የማቲዎስ ምትክ ቤተሰቦችን ማፍራት የቻለው የ20 አመት ተቋም

የመረዳዳትና ለተቸገሩ ሰዎች የመድረስ ባህል ኢትዮጵያ ውያን ከሚታወቁባቸው መገለጫዎቻቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ባህል ከራስ አልፎ ለሌሎች ተስፋ መሆን የቻሉ ተቋማት እንዲገነቡ እያደረገም ነው፡፡ እነዚህ ተቋማትም መነሻቸው ለሌሎች መትረፍ ነውና በትጋትና በለውጥ ዓመታትን እየተሻገሩ ይገኛሉ፡፡ ‹‹የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ›› ምግባረ ሰናይ ተግባርም የዚሁ ማሳያ ነው፡፡

የማቴዎስ ወንዱ መስራቾች አቶ ወንዱ በቀለ እና ወ/ሮ አምሳለ በየነ በተለያየ የሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና በሁለት ልጆች ተወስነው ይኖሩ ነበር፡፡

ይህን ኑሯቸውንና የልጆቻቸውን ሁለት ብቻ መሆን የተመለከቱ የቅርብ ወዳጆቻቸው ሦስተኛ ልጅ እንደሚጨምሩ በተደጋጋሚ ወተወቷቸው፤ እነአቶ ወንዱ ግን ‹‹ያሉን ይበቁናል›› ብለው ተቀመጡ፤ ይሁንና ውትወታው በዛና ልባቸውን አሸፈተው፤ ሁለተኛ ሴት ልጃቸውን ከወለዱ ከ10 አመት በኋላ አዲስ የቤተሰብ አባል ተቀበሉ፡፡

ከእርግዝናው ጊዜ ጀምሮ በብዙ ጉጉት እና ናፍቆት ተጠብቆ የመጣው ሕፃንም ማቲዎስ ተባለ፡፡ ማቲዎስ የቤተሰቡን ደስታ ጨመረው፡፡ ወላጆችም ለማቲዎስ ትኩረት ሰጥተው ሕይወታቸውን በደስታ መምራት ጀመሩ፡፡

ማቲዎስ የሁለተኛ አመት የልደት በዓሉን ለየት ባለ መልኩ ካከበረ በኋላ ግን ወላጆች ልጃቸው ላይ አዲስ ነገር ማስተዋል ጀመሩ፡፡ ‹‹እኔና ባለቤቴ በጣም በመጓጓታችን ትኩረት አደረግንበት መሰለኝ የሁለተኛ አመት ልደቱን ያከበርነው እጅግ ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ነበር›› ሲሉ የማቲዎስ አባት ያስታውሳሉ፡፡

ሕፃን ማቲዎስ ላይ የህመም ምልክት ሲያስተውሉ ለሕክምና አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ሆስፒታል አቀኑ፤ ሕፃን ማቲዎስ ላይ የተለየ ነገር የተመለከተው ሐኪም፣ ለሌላ ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መሯቸው፡፡ ልጃቸው በደም ካንሰር ህመም መጠቃቱን የማቲዎስ ወላጆች ሰሙ፡፡

‹‹በአንድ ወቅት በመሥሪያ ቤቴ በካንሰር ታሞ የሞተ ወጣት አውቃለሁ፤ ከዚያ ውጪ ግን በፍጹም ስለ ካንሰር የማውቀው አልነበረም›› የሚሉት አቶ ወንዱ፣ በጊዜው እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው በተፈጠረው ነገር ፍጹም መደንገጣቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ቀጣዩ አማራጭ ክትትላቸውን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ማድረግ ሆነ፡፡

የካንሰር ሕክምና ለታካሚውም ሆነ ለአስታማሚው እጅግ በጣም ፈታኝ መሆኑን የሚያናገሩት አቶ ወንዱ፣ በሆስፒታሉ ለካንሰር ህሙማን ታካሚዎች ያለው ቦታ ምቹ አለመሆን፣ የምርመራ መሣሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመገኘት፣ መድኃኒቶችን በፍጥነት ለማግኘት መቸገር የሕክምና ክትትል ሂደቱን ከባድ አደረጉት፡፡

የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ህሙማን የሚታከሙበት በመሆኑ አንዳንዴ ህሙማን በጊዜያዊ መቆያ ክፍል ኮሪደር አግዳሚ ወንበር ላይ ለመተኛት ይገደዳሉ፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ ለካንሰር ታማሚዎች ተብሎ የተለየ የማቆያ ቦታ የለም፡፡ በካንሰር የተያዙ ሰዎች ደግሞ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ስለሚዳከም በተለያየ ኢንፌክሽን የሚያዙበት ሁኔታ ሰፊ በመሆኑ ለማገገምና ለመዳን ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡

አቶ ወንዱ እና ቤተሰቦቻቸው ለልጃቸው ማቲዎስ የሚታዘዘውን መድኃኒት በቀላሉ የማግኘት ዕድል ስለነበራቸው በሆስፒታሉ ለሚታከሙ ሰዎችም ይተርፉ እንደነበርም አቶ ወንዱ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ወንዱ የልጃቸውን የሕክምና ሁኔታ አሜሪካ ከሚገኘው ‹‹ሴንት ጁድ›› የተሰኘ የሕፃናት ሆስፒታል ጋር በኢ-ሜይል ግንኙነት በማድረግ በቅርበት ይከታተሉ ነበር፡፡ ሆስፒታሉም ከሚሰጠው ሕክምና በመነሳት ይድናል የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡

ሕፃን ማቲዎስ ለሁለት አመት ባደረገው ሕክምና ሰውነቱ ውስጥ የነበሩት የካንሠር ሴሎች መሞታቸው ተረጋግጦ ከዚያ በኋላ ይደረግ የነበረው ሕክምና የካንሰር ሴሎች ዳግም እንዳይከሰቱ የማረጋገጥ ሥራ ነበር፡፡ ‹‹የሕክምና ጊዜው ውጤታማ ነበር›› የሚሉት አቶ ወንዱ፣ የመዳን ዕድሉ ተስፋ ሰጪ በነበረበት ሰዓት የካንሰር ሴሎች እንደገና በመከሰታቸው ወደ ውጭ እንዲታከም በሐኪሞች ቦርድ ተወሰነ›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

አቶ ወንዱ እና ቤተሰባቸው በሀገር ውስጡ ሕክምና የፋይናንስ አቅማቸው በመዳከሙ አማራጫቸው መኖሪያ ቤታቸውን መሸጥ ነበር፡፡ በቅርብ ሰዎቻቸው አማካኝነት ነፃ ሕክምና የሚያገኝበትን ዕድል አግኝተው የመሄጃ ቀናቸውን ሲጠባበቁ የጓጉለትን ልጃቸውን ማዳን ሳይችሉ ቀሩ፤ ሕፃኑ ማቲዎስ መስከረም 13 ቀን 1996 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

አቶ ወንዱ ልጃቸውን በሚያሳክሙበት ወቅት ሰዎች ስለ ካንሰር ህመም የተሳሳተ አመለካከት እንዳላቸው እና ከሕክምና ባለሙያዎች ገጽ ላይ ተስፋ አስቆራጭ መልዕክት አስተውለዋል፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጡ ለልጃቸው መድኃኒት በሚገዙበት ጊዜም ሰዎች የመዳን ዕድሉ አናሳ መሆኑን በመጥቀስ ገንዘባቸውን እንዳያባክኑ ሊመክሯቸው ሞካክረዋል፡፡

‹‹ማቲዎስን ለማሳከም የመጨረሻው ዕድል ድረስ ሞክረናል፤ ነገር ግን ፈጣሪ አልፈቀደውም›› የሚሉት አቶ ወንዱ፣ ልጃቸውን የነጠቃቸውን ህመም የሌሎችን ሕይወት እንዳይነጥቅ የበኩላቸውን ለማድረግ፣ ሊድንና አስቀድሞ ሊከላከሉት በሚቻል ህመም ላይ ሰዎች የነበራቸውን ‹‹ካንሰር አይድንም›› የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ማስተካከል እንደሚገባ ወሰኑ፡፡

