«በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ገነት ትምህርት ቤት አይዘጋም፤ ለማንም አይሰጥም» ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) -የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ፍረዱኝ በተሰኘው አምዱ ታኅሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም «ያለ ካርታ 52 ዓመታትን የዘለቀው የገነት አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት» በሚል ርዕስ አንድ የምርመራ ዘገባ ለሕዝብ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዘገባ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ቀሪ የምርመራ ዘገባዎች እንደሚኖሩ እና ቀጣይ በሚኖሩን ዝግጅቶች ከጉዳዩ ጋር የሚገናኙ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ግለሰቦችን ይዘን እንደምንቀርብ ገልጸን ነበር፡፡

በዚህ መሠረት በዛሬው ዘገባችን ተፈጠረ ስለተባለው ችግር በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 የተማሪ እና ወላጅ ኅብረት ሰብሳቢ፣ የአዲስ አባበ ትምህርት ቢሮ ኃላፊን፣ የፌዴራል ኪራይ ቤቶች ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና በፌዴራል ቤቶች ቅርንጫፍ አራት ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችን ምን ያውቃሉ ስንል ጠይቀናል?

ወረዳ 6 የተማሪ እና ወላጅ ኅብረት ሰብሳቢ ምላሽ

አቶ ወንድወሰን ፍታሌ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የተማሪ እና ወላጅ ኅብረት ሰብሳቢ ናቸው። ስለትምህርት ቤቱ ምን እንደሚያውቁ ጠይቀናቸው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

ትምህርት ቤቱ በቀድሞ ከፍተኛ 13 ቀበሌ 03 ሥር የነበረ ሲሆን የ47/67 አዋጅ በታወጅ ጊዜ በመንግሥት ተወርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ቤቱ ሲወረስ ኪቤአድ የሚባለው ተቋም እንደሀገር አልተመሠረተም ነበር፡፡ በአዋጅ 47/67 ቤቱ ሲወረስ ያልነበረ ተቋም እንዴት አድርጎ ቤቱን ሊያገኝ ቻለ? ሲሉ ይጠይቃሉ።

እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ፤ የ47/67 አዋጅ ሲታወጅ ከገነት አጻደ ሕፃናት ጋር የሚመሳሰል “ኬዝ” የነበረባቸው ትምህርት ቤቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አጼ ናኦድ፣ በላይ ዘለቀ፣ አፍሪካ ኅብረት እና ሌሎችም። እነዚህ ትምህርት ቤቶች በአዋጁ ከተወረሱ በኋላ የሕዝብ ትምህርት ቤት የነበሩ ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም በወጣው መመሪያ ወደ መንግሥት የዞሩበት አግባብም ከገነት ትምህርት ቤት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች አንድም ቀን ኪራይ ክፈሉ ተብለው አያውቁም፡፡ ገነት ትምህርት ቤት ግን ተለይቶ ኪራይ እንዲከፍል የሚጠየቅበት አግባብ ትክክል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

ቤቶች ኮርፖሬሽን የገነት ትምህርት ቤትን ከወይዘሮ ትዝታ ዳንኤል ወረስኩት ያለው ትክክል አይመስለኝም ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ ምክንያቱም ተወረሰ የተባለው የወይዘሮ ትዝታ ቤት ይገኛል የተባለው በቀድሞ መጠሪያው መሐል ከተማ ወረዳ 09 ነው፡፡ ነገር ግን ገነት ትምህርት ቤት ይገኝ የነበረው በከፍተኛ 13 ቀበሌ 3 ነው፡፡ ከፍተኛ 13 እና መሀል ከተማ ደግሞ መገኛቸው የተለያየ ነው። ስለዚህ ቤቶች ኮርፖሬሽን የእኔ ነው የሚለው ትምህርት ቤት የገነት ትምህርት ቤት ሳይሆን የሌላ ትምህርት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

