ዳጉ – የአፋር ባሕላዊ የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት

የሰው ዘር መገኛዋ አፋር ሙቀቷ ግሏል። የሙቀት ምጣኔው 42 ሴንቲ ግሬድ ደረጃ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከሰውነት የሚመነጨው ላብ የአካባቢው ነዋሪዎች የሙቀቱን ደረጃ የሚነግራቸው ምልክታቸው ሆኗል። ልብሳቸው ረጥቦ ፊታቸው ወዝቶ በየጥላው ስር ተቀምጠው ይጨዋወታሉ። በአፋር አንድ ዛፍ ትልቅ ዋጋና ክብር አላት ምክንያቱም በስሯ የሚቀመጡና የእሷን ጥላነት የሚፈልጉ ብዙ ናቸው። በዚህ ሙቀት ውስጥ ሆኖ ሕይወት ይቀጥላል፤ እየተጓዙም መረጃ እየተቀባበሉ ማለፍ ግድ ይላል። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመረጃ መለዋወጫ ባሕላቸው ዳጉ በመባል ይታወቃል። ይሄ የመረጃ መለዋወጫ መንገድ በምሁራን አተያይ እንዴት ይገለጻል ስንል በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአፋር ሀገር በቀል እውቀቶችና ጥበቦች የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አሕመድ አነጋግረናቸዋል።

“አፋር በኢትዮጵያ፤ በጅቡቲ እና በኤርትራ በድምሩ በሦስት ቦታዎች ይገኛል” የሚሉት ዳይሬክተሩ የአፋር ባሕላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥነ ሥርዓቱን ዳጉ ሁሉም ሕዝብ በየሰፈረበት ምድር የሚያውቀው በየትኛውም መንግሥትም ሆነ ሁኔታ የነበረና አሁንም ያለ ባሕል እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ አፋር «አፋሪ» የተሰኘ ባሕላዊ ሕግ አለው። የአፋር ባሕላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥነ ሥርዓት ዳጉም ከዚህ ሕግ የተመዘዘ እና ራሱን ችሎ በአንድ አንቀጽ የተደነገገ የአፋር ባሕላዊ ሀገር በቀል ሕግ ሆኖ ከጥንት ጀምሮ ሲያገለግል የኖረ ፤ አሁንም እያገለገለ ያለ ነው።

እናም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ያለው የአፋር ተወላጅ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ከገዛ ባሕሉ እና መተዳደሪያ ሕጉ የተቀዳ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን አሳምሮ ያውቀዋል። እናም አፋር የተከሰተውን ከአፋር የተነሳው አዋሽ ፤ የአዋሹ፤ አዲስ አበባ ላለው፤ አዲስ አበባ ያለው ደግሞ ለሌላው እንዲደርሰው ያደርጋል። በደምሳሳው አንዱ ከዚያኛው ድንበር ላይ የተከሰተውን በባሕላዊ መረጃ ልውውጥ መንገድ ለዚህኛው ያጋራዋል።

«ዳጉ» ምን ማለት ነው ከሚለው ስያሜ ጀምሮ እንዳብራሩትም፦ በቀይ ባሕር ዳር የተከሰተውን አንዱ ወደሄደበት የሚያደርስበት መንገድ ነው። ይሄኛውን ደግሞ የዚህኛውን መረጃ ይዞ ወደሚሄድበት የሚያሰራጭበት ባሕላዊ መንገድ እንጂ ከዚህ የተለየ አይደለም።

ያም ሆኖ ዳጉ የሚለው ጥሬ ትርጓሜ ወደ አማርኛ ሲመለስ የአፋር ባሕላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥነ ሥርዓት ማለት ስለመሆኑ ያነሳሉ። ይህ የመረጃ ሥነ ሥርዓት ብዙ ዓይነት የአተገባበር እና ይዘት ያለው ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ። ራሱን የቻለ የአጠቃቀም ሕግ እና መርህ እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ የሚናገሩት።

ደጉ የተሰኘው ይሄው ባሕላዊ የመረጃ ሥነ ሥርዓት ካለ ምንም ዓይናት የዘመናዊ መሳሪያ አጠቃቀም በክልሉ ተወላጆችም ሆነ ነዋሪዎች ዘንድ ትግበራ ላይ የሚውል ነው። ቀጥታ ቃል በቃል የሚደረግ ከአንዱ ተናጋሪ ወደ ሌላኛው የሚተላለፍ ፈጣን እና ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ ሂደት ነው።

ለመሆኑ በዳጉ መረጃ ሥርዓት ውስጥ የአፋር ሕዝብ ዕለት ከዕለት ምን እና ምን ዓይነት መረጃ ይለዋወጥ ይሆን? ለሚለውም ዳይሬክተሩ ምላሽ አላቸው። በሰጡን ምላሽ መሠረት ታዲያ ሕዝቡ በአጠቃላይ በመረጃ ሥርዓቱ የኅብረተሰቡን ኑሮ እና ሕይወት ከቅርብም ከሩቅ ምን እንደሚመስል ቃል በቃል ይለዋወጣል። የማኅበረሰብ ጤና እና ምቾት፤ የጋራ ጉዳይ እና የግል ርዕሰ ዘውጎችን፤ በተጨማሪም የዕለት ከዕለት ውሎ እና አዳር በጋራ ያነሳበታል። የአካባቢውን የአየር ፀባይ፤ የአካባቢውን የፀጥታ ሁኔታ፤ የማኅበረሰቡን የደህንነት ሁኔታ፤ የጋራ ጉዳይ ያወጋበታል፡፡

ሕዝቡ መረጃውን ማን ከማን፤ መቼ እና የት፤ እንዴት ነው የሚለዋወጠው ? የሚለውን ሲያስረዱ ፦በእድሜ ገደብና በጾታ አይወሰንም ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል መረጃ የሚለዋወጥበት መንገድ ነው ይላሉ። እንደሳቸው ገለፃ የሀብት እና ሥልጣን ፤ የቀለም እና የጎሳ ፤ የአካባቢ ልዩነት ሳይኖር አንዱ ከሌላው አዲስ መረጃ ልውውጥ ሊያደርግ ወይም ሊያጋራ ይችላል። ሆኖም ይሄን ማድረግ በአፋሮች ባሕል ልክ እና ገደብ አለው፡፡

በባሕሉ እንዲህ ዓይነቱን የመረጃ ልውውጥ ማድረግ የሚቻለው እና የሚፈቀደው መረጃ እስከ ሆነ ድረስ እና ምስጥር እስካልሆነ ድረስ ብቻ ነው። መቼ እና የት ይለዋወጣሉ ? ለሚለው ምላሽ ሲሰጡም፦ ደጉ ማለት የማኅበረሰቡ አስፈላጊ የዕለት ከዕለት የኑሮ የዝውውር መረጃ ልውውጥ በመሆኑ ጊዜ እና ቦታ ሳይወስነው የትም እና መቼም ቢሆን ሊደረግ የሚችል የመረጃ ልውውጥ ነው ሲሉ ይገልፁታል። ሲያልፍ ሲያገድም፤ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር እና ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ ርቆ በመሄድ ድንበር ሲሻገር ይሄን መረጃ መለዋወጥ ለአፋር ሕዝብ የመረጃ ባሕሉ ከተቀዳበት ሕጉ በመነሳት የተጣለበት ግዴታው ነው። ያለውን እና የሆነውን በትክክል ከምንጩ አስተላልፎ መጓዝ አለበት፡፡

