የመጀመሪያው ታላቁ የወንጪ ሩጫ ነገ ይካሄዳል

የአሜሪካዎቹ ሆፕኪፕተን ስቴት ፓርክ፣ ግራንት ፓርክ እና ሴንትራል ፓርክ በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው ስድስቱ ዋና ዋና የማራቶን ውድድሮች መካከል የሆኑት የቦስተን፣ ቺካጎ እና ኒውዮርክ ማራቶኖች የሚካሄዱባቸው ስፍራዎች ናቸው፡፡ ለንደንን የመሰሉ ትልልቅ ከተሞችም በፓርኮቻቸው ውስጥ የተለያዩ ስፖርታዊ ሁነቶችን ያስተናግዳሉ፡፡ በእርግጥ ነፋሻማ አየር ያላቸውና በውሃማ ስፍራዎች ዳርቻ የሚደረጉ ሩጫዎች በብዛት የተለመዱ ናቸው፡፡

በአትሌቲክስ ስፖርት የሚካሄዱ የጎዳና ሩጫዎች ጥንታዊ ስፍራዎችን፣ የተንጣለሉ ዘመናዊ ጎዳናዎችን እንዲሁም ለቱሪዝም መስህብነት የተገነቡ ፓርኮችን መሠረት አድርገው ይካሄዳሉ፡፡ ከ1990ዎቹ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማደግ ላይ ካሉ ዘርፎች መካከል ስፖርትና ቱሪዝም ይጠቀሳሉ። ስፖርታዊ ውድድሮች ቱሪስቶችን የመሳብ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ሁሉ የቱሪዝም ስፍራዎችም ስፖርታዊ ሁነቶችን ለማስተናገድ ተመራጭ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ትልልቅና ዓመታዊ ውድድሮች ለዚህ ማሳያ ማድረግ ይቻላል፡፡ አዳዲስ የቱሪዝም ፕሮጀክቶችን ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅም ሆነ ይበልጥ ሳቢ ለማድረግም ስፖርታዊ ሁነቶችን ማዘጋጀት አንደኛው መንገድ መሆኑንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኢትዮጵያም ይኸው ሁኔታ እየተለመደ የመጣ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገነቡ የቱሪስት መስህቦችና ፓርኮች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችንም ያካተቱ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት የወዳጅነት አደባባይ ቁጥር 1 እና 2፤ እንዲሁም የእንጦጦ ፓርክ የጤና ቡድኖች እንዲሁም በግላቸው ስፖርት ለመሥራት የሚፈልጉ ሰዎች የሚመርጧቸው ስፍራዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫም በእንጦጦ ፓርክ ሳምንታዊ የሆነ የሩጫ ውድድር በተከታታይ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ነገ ደግሞ ሀገራዊ ከሆኑ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሆነው የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ይህ የቱሪስት መዳረሻ ከሳምንታት በፊት መመረቁን ተከትሎ በደንዲ ሐይቅ ዳርቻ ባህላዊ የፈረስ ግልቢያ እና የፈረስ ጉግስ ተካሂዷል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲገነባ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ስፖርታዊ፣ ባህላዊና ኪነጥበባዊ ሁነቶችን ማስተናገድ እንዲችል ታስቦ ሲሆን፤ የወንጪና ደንዲን ሐይቆች የሚያገናኝ 21 ኪሎ ሜትር (ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የግማሽ ማራቶን) ትራክን አካቷል፡፡

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንዲሁም በወንጪና ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት አስተባባሪነት የሚደረገው ታላቁ የወንጪ ሩጫ ነገ ጥር 18/2016 ዓ∙ም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ በቀጣይነት በየዓመቱ የሚካሄድም ይሆናል። የቱሪዝም መዳረሻውን እንዲሁም ውድድሩን ለማስተዋወቅ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር፤ የኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫው እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማኅበር ተወካዮችም በዚህ ውድድር ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ በውድድሩ 2 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 22 ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት ይሳተፋሉ፡፡ 186 ወንድና 116 ሴት በጥቅሉ 302 አትሌቶች ሲሮጡ፤ በዓለምና ሀገር አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ በዚህም በወንዶች በኩል ሞገስ ጥኡማይ፣ ጫሉ ዴሶ፣ ካሌብ ካሼቦ፣ ሰለሞን በሪሁ፣ ቢተው አደመ፣ ገመቹ ኢዳኦ፣ ሮባ መርጋሳ እና ሌሊሳ አራርሳን የመሳሰሉ ታዋቂ አትሌቶች ውድድሩን በጠንካራ ፉክክር እንዲታጀብ ያደርጋሉ በሚል ይጠበቃል፡፡

በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድርም አሸቴ በከሪ፣ ትዕግስት ከተማ፣ ደራ ዲዳ፣ በቀለች ተኩ፣ ብዙሀገር አደራ፣ በቀለች ዳባ፣ ትዕግስት ጌትነት፣ መሰሉ በርሄ እና አዌ መገርሳን የመሳሰሉ አትሌቶች ለመሸናነፍ እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት ፉክክር ውድድሩን አጓጊ ያደርገዋል፡፡ ውድድሩ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚከናወን ሲሆን፤ አንጋፋ አትሌቶች እንዲሁም የሕፃናት 1 ኪሎ ሜትር ሩጫ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም 33 አንጋፋ፤ እንዲሁም 300 ሕፃናት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከሜዳሊያ ባለፈ እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁ የገንዘብ ሽልማትም ያገኛሉ፡፡ ለሽልማቱ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የተመደበ ሲሆን፤ አሸናፊ አትሌቶች 150ሺህ፣ ሁለተኛ የሚሆኑ 100ሺህ፤ እንዲሁም፣ በሦስተኛነት ደረጃ ለሚገቡ 70ሺህ ብር ይበረከትላቸዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You