ተወልጄ ያደግኩት ገነት ትምህርት ቤት አካባቢ ነው የሚሉት አቶ ወንድወሰን፤ የገነት ትምህርት ቤትን ቀበሌ 03 በጽሕፈት ቤትነት ሲጠቀምበት አይተው እንደማያውቁ እና ከመወረሱ በፊት እና በኋላም የትምህርት ቤት አገልግሎት ብቻ ሲሰጥ እንደሚያውቁት ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በ1973 ዓ.ም የቤቶች ኮርፖሬሽን ለቀበሌ 03 አከራይቶት እንደነበር የሚያትተው ሰነድ ፈጽሞ ስህተት መሆኑን ይገልጻሉ፡ ምናልባትም ሰነዱ ስለገነት ትምህርት ቤት ሳይሆን ስለሌላ ቦታ የሚናገር ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ምላሽ

ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ ያቀረቡት መምህራን እና ወላጆች እንደሚሉት የገነት ትምህርት ቤት ለ52 አመታት ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ሆኖ ቢቀጥልም የራሱ የሆነ ካርታ የለውም፡፡ በተጨማሪም በ2004 ዓ.ም የፌዴራል ቤቶች ካርታ አውጥቶበታል፡፡ ይህም ከጊዜ በኋላ ባለይዞታው ጥያቄ አቅርቦ ትምህርት ቤቱን ወደ አለመኖር ሊያመጣው ይችላል የሚል ስጋት አለባቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ይላሉ? ስንል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊን ዶክተር ዘላለም ሙላቱን ጠይቀን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አሁን ላይ ስለገነት ትምህርት ቤት ለማውራት ጊዜው ገና ነው፡፡ ጉዳዩ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም እንደ ችግር አልተነሳለትም፡፡ ችግር ሆኖ እንኳን ቢገኝ ብዙ መፍትሔዎች አሉት፡፡ እስከዛሬ ድረስ ትምህርት ቤቱም ለቤቶች ኮርፖሬሽን ኪራይ ከፍሎ እንደማያውቅ እና እንዳልከፈለ አመላክተዋል። የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጉዳዩን በሕግ ይዞ ቢሮውን እንዳልጠየቀ ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ባከናወቸው እና እያከናወናቸው ባሉት ተግባራት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሞዴል ተብሎ የተመረጠ መሆኑን የሚያስረዱት ኃላፊው፣ በዚህም በተማሪዎች እና በወላጆች በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ። በትምህርት ቢሮውም ለትምህርት ቤቱ ካለው ደረጃ አንጻር ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

ከካርታ ጋር ተያይዞ በትምህርት ቤቱ ላይ ካርታ ያወጣ አካል እንደሌለ ለዝግጅት ክፍሉ አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የዝግጅት ክፍሉ በትምህርት ቤቱ ካርታ እንደወጣበት እና ለዚህም ማስረጃዎች እንዳሉ በተገለጸላቸው ጊዜ ምንም እንኳን ፌዴራል ቤቶች ካርታ ቢያወጣበትም ሁለቱም የመንግሥት ተቋማት ስለሆኑ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፍርድ ቤቱ ለቤቶች ኮርፖሬሽን ቢፈርድ እንኳን ጉዳዩን በድርድር መፍታት እንደሚቻል የሚናገሩት ዶክተር ሙላቱ፤ ትምህርት ቤቱን የቤቶች ኮርፖሬሽን ይወሰድ ቢባል እንኳን ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ አማራጮች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡ ከወረዳ 06 ቦታ ይፈለግና ገነት ትምህርት ቤትን በሌላ ቦታ እንገንባው፤ አማራጭ ቦታ ለፌዴራል ቤቶች እንስጣቸው ወዘተ የሚሉትን መሰል አማራጮች መኖራቸውን ተናግረው፤ አሁን ላይ ግን ጥያቄው እስኪነሳ መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ያለው አንድ እና ብቸኛዋ የአጸደ ሕፃናት የገነት አጸደ ሕፃናት በመሆኑ በየዓመቱ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ገነት አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ ሲጋፉ እና ሲጎርፉ ይታያል። በመሆኑም ይሄን ለወረዳው ብቸኛ ትምህርት ቤት ለሌላ ተቋም አሳልፎ መስጠት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለተጨማሪ ጉዳት እና እንግልት መዳረግ አይሆንም? ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው «በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ገነት ትምህርት ቤት አይዘጋም፤ ለማንም አይሰጥም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ የተያዘው በሸማቾች ቢሆን እንዳይሸጠው ስጋት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን የተያዘው በመንግሥት ተቋም በመሆኑ ሊዘጋ ይችላል ከሚል እሳቤ የራቀ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሸማች በሚስተዳድራቸው 28 በሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ላይ ጥናት ማስጠናታቸውን ተናግረው፤ አፈጻጸማቸው ጥሩ ባለመሆኑ ትምህርት ቤቶችን ከሸማቾች ወደ መንግሥት ለማስቀየር ለከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በማሳወቅ ውሳኔ እየጠበቁ እንደሚገኝ ተናግረዋል። «ይሁን እንጂ የገነት ትምህርት ቤት ጋር በተያያዘ ከወላጆች የቀረበው ስጋት “ፕሪ ማቹርድ” ነው» ሲሉ መልሰዋል፡፡

