መንግሥት ዳያስፖራውን ሁለንተናዊ አጋር አድርጎ ይመለከታል

– ከፍተኛ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም ተመሰረተ

አዲስ አበባ፡- መንግሥት ዳያስፖራውን በአሉታዊ መልኩ ሳይሆን ሁለንተናዊ አጋር አድርጎ እንደሚመለከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከፍተኛ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ዲፕሎማሲያዊ መድረክ ትናንትና በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል፤ በወቅቱ ዳያስፖራው ሀገሩን ሊጠቅም በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንደገለጹት፤ በርካታ ዳያስፖራዎች ለሀገራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ መንግሥትም ይህን በመረዳት ከፍተኛ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የተወሰኑ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ስለ ኢትዮጵያ ሌትና ቀን አሉታዊ ጉዳዮችን ያሰራጫሉ ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ፤ ኢትዮጵያ ግን በልማትና ዕድገት ጉዳና ላይ በመሆኗ ዳያስፖራዎችን እየተቀበለች ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

መንግሥት ዳያስፖራውን የሁለንተናዊ አጋር አድርጎ ስለሚመለከት የሁላችንም ሀገር በሆነችው በኢትዮጵያ ጉዳይ በመነጋገርና በመግባባት ለሁለንታዊ ዕድገት አብሮ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ልዩነቶችን በማቻቻል አብሮ በመስራት ለኢትዮጵያ ልማት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር አብሮ በመስራት ለትውልድ አመቺ የሆነች ሀገርን የመገንባት ፍላጎት አለው፤ እየገነባም ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳመለከቱት፤ ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መስራት በመሆኑ የተስተካከለ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ለማካሄድ የሁሉም አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው፡፡

ውጤታማ የሆኑ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ ለመጪው ትውልድ ምቹ የሆነች ሀገር መፍጠር እንደሚገባ አምባሳደር ምስጋኑ አስገንዝበዋል።

አብዛኛው ዳያስፖራ ለሀገሩ በመቆርቆር የፖሊሲ ግብዓት ያቀርባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግሥት ስለሰላም ያልተገደበ ድጋፍ በማድረግ ለሀገራቸው ዕድገት አይተኬ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትን አስተያየት በመቀበል አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እንድሪስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዳያስፖራው ለሀገሩ አስፈላጊውን ጥቅም እንዲሰጥ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረም መመስረቱን አስታውቀዋል።

ፎረሙ ከ25 ሀገራት በተውጣጡ ከ300 በላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የዳያስፖራ አባላት የተቋቋመ መሆኑን ገልጸው፤ የፎረሙ መቋቋም ዳያስፖራው ለሀገሩ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ በጥናት በመለየት ወደ ተግባር እንዲቀየር ያደርጋል ብለዋል፡፡

የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፎረሙ ለፖሊሲ ግብዓት በማቅረብና ዳያስፖራው ሀገሩን ሊጠቅም በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዲሰራ ሰፊ ጥረት እንደሚያደርግ ዶክተር መሐመድ አመላክተዋል።

በመድረኩ በተለያዩ ሀገራት እየሰሩ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You