ዳር ታደርሻለሽ ተብላ የተጠጋችውን በእሷ አጠራር የአጎቷን ጉንተላ ለማስቆም አቅም ተሳናት።

በቤት ውስጥ ሥራ ድካም የተጫጫናት ወጣት የጀመረቻትን ለመጨረስ ከእንቅልፍ ጋር እየታገለች ጥናቷን እያጠናች በነበረችበት ወቅት ነበር የተቀመጠችበት የመኝታ ቤቷን በር ገፋ ተደርጎ የተከፈተው። የምትተኛው ከዕቃ ቤቱ አንድ ጥግ ላይ ስለነበር ውሃ ፈልጎ ወደ ክፍሉ የመጣ መሰሏት ስለነበር ከተቀመጠችበት ተነስታ ልታቀብለው ስትሞክር ነበር ወትሮም ተዘጋጅቶ የመጣው ሰው ባላሰበችው መልኩ እጅና አፏን ይዞ አልጋ ላይ የጣላት።

የምትወደውን ትምህርቷን እንዳያስተጓጉላት ከተወለደችበት ቀዬ ያሉ ጎረምሶችን ሽሽት የተጠጋችው ሰው የፈራችውን ነገር ፈፀመባት። ህልሟን ለማሳካት የተጠጋችው ግንብ ባላሰበችው መልኩ ህልሟን ደፍልቆ ጣለው።

አስጠጊው አጥቂ

ይድነቃቸው በላይ ይባላል። ከተወለደበት አካባቢ በትምህርቱ የገፋ ስለነበረ በአካባቢው ሰው የተከበረ የችግር ጊዜ መወጫ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰብ ሰው ነበር። ትንሽ ትልቁ ጎንበስ ብሎ ሰላም የሚለው ኮሌጅ የበጠሰ ነው የሚባለው ይህ ሰው በአጋጣሚ ወላጆቹን ሊጠይቅ ወደ ተወለደባት ቀዬ ሲሄድ ነበር የማስተዋልን ወላጆች ያገኛቸው።

በአካባቢያቸው የተማረ ከተማ የሚኖር አንድ እሱ በመሆኑ ነገ ተምራ ሰው የደረሰበት ትደርሰላች ያሏትን የዓይን ማረፊያ የሆነችውን ልጃቸውን ወስዶ እንዲያስተምርላቸው ይለምኑታል። ወላጆቹን ለመጠየቅ ብሎም ባለቤቱ አጋዥ ያስፈልጋት ስለነበር ሰው ይዞ ለመመለሰ አቅዶ የነበረው ይህ ሰው ጥያቄው ከነሱ ከመጣ ብሎ ይስማማል።

ባለቤቱም እየረዳቻት ራሷን ለመቻል የምትታትር ቀልጠፍ ያለች ልጅ ስለመጣች ደስ ብሏት እየተጋገዙ እንድትማር ትፈቅዳለች። ዘመዳችን ነው ላሉት ሰው ልጃቸውን አምነው የሰጡት ወላጆች አመት አመትን እየወለደ ልጅቱም ጠንክራ እየተማረች መሆኑን ሲረዱ ሃሳባቸውን ጥለው በሰላም ኑሯቸውን ቀጠሉ።

ማስተዋልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልና ሚስቱ በምን ምክንያት እንደሚጣሉ ባይገባትም መጨቃጨቃቸው እያሳሰባት ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ችግር ከመጣች ጊዜ አንስቶ ገጥሟት አያውቅም ነበር።

ከቀየዋ ያመጣትም ሰው አስፈላጊውን ነገር እያሟላላት ያስተምራት ስለነበር አስብቶ ያርደኛል የሚል ግምት አልነበራትም። ከሚስቱ ጋር ግጭት የጀመረው ይህ ሰው የቤቱ ሰላም ሲደፈርስ ዓይኑ ውጪን ማማተር ጀመረ። ውጭ ላይ ያሰበውን ያህል ነገር ሳያገኝ ቀርቶ ዓይኑን መለስ ሲያደርግ ነበር የልጅነት መልኳ ወጥቶ አዩኝ አዩኝ የምትለው የዘመድ ልጅ ናት የተባለችው ማስተዋል ላይ ዓይኑ ያረፈው።

አይቶ ልቡ ካሰባት ቀን ጀምሮ ይከታተላት የነበረው

 ይህ ሰው አምሽታ እያነበበች ቆይታ በዚያው እንቅልፍ እንደሚወስዳት አስተውሏል። ይህን ተገን አድርጎ ቀኑን ጠብቆ የባለቤቱን እንቅልፍ ውስጥ መሆን በመመልከት ወደ ልጅቷ መኝታ መጣ። ልጅቷ የሥራ ጫናና እንቅልፍ አዳክመዋት በነበረበት ሰዓት አግኝቶ የፈራችውን ነገር በሙሉ ፈፀመባት።

በዚህ ቢበቃው መልካም ነበር። ልጅቷ ባልና ሚስቱ እንዳይጣሉ በመስጋት ዝም ስትል እያስፈራራ በተደጋጋሚ ይደፍራት ጀመር። በዚህም የተነሳ እርግዝና የተከሰተባት ይህች ልጅ የሆነችውን በሙሉ አብራት ወደ ትምህርት ቤት ለምትሄድ ለጎረቤት ልጅ ተናገረች።

ጎረቤቶቹ

በየዕለቱ እየተፈፀመባት ያለውን ነገር አብራት ለምትሄደው የጎረቤት ልጅ የተናገረችው ማስተዋል መሄጃ በማጣቷ ጉዳዩን አፍና መቀመጧን ታስረዳለች። ይህን የሰሙ ጎረቤቶች ጉዳዩን በደንብ በማጣራት ለፖሊስ መረጃውን ያቀብላሉ። ፖሊስም ጥቃት የደረሰባትን ልጅ መርምሮ ደህንነቱ በተጠበቀ ማረፊያ ውስጥ ካኖራት በኋላ ነበር ጥቃት አድራሹን በቁጥጥር ስር ያዋለው።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ በሕክምና ምርመራ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈፀሙን ከመረዳቱ ባሻገር ይህች ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች አፍላ ወጣት ልጅ ተገዳ በተደፈረችበት ሁኔታ ውስጥ ሆና መፀነሷን ማወቁ አሳሰቦታል። ይህን እምነቱን ያጎደለ ሰው በምስክሮችና በተጠናከረ መረጃ በቁጥጥር ስር አውሎ ቃሉን ተቀብሏል።

ተከሳሽ ይድነቃቸው በላይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ኪንባ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ነው። ይህ ሰው በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በግምት 12፡30 ሰዓት ሲሆን ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ልጅ ላይ የግብረ ስጋ ድፍረት በመፈፀሙ የተነሳ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 626/4/ሀ/ እና 628/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል በመክሰስ ፖሊስ መረጃውን ለአቃቤ ሕግ አቅርቧል።

የዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

ዐቃቤ ሕግም የክስ መዝገቡ እንደደረሰው ጉዳዩን መመልከት ጀመረ። የክስ ዝርዝሩ እንደሚያስረዳው የግል ተበዳይ ከ17 እስከ 18 ዓመት የምትሆን እና በተከሳሽ ቤት ውስጥ በጥገኝነት የምትኖር ስትሆን ተከሳሽ ቀኑ ባልታወቀ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በራሱ የመኖሪያ ቤት ውስጥ በተደጋጋሚ የግብረስጋ ግንኙነት በመፈፀም ተበዳይዋን ለእርግዝና የዳረገ መሆኑ እና ቀኑ ባልታወቀ ግንቦት ወር 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት እስከ 4፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በተከሳሽ መኖሪያ ውስጥ በተደጋጋሚ በማስፈራራት እና በማስገደድ የግብረ ስጋ ግንኙነት የፈፀመባት በመሆኑ ተከሳሽ በተበዳይ ላይ የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል የፈፀመባት በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡

ዐቃቤ ሕግ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ያስረዳሉ ያላቸውን 2(ሁለት) የሰው ምስክሮችን እና 2(ሁለት) የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የተከራከረ ሲሆን ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ ያቀረበው የመከላከያ ምስክር ጥፋቱን ያላስተባበለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ብሎታል፡፡

 ውሳኔ

 በመጨረሻም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 12 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን በስምንት (8)ዓመት ፅኑ እስራት እና ከሕዝባዊ መብቱ ለ2 (ሁለት ዓመት) ተገድቦ እንዲቆይ በማለት ወስኖበታል፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You