የጥምቀት በዓል አከባበር በሀገራችን

ልጆችዬ ሰላም ናችሁ? እንዴት ናችሁ? እንኳን አደረሳችሁ ብለናል በዓሉን ለምታከብሩት ሁሉ። ‹‹እንኳን አብሮ አደረሰን›› አላችሁ አይደል? ጎበዞች። ልጆች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ነው።

የበዓሉ ክዋኔ የሚጀመረው የከተራ ዕለት ማለትም ጥር 10 ቀን ነው። ታዲያ ልጆችዬ በዚህ ወቅት ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው (በክብር ከሚቀመጡበት ቦታ) በካህናት፣ ቀሳውስት ዝማሬ፣ ሽብሸባ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ሕፃናትና ወጣቶች ኅብረ ዝማሬ፣ በእናቶች እልልታ፤ እንዲሁም በአባቶች ጭብጨባ የታጀበ ነው።

ታዲያ ልጆችዬ ከበዓሉ ቀደም ተብሎ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። እነርሱም የታቦት ማደሪዎችን፤ እንዲሁም፣ ታቦታቱ የሚያርፉበትን ስፍራ፣ መንገዶችን ማስተካከል፤ አደባባዮችን እና ሌሎችን የማስዋቡ ሥራ የሚጀምረው ከበዓሉ በፊት ሲሆን፤ አካባቢዎችን የማጽዳቱ ሥራ ላይም የሃይማኖቱ ተከታዮች በተጨማሪ ተከታይ ያልሆኑትን ጨምሮ ተሳትፎ በማድረግ በፍቅር እና በመተሳሰብ አንዱ ሌላውን ሲያግዝ በሚገባ ተመልክታችኋል ብዬ እገምታለሁ።

ልጆችዬ የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያው በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በፈለገ ዮርዳኖስ (በዮርዳኖስ ወንዝ) በውሃ እንደተጠመቀ የሃይማኖት አባቶች ያስረዳሉ። አምላክ ሆኖ ሳለ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ (በሰው እጅ) መጠመቁ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ እና ትሕትና ለማስተማር እንደሆነ መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ያስረዳሉ። እርሳቸው እንደሚያስረዱት ከሆነ በዓሉ “የአስተርዮ በዓል” ወይም “የመገለጥ በዓል” ተብሎ ይጠራል።

ይህንን አብነት በማድረግ በጥምቀት ዕለት ካህናት አባቶች በዓሉን ለማክበር ከተለያየ ሥፍራ የተሰባሰበውን ምዕመን (የሃይማኖቱን ተከታይ) ፀበል በመርጨት እና ሌሎች ሥርዓቶችን በመከወን በድምቀት ያከብሩታል። በተጨማሪም፣ ታቦታቱ ባረፉበት ስፍራ ላይ ምዕመናን ተሰባስበው በዝማሬ፣ በቅዳሴ፣ በስብከት፣ ፀበል በመርጨት እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ያከብሩታል።

የጥምቀት ቀን በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበር ሲሆን፤ በካህናት፣ ዲያቆናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በያሬዳዊ ዝማሬ ታቦታቱ ካደሩበት ስፍራ ወደ መንበረ ክብራቸው ይሸኛሉ። በዚህ ወቅት እናቶች፣ አባቶች፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ወጣቶች እና ልጆች ነጭ ልብሳቸውን ለብሰው፤ የሌላቸው ደግሞ አጥበው እንዲሁም አሳምረው በድምቀት የሚከብሩት ታላቅ በዓል ነው።

ልጆችዬ፣ የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ ክንውኑ ጎን ለጎን በባሕላዊ መንገድ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ይከበራል። ልጃገረዶች፣ እናቶች እና ወጣቶች ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› ብለው አዲስ ልብስ አዘጋጅተው፤ ፀጉራቸውን ሹሩባ ተሠርተው፤ አምረው እና ደምቀው ወደ አደባባይ በመውጣት በነፃነት ያከብሩታል።

ወጣት ወንዶች እና አባቶችም በተመሳሳይ ራሳቸውን በሚገባ አስውበው በጋራ በመጨፈር የጥምቀትን በዓል በዚህ መልኩ ያከብሩታል። በዚህም ምክንያት ነው በዓሉ ከሀገራችን አልፎ የውጭ ሀገራት ዜጎች ትኩረትን መሳብ የቻለው፤ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከልም ተጠቃሽ ለመሆን የበቃው።

ልጆችዬ፣ እናንተስ እንዴት ነው በዓሉን ያከበራችሁት? በቤተክርስቲያኒቱ ጥር 12 ቀን ቃና ዘገሊላ ተብሎ ይጠራል። ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት በቀር ሁሉም ታቦታት ወደ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ። ስለዚህም የሚካኤል ታቦትን ለማስገባት ከጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር 12 ድረስ በአደባባይ ታቦታቱን በመሸኘት እና በማስገባት እንደየቦታዎቹ መለያየት የሚከበር ይሆናል።

የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ እናተም በዝማሬ፣ በእልልታ እና በደስታ ከቤተሰባችሁ ጋር በጋራ እንደምታሳልፉ ምንም ጥርጥር የለኝም። ደግሞ ከቦታ ቦታ ስትንቀሳቀሱ ከረሜላ፣ ፕሪም፣ ብስኩት እና የለስላሳ መጠጦችን እየጠጣችሁ ዘና እያላችሁ እንደምታከብሩት ተስፋ አደርጋለሁ።

ሌላው ደግሞ ልጆችዬ፣ የጥምቀት በዓል ከሌሎች በዓላት በአደባባይ የሚከበር በዓል ሲሆን፤ መዘምራን እንደ በገና፣ መሰንቆ፣ ከበሮ፣ ጸናጽል እና ሌሎች ለመዝሙር የሚያገለግሉ መንፈሳዊ የመዝሙር መሣሪያዎች በስፋት ግልጋሎት ላይ ሲውሉ ይስተዋላል።

እንዲሁም ወጣቶች በጋራ አንድ አይነት ልብስ በማሰፋት፤ ጸጉራቸውን በማስዋብ በዓሉን በድምቀት ሲያከብሩ ተመልክታችኋል ብዬ እገምታለሁ። ልጆችዬ፣ በድጋሚ እንኳን አደራሳችሁ በማለት፤ መልካም መልካሙን ሁሉ እየተመኘን ለሳምንት በሰላም ያድርሰን ብለን በመመኘት እንሰነባበት።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You