በአምራች ዘርፉ እድገት ላይ ከተጋረጡ መሰናክሎች መካከል አንዱ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ በፍጥነት የተሳለጠ አለመሆኑና በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው የዋጋ ውድነት ነው። የሎጂስቲክስ ሥርዓት ከአምራች ዘርፍ ውጤታማነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው። ፈጣንና ቀልጣፋ የምርት ግብዓቶችና የምርቶች ዝውውር በአምራች ዘርፉ ውጤታማነት ላይ ያለው ተጽእኖም ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነው። ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ምርት እንዲጨምር እንዲሁም የምርት ስርጭት ፈጣንና የተሳለጠ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ግብዓቶችንና ምርቶችን በፍጥነት የማያገኙ አምራቾችና ምርት አከፋፋዮች፣ በምርት ሰንሰለት ውስጥ ውጤታማ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም።
ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ 40 በመቶ ድርሻ ያለው የሎጂስቲክስ ዘርፍ፣ በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉበት። ከእነዚህ ሰንኮፎች መካከል የጭነት ዓይነቶችንና ብዛትን የሚያስተናግድ አቅም አለመኖር፤ መርከቦች በወደቦች አካባቢ ጭነት ለማራገፍ የሚያጠፉት ጊዜና በዚያም ሳቢያ የሚፈጠረው የወደብ መጨናነቅ፤ የተጓተተ የመርከቦች ኦፕሬሽን፤ የማከማቻና የጎተራዎች እጥረት፤ የጭነት መኪኖች በወደብ፣ በኬላዎች፣ በድንበርና በጭነት ክብደት መመዘኛ ጣቢያዎች የሚያጠፉት ጊዜ መብዛት ጥቂቶቹ ናቸው።
ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ (National Logistics Strategy) እንደሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ሥርዓት የሎጂስቲክስ ሥርዓት ውጤታማነት መለኪያ በሆኑት የሎጂስቲክስ ጊዜና ወጪ መመዘኛዎች ሲመዘን በእጅጉ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በትራንዚት ጊዜ፣ በዕቃዎች እና በመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታ፣ ጭነት ከወደብ በማንሳት አቅምና በመሰል የሎጂስቲክስ የአፈጻጸም መለኪያዎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ ነው። በችግሩ ውስጥ ዘርፉ የሚመራበት ሕግና ፖሊሲ፣ የተዘረጋው መሠረተ ልማት፣ ዘርፉን የሚመሩና የሚቆጣጠሩ ተቋማት አሠራር፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎችና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብቃት እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች የየራሳቸው ድርሻዎች አሏቸው።
የዓለም ባንክ የሎጂስቲክስ አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ በዋና ዋና የሎጂስቲክስ ክዋኔ መለኪያዎች (የጉምሩክ አገልግሎት፣ መሠረተ ልማት፣ ዓለም አቀፍ ጭነት፣ የሎጂስቲክስ ብቃት፣ ክትትል እና ጭነትን በወቅቱ ማድረስ) ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላት ሀገር ናት። ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው ብዙ ሀገራት የሎጂስቲክስ አፈፃፀማቸው እየተሻሻለ ሲሄድ የኢትዮጵያ ግን የበለጠ ማሽቆልቆሉ ነው።
ሀገሪቱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበችውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ተከትሎ የገቢና የወጪ ዕቃዎችና የሀገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ በመጠንና በዓይነት በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል። በመሆኑም የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ልማት ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል አንዱ ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጂስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት ነው።
ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ ሥርዓትን እውን ለማድረግ በብዛትና በጥራት ያደገ ውጤታማ የወደብ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። ይህ ዓይነቱ የወደብ አጠቃቀም ከላይ ለተጠቀሱት የሎጂቲክስ ሥርዓቱ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ይሰጣል። በቀደመው ታሪኳ የብዙ ወደቦች ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት 30 ዓመታት በወደብ እጦት ምክንያት ለከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ተዳርጋለች። ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣች ነው፤ የጭነት አገልግሎት ሥርዓቱ ፈጣንና ቀልጣፋ ባለመሆኑ የሀገሪቱ የአምራች ዘርፍ የምርት ግብዓቶችን በሚፈለገው ፍጥነት እንዳያገኝና በሀገር ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በአጭር ጊዜ ለዓለም ገበያ እንዳይደርሱ ትልቅ መሰናክል ሆኗል።
በሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥረው የወደብ ጉዳይ፣ በአምራች ዘርፍ እድገት ላይ የሚኖረው ሚና በሌሎቹ ዘርፎች ላይ ካለው ተፅዕኖ ይበልጣል። የወደብ ተጠቃሚነት ለአምራች ዘርፍ ወሳኝ እድገት መሠረታዊ ግብዓት/መደላድል ነው። የበርካታ ባለሙያዎች የጥናት ግኝቶችም ይህን እውነት በብርቱ ይደግፋሉ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሰር ፖል ኮሊየር፣ ድህነት በተንሰራፋባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወደብ አልባ ሀገራት በወደብ አልባነታቸው በእጅጉ እንደሚፈተኑ አስረድተዋል። ወደብ ያላቸው ሀገራት ሰፊና በርካታ የገበያ አማራጮች ሲኖራቸው ወደብ አልባዎቹ ግን የገበያ ሽርክናቸው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል።
ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ የተባሉ የምጣኔ ሀብት ምሁር፣ የወደብ ተጠቃሚነት ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ላስመዘገቡ የእስያ ሀገራት ባለውለታ እንደሆነ በስፋት አብራርተዋል። ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሲንጋፖር… በወደብ ተጠቃሚነታቸው ምክንያት የማምረቻ ዘርፋቸው አስገራሚ የሆነ እድገት ማስመዝገቡንና ይህ እድገትም ለጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ዋና ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹አሰብ የማን ናት?›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ‹‹… በ2008 ዓ.ም. በዓለም 44 ወደብ አልባ ሀገሮች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ ሠላሳ አንዱ ድሃ ሲሆኑ፣ አሥራ ሦስቱ ደግሞ የድሃ ድሃ የሚባሉ ናቸው። እነዚህ አሥራ ሦስት የድሃ ድሃ ሀገሮች በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከእነዚሁ አሥራ ሦስቱ ሀገሮች ተርታ ትሰለፋለች። እነዚህ ወደብ አልባ ድሃ ሀገሮች ወደ ውጭ የሚልኳቸው ምርቶች በአንድና በሁለት ሰብሎች ወይንም በአንድና በሁለት የኢንዱስትሪ ውጤቶች ወይም ጥሬ ዕቃ የተወሰኑ ናቸው። ስለሆነም ከድህነት የመላቀቅ ዕድላቸው በጣም የመነመነ መሆኑን ሊቃውንት ይናገራሉ…›› ብለዋል።
እነዚህ ሁሉ የባለሙያ ጥናቶች የሚያረጋግጡት የወደብ ተጠቃሚነት በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት፣ በተለይም በአምራች ዘርፉ፣ እድገት ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ እንዳለው ነው። የኢትዮጵያ አምራች ዘርፍም ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውጪ አይደለም። ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ባከበረ መልኩ የወደብ ተጠቃሚ ለመሆን በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት፣ የአምራች ዘርፉ በሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ደካማ አፈፃፀም ምክንያት የሚያጋጥሙትን ችግሮች የሚያቃልል እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንደሚሉት፣ ወደብ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እድገት ልዩ ሚና አለው። ማኑፋክቸሪንግ ከሚቀላጠፍባቸውና ውጤታማ ከሚሆንባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ነው። የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ውድና ጊዜ የሚፈጅ ነው፤ የወደብ ባለቤት መሆን ፈጣን የወጪና ገቢ ንግድ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ችግሮች ይፈታል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ማብራሪያ፣ የወደብ ተጠቃሚነት በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ያስችላል። አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለውጭ ሀገር ገበያ እንዲያቀርቡ ብሎም ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚረዱ ግብዓቶች በፍጥነት እንዲደርሳቸው መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ስለሆነም በወጪ ገቢ ንግድ ፍሰት ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።
የምርት ግብዓቶችንና ምርቶችን ወደ ሀገር ለማስገባት የሚፈጀውን ረጅም ጊዜና የተንዛዛ ቢሮክራሲ ለማሳጠር፤ የተመረቱ ምርቶችን በሚፈለገው ፍጥነትና መጠን ያለመድረስ አሁናዊ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ብሎም በወደቦች አካባቢ ያሉ አላስፈላጊ ተጨማሪ ወጪዎችንና መጉላላቶችን ለማስቀረት የወደብ ባለቤት መሆን ምርጫ የሌለው መፍትሔ ነው።
‹‹ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እና ለማልማት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር መፈፀሟ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ነፃ ንግድ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ አምራች ኩባያዎች የወጪ ንግዶቻቸውን እንዲያቀላጥፉ ብሎም ሀገራችን ለዘመናት የባህር በር በማጣቷ ያላገኘቻቸውን ግዙፍ ሀገራዊ ጥቅሞች እንድታገኝ የሚያስችል ነው›› ይላሉ።
‹‹የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች፣ በቀደመው ታሪኳ የብዙ ወደቦች ባለቤት የነበረች፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት … ሀገር፣ አሁን ወደብ አልባ መሆኗ ፍትሐዊ አይደለም›› የሚሉት አቶ አክሊሉ፣ ስምምነቱ ሁሉንም ወገን አሸናፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ያከበረ(Win-Win) እና ለአምራች ዘርፉ እድገት ትልቅ ሚና ያለው ስምምነት መሆኑንም ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ‹‹ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ያደረገችው ስምምነት የ120 ሚሊዮን ሕዝብ የህልውና ጥያቄ እንጂ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር በእጅጉ የሚያስፈልጋት፤ የሚገባትና ለስኬታማነቱም በፅናት የሚቆም ሕዝብና መንግሥት ያላት ሀገር ናት›› በማለት ይገልፃሉ።
የ«ጵንኤል ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር» መሥራችና ባለቤት ወይዘሮ ብርቱካን አበበ፣ ‹‹ስምምነቱ ትልቁን ባዶነታችንን የሚዘጋ እርምጃ ነው›› ይላሉ። እሳቸው እንደሚናገሩት፣ የወደብ ክፍተቱ ሁሉም አምራች በብዙ ነገሮች እንዲቸገር አድርጎታል። የሎጂስቲክስ ክፍያው ውድ ስለሆነ አምራቹ ምርቱን ለገበያ የሚያቀርበው በውድ ዋጋ ነው። የወደብ ተጠቃሚ መሆን ይህን ችግር ለማቃለል ይረዳል። ለአምራች ዘርፉ እድገት በጎ አስተዋፅዖ የሚኖረውን ይህን ስምምነት፣ በተቻለ ፍጥነት ወደ ተግባር መቀየር ይገባል።
ዶክተር ዮሐንስ ብርሃነ ወደ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ለመሰማራት በቅርቡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የሥራ ስምምነት የፈፀመው የ‹‹ተርትል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› ባለቤት ናቸው። ‹‹የስምምነቱ ዜና በተለይ ለአምራች ዘርፉ መልካም ብስራት ነው›› ይላሉ። በሀገሪቱ በኢንቨስትመንት መስክ ካሉ ችግሮች አንዱ የወደብ ችግር እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ዮሐንስ፣ ስምምነቱ ምርቶችን ወደ ውጭ በፍጥነት ለመላክ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያሳልጠው ይገልፃሉ።
በዓለም ላይ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ኖሯት ወደብ የሌላት ትልቋ ሀገር ኢትዮጵያ የመሆኗ መራራ ሃቅ፣ የወደብ ተጠቃሚነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ አመላካች ነው። የወደብ ተጠቃሚነት ጉዳይ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የተቆራኘ ነው፤ የወጪና ገቢ ንግድ ደግሞ በአምራች ዘርፉ ውጤታማነት ላይ የሚወሰን ነው። ስለሆነም በስምምነቱ መሠረት ለወደብ ተጠቃሚነት ጉዳይ ላቅ ያለ ትኩረት በመስጠት የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም ማሻሻልና መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ማሳካት ይገባል ሲሉ ዶክተር ዮሐንስ ብርሃነ ተናግረዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2016