እንዲህ ጆሮ በዘግናኝ ዜና ሲደማ፤ ዓለም ከውበቷ የደበዘዘች እስኪመስል መሰልቸትን ደጋግማ ስታድልህ፤ ነባራዊው ዓለም የሰዎችን ማንነት መልሶ በማንፀባረቅ ጥላቻን፣ ፀብን፣ አመፃን፣ መታበይን እኩይን ሁሉ ተላብሶ ስጋት ውስጥ ሲጨምርህ የዛን ሰዓት ካለህበት ፈቀቅ በል፣ መጽሐፍ ግለጥ! በዚያ እረፍት፣ በዚያ ትምህርት፣ በዚያ መፍትሄ አለ፤ ከምድር ትርጉምና ፍቺ እስከ ሰማያት ቁልፍ ብራና ውስጥ በፊደል ተሰድሮ አለ!
ፍጥረት በግብሩ ዝቅ ሲል አንተ ግን ተነጠል፣ በርሀን ዘርግተህ መገለጥን ሻት፣ ወደ ከፍታህ ተጓዝ። ንባብ አይነተኛው የመገለጥ መንገድ ነው። ታዲያ ይህንን መንገድህን ቀና እና ቀጥተኛ ከሚያደርጉልህ ነገሮች አንዱ በመንደርህ እና በአካባቢህ ቤተ መጻሕፍትን የሚያቋቁሙ ብርቱ ልብ እና ነፍስ ያላቸው ሰዎች ናቸው።
ዛሬ ከእነዚህ መልካም ስብእና ባለቤት ከሆኑ ሰዎች መካከል ከወደ ደብረ ብርሃን የፈለቀው የደጋዋ ፈርጥ መምህር መዘመር ግርማ አንዱ ናቸው። መምህር መዘምር ግርማ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆን የራስ አበበ ወልደ አረጋይ ቤተ መጽሐፍ መሥራች እና ባለ ራዕይ ናቸው።
የራስ አበበ ወ/አረጋዊ ቤተ መጻሕፍት
መምህር መዘመር በቅድሚያ “ሁቱቱሲ” የተባለችውን የማካሌሌ መጽሐፍ ተረጎሙ፤ በመቀጠልም ይህንኑ መጽሐፍ ለማስተዋወቅ ማሰባቸውን ይናገራሉ። በመምህር መዘምር ግርማ ተተርጉማ የቀረበችን አንድ መጽሐፍ ከማስተዋወቅ ብቻ ለምን ሌሎች መጽሐፍትን አምጥቼ እያስነበብኩ እንዲሁም እየሸጥኩኝ አልቀሰቅስም በማለት የተለያዩ መጽሐፍትን ከአዲስ አበባ በማምጣት ወደ ተግባር ገብተዋል። በዚህም ምክንያት ራስ አበበ ወ/አረጋዊ ቤተ መጽሐፍ ተመሰረተ፤ ስራም ጀመረ።
ለምን በራስ አበበ ወ/አረጋዊ ስም ተሰየመ የሚለውን መምህሩ ሲያብራሩ፤ ራስ አበበ ፋሽስት ጣሊያንን ዕድል ነፍገው ኢትዮጵያን በቀላሉ ነጻ እንድትወጣ ያደረጉ እና በሸዋ ያሉ አርበኞችን በማስተባበርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አርበኛ በመሆናቸው እና መታሰቢያ ስለሚስፈልጋቸው በስማቸው ቤተ መጽሐፉ እንዲሆን አድርጌያለሁ ብለዋል።
ቤተመጽሐፉ በደብረ ብርሃን ከሚገኙ ሁለት የመንግሥት ቤተ መጽሐፍት ቀጥሎ በግል የተቋቋመ ቤተ መጽሐፍ ነው። ስለሆነም የመጀመሪያ ስራው ማንኛውም አንባቢ በቤተ መጽሐፍ ቤቱ ተገኝቶ በነጻ መጽሐፍትን ማንበብ እንዲችል ማድረግ ሲሆን ይህንን እያደረገም ይገኛል። አንዳንዴ ቤተ መጽሐፍት ብዙ አንባቢ ሲበዛ አንባቢው ውጭ ቁጭ ብሎ ያነባል፤ የማስፋፋት ስራ መስራት አለብን ብለዋል።
ሌላኛው መፅሀፍ የማዋስ ስራ የሚሰራ ሲሆን መምህር መዘመር ግርማ እንደሚሉት ቤተ መጽሐፉ በቀን ቢያንስ ከ70 እስከ 80 መጽሐፍ ያውሳል። ይህ አገልግሎት ወጣቶች የፈለጉትን መጽሐፍ የፈለጉበት ቦታ ሆነው እንዲያነቡ ለማበረታታት እንዲሁም እድሉን ለመፍጠር ተብሎ የተዘጋጀ ሲሆን መጽሐፉን በሚዋሱበት ጊዜም የሚጠይቁት መታወቂያ ብቻ ነው። በብዛት የሚያነቡትም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ቤታቸው ለማንበብ የሚ ረብሻቸው ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ጫካ ሄደው ያነባሉ።
ፊደል ላላወቁ ልጆች ፕሮግራም
ይህም ልጆች ፊደላትን እንዲለዩ የሚያደርግ የተለያዩ ስልቶችን የያዘ እና የፊደል ማንበብ ክህሎትን የሚጨምር መጽሐፍትን በውስጡ የያዘ ቤተ መፅሐፍ ነው። በብዛትም ህጻናት የሚገኙበት ቤተ መጽሐፍ ነው። ሌላኛው ደግሞ በአፍሪካ ኢኒሼቲቭ አማካይነት የሚዘጋጅ ልጆች የውይይት እና የስልጠና አገልግሎትም ይሰጣል፤ ህጻናት የተረት መጽሐፍት ሲጻፉ ይወያያሉ እንዲሁም አስተያየት ይሰጣሉ።
ተረት ላነበቡ ልጆች ሽልማት
በዚህም ደብረ ብርሃን የሚገኙ ህጻናት በአንድ ዓመት 42 ተረቶችን ካነበቡ የሚሸለሙ ሲሆን ከዚህ ቀደም በዓመት 42 ተረት ላነበቡ 24 ህጻናት ሽልማት ተሰጥቷል። እንደ መምህር መዘምር ገለጻ ህጻናቱ አንድን ተረት ከማናበብ ባሻገር በተለያዩ ተግባራት መግለጽ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህም በስዕል፣ በድራማ፣ መልሶ በመናገር እና በመሳሰሉት ተግባራት እንዳይረሱት እንዲማሩበት ይደረጋል።
ልጆች ቆመው እንዲያነቡ
ይህ ስልት ከንባብ ባሻገር በራስ መተማመን እንዲያዳብሩ ብሎም በየትኛው ሁኔታ ያወቁትን ለሰው እንዴት ማቅረብ እንደሚችሉ የሚረዳ አንዱ ክህሎት ሲሆን ይሄ ቤተ መጽሐፉ የሚሰጠው አገልግሎት ነው። እዚህ ጋር ልብ ልንለው የሚገባው አንድ ነገር አለ፤ ይላሉ መምህሩ፤ ‹‹ህጻናት ላይ በጣም የምናተኩረው ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሳትንበረከክ በአባቶቻችን ጀግንነትና የሃገር ፍቅር ስሜት ተከብራ የቆየች ቢሆንም፤ ከምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ከካፒታሊዝም የውድድር መንፈስ፣ ከኢምፔሪያሊዝምና ከሉላዊነት (Globalization) የባህል ወረራ የተነሳ ባህላዊ አስተሳሰብ ሁሉ የዘመናዊ ተቃራኒ፣ የበታችና ኋላቀር እንደሆነና በ“ዘመናዊው አስተሳሰብ” ሊተካ እንደሚገባ የሚያወሳ የተዛባ ግንዛቤ ይዘው በልበ ሙሉነት የሚሞግቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍ ያለ ነው።
እናም ይህንን አስተሳሰብ ለመምራት እና አገራዊ እውቀቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንሰራለን›› ይላሉ መምህር መዘምር ግርማ። ከዚህም ባሻገር ምዕራባውያን “ዘመናዊነት” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጀማሪ ስለሆኑና ኢትዮጵያም በማደግ ላይ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ስለሆነች፤ ዘመናዊ ለመሆን ምዕራባውያንን መምሰል አለባት በሚል የአስተሳሰብ ህጸጽ (Fallacy) ተነድተው ዘመናዊነትን ከምዕራባዊነት ጋር እስከማቆራኘትና የራስን ባህልና ስልጣኔ እስከ ማንቋሸሽ የደረሱም አሉ።
በአንዳንድ የማህበረሰቡና የግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት ተማሪዎች በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሳይኛ ካልሆነ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መናገር፣ ማንበብና መጻፍን እንደ አሳፋሪ ነገር ሲቆጥሩና በሚሞክሯቸው የአውሮፓ ቋንቋዎች ሲመጻደቁ መመልከት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ለጉዳዩ አሳሳቢነት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በእርግጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ቀድመው ከሰለጠኑ ሃገሮች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፍልስፍና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ልማትን ለማፋጠን መገልገላቸው ከበደል የሚቆጠር ሆኖ አይደለም።
ነገር ግን “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንዲሉ የሌሎችን እያደነቁ የራስን ስልጣኔ መናቅ፤ የሌሎችን ባህል እያስፋፉ የራስን ማዳከምና ማጥፋት ግን ተሞክሮ ከመውሰድ በእጅጉ የራቀ ነው። ስለዚህም በቤተ መጽሐፉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ክብር ተሰጥቶት እንዲያውቁት ያደርጋል። ከዚያም ባሻገር በውጭ የተጻፉ የተረት መጽሐፍት እንኳን እንዲተረጎሙ በማድረግ ለህጻናቱ ይቀርባል። አገራዊ እውቀት ትልቅ ክብር እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ሌላኛው ደግሞ ከንባብ አገልግሎት በተጨማሪም የስነጽሁፍ ምሽት ይዘጋጃል። ይህም ጀማሪ እና ወጣት ጸሐፊዎች ፅሑፋቸውን የሚያቀርቡበት የሚለማመዱበት እንዲሁም ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ ነው።የመምህር መዘመር ግርማ ስራ እጅግ ሊበረታታ እና ሊደገፍ የሚገባ የጀብደኝነት ስራ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011
አብርሃም ተወልደ