አፋሮች በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ እንደመገኘታቸው በተለይ በነዚህ አካባቢዎች ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ማዕከል በማድረግ ሲንቀሳቀሱ መረጃ ልውውጡን አበክረው ይጠቀሙበት እና ይተገብሩታል። አፋሮች የሕዝብ ብዛታቸው የጅቡቲን ግማሽ ያህል እንደሚሆን የሚነገርላቸው ከመሆኑ አንፃር የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱ ሌላው ቀርቶ እርስ በእርሳቸው ላላቸው ማህበራዊ መስተጋብር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚናቅ እና በቀላሉ ታይቶ የሚታለፍ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

ሆኖም በዚህ መረጃ ልውውጥ ውሸት ማስተላለፍ የሚታሰብ እና የሚሞከር አይደለም። በአፋር ማህበራዊ መስተጋብርም ዘንድ የሀሰት መረጃ መለዋወጥ በብርቱ ያስወግዛል። ዳጉ የተሰኘው ጥንታዊ ሀገር በቀሉ የአፋር ባሕላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥነ ሥርዓት መተግበር ከጀመረ ጀምሮ እንዲህ ዓይነት ባሕሉን የሚያጠለሽ የሀሰት መረጃ ልውውጥ ተከሰተ ሲባል ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም።

ቢከሰት ግን በአፋር ሕዝብ ዘንድ እንዲሁም ባሕሉን እና አስተማማኝ መረጃውን ጠንቅቀው በሚያውቁት በአጎራባች ክልሎች ዘንድ በራሱ አንድም የሀሰት መረጃ አስተላላፊውን ያስወግዘዋል። ሁለትም ከማህበራዊ ሕይወት ያገልለዋል፤ ሦስትም ሥርዓቱ የመነጨው አፋሪ ከሚለው ከአፋር ጥንታዊ ሕግ ከሕጉም ክፍል ሥርዓቱ ራሱን የቻለ አንድ አንቀጽ እንደመሆኑ የሚያስቀጣበትም ሁኔታ ተደንግጓል፡፡

በመሆኑም ሕዝቡ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ሁሉ ጎጅነቱም የዚያኑ ያህል መሆኑን ስለሚረዳ በፍፁም የሀሰት መረጃ እንደማይለዋወጥ፤ እስካሁንም ተለዋውጧል ሲባል ተሰምቶ እንደማይታወቅ ይናገራሉ።

አቶ መሐመድ እንዳሉት፤ ወደ ሕጉም ሳይኬድ አንድ አፋር የሀሰት መረጃ ነው ያስተላለፈው ተብሎ ከተጠረጠረ ድጋሚ ለእሱ መረጃ የሚያቀብለው ሌላ አፋር አይኖርም። ሲገናኙ ዝም ብሎ ምንም መረጃ ሳያቀብለው ነው የሚያልፈው። ይሄኔ ደግሞ ያ ዝም ብሎ የታለፈው እና የሀሰት መረጃ በማስተላለፍ የተጠረጠረው አፋር ራሱን ስጋት ውስጥ ይከተዋል። ምን አድርጌ ነው መረጃ ሳይሰጠኝ ያለፈው የሚል ከፍተኛ ጭንቀትም ይገባዋል። በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚገለልበት ሁኔታም ስለሚገጥመው ይፈራል። በመሆኑም በመረጃ ማስተላለፍ ላይ እንደ ቀላል ጉዳይ የሚታይና የሚታለፍ ጉዳይ የለም። ትክክለኛ መረጃ ለማስተላለፍም ብርቱ ጥንቃቄ ይደረጋል።

የሀገር በቀሉን የዳጉ የአፋር ባሕላዊ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ፋይዳን አስመልክተው እንደነገሩን ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው። የመረጃ ልውውጡ እንደ መሬት መንሸራተት፤ መሬት መንቀጥቀጥ ያሉ አደጋዎች ሲከሰቱ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ቃጠሎ፤ ከውሃ፤ ከሳርና ግጦሽ እጦት ጋር የተያያዘ ድርቅ፤ የግለሰብ፤ የቡድን እንዲሁም የድንበር ግጭት ሲፈጠር፤ ፀብ ሲኖር ጉልህ አበርክቶ አለው። ቀድሞ መረጃውን መለዋወጥ ግጭቱ እንዳይባባስ ፤ ሳር እና ግጦሽ በድርቅ ከጠፋ ወደዚህ አካባቢ በመሄድ ሰው በመንገድ እንዳይጉላላ ሰውነቱም በድካም እንዳይዝል ያደርጋል።

በተለይ ከእሳት፣ ከመሬት መንሸራተት እና ከሌሎች ጋር በተያያዘ ያለውን መረጃ ቀድሞ መንሳት በዛ አካባቢ ያሉ ሰዎችን የሚመለከተው አካል ከአደጋው ቀድሞ በማንሳት ወደሌላ አካባቢ እንዲያሰፍር የሕይወት አድን ሥራም እንዲሠራ ይረዳል። አብዛኞቹ አፋር የሚለዋወጣቸው መረጃዎች ግጭቶች ተባብሰው ስር እንዳይሰዱ፤ ለሕገ ወጥ መጥፋት ምክንያት እንዳይሆኑ የሚያደርጉ እና ችግር ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚያስችል ጥንቃቄ የሚወሰድባቸው ማስጠንቀቂያ ጭምር ናቸው።

በአጠቃላይ ዳይሬክተሩ የመረጃ ልውውጥ ባሕላዊ ፋይዳውን ጠቅለል አድርገው አስተዋጽኦ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሊከሰቱ ሲሉ አስቀድሞ አውቆ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይረዳል። የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅም ያስችላል። እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ቢከሰቱ አስቀድሞ ጥንቃቄ ለመውሰድና ሕዝቡ ከአካባቢው አስቀድሞ ገለል እንዲል አስቀድሞ መረጃን ይሰጣል። በአጠቃላይ የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የተከፈቱ ጠቃሚ ነገሮችም ካሉ ይሄንኑ ጠቃሚ ነገር ለመለዋወጥ ያግዛል ብለውናል፡፡

የዳጉ መረጃ መለዋወጫ ሥርዓት ሲተገበር በቆየባቸው ረጅም ጊዜያት በተለይ ባለፈው በኢትዮ ኤርትሪያን ድንበር ጦርነት፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክልል በነበረው ግጭት በተለያዩ ወቅቶች የሕዝቡን ደህንነትን ከመጠበቅ፤ የአደጋ ምንጮችን ከማረጋገጥ እንዲሁም አጠቃላይ ክልሉን ከአደጋ ከመከላከል አንፃር ውጤታማ ተሞክሮ ተቀስሞበታል።

“ይህ ዓይነት የዳበረ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ አንድ የባሕል ቅርስ እንዲሁም ዕሴት ነው፡፡” የሚሉት ዳይሬክተሩ በዘመናዊ የዓለም አቀፍ የመረጃ ልውውጥ ሂደት ላይ አፋር ራሱን የቻለ የተሳትፎ አቅምን ማጎልበት የሚችል እምቅ አቅም ያለው ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ይሄን እሴት ተጠቅመንበት ብዙ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል ያስችላል የሚል እምነትም አላቸው። በተለይ አሁን ላይ በሀገር ደረጃ ብዙ ያለብንን የመረጃ ሚዛናዊናት መዛባት ሊያስተካክል ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ይሄን የመረጃ ልውውጥ እሴት ወደፊት በሀገር ደረጃ ከመጠቀም ባለፈ በዓለም መድረኮች ላይ የማስተዋወቅ እቅድ አለ። በዩኒስኮ ማስመዝገብ አንዱ ነው። ለዚህ ደግሞ ባሕላዊ መረጃ ምንጩ አፋሮች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያኖች በሙሉ በአካልም በተግባርም ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ አቶ መሐመድ።

ልክ እንደ ዳጉ ሁሉ ሌሎች ጠቃሚ ሀገር በቀል እውቀቶችንና ሀገርኛ ባሕሎቻችንን ጠብቀን ማቆየት እና ማሳደግ ይገባል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You