አቶ ወንዱ ‹‹እኛ ለልጃችን ስለምንሰጠው የምግብ ዓይነት በምንጨነቅበት ሰዓት በሆስፒታሉ ግን ለልጆቻቸው በቂ ምግብና ሕክምናም መስጠት ያልቻሉ መኖራቸው በጉዳዩ ላይ እንደሠራበት አድርጎኛል›› ይላሉ፡፡ እናም ልጃቸው ካረፈ ከስድስት ወራት በኋላ በልጃቸው ስም ‹‹የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ››ን ሚያዝያ ዘጠኝ ቀን 1996 ዓ.ም ከባለቤታቸውና ከሌሎች 13 ሰዎች ጋር በመሆን አቋቋሙ፡፡

አቶ ወንዱ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ባለቤታቸው ደግሞ ፀሐፊና ገንዘብ ያዥ ሆነው በልጆቻቸው አጋዥነት ለስድስት አመታት ያህል በራሳቸው መኖሪያ ቤት ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ሶሳይቲው የተቋቋመበት ዓላማ በካንሰር ታማሚ ሕፃናት ላይ አተኩሮ መሥራት ሲሆን፣ በካንሰር ህመም ላይ የሚታየውን የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር ኅብረተሰቡ ትክክለኛውን የካንሰር ምንነት፣ የመከላከያና መታከሚያ አማራጮቹን እንዲያውቅ ማድረግ፣ በሀገሪቱ የካንሰር ሕክምና ተሟልቶ የሚሰጥበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር፣ አቅሙ ለሌላቸው አስፈላጊውን የሞራልና ማቴሪያል ድጋፍ መስጠት፣ የካንሰር ሕክምና ተሟልቶ የሚሰጥበትና ምርምርና ስርፀት የሚካሄድበት የካንሰር ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም መርዳትና የሀገሪቱ የሕክምናና የትምህርት ተቋማት በካንሰር ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ማበረታታት የሚሉት ናቸው፡፡

ሶሳይቲው በአሁኑ ወቅት 30 ቋሚ ሠራተኞች አሉት፣ በስምንት ፕሮጀክቶች ላይም አተኩሮ ይሠራል፡፡ ከፕሮጀክቶቹ አንዱ የካንሰር ህሙማንን እና ቤተሰባቸውን መርዳት ነው፡፡ የካንሰር ሕክምና በሀገሪቱ በሁሉም ቦታዎች ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት ሕክምናውን ለማግኘት በርካታ ታካሚዎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡

ሶሳይቲው ለአስታማሚዎች ማረፊያ በማዘጋጀትና በመስጠት፣ ለታካሚዎች የሚታዘዝላቸውን እና ማግኘት ያልቻሉትን መድኃኒት በመግዛት፣ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን በማሰራት፣ በቀን አራት ጊዜ የሚመገቡትን ተቋሙ አዘጋጅቶ በማቅረብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በሶሳይቲው አርፈው ሕክምናቸውን ለሚከታተሉ ታካሚዎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል ወስዶ የሚመልስ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህን አገልግሎት 154 ለሚሆኑ የካንሰር ህሙማንና ቤተሰቦቻቸው እየሰጠ ይገኛል፡፡

ተላላፊ ስላልሆኑ በሽታዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ የሚሠራባቸው ፕሮጀክቶችም አሉት፡፡ የመጀመሪያው ፕሮጀክት በሕፃናት ካንሰር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን፣ በካንሰር የተጠቁ ሕፃናትን ቤተሰቦች በማገዝ የሕክምና ሂደታቸውን ይከታተላል፤ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር የሕክምና ክፍል ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ከሌሎች ተቋማት ጋር ባደረገው ጥናት በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚጠቁ እና ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ በሀገሪቱ ከሚከሰተው ሞት 52 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚይዝ ማወቅ ተችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ካንሰር አሶሲዬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኩላሊት ህመም ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማኅበር እና ከኢትዮጵያ የልብ ህመም ማኅበር ጋር የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ማኅበርን አቋቁሟል፡፡ ኅብረቱም በህመሞቹ ላይ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮችን ያግዛል፡፡ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር እና የጡት ካንሰር፣ የትምባሆ ስርጭትን ለመቆጣጠር፣ የሳንባ ካንሰር ቁጥጥርና ስርጭትን ለመግታትና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የአመጋገብ ሥርዓትን እና የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል በእጅጉ የሚረዳ ነው በማለት ሶሳይቲው ሰዎች የምግባቸውን ምንነት እንዲያውቁትና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን እንዲከተሉ ይሠራል፡፡

ሶሳይቲው ከተመሠረተ 20 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በነዚህ ዓመታትም በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ከ‹‹ፒንክ ሪበን ሬድ ሪበን›› (Pink Ribbon Red Rib­bon) ከተሰኘ ድርጅት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር አቀፍ የካንሰር መከላከልና ቁጥጥር ዕቅድ እንዲኖራት አድርጓል፡፡ በሥራ ላይ የዋለው ይህ የብሔራዊ ካንሰር መቆጣጠሪያ እቅድ ትኩረቱን ያደረገው በጡትና ማህፀን በር ካንሰር ላይ ነው፡፡

ሶሳይቲው በሀገር ውስጥ ካሉ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎችና ከ‹‹አሜሪካ አካዳሚ ኦፍ ፔዲያትሪክስ›› ባገኘው ድጋፍ የኢትዮጵያ ሕፃናትና ታዳጊዎች ካንሰር መቆጣጠሪያ እቅድ እንዲጸድቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሚሠራው የትምባሆ ቁጥጥር ፕሮጀክት ሥራ በኢትዮጵያ የትምባሆ፣ አልኮልና የመድኃኒት ቁጥጥር አዋጅ እንዲጸድቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የማህፀን በር እና የጡት ካንሰር አስቀድሞ መከላከል እና በተወሰነ መልኩ ቅድመ ምርመራ ማድረግ የሚቻል በመሆኑ ሶሳይቲው የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስለ ጉዳዩ በሀገራችን ያለው መነሳሳት፣ ምርመራው በመንግሥት ጤና ጣቢያ ከሞላ ጎደል በነፃ እንዲሰጥ እና 14 አመት ለሆናቸው ሴቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ክትባት እንዲሰጥ መደረጉ ከዚሁ የተገኘ ውጤት ነው፡፡

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጥምረት ይሠራል፤ በካንሰር ዙሪያ ለሠራቸው ሥራዎች በሦስት አመት ውስጥ ብቻ አምስት ዓለምአቀፍ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ በተለያዩ አህጉራት ካሉ ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋርም ምክክር ማድረግ ችሏል፡፡

ሶሳይቲው በተለያዩ ጊዜያት ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር ተባብሮ በመሥራት የካንሰር ሕክምና ክፍሎችን የማደስ እና ዘመናዊ የመመርመሪያ መሣሪያዎችን የማስገባት ሥራዎችን የሠራ ሲሆን፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ሰዎች በአቅራቢያቸው የካንሰር ምርመራ ማድረግ እንዲችሉ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለታካሚዎች የሚውል የሕክምና እና ለሚሰጠው አገልግሎት ከሚያወጣው ወጪ ባሻገር ለመኖሪያ ቤት ብቻ በቀን እስከ አምስት ሺህ ብር፣ በወር 120 ሺህ ብር፣ በአመት ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ያወጣል፡፡

ወይዘሮ ፀሐይ ተሾመ ሶሳይቲው ለካንሰር ህሙማንና ለቤተሰባቸው በሚያደርገው ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል፡ ፡ ወይዘሮ ፀሐይ በደሴ ከተማ የሚኖሩ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ልጃቸውን ወልደው ሁለተኛ ልጅ ለመጨመር ሳይሳካላቸው ቀርቶ ከ28 አመታት በኋላ ሴት ልጅ ይወልዳሉ፡፡ ‹‹በፈጣሪ ፍቃድ አገኘኋት›› የሚሏት ይህች ሁለተኛ ልጃቸው እስከ ሦስት አመቷ ድረስ በጥሩ ጤንነት ላይ ትገኝ ነበር፡፡

ነገር ግን የጤናዋ ሁኔታ እየተቀየረና አሳሳቢ እየሆነ መጣ። ከብዙ ፀሎት በኋላ ያገኟትን ልጃቸውን ይዘው በደሴ ከተማ የተለያዩ ምርመራዎችን እያደረጉ ከአንድ ወር በላይ ከቆዩ በኋላ በልጃቸው ሃይማኖት ኩላሊቷ ላይ የተከሰተው ዕጢ ወደ ካንሰር መቀየሩ ተነገራቸው። ለተሻለ ሕክምናም ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተላኩ፡፡

ወይዘሮ ፀሐይ ስለሆስፒታሉም ሆነ ስለሚያሳክሙበት ሁኔታ አስቀድመው የሰሙት መረጃ የሚያስፈራና ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡም ልጃቸውን ለማሳከም የሚያርፉበት ቦታም ሆነ ዘመድ እንዲሁም የገንዘብ አቅምም አልነበራቸውም፡፡ ወይዘሮ ፀሐይ ሲወራ የሰሙትና መጥተው በአካል ያዩት አንድ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ልጃቸው የኪሞቴራፒ ሕክምናውን በሆስፒታሉ ተኝታ ካደረገች ከአንድ ወር ከ15 ቀን በኋላ ቀሪውን ሕክምና ከቤታቸው እየተመላለሱ እንዲያደርጉ ተነገራቸው፡፡

ለወይዘሮ ፀሐይ ይህን ማድረግ ከባድ በመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ከነገሯቸው በኋላ ወደ ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ መምጣት ቻሉ፡፡ ‹‹ወደ ማቲዎስ ወንዱ ከመጣው በኋላ ማረፊያ አገኘሁ፣ ለልጄ የሚያስፈልጋት መድኃኒት ተሟልቶልኝ፣ ትልቁን ጭንቀት አቅልለውልናል›› በማለት በሶሳይቲው ስለሚያገኙት የአገልግሎት ጥራትና ስለተሰማቸው እፎይታ ይናገራሉ፡፡

በቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረን አንድ አሳዛኝ አጋጣሚ ወደ መልካም ነገር በመቀየር የተቋቋመው የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የሚሠራቸውን ሥራዎች በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት ጤናማ አፍሪካ የሚል ትልቅ ፕሮጀክት ቀርጾ እውን ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች የልህቀት ማዕከል ማቋቋም ሲሆን፣ ዋና ዓላማው ተላላፊ ስላልሆኑ በሽታዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የልየታና የምርመራ ክፍል ለታካሚዎች እንክብካቤ በመስጠት እና ህሙማን ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ለመታከም የሚያዩትን እንግልት ማስቀረት ነው፡፡

ማዕከሉ በውስጡ ከ45 በላይ የሥራ ክፍሎች (ዲፓርትመንቶች) ያሉት ዘመናዊ የምርመራና የሕክምና ማዕከላት፣ የምርምርና ስርጸት ማዕከል የህሙማንና ቤተሰቦቻቸው ማረፊያ፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን የሚያጎለብቱ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና ካፍቴሪያዎች ለመገንባት በእቅድ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህና መሰል ሀገር በቀል ተቋማት መስፋፋታቸው እንደሀገር ያሉብንን ችግሮች ከመቅረፍ እና በተለያዩ ዘርፎች የተሻለች ሀገር ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ የሶሳይቲው ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You