ቡና ቀማሹ ሥራ ፈጣሪ

 የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ ምኒልክ ሀብቱ ይባላሉ። የምኒልክ ኢንጅነሪንግና የ‹‹ቲፒካ ስፒሻሊቲ ኮፊ›› ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው። ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ከ11 ቤተሰብ አባላት ካሉበት ቤተሰብ የወጡት እኚሁ ሰው ወላጆቻቸው ሥራ ወዳድና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሥራ ሳይንቁ እንዲሰሩ በማድረግ ያሳደጓቸው መሆኑን ያነሳሉ። በተለይ ደግሞ ታታሪው አባታቸው ሰርተው በማሰራት ልጆቻቸው ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት ብቃት እንዲያዳብሩ ያደረጓቸው መሆኑን ያስታውሳሉ።

አሁን ለደረሱበት ደረጃ እርሾ ሆና የጠቀመቻቸውን ገጠመኝ ሲያስታውሱ ‹‹የመጀመሪያ ገንዘብ ያገኘሁባት ሥራ የትምህርት ቤት ሽንት ቤት ጉድጓድ በመቆፈር ነው›› ይላሉ። በአንድ ወቅት ኳስ እየተጫወቱ ሳለ በአቅራቢያቸው ያለ አንድ ትምህርት ቤት መምህራን ሽንት ቤቱን ሳያስጠርጉ የትምህርት ቤት መከፈቻ ጊዜ መድረሱ አስጨንቋቸው ሲወያዩ ያደምጣሉ። ከሥራ ወዳድ ቤተሰብ የወጡት የያኔው ታዳጊ ምኒልክ፣ የመምህራኑን ጭንቀት አይተው ማለፍ አልቻሉም፤ ይልቁንም የመፍትሔ አካል ለመሆን ወደዱና እንደምንም አሳምነው ሊያግዟቸው ጥያቄ ያቀርባሉ። ይሁንና መምህራኑ በታዳጊው ልጅ ላይ እምነት ለመጣል አልደፈሩም።

ከብዙ ንግግር በኋላ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪው ምኒልክ ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ። ከወንድሞቻቸው ጋር በመሆን በአንድ ሳምንት ውስጥ ሌላ ጉድጓድ ቆፍረው መፀዳጃ ቤቱን አድሰው ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ አስረከቡ። ‹‹የትምህርት ቤቱ አመራሮች በሠራሁት ሥራ በጣም ስለተደሰቱ፤ ከውላችን ውጭ በእጥፍ ከፈሉኝ›› ይላሉ።

በዚያች አጋጣሚ በራስ ልፋት ገቢ ማግኘት የለመዱት እኚሁ ሰው 11ኛ ክፍል ሳሉ ደግሞ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለቴክኒክና መጋዘን ተቆጣጣሪ ባለሙያ ቅጥር ማውጣቱን ይሰሙና ሙያውን ያውቁት ስለነበር በድፍረት ይወዳደራሉ። እናም የ16 ዓመቱ ምኒልክ ዲግሪና ሰፊ ልምድ ከነበራቸው አንጋፋ ሰዎች ጋር ተዋዳድረው ፈተናውን በአንደኝነት አልፈው ተቀጠሩ። ግማሽ ቀን እየተማሩ በሥራቸው ረዳቶችን ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ። የወጣቱን ቅልጥፍና እና ትጋት ያዩ የወባ መከላከል ተቋም የሥራ ኃላፊዎች የመድኃኒት ማውረድና መጫን ሥራን በኮንትራት ሰጧቸውና ጎን ለጎን ሠራተኛ ቀጥረው በማሰራት የፋይናንስ አቅማቸውን አጎለበቱ።

ከቴክኒሻን አባታቸው ሥር ሆነው ልምድ እየቀሰሙ ማደጋቸውን የሚናገሩት አቶ ምኒልክ፤ ይሁንና ሙያውን ገንዘብ ለማግኛ እንጂ ወደውት ይሰሩት እንዳልነበር ይናገራሉ። ‹‹የእኔ ምኞት ፓይለት ወይም ሐኪም መሆን ነበር፤ አባቴም ‹ፓይለት ትሆናለህ› እያለ ነው ያሳደገኝ፤ ግን የሚጠየቀውን መስፈርት ማሟላት ባለመቻሌ የምፈልገውን መሆን አልቻልኩም›› ይላሉ።

