ፆታን መሰረት አድርገው በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ በደሎችና ጥቃቶች አሁንም እንዳልተወገዱ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ም/አፈጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ተናገሩ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሰራተኞች ዛሬ በምክር ቤቱ አደራሽ የነጭ ሪቫን ቀንን አክብረዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ም/አፈጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት በየትኛውም አገርና ህዝብ ዘንድ የሚፈፀም መሆኑን በመግለፅ ድርጊቱን ለማስቆም እንደ አገርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር አሁንም ትኩረት ተሰቶት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ም/ አፈጉባኤዋ በንግግራቸው ፆታን መሰረት አድርገው በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ በደሎችና ጥቃቶች አሁንም እንዳልተወገዱመም ብለዋል፡፡
በሴቶችና ህፃናት ሚኒስቴር የተዘጋጀ በሴቶች ጥቃትና በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት ላይ የሚያተኩር የመወያያ ሀሳብ በበአሉ አከባበር ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦች ትኩረት ተሰቶባቸው ሊሰራባቸው እንደሚገባም ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ሁሉ ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው ም/አፈጉባኤዋ አሳስበዋል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ከህዳር 16-ታህሳስ 1/2011 በመከበር ላይ ያለው ይህ በአል ‹‹ጀግኒት ወንድ ልጅን በማስተማር ፆታዊ ጥቃትን ትከላከላለች›› በሚል መሪ ቃል በሀገራችን የተለያየዩ ቦታዎች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በሐይማኖት ከበደ