የስፖርት ታሪክ አዋቂው ስንብት

ተወዳጁ የስፖርት ጋዜጠኛ፣ ጸሐፊ እና የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ገነነ መኩሪያ ‹‹ሊብሮ›› የቀብር ሥነሥርዓት ዛሬ በ9፡00 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡

መጋቢት 5 ቀን 1957 ዓ.ም በይርጋለም ከተማ የተወለደው ገነነ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በሻሸመኔ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት አጼ ናዖድ ትምህርት ቤት ለስፖርትና ጋዜጠኝነት መሠረት የጣለ ሲሆን፤ የእግር ኳስ ችሎታውን በማዳበርም የተለያዩ ቡድኖችን ተቀላቅሏል፡፡

ከተግባረ ዕድ በጄነራል መካኒክነት ከተመረቀ በኋላም ለሜታ ቢራ እግር ኳስ ቡድን እየተጫወተ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይጽፍ ነበር። በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑም እስካሁንም የሚታወቅበትን ‹‹ሊብሮ›› የሚል ቅጽል ስም አትርፏል፡፡

ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ከተሰናበተ በኋላ ያሉትን ሦስት አስርት ዓመታት ደግሞ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በስፖርት ጋዜጠኝነት ሠርቷል፡፡ የሊብሮ ጋዜጣ ባለቤት የሆነው ገነነ በተለይ በቴሌቪዥን በሚያቀርባቸውና ታሪክን በሚያወሱ ዝግጅቶች ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡

የኢትዮጵያን ስፖርት ጠንቅቆ በማወቅና በታሪክ አዋቂነቱ በበርካቶች ዘንድ ‹‹ተንቀሳቃሽ ቤተመጻሕፍት›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ ኢህአፓ እና ስፖርት (ከ1 እስከ 3)፣ ፍትሃዊ የጠጅ ክፍፍል፣ ሊብሮ ኢትዮጵያዊ ስልጠና፣ መኩሪያ፣ … የተባሉ መጻሕፍትን ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡ ለእግር ኳሱ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦም በአዲስ አበባ በተካሄደው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አገልግሎት ሜዳይ ተበርክቶለታል።

ባለ ትርዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው፣ ተወዳጁ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ጋዜጠኛ እና ጸሐፊ ገነነ መኩሪያ ‹‹ሊብሮ›› ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥር 14/2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የቀብር ሥነሥርዓቱም ዛሬ በ9፡00 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You