በአስደናቂ ክስተቶች የታጀበው የአፍሪካ ዋንጫ

 ለዋንጫ ተጠባቂዋ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ኮትዲቯር ከውድድሩ በጊዜ የተሰናበተችበት፣ ታላላቅ ቡድኖች አጣብቂኝ ውስጥ የገቡበት፣ ያልታሰቡ ቡድኖች ተጠናክረው የተገኙበት፣ ጥሎ ማለፉን የሚቀላቀሉ ቡድኖችን አስቀድሞ መገመት አዳጋች የሆነበት 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በድራማዊ ክስተቶች ተሞልቶ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ገናና ስም ያላቸው አፍሪካዊ ቡድኖች እንደታሰቡት አለመሆናቸውን ተከትሎም ዋንጫ ሊያነሳ የሚችል አዲስ ቡድንን ያስተዋውቅ ይሆን የሚለውም የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል፡፡

በቀድሞ የእግር ኳስ ጀግናቸው ዲዲየር ድሮግባ እና ሕዝባቸው ፊት ከውድድሩ መሰናበታቸውን ያረጋገጡት ዝሆኖቹ፤ ባልተጠበቀ ሁኔታ በኢኳቶሪያል ጊኒ በተቆጠሩባቸው 4 ግቦች እፍረትን ተከናንበዋል፡፡ የአጀማመራቸውን እንጂ የአጨራረሳቸውን አለማማር ተከትሎም ደጋፊዎች ከስታዲየም ውጪ ያገኙትን አውቶቡስ በመሰባበር ጭምር ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ ከምድብ ጨዋታዎች አልፈው ተፎካካሪነታቸውን ማስመስከር ያልቻሉት ጋናዎች ስንብታቸውን ተከትሎ፤ ደጋፊዎቻቸው የቡድኑ አባላት ከስታዲየም ሲወጡ ጠብቀው ንዴታቸውን አንጸባርቀዋል። ለዋንጫ ተጠባቂው ሌላኛው ቡድን ካሜሮን ውጤትም በተመሳሳይ ውድድሩን ልዩ መልክ እንዲኖረው ካደረጉ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡

ከሞዛምቢክ፣ ጋና እና ኬፕቨርዴ ጋር አቻ በመለያየት በሰበሰበቻቸው ሦስት ነጥቦች ወደ ቀጣዩ ዙር መሸጋገሯን በመጨረሻ ሰዓት ያረጋገጠችው ግብጽም በውድድሩ ከአስገራሚ ቡድኖች አንዷ ናት፡፡ የበርካታ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለድሏ ግብጽ በሁለቱ ጨዋታዎች ተጨማሪ ሰዓት ያስቆጠረቻቸው ግቦች ታድገዋታል፡፡ እንደ መርፌ ቀዳዳ በጠበበው የማለፊያ ዕድል የተጠቀሙት ፈርኦኖቹ ከጋና ጋር 2 እኩል በተለያዩበት ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት ብሔራዊ ጀግናቸው ሞሃመድ ሳላህ፤ አገግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የመመለስ ዕድል እንደሌለው መሰማቱ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡

ወሳኞቹና የመጨረሻዎቹ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው የሚከናወኑ ሲሆን፤ ምድብ አምስትን በመምራት ላይ የምትገኘው ማሊ ናሚቢያን ትገጥማለች፡፡ ለማለፍ አቻ መውጣት ብቻ የሚጠበቅባት ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በአንድ ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ ተቀምጣ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መተላለፏ ጥያቄ ውስጥ ከገባው ቱኒዚያ ጋር ትጫወታለች፡፡ በምድብ ስድስት መሪዋ ሞሮኮ ከዛምቢያና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር በእኩል ነጥብ ከተለያየችው ዛምቢያ ጋር ትገናኛለች፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በሞሮኮ የ3 ለምንም ሽንፈት የደረሰባትና የመመለሻ ቲኬቷን አስቀድማ የቆረጠችው ታንዛኒያ ደግሞ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆነችው ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የስንብት ጨዋታዋን ታከናውናለች፡፡

ኮትዲቯርን ጨምሮ ከየምድባቸው ሦስተኛ ደረጃን በመያዛቸው 16ቱን መቀላቀል ከተሳናቸው ቡድኖች አራቱ ምርጥ ሦስተኛ በመሆን ሁለተኛውን ዙር የመቀላቀል ዕድላቸውን የሚጠብቁም ይሆናል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You