የሀገር ባህል ልብስን ለአዘቦት ቀን

 አቤል ተስፋዬ ይባላል፡፡ በሀገር ውስጥ የሚሰሩ ልብሶችን በማምረት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያከፋፍላል። የልብስ ዲዛይንም ያወጣል፡፡

እናት እና አባቱ በተሰማሩበት ሙያ እሱና ወንድሙም ተስበው የስራው አንድ አካል ሆነዋል፡፡ ወላጅ እናቱ አረጋሽ ተሾመ በጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ሰርተዋል፤ ይህን ልምዳቸውን ይዘው ሙሉ ለሙሉ በእዚህ የአልባሳት ሙያ ውስጥ ይሰራሉ፡፡ አባታቸው አቶ ተስፋዬ አበራም አስድቀድመው ይሰሩ ከነበሩት ስራቸው ወጥተው ሙሉ ለሙሉ ወደ ልብስ ዲዛይን ስራ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በልብስ ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር ናቸው ፡፡

አቤል ከቤተሰቦቹ በተቀበለው የልብስ ዲዛይን ስራና በሀገር ውስጥ አልባሳት ማምረት እየሰራ ይገኛል። ‹‹ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም ነገር እዚሁ በሀገራችን አምርተን እንድንጠቀም እፈልጋለሁ›› የሚለው አቤል፣ ከአልባሳት እና ጨርቃጨርቆች ጋር በተያያዘም የራሳችን የሆነ ምርት ለምን አንጠቀምም የሚል እምነትም አለው ፡፡

የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርትን በሀገር ልጅ በማለት የራሱን አስተዋጽኦ በጨርቃ ጨርቅ አልበሳት ላይ እያሳረፈ ይገኛል፡፡ የሀገር ባህል ልብስ መስሪያ ግብዓቶችን በመጠቀም ወጣ ያሉና ሰዎች በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ሊለብሷቸው የሚችሏቸውን ልብሶችን ይሰራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጋቢ የሚሰራበትን ‹‹ፈትል›› ጨርቅ በመጠቀም ለእለት ተዕለት አልባሳትነት የሚውሉ አልባሳትን በማምረት ወደ ገበያው ለማስገባት እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡

ይህ ስራው በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ከተቋቋመ ቆየት ቢልም፣ አቤል ‹‹ 77 ልብስ ዲዛይን ›› የሚል ስያሜ የሰጠው የአልባሳት ስራ 2014 ዓ.ም ላይ ስራውን እንደ ጀመረ ይናገራል፡፡ ‹‹ምርቶቹን መጀመሪያ ቤት ውስጥ እየሰራሁ ለቤተሰቦቼ እና ለጓደኞቼ አለብሳቸው ነበር›› የሚለው አቤል፣ ተምሮ ከጨረሰበት እና ተቀጥሮ ይሰራበት ከነበረው ስራ ይልቅ ከልጅነቱ ጀምሮ ቤት ውስጥ ይመለከተው የነበረውን የወላጆቹን ስራ በመምረጥ በተሻለ መልኩ በማሳደግ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራው መግባቱን ያስታውሳል።

የሀገር ባህል ልብስ አልያም የጨርቃጨርቅ አልባሳት ስራ የብዙ እጅ ስራዎች እና ባለሙያዎች ውጤት መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህንን ስራ ከባለቤቱ ሀና ታለጌታ ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ‹‹ባለቤቱ በሽመና ስራ እውቀቱ እንዳላት ጠቅሶ፣ የሽመና ስራውን ከሷ ከዲዛይን እና ከስፌት ጋር የተያያዘውን ደግሞ ከእኔ ጋር አድርገን እንሰራለን፡፡›› ይላል፡፡

ምርቱንም በሰፊው ለገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሶ፣ የሀበሻ ልብስ የሚሰራበትን ግብዓት ለመስራት እና በሚፈለገው መልኩ ለመቆራረጥ ብዙ ሂደቶችን እንደሚያልፍ ይናገራል፡፡ ይህ ሁሉ ሁኔታ ጊዜ እንደሚወስድና በፈለገው ልክ ከመጓዝ እንዳገደው አመልክቷል፡፡

አቤል የሀገር ባህል አልባሳትን በፋብሪካ ደረጃ መስራት የወደፊት እቅዱ ነው፡፡ በዋናነት የሚጠቀመው ግብዓትም ‹‹ፈትል›› መሆኑን ይገልጻል፡፡ ጋቢ የሚሰራበት ባህላዊ ጨርቅ ሙሉ ለሙሉ ከጥጥ እንደሚመረት ገልጾ፣ በተለያየ ቀለማት የሚቀርበውን ‹‹ሱፍ›› ጨርቅ የሚባለውንም በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡

‹‹የሀገር ባህል ልብሶች የተለየ ውበትን የሚፈጥሩ እና ሞገስን የሚያላብሱ ቢሆኑም፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት በብዙ ምክንያት እንዳይለመዱና አልባሳቱ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን እንዳይዘወተር አደርጎታል›› የሚለው አቤል፣ የሀገር ባህል በተለየ መልኩ ቢሰራም በሚለበስበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግን እንደሚጠይቅ ይገልጻል፡፡ በዚህ የተነሳም ሰዎች በሀገር ውስጥ ለተሰሩ ምርቶች ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን አመልክቷል።

‹‹እንደ አጋጣሚም እንደ እድልም ሆኖ በአብዛኛው የኛን ምርቶች የሚጠቀሙት የውጭ ሀገር ዜጋዎች፣ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ድምጻውያን ናቸው›› የሚለው አቤል፣ በሌላ ሀገር የሚገኙ ዜጎች አልባሳቱ የሀገር ባህል ልብሶች ከመሆናቸው ባሻገር በእጅ የተሰሩ መሆናቸው በራሱ ልዩ ስሜትን ይፈጥርላቸዋል ሲል ያብራራል፡፡

አቤል እነዚህን የሀገር ውስጥ እና ሌሎች ከሀገር ውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን በመጠቀም ለእለት ተዕለት የሚሆኑ ሸሚዞች፣ ጃኬቶች እና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች የሚሆኑ እና በበጋ መለበስ የሚችሉ ልብሶችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል፡፡

የሀገር ባህል አልባሳት ኢትዮጵያን ከሚገልጹ እና ከሚያስተዋውቁ መገለጫዎቻችን መካከል ይጠቀሳሉ ያለው አቤል፣ ወቅትንና ፋሽንን በጠበቀ መልኩ እየተሰሩ መሆናቸውንም ይገልጻል፡፡ በሽመና እና በጥልፍ ስራው ላይ የምናስተውላቸው ባለሙያዎች በዘርፉ ረጅም ዓመት የሰሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ዘርፉ ጊዜውንም ያማከለ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ራሳቸውን ማብቃትና የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንደሚገባቸውም አስታውቋል፡፡

እሱ እንዳለው፤ ስራዎቹ ተፈላጊ እንዲሆኑ በተለያዩ ገበያዎች፣ ባዛሮች ላይ ምርቶቹን ይዞ ይቀርባል፡፡ በዚህም ራሱን ያስተዋውቃል፤ በዘርፉ ከተሰማሩ ሌሎች ባለሙያዎች ጋር የልምድ ልውውጥ ያደርጋል፡፡ በሀገር ልብሶች እና በሌሎች የአፍሪካውያን ጨርቆች የተሰሩ ቦርሳዎችም እያመረተ ለገበያ ያቀርባል፡፡

እሱ እንዳለው፤ የሀገር ባህል ልብሶች በሀገር ውስጥ አምርቶ ለመጠቀም ገበያው ገና አልተነካም ፡፡ የሀገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ አልበሳት ዘርፍ በብዙ ሊሰራበት ይችላል። በጨርቃጨርቅ አልበሳት ዘርፉ ላይ በአብዛኛው የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ይስተዋላል፡፡ በገበያው ላይ የሚገኙት ግብዓቶችም ቢሆኑ የሚሸጡበት ዋጋ ከጊዜ ጊዜ የሚለዋወጥ እና ውድ ናቸው፡፡

ጥራት ያላቸው ልብሶችን አምርቶ ወደ ገበያ ለማቅረብ በጥሬ እቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ውድነት ተግዳሮት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህ ችግር ልብሶቹ የሚሸጡበትን ዋጋ ከፍ እንዲል እንዳደረገውም ይናገራል፡፡

በጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ እንደምትልካቸው እንደ ቡና ያሉ ምርቶች ኢንዱስትሪው ደረጃውን የጠበቀ ኩባንያ ገንብቶ አልባሳትን በማምረት ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተግዳሮት እንደሆነበት ጠቁሟል፡፡ የግብዓቶች ችግር ምርቱ ደረጃውን እንዳይጠብቅ እያደረገው መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህ ችግር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ከሀገር ውጭ ላሉ ደንበኞቻቸው የሚሆኑ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል ይላል፡፡

 ሰሚራ በርሀ

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You