በመሆኑም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በ‹‹ላይብረሪ ኤንድ ኢንፎርሜሽን ሳይንስ›› ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተው እንደወጡ በቀጥታ አባታቸውን በቴክኒኩ ያግዙ ጀመር። በኋላም አባታቸውን በሞት ሲያጡ ምኒልክ ኢንጂነሪግ የተሰኘውን የአባታቸውን ድርጅት የመረከብና ቤተሰቡን በፋይናንስ የማስተዳደር ኃላፊነት እሳቸው ላይ ወደቀ።

‹‹በወቅቱ ሥራውን ስረከብ እኔና ታናሽ ወንድሜ ብቻ ነበርን፤ በሂደት ግን ሌሎቹ ልጆች በእረፍት ጊዜያቸው አብረውን እንዲሰሩ በማድረግ ምኒልክ ኢንጅነሪንግን እያሳደግን መጣን›› ይላሉ። በየጊዜው ከውጭ ሠራተኞችን በመቅጠርም ትልልቅ የኢንጂነሪንግ ሥራዎችን ተረክበው የመሥራት አቅም ማጎልበታቸውን ይናገራሉ።

‹‹አልችልም›› የሚሉት ሥራ እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ምኒልክ፣ ከሙያቸው ውጭ የሆነ ሥራ እንኳን ሲታዘዙ ተረክበው የሚችሉ ሠራተኞች ቀጥረው በማሰራት ለደንበኞቻቸው እንደሚያስረክቡ ያስረዳሉ። ‹‹በዚያ ሥራ ባላተርፍበትም እንኳን ሙያ እለምድበታለሁ፤ ደንበኞችን አፈራበታለሁ ብዬ ስለማምን አልችልም ብዬ የምገፋው ሥራ የለም›› በማለት ይገልፃሉ።

ይህም ጥረታቸው ታዲያ ለፍቶ መና አላስቀራቸውም። የኢንጂነሪንግ ኩባንያቸው እየተስፋፋ ሄዶ ‹‹ቲፒካ ስፔሻሊቲ›› የተባለውን ድርጅት ወለደ። ይህን ድርጅት የከፈቱበትን አጋጣሚ ሲናገሩ ‹‹እኛ የተለያዩ ማሽኖችን እናመርታለን፤ ግን ደግሞ የምናመርታቸው ማሽኖችን ጥራት ሞክሮ ማሳየት ይጠበቅብን ነበር፤ በዚህ ምክንያት የቡና መቁያ ማሽናችንን ጥራት ለደንበኞቻችን ለማሳየት ስንል ቡና ቆልተን ማሳየት ነበረብን፤ ነገር ግን ቡናውን ቆልተን ማስቀመጥ ኪሳራ በመሆኑ ቡናውን ቆልተን የምንሸጥበት ሌላ ድርጅት ከፈትን›› ይላሉ።

‹‹ቲፒካ›› ማለት የመጀመሪያው የቡና ዘር ሳይንሳዊ ስያሜ እንደሆነ አስረድተው፤ ‹‹ቲፒካ ዓለም ላይ የሚታወቀው አረቢካ ቡና ዋና ዘር ነው፤ የኢትዮጵያን ቡና ወደ ገበያ ያወጡት አረቦች በመሆናቸው የእኛን ቡና በራሳቸው ስም መሰየሙ ሁልጊዜም ስለሚቆጨኝ ነው በሳይንሳዊ ስሙ እንዲታወቅ ስል የሰየምኩት›› ሲሉ ያብራራሉ። ድርጅቱ አረንጓዴ እና የተቆላ ቡና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑን አንስተው፤ በስሩ አምስት ራሳቸውን የቻሉ ተቋማትን መፍጠሩን ይገልጻሉ። ከእነዚህም መካከል በቡና አቆላልና አፈላል እንዲሁም ቡና የመቅመስ ችሎታን የሚያዳብሩ ስልጠናዎችንና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መክፈቱን ያመለክታሉ።

በዓለም የተመሰከረለት ቡና ቀማሽ እንዲሁም ቆዪ የሆኑት አቶ ምኒልክ፣ በግላቸው ጥረት በቡና ላይ ባደረጉት ጥናትና ምርምር እንዲሁም የተለየ ጣዕም ያለው የኢትዮጵያ ቡና ራሱን ችሎ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ባበረከቱት አስተዋፅኦ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል። ‘ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ’ በተባለው ሀገር አቀፍ የቡና ቅምሻ ውድድር ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው እኚሁ ሰው በቡና መቁላት፤ በካይዘንና በመሳሰሉት ዘርፎች በርካታ ሰርተፊኬቶችን አግኝተዋል።

በቡና ላይ ያገኙትን እውቀትና ልምድ ግን ብቻቸውን ይዘው ለመዝለቅ አልወደዱም፤ ይልቁንም ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ በከፈቱት የስልጠና ተቋም ከሙያ ተቋማት የሚወጡ ወጣቶችን በመመልመል አጫጭር ሥልጠናዎችን መስጠት ጀመሩ።

ይህም በሀገር ውስጥ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲበራከት አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፤ በተለይም ቡናው የእኛ ሆኖ ሳለ የጥራት ደረጃውን የሚሰጠው አካል በውጭ ምንዛሬ ከሌላ ሀገራት የሚመጣ መሆኑ፤ ይህም የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጉዳይ በሌላ ሀገር እጅ ስር እንዲወድቅ የሚያደርግ መሆኑን በመረዳት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየተጉ ይገኛሉ። ‹‹ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከቡና መቁላት ጀምሮ እስከ ማፍላት ድረስ ባለሙያዎችን እናሰለጥናለን፤ ያሰለጠንናቸውንም መልሰን እንቀጥራለን፤ ሌሎችም እኛ አሰልጥነናቸው ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረዋል›› ይላሉ።

የኢትዮጵያ ቡና ቆዪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው ለስምንት ዓመታት ያገለገሉት አቶ ምኒልክ፣ ድርጅታቸው ለማህበሩ አባላትና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት በሙሉ በየዓመቱ ስልጠና ይሰጥ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም ከ100 ያላነሱ እውቅ የቡና ባለሙያዎችን ለሀገሪቱ ማበርከታቸውን ይገልፃሉ። በተያዘው በጀት ዓመት ማሰልጠኛ ተቋማቸው በጀማሪ ደረጃ 26፣ በመካከለኛ ደረጃ ደግሞ ስምንት ሰዎችን ማሰልጠኑን ይናገራሉ።

ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅታቸው ገበያው የሚፈልገውን በማጥናት የተለያዩ ሥራዎችን መስራቱን የሚናገሩት አቶ ምኒልክ፤ በአንድ ወቅት የኮንስትራክሽን ዘርፉን በመቀላቀል በቤቶች ግንባታ ላይ ከብሎኬትና ፕሪካስት ማምረት እስከ ቤት ግንባታ ድረስ ተሳትፎ ማድረጉን ይገልፃሉ። በተለይም ከሜቴክ ጋር በመተባበር የትራክተር ተጎታቾች፤ የመኪና ላይ ቆሻሻ መጫኛዎች፤ ሲሚንቶ ማቡኪያ መሳሪያ፤ ትልልቅ የውሃና የነዳጅ ታንከሮች የመሳሰሉትን ማምረቱንም ያመለክታሉ። ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በሀገሪቱ እጥረት በሚታይባቸው ዘርፎች ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ ለወጣቶች የተለያዩ ስልጠናዎችን በነፅ በመስጠት የሥራ እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን በመፍጠርም አቶ ምኒልክ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። በሀገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች በከፈቷቸው ሱቆች የተቆላ ቡና የሚያከፋፍሉ ሲሆን በተወሰነ ደረጃ ወደ ውጭም ይልካሉ። ሁለት ጊዜም ድርጅታቸው ያመረተውን የቡና መቁያ ማሽን ሃጂ ቱሬ በተባለ ድርጅት አማካኝነት ቻይና እና የመን መላካቸውን አቶ ምኒልክ ያመለክታሉ። በወቅቱ አምነው ሥራ ይሰጧቸው የነበሩ ተቋማት አሁን ለደረሱበት ደረጃ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ያነሳሉ። ‹‹እንደኛ ራሱን ለመቻል ጥረት የሚያደርግ ድርጅት የፋይናንስ አቅርቦት ማግኘት ከባድ በሆነበት ጊዜ እንደ ሜቴክና ሃጂ ቱሬ ያሉ ድርጅቶች አምነውን ቅድሚያ ክፍያ ሰጥተው ባያሰሩን ኖሮ እዚህ መድረስ አንችልም ነበር›› ሲሉ ይገልፃሉ።

አሁን ባለው የዓለም ገበያ ቡና ብቻውን ወደ ውጭ መላክ አትራፊ አለመሆኑን የሚያስረዱት አቶ ምኒልክ፤ በተለይም ጥሬ ቡና ወደ ውጭ ልኮ ገቢ ለማግኘት ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚፈልግ መሆኑን ይናገራሉ። በሌላ በኩል የሀገር ውስጡ የቡና ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛውን የቡና ምርታቸውን እዚሁ ሀገር ውስጥ ለመሸጥ መገደዳቸውን ያመለክታሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን የማስልጠንና ማማከር ሥራቸውን አጠናክረው ማስቀጠላቸውን ነው የሚያብራሩት።

በሌላ በኩል ከወጪ ንግዱ ጋር ተያይዞ የሚወጡ መመሪያና ደንቦች በአግባቡ የማይተገበሩ በመሆናቸው ሃቀኛ ነጋዴው ከገበያ ውጭ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ይናገራሉ። ለአብነት አድርገው ሲጠቅሱም ‹‹ቱሪስቶች የእኛን ሀገር ቡና በጣም ስለሚወዱ ወደ ሀገራቸው ይዘው መሄድ ይፈልጋሉ። ይሁንና እሴት የተጨመረበት ቡና በውጭ ምንዛሬ ቢገዙም ከሁለት ኪሎ በላይ ይዘው መውጣት ይከለከላሉ። እኔ ታክስ ከፍዬ የምሰራ ሰው ሆኜ ሳለ የተወሰኑ ተቋማትን ለመጥቀም ሲባል ብቻ ኤርፖርት ላይ ካልተገዛ ይዞ ለመውጣት መከልከሉ ተገቢ አይደለም›› ሲሉ ይናገራሉ። በመሆኑም መንግሥት ቱሪስቱ ይዞ የመጣውን የውጭ ምንዛሬ እዚሁ ሀገር ውስጥ እንዲያስቀር ከተፈለገ ለጉብኝት በመጣበት አጋጣሚ ቡናውን ቀምሶ የሚገዛበት ሁኔታ ማመቻቸትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማበረታታት ይገባዋል ባይ ናቸው። ይህም ሲሆን የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ይነቃቃል የሚል እምነት አላቸው።

ድርጅቱን ከአባታቸው ተረክበው ሥራ ሲጀምሩ ከ70 ሺ ብር የማይበልጥ ካፒታል እንደነበረው የሚያስታውሱት አቶ ምኒልክ፤ የራሳቸውን ማምረቻ ሕንፃ ቃሊቲ ላይ ከመገንባታቸውም ባሻገር ካፒታላቸውንም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳደጋቸውን ይናገራሉ። በቀጣይ ድርጅታቸው የሚያመርታቸውን ማሽኖች በምስራቅ አፍሪካ ተደራሽ ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ። በተለይ ልክ እንደ ቡናው ሁሉ ኢትዮጵያን በቡና ማሽኖች በአፍሪካ መሪ የማድረግ ራዕይም እንዳላቸው ይጠቁማሉ። በተጨማሪም የተቆላ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስገባትም የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉም ስለመሆኑ ይገልፃሉ።

 ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You