በቅርቡ በአዲስ ክልልነት የተደራጀ ነው፤ የልዩ ልዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መገኛ እንደመሆኑም፣ ለቱሪስት መስህብነት ሊውሉ የሚችሉ ባህላዊ እሴቶች ሞልተዋል። የበርካታ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶች መገኛም ነው። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል።
የክልሉ የቱሪስት መስህቦች እንዲለሙ ቢደረግ የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ሊሆኑም ይችላሉ፣ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹ መስህቦች እንዲለሙ ሳይደረጉ ቆይተዋል። በክልሉ በእነዚህ መስህቦች አካባቢ ሪዞርቶችንና ሆቴሎችን ሎጆችን ለማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም ክልሉ ምቹ አሰራር ዘርግቶ እየተጠበቀ ይገኛል።
ከሀገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ክልል፤ ስሙ እንደሚያመለክተውም በሀገሪቱ መካከለኛ ስፍራ ላይ ይገኛል። ከኦሮሚያና ከአዲሱ የደቡብ ክልል ጋር ይዋሰናል። መነሻቸውን አዲስ አበባን ያደረጉና በቱሪስቶች በመጎብኘት ወደሚታወቁት የሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚጓዙ ቱሪስቶች ከሚተላለፉባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ይህን ክልል ሰንጥቆ ነው የሚያልፈው።
የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ወንድሙ አባተ እንደሚሉት፤ ክልሉ የቱሪስቶች መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ የበርካታ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቦች መገኛ ነው። ከተፈጥሮ ጸጋዎቹ መካከል ፓርኮች፣ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች ይጠቀሳሉ። ፓርኮቹ የአያሌ የዱር እንስሳትና አእዋፋት እንዲሁም እጽዋት መገኛ ናቸው፤ ጊቤ ወንዝን የመሳሰሉ ወንዞችና በርካታ ፏፏቴዎችም የሚገኙበት ሲሆን፣ ሐይቆች፣ ለቱሪስት መስህብ ሊውሉ የሚችሉ ተራራዎች፣ ዋሻዎች በብዛት ይገኙበታል።
ከሀገሪቱ 87 ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ በዚህ ክልል ይገኛል፤ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ ከሚገኙ ፓርኮች አንዱ ነው። በፓርኩ አጥቢ የዱር እንስሳትና ልዩ ልዩ አእዋፋት ይገኛሉ፤ ፓርኩም ፣ ሸለቆውም፣ እነዚህ አእዋፋቱም የዱር እንስሳትም ለቱሪስት መስህብ መሆን የሚችሉ ናቸው። ይህ ፓርክ የሚገኘውም በክልሉ ጉራጌ ዞን ነው።
ጊቤ ሸለቆ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የዓሣ ሀብት እንዳለ አቶ ወንድሙ ጠቅሰው፣ በአካባቢው ሳሮ ቢራ የሚባል መስህብ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት። ሳሮ ቢራ ግልገል ጊቢ ሶስት አካባቢ ያለ ትልቅ ሀብት ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፣ ያ ቦታ ቢለማ ለሀገሪቱም ትልቅ የቱሪዝም መስህብ ሊሆን እንደሚችል አስታውቀዋል።
ክልሉ በሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብቶቹም እንደሚታወቅ የቱሪዝም ባለሙያው ይናገራሉ። እአአ በ1980 በዩኔስኮ የተመዘገበውና በጉራጌ ዞን የሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋይ በቱሪስቶች በእጅጉ የሚታወቅና የሚዘወተር እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ዋሻዎች፣ የቱሪስት መስህብ ሊሆን የሚችለው የዘበይደር ተራራም ሌላው የዚህ ዞን የቱሪስት መስህብ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከንባታ ዞን የሚገኘው የአምበሪቾ ተራራ የኮሙኒቲ ቱሪዝም መስህብ ሌላው የክልሉ መስህብ ነው። ይህ መስህብ በዞኑ አስተዳደርና ተወላጆች ተደርጎ የቱሪስት መዳረሻ መሆን ችሏል። ከዚህ በዞኑ አስተዳደር እየተዳደረ የሚገኝ የቱሪስት መስህብ ተራራ አናት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ 777 ደረጃዎች ተሰርተዋል፤ ተራራው ከባህር ወለል በላይ ያለው ከፍታም ወደ 3ሺ80 ሜትር ነው። በጣም ያምራል፤ ጉም ይመላለስባታል፤ ቅዝቃዜው አይጎዳም ሲሉም አቶ ወንድሙ ያብራራሉ።
‹‹በጣም የሚገርመው ገና ተራራው ግርጌ ላይ ስትደርስ በእድሜህ ላይ አምስት ዓመት፤ ስታጋምስ ሌላ አምስት ዓመት፣ ደረጃውን ስትጨርስ ሌላ አምስት ዓመት ትጨምራለህ ይባልለታል ሲሉ የቱሪዝም ባለሙያው ጠቅሰው፣ ተራራውን በመጎብኘትህ በጥቅሉ በእድሜህ ላይ አስራ አምስት ዓመት ትጨምራለህ እየተባለ እንደሚነገርለትም አብራርተዋል።
‹‹777›› የሚለው ትርጉም እንዳለውም ነው የገለጹት። ሰባት ቁጥር በብሔረሰቡ ብዙ ትርጉም አለው፤ ከሶስቱ አንዱ ሰባት ወንዞችን ያመለክታል፤ ሌላው ሰባት በአካባቢው ያሉ ሰባት ተራራዎችን እንዲሁም ሌላው ሰባት ጥንት የከንባታ ማህበረሰብ ሰባት ጎሳ ሆኖ ወደ አካባቢው በመምጣት እዚህ ተራራ ሥር መኖር እንደጀመረ ያመለክታል።
አቶ ወንድሙ እንዳሉት፤ የአምበሪቾ ተራራ አናት ላይ መቶ ሺ ሰው ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ሜዳ ይገኛል። ሜዳው አውሮፕላን ማሳረፍ እንደሚችልም ይገለጻል፤ ከ777 ደረጃው በላይ ገና ደረጃ አልተሰራም፤ ሳያልቅ መናገር ስለማያስፈልግ እንጂ አሁንም በአካባቢው ብዙ እየተሰራ ነው ይላሉ።
የአምበሪቾ ተራራ በጣም ያምራል፤ ተራራው ስር ባለው ሜዳማ ቦታ ላይ ጥንት የፈረስ ግልቢያ ይካሄድበት ነበር፤ አሁንም ቱሪስቶች ፈረስ መጋለብ ከፈለጉ ሜዳው ምቹ ነው፤ በግልም ሆነ በቡድን ቱሪስቶች ወደ አካባቢው መጥተው ካምፕ ሲያደርጉ የአካባቢው ማህበረሰብ እንሰት እንዴት እንደሚፋቅ፣ እንዴት ምግቡ እንደሚዘጋጅ ያሳያል ሲሉም ያብራራሉ።
አቶ ወንድሙ ሌላው የክልሉ የቱሪስት መስህብ በወላይታ ድንበር ላይ የሚገኘው የአጆራ ፏፏቴ መሆኑን ጠቁመዋል። በጉራጌ ዞን ከሚገኘው ትክል ድንጋይ በተጨማሪ በዩኔስኮ ያልተመዘገቡ ትክል ድንጋዮች በክልሉ ስልጤ ዞን፣ በየምም እንዳሉ ይናገራሉ። ይህ ክልል በትክል ድንጋይ ዙሪያ ብዙ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ሊደረግበት እንደሚችልም ነው ያመለከቱት።
ሐይቆች ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ናቸው። በርካታ ትንንሽ ሐይቆች በክልሉ የሚገኙ ሲሆን፣ በሀዲያ ጭፍራ መሀሉ ደሴት ያለበት በርካታ ወፎች የሚታዩበት ሐይቅ እንዳለ ጠቁመዋል። በዚሁ ዞን ጉማሬ በስፋት የሚታይበት ቡዳ ማዶ በሚባል አካባቢ ጉዮ የሚባሉ ሐይቆች እንዳሉም አመልክተው፣ በስልጤ ዞን ላይ ቀለሙን የሚቀያይር ‹‹ሀረ ሼጣን›› የሚባል ሐይቅ እንዳለም አስታውቀዋል። አካባቢው ኢንቨስትመንት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ምቹ ሥፍራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀላባ የአልቶ ፍልውሃ፣ ሌሎችም ለቱሪስት መስህብነት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ፍል ውሃዎች በክልሉ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት። በክልሉ ሁሉም ዞኖች ዋሻዎችም እንዳሉም ጠቅሰው፣ ከንባታ ዞን ላይ አንድ ሺ ሰዎችን መያዝ የሚችል ሶኪቾ የሚባል ዋሻ እንዳለም አመልክተዋል።
በክልሉ በዓመት አንዴ ለባህላዊ መድኃኒት የሚውሉ እጽዋት ለቀማ የሚካሄደበት አካባቢ እንዳለም ገልጸው፣ ይህ በየም ብሔረሰብ ዘንድ የሚካሄደው ባህላዊ ዓመታዊ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት የቱሪዝም መስህብ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የየም ብሔረሰብ በየዓመቱ ጥቅምት 17 በየዓመቱ የሚፈጸመው ይህ ሥነ ሥርዓት ከኢትዮጵያ ውጭ በየትኛውም የዓለም ክፍል አይፈጸምም። ማኅበረሰቡ መድኃኒቱን ለእንስሳትም ለሰውም ህመም መፈወሻነት ይገለገልበታል፤ በዓመት አንዴ የሚሰበሰበውን ይህ ባህላዊ መድኃኒት ማህበረሰቡ ዓመቱን ሙሉ ይጠቀምበታል።
ክልሉ ባለፈው ጥቅምት ወር በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ የቱሪስት መዳራሻዎቹንና መስህቦቹን አስጎብኝቷል። አቶ ወንድሙም እነዚህን መስህቦች አስመልክቶ መረጃ በሰጡን ወቅት የክልሉን መስህቦች የተመለከቱ ምስሎች በቪዲዮ እንዲሁም የክልሉ ብሔረሰቦች ከሚገለገሉባቸው ቁሳቁስ የተወሱነት ቀርበው ታይተዋል። የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች የሚያመለክቱ ቁስቁስንም አስጎብኝተዋል።
ከክልሉ ባህላዊ ቁሳቁስ መካከልም ጥቁቱ በአውደ ርዕዩ ቀርበዋል። ከቀንድ የተሰሩ ማንኪያዎች፣ የምግብ ማውጫዎች፣ መጠጫ ዋንጫዎች፣ መለኪያ፣ ሌማትና የመሳሰሉትን አስጎብኝተዋል። በሀላባና ከንባታ ብሔረሰቦች ዘንድ ፀሐይ መከላከያ ስለሚጠቅመው ቆቤ የተሰኘው ኮፍያ አሰራርና ጠቀሜታ አብራርተዋል።
በክልሉ ከእንሰት ልዩ ልዩ ምግቦች ከመመረታቸው ባሻገር ተረፈ ምርቶቹም ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚውሉ ተናግረዋል። የእንሰት ምርት የመጨረሻው ተረፈ ምርት ቃጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ተረፈ ምርት በርካታ ቁሳቁስ እንደሚመረቱም ነው ያብራሩት። ከቃጫ ውጤት የሚመረተው ቦርሳ እስከ አንድ ሺ ብር እንደሚሸጥም ጠቁመዋል።
በሀዲያ ለጋብቻ ቃል ኪዳን ሲታሰርና እርቅ ሲፈጸም በጋራ ወተትና የመሳሰሉት የሚጎነጩበት ሁለት አፍ ስላለው ቁስም /ገንቦ/ አቶ ወንድሙ አብራርተዋል። በሀዲያ ብሔረሰብ ዘንድ በዚህ ሥነ ሥርዓት የተጋቡ ጥንዶች ተፋትተው አያውቅም ተብሎ እንደሚነገርም ገልጸዋል። በነፍስ የሚፈላለጉ ጠበኞች ከእርቅ በኋላ በዚህ ቁስ ከጠጡ ሁሉም ነገር እንደ ቀድሞው መሆን አለበት ተብሎ ይታሰባል ሲሉም ነው ያብራሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ በክልሉ የቱሪዝም እምቅ አቅሞች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው። በማስተዋወቅ በኩል እየተከናወኑ ካሉት ተግባሮች መካከልም ባለፈው ጥቅምት ወር በሳይንስ ሙዚየም የተከናውነው ተግባር አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል።