አያይዘውም የዝግጅት ክፍላችን ስጋት እንደሚረዱት በመናገር፤ «ገነት የትም አይሄድም፤ ገነት አይዘጋም» ሲሉ ገልጸው፤ ይሁን እንጂ ባለይዞታ ነኝ የሚለው አካል ገና ጥያቄውን ሳያነሳ ይሄንን ነገር ወደ ሚዲያ ማምጣቱ በሁለቱ ተቋማት በኩል የሚኖረውን ግንኙነት ሊያሻክር እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቢሮው ለትምህርት ቤቱ ወጪ በማውጣት የተሻለ ትምህርት እንዲሰጥ ለማስቻል የተለያዩ ተግባራትን እየከወነ ሲሆን በዚህም እስካሁን ባለይዞታ የሆነው የፌዴራል ቤቶች ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ አሰምቶ እንደማያውቅ አመላክተዋል፡፡

ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ሊቀርብና አስረክቡ ሊባል ይቅርና በጥያቄ መልክ እንኳን ለትምህርት ቢሮ አለመድረሱን ተናግረው፤ ነገር ግን የሆነ ቡድን ፍላጎት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡ ምናልባት በትምህርት ቤቱ ዙሪያ የሚገኙ መጠጥ ቤቶች ከኪራይ ቤቶች ሰዎች ጋር በመሆን አንዳንድ ሙከራዎችን አድርገው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ብዙ ርቀት አልሄዱበትም። ምክንያቱም የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ገነት የሚባል ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ግን ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምላሽ

ወይዘሮ አጸዱ ረጋሳ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው።  የዝግጅት ክፍሉ ስለጉዳዩ ምን ያውቃሉ ሲል ጠይቆ ዳይሬክተሯ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በአዋጅ 47/67 ከተወረሰበት ጊዜ ጀምሮ ቤቱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሲያስተዳድረው የቆየ ነው። በአዋጅ 47/67 የተወረሰ ቤት ስለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ከማስረጃዎች መካከል እንደማሳያ አንድ ቤት ሲወረስ የሚሞላ ቅጽ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ቅጽ ከማን ተወረሰ ከሚለው በደንብ የሚገልጽ ነው፡፡

ቤቱ የተወረሰው ወይዘሮ ትዝታ ዳንኤል ከሚባሉ ግለሰብ ነው፡፡ ወይዘሮ ትዝታ ትምህርት ቤቱን ከአባታቸው ከአቶ ዳንኤል የወረሱት ነበር። ነገር ግን ቤቱን ያከራዩት ስለነበር በትርፍ ቤትነት መንግሥት በአዋጅ 47/67 ወረሰው፡፡ ትምህርት ቤቱ የመንግሥት ስለነበር በወቅቱ አጠራር ኪቤአድ (የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ) ይባል ለነበረው በአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲሰጥ ሆነ፡፡

ከግለሰቧ ወደ መንግሥት የተወረሰበት 004 ቅጽ በእጃቸው መኖሩን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ቅጽ 004 አንድ ግለሰብ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሚያከራየው ቤት ካለ የሚፈልገውን ቤት አስቀርቶ ቀሪውን ለመንግሥት የሚያስረክብበት ማማረጫ ቅጽ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ቅጽ 003 ደግሞ መውረሻ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ቅጽ 004 ማማረጫ ከሆነ ሌላኛው ወይዘሮ ትዝታ ቤት የት ይገኛል? ቁጥሩስ ስንት ነው? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ዳይሬክተሯ፤ ወይዘሮ ትዝታ መርጠው ያስቀሩበት ቤት የት ክፍለ ከተማ እና ቁጥሩ ስንት እንደሆነ እንደማያውቁ ይናገራሉ። «ወይዘሮ ትዝታ ስለመረጡት ቤት ማስረጃ የሚገኘው ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ነው» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ወይዘሮ ትዝታ ትርፍ ቤት የላቸውም ግን የወረሱትን ቤት ያከራዩ ነበር፡፡ ስለዚህ የሚከራየው ቤት ደግሞ ትምህርት ቤት ስለነበር ለአከራይዋ ምትክ ቤት ተሰጥቷቸው ይህ ቤት ተወርሷል፡፡ አንድ ሰው በስሙ የተመዘገበ ትርፍ ቤት ሳይኖረው ቤቱን ስለአከራየ ብቻ እንዴት ሊወረስ ይችላል? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ዳይሬክተሯ፤ «አዋጁ ላይ በተገለጸው መሠረት ግለሰብ ቤት ማከራየት አይችልም፡፡ ስለሆነም ተወርሷል፡፡» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአዋጅ ከተወረሰ በኋላ ከትምህርት ቤቱ ጋር የነበራችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ትምህርት ቤቱ ላይ የእናንተ ሚና ምን ነበር? ተብለው የተጠቁት ዳይሬክተሯ፤ ትምህርት ቤቱ ኪራይ ለመክፈል ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህን ተከትሎ በ1973 ዓ.ም ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ደብዳቤ ተጽፎላቸው ነበር፡፡ የቤቱ ኪራይ ግምት በወር 255 ብር እንዲከፍሉ የሚል ነው። ይሁን እንጂ በዚያ ደብዳቤ መሠረት ኪራይ ሊከፍሉ አልቻሉም፡፡

ትምህርት ቤቱ ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ የኪራይ ውል እንዲዋዋል የተጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ሳይዋዋል እየኖረበት ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የመንግሥት ስለሆነ ኪራይ እንዲከፍሉ ለማስገደድ በኮርፖሬሽኑ ብዙም ተገፍቶ አልተሄደበትም። ለዚህም እንደ ምክንያቱም ያነሱት ተማሪዎችን የሚያስተምር እና ማኅበራዊ አገልግሎት እየሰጠ ያለን ተቋም ኪራይ አልከፈልክም ብሎ ተማሪ በትኑ ማለት ተገቢ አለመሆኑን ነው። ለተከራየው ቤት ኪራይ አልከፍልም ያለው ግለሰብ ቢሆን ኖሮ ከቤቱ እንዲወጣ ይገደድ እንደነበር አመላክተዋል።

«ሕግ እና መመሪያን እስካልተከተለ ድረስ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ቢሆንስ ለምን  አይጠየቅም?» ተብለው የተጠየቁት ወይዘሮ አጸዱ፤ በቤቱ አንድ ሰው ብቻ አይደለም የሚኖረው፤ ትምህርት ቤት ነው ፣ ትውልድ ነው እየተገነባበት ያለው፡፡ ሕግ ሕግ ነው ብለን መንግሥት ያገኘው የነበረውን ኪራይ ስላላገኘ ብቻ ትምህርት ቤቱ አይበትንም፡፡ እስካሁን ድረስ የቤቶች ኮርፖሬሽን ነገሩን አለሳልሶ ለማለፍ የሞከረው በዚሁ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እንደዳይሬክተሯ ገለጻ፤ የቤቶች ኮርፖሬሽን በ2011ዓ.ም የኪራይ ተመን ማሻሻያ ባደረገበት ወቅት ኪራይ እንዲከፍል ለትምህርት ቤቱ ደብዳቤ ጽፎ ቢጠይቅም ኪራይ ሊከፍሉ ፈቃደኛ አልነበሩም። ይህን ተከትሎ ኪራይ የማይከፍሉ ተቋማት እና ድርጅቶችን ዝርዝር አዘጋጅተው ለአራዳ ክፍለ ከተማ እና ለአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ አሳውቋል። ከአሳወቃቸው መካከል የገነት አጸደ ሕፃናት አንዱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ነገር ግን ሕግ እና መመሪያ ስለሚድግፋቸው ብቻ ትምህርት ቤቱ እንዲበተን አለማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ እስከዛሬ ድረስ ከትምህርት ቤቱ ጋር የአከራይ እና ተከራይ ውል የላችሁም? ተብለው የተጠየቁት ወይዘሮ አጸዱ፤ ከትምህርት ቤቱ ጋር የአከራይ እና ተከራይ ውል እንዳላቸው ገልጸዋል። በ2004 ዓ.ም ከትምህርት ቤቱ ጋር የአከራይ እና ተከራይ ውል መዋዋላቸውን ያስረዳሉ፡፡ ሰነድም አቅርበዋል። ለዝግጅት ክፍላችን የቀረበው ሰነድ የሚያመላከተው ግን የኪራይ ውሉ ከትምህርት ቤቱ ጋር ሳይሆን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11/12 ወከለዋል በተባሉ ከአቶ አበበ የኔታ ጋር መሆኑን ማየት ችሏል፡፡

ለወይዘሮ አጸዱ ከተነሳላቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል እንደ ተቋም ካርታ ባላወጣችሁበት ቤት የምትዋዋሉብት አሠራር እና መመሪያ አለ? የሚል ነበር። «ከዚህ ቀደም በርካታ ቤቶች ካርታቸው የጠፋባቸው እና ካርታ የሌላቸው ነበሩ፡፡ በመሆኑም ቤቶች ካርታ ሳይኖራቸው ሊከራዩ የሚችሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን የኮርፖሬሽኑ ቤቶች መቶ በመቶ ካርታ ያላቸው በመሆኑ ካርታ ሳይኖራቸው አይከራዩም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ቤቶች ኮርፖሬሽን ውዝግብ በተነሰባት ቤት ካርታ ያወጣው ሐምሌ 2004 ዓ.ም ነው። ከአቶ አበበ የኔታ ጋር የኪራይ ውል የተዋዋሉት ደግሞ ካርታ ከማግኘታቸው ቀደም ብሎ መሆኑን የመልካም አስተዳደርና ሥነ ምግባር ዝግጅት ክፍል ካገኛቸው የሰነድ ማስረጃዎች አረጋግጧል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ቤቱ የራሱ ከሆነ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ ለምን ውል አልተዋዋለም? ተብለው የተጠየቁት ወይዘሮ አጸዱ «ትምህርት ቤቱ ንብረቱ የእሱ ከሆነ ለምን በፍርድ ቤት ሄዶ ንብረቱን አያስመልስም ?» ሲሉ ጥያቄን በጥያቄ መልሰዋል፡፡

በ2004 ዓ.ም የኪራይ ውል የተዋዋሉት አቶ አበበ የኔታ በክፍለ ከተማው የነበራቸውን የሥራ ኃላፊነታቸው በውል ሰነዱ ላይ ስላልተገለጸ የአቶ አበበን የሥራ ኃላፊነት እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ ካርታ ሲወጣ የሲአይኤስ እና የጂአይኤስ ማስረጃዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ቤቱ የቤቶች ኮርፖሬሽን ስለመሆኑ የሲአይ ኤስ ማስረጃ ክፍለ ከተማ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፤ ነገር ግን የሲአይኤስ ማስረጃው በተቋማቸው መኖር እና አለመኖሩን እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ ቦታዎች የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከአዋጅ 47/67 በኋላ በተጠቀሰው ቤት ትምህርት ቤቱ የተለያዩ ግንባታዎችን አካሂዷል፡፡ ይህ ሲሆን እንናተ አልተቃወማችሁም። ወይስ ፈቅዳችሁ ነው ቤቶች የተገነቡት? ለምሳሌ በመስከረም ወር 1997 ዓ.ም በተጠቀሰው ቦታ ላይ በርካታ ቤቶች ተሠርተዋል። አሁንም ቤቶቹ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። እንደዚህ ዓይነት ግንባታዎች ሲካሄዱ ቤቶች ኮርፖሬሽን እንደባለቤት ምን ዓይነት እርምጃዎችን ወሰደ? ተብለው የተጠቁት ዳይሬክተሯ «ስለጉዳዩ መረጃ የለኝም፡፡ እንደዚህ ነው ብዬ መግለጽ አልችልም፡፡» ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቤቶች ሲሠሩ የግንባታ ፈቃድ ከክፍለ ከተማ ወይም ከወረዳ ተሰጥቷቸው ነው የሚገነቡት፡፡ የሲአይ ኤስ መረጃ የእናንተ መሆኑን የሚያሳይ ከሆነ እንዴት በሰው ይዞታ የግንባታ ፈቃድ ሊሰጥ ቻለ? ተብለው በዝግጅት ክፍሉ የተጠቁት ዳይሬክተሯ «ይህንን ክፍለ ከተማ ነው መጠየቅ ያለባችሁ፡፡ እኛ በይዞታችን ላይ የተጨማሪ ግንባታ አንፈቅድም። በቦታው ላይ ተጨማሪ ግንባታ ተካሂዶ ከሆነ የሚጠየቀው ከተማ አስተዳደሩ ነው፡፡ የእኛ ተቋም አዲስ የግንባታ የሚፈቅድ ሳይሆን የነበረን ማደስ በተመለከተ ነው ሥልጣን ያለው ፡፡» ሲሉ መልሰዋል፡፡ በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ሲወረስ የቤቶች ብዛት ስንት እንደነበር እንደማያውቁ የሚገልጹት ዳይሬክተሯ፤ የተወረሱ ቤቶችን ቁጥር ከተወረሰበት ቅጽ ላይ ማግኘት እንደሚቻል አመላከተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ካርታ ለማሠራት እና መብት ለማስፈጠር በሚንቀሳቀስበት ወቅት ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ በስሙ የተመዘገበ የመብራት መሠረተ ልማት፣ ሌሎች የግብር ክፍያዎች መኖራቸውን ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እናንተስ በቤቱ የተመዘገበ የመብራት እና የውሃ መሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ማስረጃዎች አሏችሁ? የአፈር ግብርስ ትከፍሉ ነበር? ተብለው አስተያየታቸውን የተጠየቁት ወይዘሮ አጸዱ፤ ትምህርት ቤቱ የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአዋጅ 47/67 አልተወረሰም ማለት ግን አይደለም። የውሃ እና የመብራት አገልግሎት የቤት ባለቤትነት መብት ሊያሰጥ እንደማይችልም ጠቁመዋል፡፡

ቤቶች ኮርፖሬሽን በ2004 ዓ.ም ካርታ ሲያሠራ በሰነድ አልባ መብት ተፈጥሮለት አይደለም በአዋጅ 47/67 በውርስ ስላገኘው ሰነድ ስላለው እንጂ ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የባለቤትነት ሰነድ ግን ለዝግጅት ክፍላችን ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጥልቅ መረጃ እንደሌላቸው እና ከካርታ ጋር በተገናኘ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቤቶች ኮርፖሬሽን ክፍሎች ስላሉ እነሱን ማነጋገር ይቻላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ወረዳ 06ን ትምህርት ቤቱን እንደሚያስተዳድረው እና እንደማያስተዳድረው ተጠይቆ ነበር፡፡ ለዚህ ምላሽ የሰጠው ወረዳ 06 «የቤት ቁጥር 1371 የገነት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቦታውን ወረዳው የማያስተዳድረው የመንግሥት ይዞታ ነው፡፡» ሲል ገልጸዋል፡፡ በዚህ ላይ የቤቶች ኮርፖሬሽን ምላሽ ምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት ዳሬክተሯ፤ በወረዳ 06 ከተሰጠው ምላሽ እንደተመላከተው የቤት ቁጥር 1371 የገነት ትምህርት ቤት ነው፤ ነገር ግን ወረዳው የማያስተዳድረው የመንግሥት ይዞታ ማለቱ ቤቱ የቤቶች ኮርፖሬሽን መሆኑን የሚጠቁም መሆኑን ዳይሬክተሯ ይናገራሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የቤት ቁጥር 1371 የገነት ትምህርት ቤት ነው፤ መሬቱን መንግሥት እንጂ ወረዳው አያስተዳድረውም ማለት እንዴት ሆኖ ነው ቤቱ ኮርፖሬሽኑ ነው የሚል ትርጉም የሚሰጠው? ተብለው የተጠየቁት ዳይሬክተሯ «እኔ የምረዳው እንደዚህ ነው!» ብለዋል፡፡

የገነት ትምህርት ቤት የሕዝብ ትምህርት ቤት የነበረ ነው፡፡ የሕዝብ ማለት ደግሞ የመንግሥት ማለት ነው በሚል የተከራከሩ ሲሆን፤ የሕዝብ ትምህርት ቤት ማለት የመንግሥት ማለት አይደለም በሚል ዝግጅት ክፍሉ ገለጻ ቢያደርግም ሊረዱት አልቻሉም፡፡ በዚህም ከ2004 ዓ.ም በፊት የሕዝብ ትምህርት ቤት የሚባሉ እንደነበሩ እና እነዚህም ትምህርት ቤቶች በመንግሥት የተቀረጸውን ሥርዓተ ትምህርት ያስተምሩ እንጂ ባለቤትነታቸው የሕዝብ እንደነበሩ መረጃው እንደሌላቸው ተረድቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው እንደ ገነት ዓይነት ትምህርት ቤቶች ይኖራሉ ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ይሁን እንጂ በቁጥር ለመግለጽ እንደሚቸገሩ አመላክተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ንብረቶች ላይ ሌላ ወገን ግብር ሊከፍልበት የሚያስችል አሠራር አለወይ? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ዳይሬክተሯ፤ «እኛ ምን አገባን እና ካርታ አለን፡፡ እኛ ካርታ ካለን በቂያችን ነው። ሌላ አካል የአፈር ግብር ሆነ የመሬት ግብር ቢገብር አይመለከተንም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የምናወራው ከሕግ እና ከመመሪያ አኳያ ነው። መመሪያ አለወይ? ተብለው ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ስለአፈር ግብር የሚገልጽ መመሪያ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ዝጅግት ክፍላችን ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ገነት ትምህርት ቤት ግንባታ ሲያከናውን ስለምን ዝም አላችሁ? ተብለው የተጠየቁት ዳይሬክተሯ፤ ስለግንባታ እንደማይመለከታቸው ተናግረዋል፡፡

የጋዜጠኞች ትዝብት

ተወረሰ የተባለው ቤት ስፋት ሁለት ሺ 380 ካሬ ሜትር ሲሆን አሁን ካርታ የተሠራበት ግን አንድ ሺ 780 ነጥብ 81 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የተወረሰው ቤት ከመሐል ከተማ ወረዳ 09 ሲሆን ውዝግብ የተነሳበት ቤት መገኛ ግን ከፍተኛ 13 ወረዳ 03 መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በመጨረሻም፡- የሰነድ ማስረጃዎችን እና ቀሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ በሚቀጥለው የምርመራ ዘገባ ክፍል ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፤ እስከዚያው ቸር እንሰንብት፡፡

ሙሉቀን ታደገ እና መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ጥር 15/2016

Recommended For You