በዓለ ጥምቀት ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባሻገር አብሮነትን፣ አንድነትን የሚያጠናከሩ ማኅበራዊ እሴቶችም አሉት። የሰላም ተምሳሌት ሆኖም ይገለጻል። በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍም ቱሪስቶችን ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በመሳብ የምጣኔ ሀብት ምንጭም ጭምር ነው። የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለሀገሪቱ እድገት ከተመረጡ ከአምስት የኢኮኖሚ ምንጮች ወይም ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
ቱሪዝም ላይ በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ደግሞ በዓለ ጥምቀት ነው። የምንገኝበት የጥር ወር በዓለ ጥምቀቱ የሚከበርበት እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በበለጠ የሚነቃቃበት ጊዜ ነው። በበዓሉ ላይም ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይታደምበታል። በተለይም በመንግሥት ጥሪ ተደርጎላቸው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ የሦስተኛው ትውልድ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ የጥምቀት በዓል ላይ መገኘታቸው የሀገራቸው አምባሳደር ሆነው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ተውፊቱን፣ ማኅበራዊ እሴቱንም ለሌላው ዓለም በማስተዋወቅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖረው በማደረግ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት መልካም አጋጣሚ ነው።
እንዲህ ዘርፈብዙ ጠቀሜታዎች ያለው የጥምቀት በዓል ሲከበር ፍጹም ሰላምና መረጋጋት ይፈልጋል። ሰላምን ለማስፈን የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ወሳኝ ነው። የጥምቀት በዓልን ለማድመቅ የእምነቱ ተከታዮች ያልሆኑ ሁሉ ሳይቀሩ ከበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በአካባቢ ጽዳትና በተለያየ መልኩ አጋርነታቸውን፣ አብሮነታቸውን በማሳየት ዘወትር ይተባበራሉ።
እንዲህ አንድ የሆነው ሕዝብ በአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን፤ በሌላው ጊዜም አንድ ሆኖ ለሀገሩ ሰላም ዘብ በመቆም ሰላሟ የተጠበቀና የተረጋጋች ሀገር እንድትሆን፣ አሁን ከምትገኝበት አለመረጋጋት ውስጥ እንድትወጣ፣ ሀገራዊ እድገቷም እንዲረጋገጥ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ሌሊት እና ቀን ሊተጋ ይገባል። ሀገርን መገንባት እንደማፍረስ ቀላል እንዳልሆነ ካለፉ የጦርነትና አለመረጋጋት ጉዳቶች እንዲሁም ሰላምም ዋጋው በገንዘብ እንደማይተመን፣ ትምህርት መውሰድ ይቻላል።
ጥምቀትና ሰላምን አያይዘው ሃሳብቸውን ያካፈሉን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ሀገረ ስብከት በየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የአራት ጉባኤያት የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህርና በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ኤዲቶሪያል ቦርድ አርትዖት ክፍል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት መልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፈንታሁን፤ በዓለ ጥምቀት የማይተዋወቁትን በማስተዋወቅ፣ የተራራቁትን በማቀራረብ፣ የተጣሉ ቢኖሩ ቂማቸውን ትተው እንዲታረቁ በማድረግ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ያስረዳሉ። አብሮ መጫወት፣ መብላት መጠጣቱም ልዩነትን ያርቃል። ‹‹አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም›› የሚባለው ለዚህ ነው ሲሉም ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ሰው አብሮ የሚሆንበት ቀን ደግሞ በዓለ ጥምቀት ነው። ስለዚህ በዚህ ወቅት ማኅበራዊ ትስስሩ የበለጠ ይጠናከራል። በሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ቢሆን የሚነገረው የእግዚአብሔር ቃል ነው። የተበደለ እንዲካስ፣ የተጣላ እንዲታረቅ፣ ሀገር ሰላም እንድትሆንም ይፀለያል። መንፈሳዊ ነገር ሁሌም ጤና ነው። የሰውን አእምሮ ጤናማ የሚያደርገው ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
