በጠንካራ ፉክክር የታጀበውና ለመገመት አዳጋች ሆኖ የቀጠለው የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ 10ኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ሀገራት ነጥብ በመጣል የምድብ ጨዋታዎቹን አጓጊ አድርገው የቀጠሉ ሲሆን፤ 16ቱን የሚቀላቀሉ የመጀመሪያዎቹ አራት ሀገራት በዛሬው ጨዋታ ይለያሉ፡፡
በስድስት ምድብ ተከፍለው እየተጫወቱ የሚገኙት 24 ቡድኖች መካከል ቀጣዩን ዙር መቀላቀል የሚችሉት ፍንጭ እየታየ ቢሆንም፤ እስካሁን ከተመዘገበው ውጤት አንጻር ከምድብ አንድ እና ምድብ ሁለት አላፊ የሚሆኑትን ቡድኖች በትክክል ለመገመት ግን አዳጋች ሆኗል፡፡ በመጀመሪያው ምድብ ከናይጄሪያ ጋር በእኩል ብትለያይም ጊኒ ቢሳውን 4ለ2 በሆነ ውጤት ማሸነፏ የሚታወስ ነው። በዚህ ጨዋታ ላይ ከተቆጠሩት ግቦች መካከልም ሦስቱን ከመረብ በማገናኘት ሀትሪክ መሥራት የቻለው 34 ዓመቱ የኢኳቶሪያል ጊኒ ተጫዋች ኢሚሊዮ ኒሱን ነው፡፡
ዛሬ አቢጃን በሚገኘው የኮትዲቯራውያን ብሔራዊ ስታዲየም አላሳኔ ኦታራ ኢኳቶሪያል ጊኒ 16ቱን የመቀላቀል እድሏን የምታረጋግጥበትን ጨዋታ ከውድድሩ አዘጋጅ ኮትዲቯር ጋር ታከናውናለች። በተፎካካሪነታቸው ጥሩ ከሚባሉ ቡድኖች አንዱ የሆነው ኢኳቶሪያል ጊኒ አራት ነጥብ በማስመዝገብ ከደረጃው አናት መቀመጥ ችሏል፡፡ ጅማሬውን በጊኒ ቢሳው ላይ 2 ለባዶ በሆነ የበላይነት ያደረገው የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን በናይጄሪያ የደረሰበት የ1 ለምንም ሽንፈት ወደ ሦስተኛ ደረጃ እንዲወርድ አድርጎታል፡፡ ይሁንና በዛሬው ጨዋታ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻለ ቀጣዩን ዙር የመቀላቀል እድሉን የሚያለመልም በመሆኑ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አጓጊ ሊሆን ችሏል፡፡
በምድቧ የተሻለ ተፎካካሪ ሆና የቀረበችው ኢኳቶሪያል ጊኒ የፈተነቻቸው ናይጄሪያዎች በኮትዲቯር ላይ የተቀዳጁት ነጥብ ወደ ቀጣዩ ዙር አንድ እግራቸውን እንዲያስገቡ ያደረጋቸው ሆኗል። በጨዋታው ዝሆኖቹን አሸናፊ ያደረጋቸው ብቸኛ ግብም ዊሊያም ተሩስት በ55ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ነው። የዛሬው የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታም በተደጋጋሚ ሽንፈት ወደ ሀገሯ የመመለሷን ነገር ካረጋገጠችው ጊኒ ቢሳው ጋር ያገናኛቸዋል፡፡ በእርግጥ ዝሆኖቹ ጨዋታውን በአሸናፊነት፣ አሊያም በእኩል ማጠናቀቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ የኮትዲቯርና ኢኳቶሪያል ጊኒ ውጤት ደግሞ ቀጣዩን ጉዞ በግልጽ የሚያመላክት ይሆናል፡፡
በምድብ ሁለት ተጠባቂዋ ግብፅ ሁለቱን ጨዋታዎች በእኩል ነጥብ መጨረሷን ተከትሎ በሁለት ነጥብ ከደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በዛሬው መርሐ ግብርም ምድቡን ስትመራ ከቆየችው ኬፕቨርዴ ጋር ይጫወታሉ። ፈርዖኖቹ በሞዛምቢክ ተፈትነው ቀጣዩን ጨዋታ ከጋና ጋር ቢያደርጉም፤ ከባድ ሚዛን በተባለለት በዚህ ጨዋታም በተመሳሳይ በእኩል ነጥብ ነበር የፈጸሙት። የጋናን ሁለት ግቦች ሞሐመድ ኩዱስ ከመረብ ሲያሳርፍ የግብፅን የአቻነት ግቦች ደግሞ ሙስጠፋ ሞሐመድ እና ማራሙሽ በ69ኛው እና 74ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ያስቆጠሩት። የግብፃውያኑ ቁልፍ ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህ ደግሞ ጉዳት አስተናግዷል። ለሰባት ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ቀዳሚ የሆነችው ግብፅ አሁንም ለሻምፒዮናነት ትጠበቅ እንጂ ዋንጫውን ካነሳች ግን 14 ዓመታት ተቆጥረዋል። የአፍሪካው ጠንካራ ቡድን ዛሬ ከኬፕቨርዴ ጋር በሚኖረው ወሳኝ ጨዋታ ተጠባቂውን ብቃት በማሳየት 16ቱን ቡድኖች እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።
የአፍሪካ ዋንጫውን በኬፕቨርዴ የ2 ለ1 ሽንፈት የደረሰባቸው ጥቋቁሮቹ ከዋክብት በቀጣዩ ጨዋታ ከግብፅ ጋር በእኩል ነጥብ በመለያየት አንድ ነጥብ ብቻ በማስቆጠር በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ለዋንጫ ሲገመት ባልተጠበቀ ሁኔታ የተገኘው ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉ አጠራጣሪ ሆኖ ዛሬ ከሞዛምቢክ ጋር ይጫወታል። ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሞዛምቢክም የማለፍ እድሏ አጠራጣሪ ሆኖ ጨዋታውን ታከናውናለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም