በአካባቢው ያለገደብ የሚጮኸው ድምጽ አዲስ ለሆነ ጆሮ ይፈትናል:: ማሽኖች ያለአፍታ ይዘወራሉ፣ አፈር ዝቀው የሚወጡ ፣ጉድጓዱ ጠልቀው የሚምሱ መኪኖች ለአፍታ ሥራ አይፈቱም:: አቧራው ፣ሲሚንቶው፣ አሸዋና ድንጋዩ ከጠንካራ እጆች ገብተዋል:: ሁሉም በየፈርጁ ከተግባር ውሎ እየተጣደፈ ነው::
ባሬላ ይዘው ከላይ ታች የሚሮጡ፣ ፌሮ ቆርጠው የሚያስሩ፣ ድንጋይ በመዶሻ የሚቀጠቅጡ ብርቱዎች ብዙ ናቸው:: ሁሉም ስላደፉ ልብሶቻቸው፣ ስለቆሸሹ እጆቻቸው ደንታ የሰጣቸው አይመስልም:: አንዳቸው ሌላቸውን ሳያዩ የድርሻቸውን ይወጣሉ::
ስፍራው አመድ መስለው፣አመድ ልሰው ለእንጀራቸው የሚሮጡ የቀን ሰራተኞች መገኛ ነው:: ለእነሱ ፊታቸውን በጨርቅ፣ ራሳቸውን በሰሌን ባርኔጣ ከልለው መጣደፍ ብርቅ አይደለም:: በየቀኑ፣ በየሰአቱ ሲደክሙ፣ ሲባትሉ ይውላሉ:: በዚህ እውነታ ካሉቱ ባሻገር በጠዋቱ የግንባታውን አጥር ተደግፈው ሥራ ለመግባት በጉጉት የሚጠብቁ ሌሎች ትኩረት ይስባሉ:: አብዛኞቹ ከወዲያ ወዲህ ዓይናቸው ይንከራተታል:: ጆሯቸውን ጥለው ከአሁን አሁን ለመቀጠር መጠራታቸውን ይጠባበቃሉ:: በየጊዜው የውስጡና የውጪ ገጽታ በተቃርኖ ይተያያል::
አሁንም ከግንባታው መንደር ነኝ:: ጆሮዬን ዘልቆ የሚያልፈው ሀያል ድምጽ አእምሮዬን ያሸነፈ እስኪመስለኝ ደንዝዣለሁ:: አቧራው ይጨሳል፣ ሲሚንቶ ፣ ድንጋዩ ፣ አሸዋ ጠጠሩ ይራገፋል:: ሰራተኞቹ እረፍት የለሽ ናቸው:: ከወዲያ ወዲህ ይሮጣሉ፣ ይራወጣሉ::
ዙሪያቸው በህንጻዎች የተከበቡ ጅምር ፎቆች ከሚበልጧቸው ግዙፋን ጋር ፉክክር የያዙ ይመስላል:: በየቀኑ ቁመት እያከሉ ፣ያድጋሉ:: ወርዳቸው እየሰፋ፣ ቅርጻቸው ይለወጣል:: እንጨታቸው እየተነሳ ዲዛይናቸው ይታያል:: አላፊ አግዳሚው የሚደመምበትን ይህን ለውጥ በስጋት የሚያስተውለው ጎልማሳ ዛሬም ትካዜ ላይ ነው:: የዚህ ሰው እሳቤ ከሁሉም ይለያል:: ለእሱ የህንፃዎቹ ዕድገት የሚሰጠው ትርጉም ሌላ ነው:: አንዳንዴ ስራው ተቋርጦ ዝምታ ቢወርሰው ይመርጣል::
አንዳንዴ ደግሞ እንደቀድሞ አረፍ እያሉ የሚቀጥሉትን አይነት ሥራ ይመኛል:: ይህን ሲያስብ የጎን ጥቅሙ ይፈትነዋል:: ስራው ቢኖር በገንዘብ ይጠቀማል:: ባይኖር ደግሞ ገቢውን ያጣል:: ይህን ይተውና ልቡ ወደፊት ወደኋላ ይመላለሳል:: መልሱን ሲያገኘው አይዘገይም:: ሚዛኑ ‹‹መኖር›› ከሚሉት እውነት ላይ ያሳርፈዋል:: ይህኔ ሀሳብ፣ ትካዜው ይጨምራል::
እነዚህ ግንባታዎች እስከዛሬ ለእሱና ለቤተሰቡ የጀርባ አጥንት ነበሩ:: በእነሱ እንጀራውን ቆርሷል፤ ልጆች አሳድጓል:: የህንጻዎቹ መቆም ለመኖሩ ምክንያት ሆኖም ዓመታትን ተሻግሯል:: ዛሬ ግን አባወራው ነገውን እያሰበ መጨነቅ ከያዘ ከራርሟል:: ጭንቀቱ ደግሞ አንዳንዴ እንደሚሆነው ልማድ አይደለም:: ጭንቀቱ ስር ሰዷል:: ከሚገነቡት ህንጻዎች የአንዱን ግድግዳ ተደግፎ ከሚተክዘው ዘውድነህ አጠገብ ደርሻለሁ:: በልዩ ትህትናው ተቀብሎኝ የልቡን እያወጋኝ ነው:: እሱ መነሻውን አይረሳም:: ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ያውቃል:: ዘውድነህ ዓመታትን በዚህ ስፍራ ሲቆይ በብዙ የህይወት ጎዳናዎች ተመላልሶ ነው::
ትናንትን በትውስታ
ገና ጨቅላ ሳለ ወላጅ እናቱን በሞት ያጣው ህጻን ከፍ ሲል የሚሰማው ወሬ ይረብሸው ይዟል:: እናቱ እሱን ሲወልዱ ስለመሞታቸው የሚነግሩት ሰዎች ለስሜቱ መጠንቀቅ ልምዳቸው አይደለም:: እንዳመጣላቸው ታሪኩን እየነገሩ ያሳዝኑታል፣ያስለቅሱታል:: ዘውድነህ እውነቱን ካወቀበት ጊዜ አንስቶ ፈገግታው ደምቆ አያውቅም:: በገዛ እጁ እናቱን የገደለ እስኪመስለው ራሱን ይወቅሳል:: ይህ ስሜት አብሮ ማደግ ቢጀምርም ውስጡን ያወቀለት ወዳጅ ዘመድ አልነበረም:: ከእኩዮቹ ተነጥሎ በብቸኝነት ሲቆዝም የሚያዩት ብዙ ናቸው::
አንድ ቀን የአባቱ ታላቅ እህት ከአዲስ አበባ ወደእነሱ መንደር ዘለቁ:: ከልጅነቱ ስለኑሮ ህይወታቸው የሚሰማው ታሪክ ጆሮውን ሲያነቃው፣ ልቡን ሲማርከው ቆይቷል:: አሁን ደግሞ በዕድሜው ከፍ ያለበት ጊዜ ነው:: አክስቱን ቀረብ ብሎ አወራቸው:: ጨዋታው ከቀድሞው የተለየ ነበር:: ከቀናት በኋላ አክስት ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ:: ዘውድነህ ከእሳቸው የሰማው የከተማ ኑሮ በህልም በእውኑ ሲመላለስበት ከረመ:: አብሮት ካደገው ብቸኝነት የሚገላገለው ቀዬውን ርቆ መውጣት መሆኑን ካመነበት ቆይቷል:: ይህ ፍላጎቱ የሚሞላው በአንድ መንገድ ብቻ ነው:: አክስቱን ተከትሎ በመሄድ ብቻ::
ከወራት በኋላ የዘውድነህ አክስት ተመልሰው መጡ:: ይህ ጊዜ ለዘውድነህ የውሳኔና የቁርጥ ቀን መጨረሻ ሆነ:: ቀድሞ ያስበው የነበረውን ጉዳይ አሳውቆ ጓዙን ሸክፎ ተነሳ:: አክስቱ ሊከለክሉት አልወደዱም:: ታዳጊውን የወንድማቸውን ልጅ አስከትለው አዲስ አበባ ተመለሱ::
አዲስ አበባ …
አዲስ አበባና ዘውድነህ ለመላመድ ጊዜ አልፈጁም:: የከተማ ህይወት ለገጠሩ ልጅ አዲስ ቢሆንም እንግድነቱ ሳይከርምበት ሁሉን ፈጥኖ ተላመደ:: ውሎ አድሮ አክስቱ ትምህርት ቤት አስገቡት:: ደብተር ይዞ ቀለም መቁጠር ጀመረ:: ትምህርቱ ላይ ያሳየው ፍላጎት እምብዛም ነበር:: ውሎ ቢመጣም ለቁምነገር የሚበቃ ዕውቀት መያዝ አልቻለም::
ስሙን ከመጻፍ የዘለለ ለውጥ ያላገኙበት አክስት እንዳይማር ምክንያት እየፈጠሩ ሊያስቀሩት ሞከሩ:: ዘውድነህ አልተቃወመም:: ሰበብ ፈላጊው ልጅ ሃሳባቸውን በደስታ ተቀብሎ ቤት መዋል ጀመረ:: በአክስቱ ቤት የዘመድ ልጆች ብዙ ናቸው:: በየጊዜው ካገር ቤት እየመጡ የተማሩ፣ሥራ የያዙ፣ጎጆ የቀለሱ ጥቂት አይደሉም::
ዘውድነህ ቤት በዋለ ማግስት የሚሰራውን አላጣም:: በጊቢው ከሚረቡት ላሞች ጋር በፍቅር ወደቀ:: ሽታቸው፣ወተታቸው፣አዛባቸው ሁሉ አስተዳደጉን አስታወሰው:: ከትምህርቱ ይልቅ ለእነሱ ጊዜ ሰጥቶ አብሯቸው መዋል ያዘ:: በኪራይ የሚሸጠውን ወተት የሚያልበው፣የሚያዘጋጀው ታማኝ እሱ ብቻ ሆነ:: ዘውድነህ አልቦዘነም:: ጊዜውን፣ ጉልበቱን ያለስስት ሰጠ::
አሁን የገጠሩ ልጅ የከተማ ወጣት ሆኗል:: ይህ ዕድሜው ብዙ እያሳየው ነው:: እንደ እኩዮቹ መልበስ፣ መዝናናትን አይጠላም:: ሴት ጓደኛ ብትኖረው፣ አብሯት ቢወጣ ቢገባ ይወዳል:: ውሎው ግን ለዚህ ዕድል አይጋብዝም:: ከሰዎች ሲውል የልብሱ ጠረን ያሳቅቀዋል:: የሰዎቹን ፊት ሲያይ ዳግም ሊያገኛቸው ይፈራል:: ሁሌም የከብቶቹ ፣ የአዛባው ሽታ ከእሱ ጋር ነው:: ይህ እውነት ዘውድነህን ገለልተኛ ያደርገው ጀመር::
ጦርነቱ…
ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የታወጀበት ነው:: ይህ ጊዜ የሀገር መወረር፣ የዳርድንበር መደፈር ያስቆጫቸው ወገኖች ስለምን ሲሉ የጀገኑበት ነበር:: የዛኔ በሙዚቃው ፣ በግጥሙ፣ በፉከራና ቀረርቶው ‹‹እምቢ ባይነት›› ደምቆ ይደመጣል:: ይህ ስሜት በርካቶችን ለጦርነት አነሳስቶ ወደ ጦር ግንባር እያዘመተ ነው::
ዘውድነህ ከበርካቶች መሀል አንዱ ለመሆን ጊዜ አልፈጀም:: ድንገት በወሰነው ሃሳብ ‹‹ማቄን ጨርቄን›› ሳይል ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተገኘ:: ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወታደር ሆኖ ዘመቻ ተላከ:: ጦርነቱ ሲፋፋም፣ ጀግኖች ሲዋደቁ ለወራት የዘውድነህ ድምጽ አልተሰማም:: ዘመቻውን ከተቀላቀለ ጥቂት ጊዚያት በኋላ አክስቱ በማረፋቸው ስለእሱ የጠየቀ፣ ያስታወሰ አልተገኘም:: ጊዚያትን የቆጠረው ጦርነት እንዳበቃ ዘውድነህ አንድ እግሩን ተመቶ ሆስፒታል መተኛቱ ተሰማ:: በወቅቱ ስለእሱ ያወቁ ጥቂት ዘመዶቹ ስፍራው ተገኝተው ጠየቁት::
ዘውድነህ ከጦርነቱ ማግስት ከቁስሉ አገግሞ ከሆስፒታል ወጣ:: ወደአክስቱ ቤት ሲገባ የትናንቱን ታሪክ አላገኘም:: ቤቱ ተሸጧል፣ ቤተሰብ ዘመዱ ተበትኗል:: ጠረን ሽታቸው የሚናፍቀው ከብቶች፣በቅርብ የሚያውቃቸው ጎረቤቶች የሉም:: ዘውድነህ ስለሁሉም አዝኖ እርሙን አወጣ:: የደግ አክስቱን ትዝታ በልቡ ይዞም በውስጡ አነባ:: ያደገበትን ሰፈር ተሰናብቶ ወደ ሌላ አካባቢ አቀና፤ መንደርተኛው ወደደው:: ካለው እያጎረሰ፣ ከእጁ እያካፈለ ቀናትን አሻገረው:: ውሎ አድሮ የሰፈሩ አካል ሆነ:: ከደስታው እየተካፈለ፣ ከሀዘኑ ታደመ:: ሰፈርተኛው በኑሮው ከእሱ የሚበልጥ ፣የሚያንስ አይደለም:: ከማንነቱ ሊዋሀድ ፣ከኑሮው ሊመሳሳል ጊዜ አልቆጠረም:: በአጭር ጊዜ ከሁሉም ተግባብቶ ኑሮ መሰረተ::
አዲስ ህይወት…
ዘውድነህ በብቸኝነት አልቀጠለም:: በዛው ሰፈር ትዳር መስርቶ ልጆች ወለደ:: ወግ ማዕረግ ባየበት አካባቢ ሀዘን ደስታውን የሚጋራው አላጣም::ትናንትን አስኪረሳ፣ ህይወቱ እንደ አዲስ ተጀመረ:: በደሳሳ ማረፊያው ቤተሰቡን ይዞ ዓመታትን ዘለቀ:: ጊዜያት አለፉ፣ እንደዋዛ ነጎዱ:: ከቀናት በአንዱ ለዓመታት ሲወራ የቆየው ጉዳይ ዕውን ሊሆን ግድ አለ:: ተዳፍኖ የኖረው ወሬም እንደ አዲስ ተቀጣጠለ:: አሁን ነዋሪዎቹ በልማት ምክንያት አካባቢውን ሊለቁ፣ከስፍራው ሊርቁ ነው:: ይህ ዜና ለአብዛኞቹ ደስታን አጎናጸፈ:: ዘመናዊ ኑሮን የተመኙ፣ ይህን ቀን ሲያልሙ የቆዩ ለመሄድ ተጣደፉ:: ጥቂቶች አቅማቸውን እያሰቡ በትካዜ ቆዘሙ:: አንዳንዶች ምትክ ቤት ለማግኘት በየቦታው ተሯሯጡ::
እነዘውድነህ በሙሉ አፍ ‹‹ቤት›› ተብሎ የሚጠራ መጠለያ የላቸውም:: እንዲያም ሆኖ ህይወታቸው ከጎረቤቶቻቸው ያነሰ አልነበረም:: እንደሌሎች መስለው፣ ተመሳስለው ዓመታትን ገፍተዋል:: በዕቁብ በማህበር፣ በዕድር ተነጥለው አያውቁም:: እንደነባሮቹ ነዋሪዎች ግን ዕውቅና ኖሯቸው ቤት አልተመዘገቡም:: እነዘውድነህ ለቤት ዕጣው አልታደሉም:: እንደገሚሱ በምትክ ስለሚሰጠው መኖሪያም ያሰበ፣ ያስታወሳቸው የለም:: ይህ እውነት ካሉበት ተነስተው ወደየትም እንዳይሄዱ ምክንያት ሆነ:: ሌሎች ጓዛቸውን ሸክፈው ሰፈሩን ሲለቁ ዘውድነህና ቤተሰቦቹ በስፍራው ሊቆዩ ግድ ሆነ::
ሰፈርተኛው ከቦታው ሲርቅ የትናንቱን ደማቅ መንደር ዝምታ ዋጠው:: ጭርታው ለነ ዘውድነህ በእጅጉ ከበደ :: ቀናትን በብቸኝነት ቆጠሩ:: ውሎ አድሮ ተጠጋግተው የተሰሩት ዕድሜ ጠገብ ቤቶች ፈረሱ:: ትናንት ህይወትን የተጋሩበት፣ ድግስ የተጠሩበት፣ አውደ ዓመት ያሳለፉበት ፣ ድንቅ ጉርብትና እንደዋዛ ራቃቸው:: እነ ዘውድነህ ተስፋ አልቆረጡም:: ሁለት ህጻናት ልጆችን እንደያዙ የላስቲክ ጎጆ ቀልሰው ኑሮን ጀመሩ:: ማንም ምንም አላላቸውም፣ አልተቃወማቸውም:: ጉርብትና አብሮ መኖር፣ ደስታ ሀዘን ይሉት ትዝታቸው ሆነ:: የጨለማውን ግዝፈት ፣ የዝናብ ጸሀዩን ፈተና ፣ የውሀ ማጣቱን ችግር ተጋፈጡት :: ነገን በተስፋ እያለሙ ወራትን ተሻገሩ::
የሰዎቹ ዓይን..
ጥቂት ቆይቶ ባለሀብቶች አካባቢውን ይዞሩት ያዙ:: በርካቶች ተመላልሰው ስፍራወን ያዩት፣ ይቃኙት ጀመር:: ይህኔ የእነ ዘውድነህ ልብ በስጋት ተያዘ:: የሰዎቹ እግር ማብዛት አንድ ቀን ከስፍራው እንደሚያርቃቸው ገምተው በሀሳብ ተዋጡ:: ያሰቡት አልቀረም :: ቦታውን ገዝቶታል የተባለ ባለሀብት በአጭር ጊዜ የህንጻ ግንባታውን ጀመረ:: እነ ዘውድነህ ከስፍራው አልራቁም:: ሰውዬውም ለምን እንዴት አላላቸውም:: የእነሱን መኖር ከበጎ ተርጉሞ ንብረት እየጠበቁ በቦታው እንዲኖሩ ይሁንታውን ሰጠ:: በሆነው ሁሉ የተደሰተው ቤተሰብ ከስጋቱ ተመለሰ:: ውሎ አድሮ የላስቲክ ጎጇቸው በቆርቆሮ ቤት ተተካ:: ቤቱን እንዳሻቸው ከፋፍለው መኖር ጀመሩ::
የህንጻው ግንባታ ተጀመረ :: ዘውድነህ የስራ ዕድል ለማግኘት አልዘገየም:: በዘበኝነት ዕቃ እየጠበቀ በቀን ስራው እንዲሳተፍ ተፈቀደለት:: ባለቤቱ ለቀን ሰራተኞች ምግብና ሻይ ቡና ማዘጋጀት ያዘች:: በአጭር ጊዜ ነገሮች መልካም ሆኑ:: ገቢያቸው ጨመረ፣ ኑሯቸው ተሻሻለ:: የልጆች ቁጥር ጨመረ:: ከፍ ያሉት ትምህርት ቤት መዋል ያዙ:: ባልና ሚስት ፈጣሪን አመሰገኑ::
አይቀሬው እውነት…
ዘውድነህ ዛሬ ላይ በፍጥነት ከሚገሰግሱት ህንጻዎች በአንደኛው ጥግ ጎጆ ቀልሶ ወግ ማዕረግ አይቷል:: ይህ ህንጻ ለዓመታት ታዛ ከለላው ነበር:: እንዲህ ሲሆን ግን በዚህ ፍጥነቱ ገስግሶ አልነበረም:: ዛሬ ይህ ሩጫው አልተመቸውም:: ስጋት ሆኖ እንቅልፍ ነስቶታል:: ዘውድነህ ከዓመታት በፊት ከዚህ ስፍራ ሲገኝ አካባቢው በደሳሳ የቀበሌ ቤቶች የተያዘ ነበር:: በነዚህ ቤቶች ውስጥ የነበረ ነዋሪ ህይወቱ ተመሳሳይ፣ ጓዳው አይደበቄ እንደነበር ያስታውሳል:: የዛኔ እሱና ባለቤቱ ከአንዳቸው በረንዳ ተጠግተው እንደወጉ ኑሮን ጀምረው ነበር::
ይህ ጊዜ ቢያልፍም ለዚህ ቤተሰብ የመነሻ ጥሪቱ ነው:: ምንም ባያገኙም ፍቅር አይተውበታል፣ ሀብት ባያፈሩም ደስታን ሸምተውበታል:: አብሮ መኖርን፣ መተባበር፣ መዋደድን አትርፈዋል ::ትናንት ይህ ታሪክ በ‹‹ነበር›› አልፏል:: ባላለፈው ዛሬ ያለው ህይወት ግን ይህ አልሆነም:: አሁን ህንጻው እየተጠናቀቀ ነው:: በዓመታት የግንባታ ቆይታው ባጋጠመው አንዳንድ ችግር ማለቅ ባለበት ጊዜ አልደረሰም:: እንዲህ መሆኑ የጎዳው ባለሀብቱን እንጂ ዘውድነህን አልነበረም:: ይህ አጋጣሚ ለእሱ ቱርፋቱ ነበር:: የቆይታው መርዘም የእሱን መኖር አዝልጎ የዓመታት ታዛ ሆኖታል:: ያለበትን እስኪዘነጋ፣ስለነገ ማሰብ እስኪረሳ ኑሮ ቀጥሎበታል::
ባለፉት ዓመታት ለዘውድነህ የተረፈው ተጠልሎ መኖር ብቻ አይደለም:: እንጨቶቹን ሸጦ እንዲጠቀም፣ የሚወገዱትን ለራሱ እንዲያደርግ ዕድል በእጁ ነበር:: በዚህ ብዙ ተጠቅሟል፣ ቤቱን ሞልቶ ልጆች አሳድጓል፣ ዶሮዎች አርብቶ እንቁላሎች ሸጧል:: ዛሬ ግን ይህ እውነት ከእሱ የለም:: የግንባታ እንጨቱ ሲነሳ ፣ልቡ ይደነግጣል፣ ህንጻው በቀለም ሲያምር ይከፋል፣ስፍራው ሲጠረግ ሲጸዳ ያዝናል፣ ይተክዛል:: ነገ በእሱ ውስጠት እንደትናንቱ አይደለም:: ቀናቶቹ ሲታዩት ልቡ ይናዳል፣ ስጋቱ ያይላል::‹‹የት እደርሳለሁ ?ምን እሆናለሁ?›› ይሉት ጭንቀት ከእሱ አልፎ ለቤተሰቡ ተጋብቷል::
ዘውድነህ ያለፈበትን የህይወት ጎዳና ሲቃኘው እምብዛም አይከፋውም:: አልፎበት ተራምዷልና ግስጋሴው ወደፊት ነው:: ዛሬ ግን ነገን ለመሻገር ያለበትን ጫና የሚያወርድለት ወገን መሻቱ አልቀረም:: ቀድሞ የሞከረው የቀበሌ ቤት ጥያቄ ባይሳካም ዛሬም ደጅ እየጠና መመላለስ ይዟል:: ይህ ህንጻ ሲያልቅ፣በስፍራው እንደማይቆ አሳምሮ ያውቃል ፤ልጆቹ ከጀመሩት ትምህርት እንዲደናቀፉ አይሻም:: ዛሬን አልፎ ከነገ ለመድረስ ሀሳብ የሆነበትን እውነት ሊደርስበት አይፈልግም:: ነገ ለእሱ ስጋቱ ነው:: ነገ ለእሱ ያልተመለሰ ጥያቄው ምላሽ ያላገኘበት ምስጢሩ ነው:: እናም መፍትሄን ይሻል::‹‹አለንህ፣ከጎንህ ነን›› የሚለውን ወገን ይናፍቃል:: ዛሬን በተስፋ አድሮ ነገን የሚሰጋው ብርቱ አባወራ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2016