በበዓለ ጥምቀቱ ታቦታት ጥንግ ድርብ በለበሱ ቀሳውስት፣ በሰንበት ትምህርት ተማሪዎች እግዚአብሔርን የሚያወድስ መዝሙር ሲዘመር፣ ለእምነቱ ተከታይ መንፈሳዊ ሀሴትን፤ ለሌላው እምነት ተከታይ ደግሞ ተዝናኖትን ይፈጥራል።
በዓለ ጥምቀትን፤ በአርመን፣ በሶርያ፣ ሕንድ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን እና የምሥራቅ አብያተክርስቲያን የሚባሉት ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ሮማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ጆርጂያ የተሰኙ ሀገሮች የሚያከብሩት ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓት፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ መውረዱን ተምሳሌት የሆነውን ታቦት ከፍተኛ ቁጥር ባለው ታጅቦ ወደ ባህረ ጥምቀት መሄዱ የተለየ ያደርገዋል።
ጥምቀት በመላው ኢትዮጵያ የሚከበር ቢሆንም በጎንደር ደግሞ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ይከበራል። በጎንደር ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጥምቀትን ለመታደም ይህን ወቅት ጠብቀው ሰዎች ይመጣሉ። እንደ መልአከ ታቦር ኃይለኢየሱስ ገለጻ፤ ጥምቀት በተባበሩት የዓለም መንግሥታት የሳይንስ፣ ባህልና ትምህርት ድርጅት(ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል። ቅርሱን የመዘገበው ተቋም ትልቅ ስም ያለው ነው። በዚህ ድርጅት ጥምቀት መመዝገቡ ፋይዳው ብዙ ነው። አንድን ነገር ዓለም እንዲያውቀው ሲደረግ የበለጠ እውቅናው ከፍ ይላል።
በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሣ ለሁላችንም ትልቅ ክብር ነው። እውቅናው ሀገር እንድትታወቅ ብቻ ሳይሆን፤ በኢኮኖሚም ተጠቃሚ እንድትሆን ያግዛል። ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በዚህ የጥምቀት ወቅት ነው። ቱሪስት በመምጣቱ በማጓጓዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በሚሰጡት አገልግሎት ደግሞ ባለሆቴሎች አትራፊ ይሆናሉ። አነስተኛ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ሳይቀሩ በዚህ ወቅት የተሻለ ገቢ ያገኛሉ።
ይህን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ በዓል ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ እንዲሸጋገር እንዲሁም በዓለም የተገኘው እውቅና ፀንቶ እንዲቆይ ማድረግ ይጠበቃል። ይህን የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ ለመንግሥት ብቻ የሚተው መሆን የለበትም። ዜጎችም ግዴታ አለባቸው ይላሉ። በተለይም የውጭ የመገናኛ ብዙኃን የጥምቀትን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዲያጎሉ እንጂ አሉታዊ የሆነውን እንዲዘግቡ ዕድል መስጠት የለበትም የሚሉት መልአከ ታቦር ኃይለኢየሱስ፤ ዓለም ያደነቀውን እኛ መናቅና ዝቅ ማድረግ የለብንም ሲሉም አስምረውበታል።
‹‹የምናተርፍበት በዓል እንደሆነ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የመገናኛ ብዙኃን መልካሙን ገጽታውን ትተው በበዓለ ጥምቀት ሰው ተደበደበ፣ ሞተ በሚሉት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የኢትዮጵያን ስም እንዳያጠፉ ማድረግ የምንችለው እኛ ነን›› በማለትም ተናግረዋል። የታሪክ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ በበኩላቸው፤ ጥምቀት ዘመን ተሻጋሪ በዓል እንደሆነ በማስታወስ፤ የበዓሉ ታዳሚ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ከማንጸባረቅ በተጨማሪ በአለባበሱ ማንነቱን፣ ባህሉን የሚያሳይበት በጋራ ደስታውንም የሚካፈልበት የአደባባይ በዓል መሆኑን ይገልጻሉ። ሕዝቡ በዚህ በዓል ላይ ሳይረበሽ ተደስቶ ወደ ቤቱ መግባቱ ለአስተዳደር፣ በአጠቃላይ ለሀገረ መንግሥቱ ያለው አክብሮትና ፍቅር የበለጠ እንዲጨምር ያደርገዋል።
‹‹ሀገራችን በተለያየ ምክንያት አለመረጋጋት ላይ የምትገኝበት፣ የተለያዩ አሉባልታዎችም የበዙበት ጊዜ ላይ ብትሆንም እነዚህ የሚያልፉ ናቸው። መንግሥትም ቢሆን ይቀየራል፤ ሕዝብ ግን ሁሌም የሚኖር በመሆኑ በዓሉን አስጠብቆ መቀጠል ይኖርበታል›› በማለትም ያስረዱት የታሪክ ተመራማሪው፤ ጥምቀት ከኢትዮጵያም አልፎ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባህልና ትምህርት ድርጅት የተመዘገበ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እንደሆነ አስምረውበታል።
በበዓለ ጥምቀት በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል ስለሰላም፣ ስለአንድነትና ስለአብሮነት የሚሰጠው ትምህርትና የበዓሉ ታዳሚም በዚህ ወቅት የሚያሳየው ትህትና ቀጣይነት ኖሮት አሁን ሀገሪቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንዲውል ምን መሠራት አለበት ለሚለው የታሪክ ተመራማሪው አየለ በክሪ እንዳስረዱት፤ በዓሉ ላይ የሚታዩት መልካም ነገሮች ሁሉ በሌላውም ጊዜ መተግበር መቻል አለባቸው። እንዲህ በመሆኑ እንዲህ ተደረገ የሚሉ አንዱ በሌላው ላይ የሚያነሳሳ ነገር በተለያየ መንገድ በማሰራጨት መጥፎ ገጽታ የመስጠት ዝንባሌ መቆም አለበት። እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች በሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅዕኖዎች የሰዎችን ሥነልቦና ከመጉዳት ባለፈ በሀገር ገጽታ ግንባታና እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል።
እንዲህ ያሉ የሕዝብ በዓላት ደግሞ የፖለቲካ አጀንዳ ከመሆን መውጣት ይኖርባቸዋል። በንግግር ወይም በድርጊት ወዳልተገቡ ነገሮች የሚወስዱ ነገሮችን በጊዜ ማረም ከተቻለ በጅምላ የሚገለጽና የሚፈረጅ ነገር ይቀራል። ሁሉን ነገር ጨለማ አድርጎ ማየትም ይቆማል። በተቻለ መጠን ሆደ ሰፊ መሆን፣ ትዕግሥትንም መላበስ ያስፈልጋል። እንዲህ ማድረግ ሲቻል፤ አሁን ሀገሪቱ በውስጥ የገጠማትን ቀውስ ወደ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ መለወጥ ይቻላል ብለዋል።
በበዓላት ወቅት አንድነቱን፣ ትብብሩን የሚያሳየው ማኅበረሰብ በሌላ ቀን ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈፅም ያላስቻሉት ነገሮች ምንድናቸው ለሚለውም የታሪክ ተመራማሪው እንዳስረዱት፤ በጥምቀት በዓል ወቅት የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአካባቢ ጽዳት ጭምር ይተባበራሉ። የኦርቶዶክስ አማኞችም በተመሳሳይ በጎ ሥራ ይሠራሉ። እንዲህ ያለው ትብብር ኢትዮጵያ የሃይማኖት ብዝሃነቷን የሚያሳዩ ናቸው።
ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሚመሩ የሃይማኖት ተቋማት የሚከናወኑ ክብረ በዓላት በጣም አስፈላጊ ናቸው። ሰው በዓሉንም የራሱ አድርጎ ስለሚወስደው በሰላምና በደስታ እንዲከበር ከፍተኛ ፍላጎት ስላለው ሥነልቦናው ለሰላም ዝግጁ ነው። ይህንን መልካም እሴት በሌላ ጊዜም ለመጠቀም ሥራዎች መሠራት አለባቸው።
ጥምቀት ለምጣኔያዊ ሀብት እድገት ካለው ፋይዳ ጋርም በተያያዘ የታሪክ ተመራማሪው፤ በዓለ ጥምቀት በጎንደር በደመቀ ሁኔታ የሚከበርና ቱሪስቶችን የሚስብ በመሆኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጎንደርን የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር ከዚህ ቀደም የነበራቸውን መረጃ አስታውሰዋል። ጎንደር ላይ በዚህ መልኩ የሚሠራው ሥራ ቢጠናከር የሚመነጨው ኢኮኖሚ በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ላይም አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ነው ያስረዱት።
የእርስ በእርስ ጦርነት ከውድቀት ውጪ የሚያስገኘው ጥቅም እንደሌለ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ደጋግመው እንደሚያነሱ የጠቀሱት የታሪክ ተመራማሪው፤ በተለይ የውስጥ ችግሮችን በንግግርና በውይይት ለመፍታት ጥረት ካልተደረገ ጦርነትን አማራጭ አድርጎ መውሰድ ሀገርን ከምጣኔያዊ እድገት ወደ ኋላ ያስቀራል። የኢትዮጵያን ለውጥ፣ መሻሻልና ካደጉ ሀገራት አንዷ እንድትሆን ለማይፈልጉ አንዳንድ ኃይሎች ደግሞ መንገድ ይከፍታል። ያለውን ክፍተት ዓላማቸውን ለማሳካት ይጠቀሙበታል ብለዋል።
በዚህ ላይ የታሪክ ተመራማሪውን ድርሻንም በተመለከተ ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፤ ታሪክ ዓላማው ማስተማሪያ እንጂ የቂም በቀል መወጫ እንዳልሆነ በመግለጽ፤ በግላቸውም ታሪክ ለማስተማሪያነት እንዲውል ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ከሃሳብ ሰጪዎቹ መረዳት እንደተቻለው፤ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ይዘት ያላቸው በዓላት የሕዝብነታቸውን ይዘው መቀጠል አለባቸው። በውስጣቸው የያዟቸው መልካም እሴቶች አንድነት፣ ሰላም እና ፍቅር ዘወትር መቀጠል እንዳለበት ያመላክታል። አሁን ሀገር ከሚታይባት አንዳንድ ግጭቶች ለመውጣት የበዓሉን ሰላም እንደአንድ ግብአት መጠቀም እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2016