ስማርት ዲፕሎማሲ ከዲጂታል ዲፕሎማሲ፤ ሳይበር ዲፕሎማሲና ቨርቹዋል ዲፕሎማሲ ጋር ብዙ የሚያመሳስሉት ጉዳዮች አሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሁሉም የዲፕሎማሲ ዓይነቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዲፕሎማሲ ሥራ የሚከናወኑባቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ስማርት ዲፕሎማሲ ከሌሎች የዲፕሎማሲ ዓይነቶች የላቀ ስፍራ ያለው ነው፡፡
በዋናነት ስማርት ዲፕሎማሲ መጠነ ሰፊ ዳታ (Big data–driven decision making) የሚፈልግና በትንተና ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ ሥራ ሲሆን የዲፕሎማቶች ውሳኔ የመስጠት አቅምና ፍጥነትን በማጎልበት የሚከናወን የዲፕሎማሲ ዘርፍ ነው። በመሆኑም ስማርት ዲፕሎማሲ ለማከናወን ጥልቅ መረጃዎችን አደራጅቶ ከሚይዝ አካል ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራ እንጂ እንደሌሎቹ የዲፕሎማሲ ዘርፎች በጥቃቅንና በተበታተኑ መረጃዎች ላይ ተሞርክዞ የሚከናወን ዲፕሎማሲ አይደለም፡፡
ከነባሩ ዲፕሎማሲ (traditional diplomacy) የሚለይበትም በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ነው፡፡ የነጋዴው፣ የሕዝቡ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት፣ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ፣ የምሁራኑን፣ አሰላሳይ ተቋማትን እና የመሳሰሉትን በመረጃ እና ግብአቶች በማሳተፍ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠራ ነው፡፡
ስማርት ዲፕሎማሲ ስፋትና ጥልቀት ያለው የዲፕሎማሲ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ማለት እንደሳይበር ዲፕሎማሲ የሳይበር ደህንነት ላይ ብቻ ያጠነጠነ አይደለም፡፡ እንደ ቨርቹዋል ዲፕሎማሲ መለስተኛ መረጃዎችን በርቀት የመቀባበልና የውይይት ሥራ የሚሠራበት ብቻ አይደለም፡፡ በተመሳሳይም እንደ ዲጂታል ዲፕሎማሲ አነስተኛ መረጃዎች ላይ (not big data) የተንጠለጠለ አይደለም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ ነው፡፡ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ የአየርንብረት ዲፕሎማሲ፣ ሳይንስ ዲፕሎማሲ፣ ሰብዓዊ ዲፕሎማሲ(humanitarian diplomacy)፣ የጾታ ጉዳይ ዲፕሎማሲ(Gender Diplomacy)፣ የባህል ዲፕሎማሲ፣ የዲያስፖራ ዲፕሎማሲ፣ የጤና ዲፕሎማሲ እና የመሳሰሉት በስማርት ዲፕሎማሲ ተቀናጅተው የሚሠሩ ናቸው።
ይህ የዲፕሎማሲ አሠራር በሀገሮች ወይም በዓለም አቀፍ ተዋናዮች መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለማሳካት የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ትንተና እና የፈጠራ ቴክኒኮችን በመጠቀም የሚከናወን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው፡፡ በዲጂታል ዘመን ውስጥ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን እና የዲፕሎማሲ ሂደቶችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው።
ዘመኑ የዋጀውን ዲጂታል መሣሪያዎችን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እና የኢንፎርሜሽን እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን (ICTs) በመጠቀም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይትን እና መድረኮችን ለማከናወን ያግዛል። እነዚህ መሣሪያዎች ዲፕሎማቶች ከብዙ ታዳሚዎች ጋር እንዲገናኙ፣ መረጃን በብቃት እንዲለዋወጡ እና ለዓለም አቀፍ ክስተቶች በቅጽበት ምላሽ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።
ውስብስብ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ባህላዊ ዲፕሎማሲያዊ አቀራረቦች ሁልጊዜ በቂ ባለመሆናቸው ስማርት ዲፕሎማሲ ክፍተቶችን ይሞላል። በዘመናዊው ዓለም የዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ውጤታማነትና ቅልጥፍና በማምጣት ዓላማን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ይህ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በአግባቡ መጠቀምን ይጠይቃል። በመሆኑም ዲፕሎማቶች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስንና ሌሎች ተዛማጅ ቴክኖሎጂዎች ላይ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ የስማርት ዲፕሎማሲ ሥራ ለማከናወን ያስችላቸዋል፡፡
ዲፕሎማቶች ስማርት ዲፕሎማሲን በመጠቀም የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ይችላሉ፡፡ የውጭ ፖሊሲ ውይይቶች ላይ ከዜጎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት፣ መረጃን ለመሰብሰብ እና ለመተንተን፣ አዝማሚያዎችን ለመለየት እና በመረጃ የተደገፈ የፖሊሲ ውሳኔ ለመስጠት ይረዳል።
አዳዲስ አቀራረቦችን በማበረታታት እና ከተለያዩ መንግሥታት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተዋናዮች፣ የግሉሴክተር እና አካዳሚዎች ጋር በመመካከር ብሔራዊ ተግዳሮቶችን፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን እና ፈጣን ምላሽ ዘዴዎችን በመጠቀም ቀውሶችን በብቃት ለመቆጣጠር እና ተጽዕኖአቸውን ለማቃለል ያግዛል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና የባህል ልውውጥ በማድረግ፣ የዲጂታል ዘመቻዎች በመጠቀም የሀገርን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ እና ዓለምአቀፍ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ ዓለምአቀፍ የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በባለ ብዙ ወገን ድርጅቶች እና መድረኮችን ለመጠቀም፣ ከዲያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር ተናቦ ለመሥራት ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
ስማርት ዲፕሎማሲ ለሁለትዮሽና ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥራ ያገለግላል። ስማርት ዲፕሎማሲ እንደሽብርተኝነት፣የሳይበርደህንነት፣ የሕዝብ ጤና እና ስደትን የመሳሰሉ ተሻጋሪ ችግሮችን ለመፍታትና በሀገሮች መካከል ትብብር ለመመስረት፤ ለዲፕሎማቶች ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል።
ዲፕሎማቶች በቴክኖሎጂ የተካኑ ከሆኑ በተለያዩ የዓለማችን ጫፍ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን በፍጥነት እንዲያገኙ፤ ከሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን መልካም ወይም ጎጂ ሁኔታዎችን ለመረዳትና ለመተንተን ያግዛቸዋል። የዲፕሎማቶችን ብቃት ለማሳደግ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ዙርያ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል። ስማርት ዲፕሎማሲ ዲፕሎማቶች የተወሳሰቡ ዲፕሎማሲያዊ ተግዳሮቶችን በብቃት እንዲወጡ ያስችላቸዋል። እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያን፣ ብሎጎችን፣ እና ሌሎች ዲጂታል መድረኮችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያግዛቸዋል።
መረጃዎችን በመሰብሰብ እና ትንታኔዎችን በማከናወን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን የተሳኩ ያደርጋል። ተዛማጅ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመተንተን፣ ዲፕሎማቶች ስለአዝማሚያዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አቋሞች፣ አስተያየቶች እና ሊኖሩ ስለሚችሉ አደጋዎች ወይም ዕድሎች ግንዛቤዎችን ማግኘት ይችላሉ።
ዛሬ እርስ በርስ በተሳሰረ ዓለም ውስጥ ቀውሶች ሊፈጠሩ እና በፍጥነት ሊዛመቱ ይችላሉ። ስማርት ዲፕሎማሲ ለሚከሰቱ ቀውሶች ፈጣን እና ውጤታማ ምላሾች ለመስጠት ያግዛል። እነዚህን ክስተቶች በቅጽበት መከታተል፣ ዲጂታል መድረኮችን ለፈጣን ግንኙነት መጠቀምን እና ቀውሶችን በወቅቱ ለመፍታት ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር መተባበርን ይጠይቃል።
የባህል ግንዛቤን በማስፋት ገር ኃይል (soft power) በሌሎች ሀገራት ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የሀገርን ባህላዊ ቅርስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ (ቨርቹዋል) ማሳየት፣ የባህል ልውውጥን ማስተዋወቅ እና የባህል ትብብርን መፍጠር ያስችላል። በአጠቃላይ ስማርት ዲፕሎማሲ ባህላዊ ዲፕሎማሲያዊ ልማዶችን ከዲጂታል ዘመን ጋር ለማጣጣም፣ ቴክኖሎጂን እና አዳዲስ አቀራረቦችን በመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ ውጤታማነትን ለማጎልበት፣ ሰፊ ሕዝብን ለመድረስ እና ተግዳሮቶችን በቀልጣፋ እና ምላሽ ሰጪ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያግዛል።
የተለያዩ ፌስቲቫሎች ለማዘጋጀትና ለበርካታ ሰዎች ተደራሽ በመሆን እና የባህል ልውውጥን በማድረግ የሀገርን ገፅታ ለማሳደግ ያግዛል። የባህል ቅርሶችን ለማስተዋወቅና ግንዛቤን በማሳደግ ቱሪስቶችን ለመሳብ፤ የሀገራችንን የባህል ቅርሶች ለማሳየት፣ የገር ኃይሏን መጠቀምና ማሳደግ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላታል።
የዲያስፖራ ማኅበረሰቦች እውቀትና ተሞክሮ በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል። ለዚህም ሥራ ከዲያስፖራዎች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የማሰባሰብ፣ የመተንተን፣ ለሀገራቸው ሊያበረክቱ የሚችሉትን ጉዳዮች ለመለየት፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለመወያየት፣ አቅምንና ችሎታን ለማስተባበር ያግዛል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማሳደግ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና ዲያስፖራዎች የባህል አምባሳደሮች ሆነው እንዲያገለግሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ስማርት ዲፕሎማሲ በሳይበር ተፅእኖ እና ተግዳሮቶች አሉበት። ዲፕሎማቶች በዲጂታል መድረኮች ሲጠቀሙ የመረጃ ደህንነት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው። በዲጂታል ዘመን የሳይበር ደህንነት እና የኢንተርኔት አስተዳደር ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ሆነዋል። ስማርት ዲፕሎማሲ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስበት ጥንቃቄን ይሻል፡፡ የመረጃ ጥበቃና የሳይበር ወንጀል መከላከል ከስማርት ዲፕሎማሲ ጋር ጎን ለጎን አብረው መሄድ አለባቸው፡፡
ስማርት ዲፕሎማሲ ምስጢራዊነት ያለው መረጃን ለመጠበቅ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ ዲጂታል የመገናኛ መስመሮችን እና የሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዙ ስጋቶችን ለመፍታት ጠንካራ ፖሊሲዎችን፤ የሕግና ደንብ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ይጠይቃል። በዲፕሎማቶች ላይ ያለ እምነትን ሊያሳጡ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሊያበላሹ የሚችሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን መከላከል አስፈላጊ ነው። ስማርት ዲፕሎማሲ ሲከናወን የሀሰት መረጃን እና የሳይበርን ተፅእኖን የመከላከል እና የመቀነስ ስልቶችን መጠቀም ይጠይቃል።
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስማርት ዲፕሎማሲ ለሚከተሉት ዋና ዋና ተግባራት አጋዥ ይሆናል፡፡ እነዚህም
• የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለመለየት፣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሳደግ ያግዛል። በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ያግዛል። የኢንቨስትመንት መድረኮችን እና ኮንፈረንሶችን ማደራጀት እና የተሳለጠ ሂደቶችን ለማከናወን ያስችላል፣
• የኢትዮጵያን የንግድ ግንኙነት ለማስፋፋትና ለወጪ ንግዷ ምቹ የገበያ ተደራሽነት እንዲኖር ያስችላል። ኢትዮጵያ ምርቶቿንና አገልግሎቶቿን ወደ ውጭ ሀገራት ማስተዋወቅ እና ወደ ዓለምአቀፍ ገበያዎች በስፋት ለመግባት ያግዛታል፣
• ስማርት ዲፕሎማሲ ውጤታማ የቀውስ አስተዳደር (Crisis Management) ለማከናወን ያግዛል። እንደተፈጥሮ አደጋዎች፣ ግጭቶች ወይም ወረርሽኞች በተከሰቱ ጊዜ፣ ዲፕሎማቶች ሕዝቡን ለማሳወቅ፣ መመሪያ ለመስጠት እና የዓለምአቀፍ ምላሽ ጥረቶችን ለማስተባበር በፍጥነት እና በትክክል ለመገናኘት ያግዛል፡፡ ለተጎዱ ሕዝቦች እርዳታ ከዓለምአቀፍ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች ተዋናዮች ጋር ሰብአዊ ምላሾችን ለማስተባበር እና የተጋላጭ ሕዝቦችን ችግር በመቅረፍ ሰብአዊ ቀውሶችን ለመፍታት ያግዛል፣
• ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ትብብርን በማመቻቸት፣ እውቀትን በመለዋወጥ እና ሀብትን በማሰባሰብ የዲፕሎማሲውን ሚና የአየር ንብረት ዲፕሎማሲን ለማከናወን ያግዛል፣
• በፀረ-ሽብርተኝነት ትብብር፣ መረጃ መጋራት እና በክልል የጸጥታ ተግባራት ለማከናወን ያስችላል። ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የጸጥታ መዋቅሯን ማጠናከር፣ የድንበር ደህንነትን ማጎልበት እና ለቀጣናው መረጋጋት አስተዋፅዖ ማድረግ ያስችላታል፣
• በአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚያዊ ውህደት፣ መሠረተልማት ዝርጋታ እና የጋራ የጸጥታ ጥረቶች ባሉ ውጥኖች ክልላዊ ትብብርን ለማጠናከር ያስችላል። ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የገንዘብ ድጋፍን፣ቴክኒካል እውቀትን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ማግኘት ያስችላል፣
• የዲፕሎማቲክ መንገዶችን በመጠቀም ኢትዮጵያ አዳዲስ የካፒታል ምንጮችን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማመቻቸት ለኢኮኖሚ እድገትና ልማት አስተዋፅዖ ማድረግ ያስችላታል፣
• ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዲያስፖራ ማኅበረሰብ በውጭ ሀገር አሏት። ስማርት ዲፕሎማሲ የዲያስፖራ ተሳትፎን እምቅ አቅም በመጠቀም፣ የእውቀት ሽግግርን እና የባህል ልውውጥን ለማስተዋወቅ ያስችላል፣
• ኢትዮጵያ የበለጸገ የባህል ቅርስ እና ልዩ የቱሪስት መስህቦች አሏት። ስማርት ዲፕሎማሲ በባህልና ቱሪዝም ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት በማድረግ የኢትዮጵያን ዓለምአቀፋዊ ገጽታ ለማሳደግ እና ዓለምአቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ ያስችላል። እንዲሁም የባህል ዲፕሎማሲ ውጥኖችን፣ የኢትዮጵያን የባህል ብዝሃነት፣ጥበብና ወግ በማሳየት፤ የቅርስ ቦታዎች እና የቱሪዝም መስህቦችን በምናብ (ቨርቹዋል) ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅና ጎብኚዎችን ከተለያዩ ዓለማት ለመሳብ ያስችላል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ስማርት ዲፕሎማሲ በመጠቀም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማሳደግ፤ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ልማት አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ አጋርነቶችን ለመፍጠር ያስችላታል።
ለማጠቃለል ያህል ስማርት ዲፕሎማሲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በዲፕሎማሲ ውስጥ ያለውን ሚና አጉልቶ ይጠቀማል። እንዲሁም በዲጂታል ዘመን የሚቀርቡትን ዕድሎችን፤ የጋራ እውቀትን እና ሀብቶችን በመጠቀም ሀገራዊ፤ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ያግዛል። ስማርት ዲፕሎማሲ በፍጥነት በመለዋወጥ ላይ ባለው ዓለምአቀፍ ሁኔታ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር ያግዛል።
ከተለምዷዊ ዲፕሎማሲያዊ መስመሮች ባለፈ ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር መቀራረብን ይጠይቃል። ይህም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከአካዳሚክ፣ ከአሰላሳይ ተቋማት (think tank) እና ከግል ድርጅቶችና ወዘተ ጋር መተባበርን ይጨምራል። ብዙ ተዋናዮችን በማሳተፍ ስማርት ዲፕሎማሲ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን በትብብር መንገድ ለመፍታት ያስችላል።
ለዚህ ሁሉ መሠረት የሚሆነው ከዲፕሎማሲ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መጠነ ሰፊ ዳታ(Big Data) ማደራጀት፤ የዳታ ትንታኔ የማከናወን፤ አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን የማሟላት፤ የዲፕሎማቶችን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም የማጎልበት ተግባራትን ማከናወን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
መላኩ ሙሉዓለም ቀ.
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ
melakumulu@yahoo.com
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም