መብራት ከሌለው መንደር እስከ ሀዋርድ መምህርነት

ውልደቱ የካቲት 1938 ዓ.ም በጎንደር ነው። የሕይወቴ ወርቃማ ጊዜ ብሎ የሚያሰበውን፣ አብዛኛውን ጊዜ በዛው በጎንደር አሳልፏል። ያኔ ኤሌክትሪክ ይሉት ሥልጣኔ እነሱ አካባቢ አልደረሰም። ቀን ቀን ከአካባቢው ልጆች ጋር ማሳ ለማሳ ሲቦርቁ ይውላሉ። አመሻሹ ላይ የቤቱ አስር ልጆች ከተሰማሩበት መስክ ወደቤታቸው ይከተታሉ። ታዲያ መብራት አለመኖሩን ተከትሎ ምሽታቸውን ሬዲዮ በመስማትም ይሁን ቲቪ በማየት ያደምቁ ዘንድ አልታደሉም። ሳይደግስ አይጣላምና የአባቱ እናት ታሪክ አዋቂ፤ ከዛም አልፎ መተረክንም በሚገባ የታደሉ ናቸው።

እንደ ሀገሩ ደንብ እቤት ውስጥ እሳት ተያይዞ፤ የቤተሰቡ አባላት እሳቱን ክብ ሰርተው እየሞቁና በብርሃኑ እየተያዩ ሴት አያቱ ታሪክን ከተረት እያዋዙ ምሽቱን ማድመቅ የቤቱ የዘወትር ደንብ ነው። በዚህ የእሳት ዳር ጨዋታ አያትዬው ልጆቹ ሊኖራቸው ስለሚገባ ሥነ-ምግባር ተረቱን ከእውነተኛ ታሪክ ጋር እየቀላቀሉ ይተርኩላቸዋል። ከፍ ሲል አባቱ ደራሲና የትያትር አዘጋጅ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ከአባቱ ሥር በመሆን አባቱ በሚያዘጋጃቸው ትያትሮች ላይ የመሳተፍና ለጥበብ ቅርብ የመሆን እድል ተፈጥሮለታል። ይህ መብራት ከሌለው መንደር ተነስቶ በአሜሪካ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ የፊልም መምህር እስከ መሆን የደረሰው የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ታሪክ ነው።

በትምህርቱና በእውቀቱ ተመዝኖ የፕሮፌሰርነት ክብር ላይ ቢደርስም በርካታ የሀገሩ ሰዎች ከስሙ በፊት “ጋሼ” ን ማስቀደም ምርጫቸው ነው። እሱም ጋሼ ሲሉት ይበልጥ ምቾት ይሰማዋል። አስተዳደጉ ከተረት ጋር ቁርኝት አለው። ታላላቆቹ ከእኩዮቹ ጋር “ተረት ተረት” ሲሏቸው “የላም በረት” እያሉና በጉጉት የሚነግሯቸውን ታሪክ ለመስማት እየተዘጋጁ አድገዋል። ያኔ ታዲያ የሰሙትን ተረት በምናባቸው ገጸ-ባህሪያት አበጅተው አይተዋቸዋል። ያም ልማድ አሁን ለሚያደርገው በፊልም ታሪክን ለመንገር መነሻ ሆኖታል።

አባቱ ደራሲ፣ የቲያትር ፀሐፊና አዘጋጅ የሆኑት ገሪማ ታፈረ ናቸው። ከአባታቸው ጋር ከጎንደር አልፎ እስከ አስመራ በመሄድ ሥራዎችን የማሳየት እድል በልጅነቱ ነበረው። አባቱ “ጎንደር በጋሻው” የተሰኘ፣ በአርበኞች ታሪክ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ጽፈዋል። “የመከራ ደወል″ የተሰኘ፣ እንዲሁም ሌሎች ቲያትሮችን ሠርተዋል። አባቱን እያየ ያደገው ጋሽ ኃይሌም የአባቱ ልጅ ነውና ከልጅነቱ ሃሳቡን በጽሑፍ እያሰፈረ አድጓል። ይሄ ጽሑፉንም ከጽሑፍነት ባሻገር ጎንደር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ወደ ድራማና ትያትር በመቀየር የአባቱን ፈለግ ለመከተል ይበልጥ ተግቷል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለሁለት ዓመት ጅማ ከተማ በሚገኘው በ“ሚያዝያ 27” ተከታትሏል። ጎንደር ሳለ አባቱ የሚሰራቸው ትያትሮች ላይ በመሳተፍ ልምድ አዳብሯልና በጅማ ጓደኞቹን ሰብስቦ እስከ አጋሮ ድረስ በመዝለቅ ትያትር ያሳይ ነበር። ቀሪውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለሁለት ዓመት በአዲስ አበባ፣ ሽመልስ ሀብቴ ተከታትሏል። ሽመልስ ሀብቴም እያለ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ከሌሎች ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርግ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው “ክሬቲቭ ሴንተር ኦፍ አርት” ትያትር የመማር አጋጣሚ ነበረው።

እ.አ.አ በ1967 ችሎታውን ያዩ የኪነጥበብ ሰዎች ገንዘብ አዋጥተው እየሰራ እውቀት ይገበይ ዘንድ ወደ አሜሪካ አቀና። ሺካጎ በሚገኘው ጉድማን የትያትር ትምህርት ቤት የትያትር ትምህርት መከታተል ጀምሮ ነበር። መጀመሪያ ላይ ሙሉ ሃሳቡ ትያትር ላይ ነበር፤ በሂደት ግን ትያትር የተወሰነ ሲመስለው ፊቱን ወደ ፊልም አዞረ። በትምህርት ቤቱ ሁለት ዓመት ከቆየ በኋላ አድራሻውን ወደ ሎስ አንጀለስ ቀየረ። እ.አ.አ በ1970 ወደ ካሊፎርኒያ በመዘዋወር በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በፊልም ዘርፍ ትምህርቱን በመከታተል በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ተመርቋል። በዛም የሎስ አንጀለስ “የጥቁር ፊልም ሰሪ ባለሙያዎች ንቅናቄ” አካል ከሆኑትና በቀዳሚነት ከሚጠሩት ተርታ ይሰለፋል። እ.አ.አ በ1976 ትምህርቱን አጠናቆ ሲመረቅ አራት ፊልሞችን ለእይታ አዘጋጅቶ ነበር። እነዚህም “አወር ግላስ”፣ “ቻይልድ ኦፍ ሬዚስታንስ”፣ “ቡሽ ማማ”፣ እና “ምርት ሦስት ሺህ ዓመት” ናቸው።

አባቱ ስለ ኢትዮጵያ አርበኞች፣ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ትያትር ሲሰራ እያየ አድጓል። ያም ቢሆን ስለ ሀገሩ በስፋት

 እንዲሰራ የአፍሪካን አሜሪካኖች እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዳነቃው ይናገራል። ስለ ሀገሩ፣ ስለጥቁርነቱ ባለው አመለካከት ጠፍቶ መመለሱን ይናገራል። “መሪጌታ ገሪማ ታፈረን ከሚያህል የታሪክ ፀሐፊ ተወልጄ ጎንደር፣ ጅማ፤ እንዲሁም አዲሳባ ሳለሁ ጠፍቼ ነበር። ” ይላል። ከሀገሩ ወጥቶ አሜሪካ ሲደርስ እድሜ ለአፍሪካን አሜሪካኖች በጥቁርነቱ እንዲኮራ አደረጉት። ከአባቱ ጋር አብሮ ስለ አፄ ዮሐንስ፣ ስለ ራስ አሉላ የማይጨው ጦርነት ትያትር የሠራ ነው። አባቱ “ጎንደሬው በጋሻው”ን ስለ አፄ ቴዎድሮስ የጻፈ ነው። አያቱ መሪጌታ ታፈረ በአፄ ቴዎድሮስ ቤተመንግሥት ውስጥ ፀሐፊ የነበረ ነው። ያም ቢሆን አሜሪካ “ስመጣ ዞሮብኝ ነበር” ይላል። ቀደምቶቹ ጣልያንን ተዋግተው አሸንፈው ቢመልሱም እሱና መሰሎቹ በሀገር ቤት ቆይታቸው በአሜሪካ ፊልም በመማረካቸው ከአሜሪካ ለማስተማር የሚመጡ ነጭ ፒሲኮሮች ፍቃደኛ አገልጋይ ለመሆን ይጥሩ ነበር። ያኔ የነሱን አለባበስ ለመኮረጅ፣ የነሱን ድርጊትና ቋንቋ ለመቻል መከራ ያዩ ነበር። ያኔ እነሱን የመሰለ፣ የተሻለ ተፈላጊ፤ ብሎም ዘመናዊ የሚል ማዕረግ ያገኝ ነበር።

ለዚህም በፍቃደኝነት ነጭ ፒስኮሮች ጋ ወዶ ገብ ሆነው ያገለግላሉ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እያለ በ21 ዓመቱ ወደ አሜሪካ መጣ። ያኔ ኢትዮጵያ እያለ ይናፍቃት የነበረችው አሜሪካ ሲደርስ እዛ ያሉት ጥቁሮች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን አግንነው ጠበቁት። በተቃራኒው እሱ በሄደበት ሺካጎ በነጮች ዘንድ ጥቁር በመሆኑ እንደ ልዩ ፍጡር መታየቱ ያልጠበቀው ሆነበት። ያኔ በሀገሩ እያለ ስለ ሀገሩ፣ ስለማንነቱ ከሚያውቀው በላይ ይበልጥ ማጥናት ጀመረ። ያኔ ከራሱ አልፎ ለጥቁር መብት የሚሟገት፣ በሥራው በሆሊውድ የተለመደውን የነጭ የበላይነት የሚጻረርና እውነታውን ቆፍሮ የሚያወጣ ኃይሌ ተወለደ።

በዚህ ሂደትም የነጭ ኃያልነትን የማይሰብኩና ከሴትና ወንድ ግንኙነት የጠለቀ ሃሳብ ያላቸው እነ አወር ግላስ፣ ቻይልድ ኦፍ ሬዚስታንስ፣ ቡሽ ማማ፣ ምርት ሦስት ሺህ ዓመት፣ ዌል ሜንቴይን፣ አሽተን ኤምበርስ፣ አፍተር ዊንተርስ፣ ሳንኮፋ፣ ኢምፐርፌክት ጆርኒ፣ ዓድዋ፣ ጤዛና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን እንካችሁ ብሏል። በእነዚህ ሁሉ ሥራዎች ፈታኙ ነገር ለፊልሙ የሚያግዝ በጀት ማግኘት ከባዱ ፈተና ነበር። በሆሊውድ የሚገኙ ድርጅቶች ፊልሙን ለመደገፍ ኃይሌ የሚያነሳው ሃሳብ ይጎረብጣቸዋል። እሱ ደግሞ ገንዘብ ለሰጠው ሥራውን፣ የአዕምሮውን ውጤት ለመቀያየር፣ ለማስገባትና ለማስወጣት ፍጹም ፍቃደኛ አይደለም። በዚህ የተነሳ አንድ ሥራ ጀምሮ ለማጠናቀቅ ረዥም ጊዜ ይወስድበታል።

በአፍሪካ ይካሄድ የነበረውን የባሪያ ንግድ አስከፊ ገጽታ የሚያሳየው “ሳንኮፋ” ፊልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅናና ሽልማት አስገኝቶለታል። ፊልሙ በሆሊውድ ከዚህ ቀደም የባሪያ ንግድን በሽፍንፍኑ ይሰሩ ከነበሩ ፊልሞች የተለየና በአስፈሪ ሁኔታዎችና በዘመኑ የነበሩ ሰዎች የተጋፈጡትን የጭካኔ በትር የሚያሳይ ነው። በፀሐፊነት፣ በአዘጋጅነትና በፕሮዲሰርነት የተሳተፈበት ሳንኮፋ የመጀመሪያው ሽልማት በጣልያን፣ ሚላን ከተማ በተካሄደው አፍሪካን ሲኒማ ፌስቲቫል ላይ በምርጥ የፊልም ቅንብር ዘርፍ፤ በቡርኪናፋሶ፣ ዱጋዱጉ በተካሄደው የአፍሪካ ቀዳሚው የፓን አፍሪካ ፊልምና የቴሌቭዥን ፌስቲቫል ላይ ተሸልሟል። ሌሎችም በርካታ ሽልማቶችን የተቀዳጀ ሲሆን በ43ኛው የበርሊን ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ “ጎልደን ቢር” ተብሎ ለሚጠራው የሽልማት ዘርፍ እጩ ሆኖ ነበር።

ያመነበትን ይሠራል፤ ገንዘብ ያመጡ ይሆን ወይ? ተመልካች ያገኙ ይሆን? ብሎ መጨነቅ የሱ ባህሪ አይደለም። ፊልም ሲሰራ ለሥራው ገንዘብ ማግኘትን ባይጠላም ገንዘብ ሰጥተንሃልና ታሪኩን እንዲህ አስተካክለው ይሉት ነገር አይወድም። ስለዚህም ከራሱ፣ ከገቢው በመቀነስ ጊዜ ወስዶ ያመነበትን ብቻ ይሠራል። “እከሌ ይከፋ ይሆን፤ እከሌ እንዲደሰት እንዲህ ልቀባባው?” ይሉት ነገር እሱ ጋ የለም። ለዚህም ይመስላል፤ ዓለም አቀፍ ዝና ያስገኘለትን “ሳንኮፋ”ን ሲሰራ ዘጠኝ ዓመት ፈጅቶበታል።

“ምርት ሦስት ሺ ዓመት” የተሰኘው ፊልሙ በሲውዘርላንድ በሚካሄድ የፊልም ፌስቲቫል ላይ ተሸላሚ ሆኗል። “ዊልሚንግተን 10 ዩኤስ ኤ” የተሰኘው እ.አ.አ በ1978 ለተመልካች የቀረበው ዶክመንተሪ ፊልም በአሜሪካ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ክፍተትና ዘረኝነት ለማሳየት በዘጠኝ ጥቁር ወንዶችና በአንድ ነጭ ሴት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ነው። “ኢምፐርፌክት ጆርኒ” በቢቢሲ ድጋፍ የተሰራ ሲሆን፣ በሀገራችን ከቀይ ሽብር እልቂት በኋላ በነበረው የፖለቲካ ድባብና የአዕምሯዊ ጫና ውስጥ ያለፈው ትውልድ ከዚህ ድብታ ለመውጣት የተጓዘበትን መንገድ የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ነው። በፊልሙ ያለፈውን ከመተረክ ባለፈ ለወደፊቱ የተሻለ የሚለውን የመፍትሔ ሃሳብ አስቀምጦበታል።

“ዓድዋ የአፍሪካ ድል” (ዓድዋ አን አፍሪካን ቪክትሪ) በሚል ርዕስ ለዕይታ የቀረበው የድራማ ዶክመንተሪ ፊልም እ.አ.አ በ1896 ኢትዮጵያዊያን ሊወራቸው ከመጣው ጣልያን ጋር ያደረጉትን ጦርነትና ኢትዮጵያ ያሸነፈችበትን ታሪክ ያስቃኛል። “ጤዛ” የተሰኘው ፊልሙ በኢትዮጵያና በጀርመን በተከናወነ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት ያስወገደው የደርግ አስተዳደር ወደ ሥልጣን በወጣ ማግሥት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ሀገሩንና ወገኑን ለማገልገል የሚሞክር የተማረው ኃይል ስለሚደርስበት መንገላታትና ስለሚሰማው ስሜት የሚቃኝ ነው። በዚህ ፊልም ላይ አብዛኛው ገጸ-ባህርያት ትወና ሥራቸው ባልሆኑ ተዋናዮች የተወከሉ ናቸው። አዲስ ተዋናዮችን መምረጥና ማሠራት አዘጋጁን የሚያለፋ ቢሆንም ኃይሌ በርካታ ተዋናይ ያልሆኑ ሰዎችን መርጦ መስለው ሳይሆን ሆነው እንዲጫወቱ ማድረግ ችሏል። ፊልሙ በጣልያን (ቬኒስ) በተካሄደው የፊልም ፌስቲቫል ላይ የዳኞች (ዘ ጁሪ) ምርጥና የምርጥ ፊልም ሽልማትን (ቤስት ስክሪን ፕሌይ አዋርድ) አሸናፊ በመሆን ሽልማት ተቀብሏል።

አባቱ በሕይወት እያሉ ጽፈው ከታተሙላቸው መጻሕፍት ባሻገር ተጽፈው ለሕትመት ብርሃን ያልደረሱ መጻሕፍታቸውን አሳዶ ማንበብ ምርጫው ነው። በቀጣይም እነዚህን መጻሕፍቶች የማሳተም እቅድ አለው። የሀገራችን አርበኞች ታሪክ በየቦታው ተበትኖ ከቀረበት መሰብሰብ ከአባቱ የወረሰውና ያስቀጠለው ተግባሩ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ አበጠርጥሮ ያውቃል። ሲናገር ያፈዛል። ያኔ የነበሩ ዶክመንቶችንና ምስሎችን ከማገላበጥ ባሻገር መላው ኢትዮጵያን በማሰስ ያኔ የነበሩ አርበኞችን አድኖ ሃሳባቸውን በምስል አስቀርቷል። ፊልሙ መንፈሴ የሚፈልገው ነው ይላል። ታሪክን ለማስቀረት ደክሟል። ሀገር ቤት በመጣበት አጋጣሚ ሁሉ ትልቅ ሰው ካገኘ አያልፍም፤ ትውስታቸውን በምስልም፣ በድምጽም ያስቀራል። በዚህ ሂደትም በርካታ ገንዘብ አውጥቷል፤ ሆኖም ያመነበት ነውና አይቆጨውም።

“የዓድዋ ልጆች” ሲል የሰየመውና ስድስት ሰዓት የሚፈጅ ፊልሙን አጠናቆ ለማሰራጨት ሁኔታዎችን እየፈለገ ነው። ፊልሙን ለመሥራት ከሠላሳ ዓመታት በላይ የፈጀ ሲሆን፤ በሀገራችን የሚገኙ አርበኞችን ቃል ከማካተቱም ባሻገር፤ በበርካታ የአውሮፓ ላይበራሪዎች በመዘዋወር በርካታ በወቅቱ የተነሱ ምስሎችን ሰብስቧል። ለዚህም ምስሎቹን ለማግኘትና ለመጠቀም ፍቃድ ለማግኘት በርካታ ብሮችን ይጠይቅ ነበርና እሱ እራሱ ጊዜውን አርዝሞታል። በማሰባሰብ ሂደቱ በጣልያን ወረራ ወቅት በርካታ ቅርሶች ወደ ጣልያን መጓዛቸውን ታዝቧል። በዚህም ሂደቱና እቅዳቸው የነበረው ኢትዮጵያን ቀኝ መግዛት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ የማጥፋት ትግል እንደነበር ገባኝ ይላል። ፊልሙ በርካታ ዓመታትን ለመፍጀቱ አንዱ ምክንያት በጣልያኖች ዘንድ የነበረው፣ እነሱ ጋ የሚገኙ የኢትዮ ጣልያን ጦርነትን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለመስጠት ማንገራገራቸው ነው።

ከሀገር ውስጥ ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ሳይቀር በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የተቀበለው ፕሮፌሰር ኃይሌ 30 ዓመታት የፈጀበትን የመጨረሻ ፊልሙን “አባቴ ምነው በኖረ፤ ማየት አለበት የምለው ነው” ይላል። በሥራው የሱን ሥራ ማስቀጠሉን ይናገራል። በትንሽ በጀት በዓለም አቀፍ ትልቅ ፌስቲቫሎች ላይ ውጤታማ የሆነ ፊልሞችን ማድረስ ተክኖበታል። እ.አ.አ ከ1975 ጀምሮ በዋሽንግተን በሚገኘው ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ለረዥም ጊዜ አገልግሏል። “ሳንኮፋ” በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ. በ1996 ያቋቋመው የመጻሕፍትና የፊልም ማዕከል በዋሽንግተን ለረዥም ጊዜ ካስተማረበት ሀርዋርድ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ይገኛል። ማዕከሉ ከመገበያያነቱ በተጨማሪ የተለያዩ መድረኮች የሚካሄዱበትና ፊልሞች ለእይታ የሚቀርቡበት ነው።

የፊልም ደራሲ፣ አዘጋጅና ዳይሬክተሩ ጋሽ ኃይሌ ብዙ ያውቃል፤ ብዙ ተምሯል፤ ብዙዎችንም አስተምሯል። ያም ቢሆን በልጅነቱ አባቱ ካስገባው የቤተክርስቲያን ትምህርት መኮብለሉ ይቆጨዋል። ማህሌት፣ ቅኔ ይሉትን ትምህርት ተከታትሎ ቢሆን ኖሮ የዛሬ ሥራው የተሻለ እንደሚሆን ያስባል። አሁንም የተጻፉ በርካታ ፊልሞች አሉት፤ እነሱን የመሥራት እቅድ አለው። “አሜሪካ እድሜ ልኬን እኖራለሁ ብዬ አልመጣሁም፤ በረዶ በመጣ ቁጥር ምን እያደረኩ ነው እላለሁ። ” ይላል። የተወሳሰቡ ዘመናዊ የሲኒማ ዓለም መሳሪያዎችን ቢጠቀምም ሞባይል ስልክና ማህበራዊ ሚዲያ ከሚባሉ ዘመን አመጣሽ ፈጠራዎች ጋር አለመነካካትን ምርጫው አድርጓል። ጊዜው ስላመጣው ብቻ መጠቀም ምርጫው አይደለም። የሚያስፈልገኝንና ለኔ ሕይወት ተስማሚውን ብቻ መርጬ እጠቀማለሁ ይላል። በርካታ ዓመታትን በአሜሪካ ቢኖርም ለፕሮፌሰር ኃይሌ ተወዳጅ ምግቦቹ ሽሮና ድርቆሽ ናቸው። “የሚወዱኝ ሁሉ ከኢትዮጵያ የሚያመጡልኝ ድርቆሽ ነው” ይላል። “ኢትዮጵያ ባንተ አልተጀመረችም፤ ባንተም አትፈርስም” በሚለው ድንቅ ንግግሩ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ የገባው ፕሮፌሰር ኃይሌ ምስላቸውንና ድምጻቸውን ባስቀረው በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተነሳ በታሪክ ፀሐፊያን ዘንድ ተፈላጊ የመረጃ ምንጭ ነው። ከ30 ዓመት በላይ የለፋበትና ሌሎች ሃሳቦቹ ወደ ስክሪን ተቀይረው ለማየት በመናፈቅ አበቃን።

 ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You