በክልሉ ከጉራጌ ዞኑ ትክል ድንጋይ እንዲሁም በቅርቡ መጎብኘት ከጀመረው የአምበሪቾ ተራራ ውጭ በቱሪስት መስህብነት እያገለገለ ያለ መስህብ የለም ይባላል፤ በዚህም የተነሳ የክልሉ ዞኖች መተላለፊያ እንጂ መስህብ አይደለንም እያሉ ናቸው፤ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ምን ሊሰራ ታስቧል የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ ወንድሙ፣ ክልላችን አዲስ ነው፤ አሁን ለመሥራት እየታሰበ ያለው ማስተዋወቅ ላይ ነው ሲሉ መልሰዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በቀደመው የደቡብ ክልል ወቅት የአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎች ተረስተው ነበር፤ ቱሪስቱ የሚሄደው ወደ ኦሞ ሸለቆና ብሔራዊ ፓርኮች ነበር። መዳረሻዎቹ ወደ አርባ ምንጭና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ነበሩ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ክልሉ የቱሪስት መስህቦቹን ማስተዋወቅ ላይ እየሰራ ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሄደውን የቱሪዝም አውደ ርዕይም ክልሉ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞበታል፤ አንድ ወር ሙሉ መስህቦቹን አስተዋውቋል፤ ሸጧል። ክልሉ ለቱሪስቶች ምቹ ቦታ ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ በሚገባ ማስተዋወቅ ችሏል። መንግሥት የክልሉን የቱሪስት መስህቦች ለማልማት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ባለሀብቶች በልማቱ እንዲሳተፉ ይፈልጋል፤ ለዚህም በክልሉ ብዙ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።
መድረኩን እንደ አዲስ ክልል ክልላችንን አስተዋውቀንበታል፤ የቱሪስት ሀብቶቻችንም በሚገባ አስተዋውቀንበታል ሲሉ አቶ ወንድሙ ጠቅሰው፣ ክልላችን በሆቴል፣ በእርሻ በቱሪዝምም ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ያለበት ሥፍራ በራሱ ምቹ ነው ይላሉ።
ከአውደ ርዕዩ እንደ አዲስ ክልል ሌሎች ክልሎች መዳረሻዎቻቸውን ያለሙበትን መንገድ መረዳት ችለናል ያሉት አቶ ወንድሙ፣ ይህን ወደ እኛም አካባቢ ወስደን እንጠቀምበታለን ብለዋል። ታዋቂ አስጎብኚ ማህበራትንም ወደ ክልላችን ለመሳብ የሚያስችለንን ሁኔታም አግኝተናል ብለዋል።
በአዲሱ ክልል በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እያሉ እንዲለሙ ሳይደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በአዲሱ ክልል ለመታየት የታጩት የጥያ ትክል ድንጋይና በቅርቡ የተዋወቀው አምበርቾ ተራራ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እነሱም ቢሆኑ በበቂ ሁኔታ የለሙ አይደሉም ነው ያሉት።
ለማልማት በቅድሚያ የመለየት ሥራ መሥራት ይኖርበታል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ ከዚያም የማስተዋወቅ ሥራ መሠራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት። እሳቸው እንዳሉት፤ አዲሱ የክልሉ መንግሥት ከቀዳሚ ሥራዎቹ መካከል ቱሪዝምን አድጓል። በክልሉ በርካታ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች አሉ። ለምሳሌ በስልጤ ዞን እኛም እናልፋለን፤ እንደ ቱሪዝም ባለሙያ ሳያቸው መስህቦቹ እንደ መስህብ አልለሙም፤ መልማት ማለት የራሱ ሳይንስ አለው፤ ካልለማ ምኑን ነው የምናስተዋውቀው። የምናስጎበኘውን በቅድሚያ ማልማት አለብን›› ሲሉ አብራርተዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም