የሊባኖሱ ልጅ . . .
አካባቢው ለም ነው። ሥፍራው ክረምት ከበጋ ያበቅላል። ገጠር ነውና አራሽ ጎልጓዩ ብዙ ነው። በተንጣለለው መስክ ከብቶች የሚያግዱ፣ ሮጠው የሚቦርቁ ሕፃናት አይጠፉም። ከፍ ያሉቱ ለወላጆች ይታዘዛሉ። እነሱ ሁሌም ውሎ ማምሻቸው ከሌሎች ይለያል። አቅም ጉልበታቸውን አይሰስቱም። ወዛቸውን አበርክተው ምርቃትን ይወስዳሉ።
በሊባኖስ ቀበሌ ይህን መሰሉ ሕይወት ብርቅ አይደለም። ሥፍራው ከደብረ ማርቆስ ከተማ በአጭር ርቀት የሚገኝ ገጠር ነው። በአካባቢው ለመኖር ሲባል መሥራት፣ ጉልበት ከፍሎ ማደር አይሸሹት ግዴታ ነው። ሁሉም በአቅሙ ሰርቶ በሚያድርበት መንደር ገበሬዎች ሥራ አይፈቱም፤ በሬ ጠምደው ሲያርሱ፣ ሲያዘምሩ ይውላሉ።
ትንሹ አለኸኝ በሊባኖስ መንደር ተወልዶ አድጓል። መልኩ የሚያሳሳ፣ ልጅነቱ የሚያጓጓ ብላቴና ነው። የቤቱ ትንሽ እሱ ነውና ሁሉም በስስት ያዩታል። ወላጆቹ አርሶ አዳሪ ገበሬዎች ናቸው። ቤታቸው የቆመው በግብርናው ከሚገኝ በረከት ነው። እነሱም እንደ ሀገሬው ከዓመት ዓመት የመሬታቸውን ፍሬ ይጠብቃሉ።
አለኸኝ ልጅነቱን ያሳለፈው እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ነው። ከብት እያገደ ከሜዳው ቦርቋል። በልጅነት ጨዋታ ስቆ አልቅሷል። ወድቆ ተነስቷል። ዕድሜው ከፍ ሲል ወላጆቹ ዕድል አልነፈጉትም። ቀለም ቆጥሮ፣ ፊደል እንዲለይ ወደ ትምህርት ቤት ላኩት። ትንሹ ልጅ የልቡ ሞላ፣ የሃሳቡ ደረሰ። እርሳስ ደብተር አስገዝቶ “ሀሁ∙∙∙ን” ለየ፤ ዕውቀት ገበየ።
አሁን አለኸኝ አስራ አንድ ዓመቱ ነው። ደስታን ከሀዘን፣ ክፉን ከደግ ለይቷል። ከፍ እያለ ሲሄድ ብዙ ማሰብ ያዘ። ነገ በትምህርቱ ማደግ፣ በዕውቀቱ መለወጥን ይሻል። በታሪክ እንደሚያውቃቸው አንዳንድ ምሁሮች ታዋቂ መሆን ፍላጎቱ ነው። ይህ እንዲሆን መሠረቱ ትምህርት መሆኑ ገብቶታል። ለዚህ ዓላማው ልዩ ትኩረት አለው። ልጅ ቢሆንም በትምህርቱ አይቀልድም። ሁሌም እየወደደው ይማራል፤ እየፈቀደው ከተማሪ ቤት ይውላል።
የእግር ነገር. . .
ውሎ አድሮ አለኸኝ አንድ እግሩ ማበጥ ያዘ። ነገ ‹‹ይጎድላል፣ ይሻለዋል›› ያሉ ወላጆች ቀን እያዩ ጠበቁ። ዕብጠቱ አልጎደለም። ይህ አጋጣሚ ለእሱ መሰል ታዳጊ ትርጉሙ ብዙ ነው። ባያመውም ለመማር ፈተና ሊሆንበት ይችላል። ከፍ ሲል ለትምህርት ከአካባቢው፣ ሰፈሩ ይርቃል። እንዲህ ከሆነ ችግር ነው።
ለእሱ እግሮቹ የልጅነት ኃይሉ ናቸው። ካሻው ይሮጥባቸዋል፣ ይዘልባቸዋል። መታመም ከያዘ ግን የልቡ አይደርስም፤ የፍላጎቱ አይሞላም። እንደዋዛ ቀናት ተቆጠሩ። አሁንም የአለኸኝ ቀኝ እግር ከእብጠቱ አልጎደለም። ሁኔታውን ያስተዋሉ አንዳንዶች ሃሳብ፣ አስተያየታቸው በዛ። ከነዚህ ብዙዎቹ ከራሳቸው ግምት ደረሱ። ውሎ አድሮ ግን ሚዛኑ ወደ ሕክምናው አደላ።
የሊባኖስ ጤና ጣቢያ አለኸኝን ተቀብሎ ተገቢውን ምርመራ አደረገ። የልጁ እግር አሁንም እንዳበጠ ነው። እንዲያም ሆኖ ህመም ይሉት ነገር የለውም። ሐኪሞቹ ጨነቃቸው። የሕክምና ምርመራው እንዳበቃ ይበጃል የተባለው መድኃኒትና መርፌ ታዘዘለት።
አለኸኝ የታዘዘለትን መርፌ ሳያቋርጥ እየተመላለሰ መወጋቱን ያዘ። መርፌውን በጀመረ ሰሞን እሱን ጨምሮ ብዙዎች መዳኑን አስበው ለውጡን ጠበቁ። ጉዳዩ እንደታሰበው አልሆነም። ይባስ ብሎ ዕብጠቱ ጎልቶ መታየት ጀመረ።
ሁኔታው ያሳሰባቸው ወላጆች የልጃቸውን እግር እየዳሰሱ ችግሩን ፈተሹ። እግሩ ከማበጥ አልፎ ውስጡ ጠንክሯል። ይህን ሲያውቁ መልሰው ከጤና ጣቢያው ወሰዱት። የጤና ባለሙያዎቹ ዳግም ሕመሙን መርምረው ከውሳኔ ደረሱ። ሕክምናው በጤና ጣቢያው አቅም የሚቻል አልሆነም። አለኸኝ ለተሻለ ሕክምና ወደ ደብረማርቆስ ሆስፒታል ተላከ።
ከሆስፒታሉ ሲደርስ ሕክምናው ቀጠለ። የላብራቶሪ ምርመራና ተጨማሪ እገዛዎችን አገኘ። እንደታሰበው ሆኖ በደርሶ መልስ ሕክምና ቤቱ አልተመለሰም። ምርመራው በሐኪሞች ዓይን ትኩረት አግኝቶ ተኝቶ እንዲታከም ተወሰነ።
አለኸኝ በሆስፒታሉ ለቀናት አልጋ ይዞ ታከመ። አሁንም እግሩ ከዕብጠቱ አልተፋታም። ዛሬም እንደተወጠረ እንዳስጨነቀው ነው። ሕክምናው በቀላሉ አላበቃም። በየቀኑ የሚጎበኙት ሐኪሞች በትኩረት አልጋውን ከበው ይወያዩበት ያዙ።
አንድ ቀን የሐኪሞቹ ውሳኔ አዲስ ሃሳብን አስከተለ። አለኸኝ አሁንም ለተሻለ ሕክምና ወደ ባህርዳር መሄድ እንዳለበት ተወሰነ። ጊዜ አልባከነም። የአለኸኝ ወላጆች ውለው ሳያድሩ ልጃቸውን ባህርዳር ሆስፒታል አደረሱት። ከሆስፒታሉ ሕክምናውን የጀመረው ታዳጊ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎለት አልጋ ይዞ መታከም ጀመረ።
ከቀናት በኋላ የታዳጊውን የሕመም ዓይነት የደረሱበት ሐኪሞች ውጤቱን ለእሱና ለወላጆቹ አሳወቁ። አለኸኝ እስከዛሬ በእግሩ ዕብጠት ሲቸገርበት የቆየው ጉዳይ ካንሰር መሆኑን አረጋግጠዋል። በወቅቱ አለኸኝን ጨምሮ መላው ቤተሰብ ስለካንሰር ምንነት አንዳች አያውቁም። የተባሉትን ሰምተው ቀጣዩን ውሳኔ ለማድመጥ ቃል ጠበቁ።
የሐኪሞች ቦርድ አሁንም ለተሻለና ለከፍተኛ ሕክምና አለኸኝ ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳለበት አስታውቋል። ይህ እውነት ከትንሽዋ ገጠር መንደር ወጥተው ለማያውቁት ቤተሰቦች ቀላል የሚባል አልሆነም።
የሊባኖስ እንግዶች
የአስራ አንድ ዓመቱ ልጅ አለኸኝ በእግሩ ላይ የተገኘበት ካንሰር አዲስ አበባ አድርሶታል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተጀመረው ምርመራ በአንድ ጊዜ የሚቋጭ አልሆነም። ልዩ ክትትል የሚያስፈልገው ሕመም በተለያዩ ቀጠሮዎች የሚያመላልሰው ነበር። የመጀመሪያውን ክትትል አጠናቆ ሀገሩ የተመለሰው ታዳጊ ከሁለት ሳምንት በኋላ አልጋ ይዞ መታከም ጀመረ።
የተጀመረለት የኬሞ ቴራፒ ሕክምና ቀላል ይሉት አልነበረም። ኬሞ ለካንሰር ሕሙማን የሚታዘዝ ሕክምና ነው። ሕክምናው ሲጀመር አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ለውጥ መኖሩ አይቀርም። ሰውነት ይጎዳል፣ ጸጉር ይረግፋል። ማቅለሽለሽ፣ ማስመለሱ፣ መበሳጨት መቆዘሙ ውስጥን ይጎዳል።
አሁን አለኸኝ በእነዚህ አይመቼ መንገዶች ሊያልፍ፣ ሊመላለስ ግድ ብሎታል። ባልጸና አካሉ፣ ባልበረታ ማንነቱ ሊቀበለው የጀመረው ሕይወት አንድም ለብርታት፣ ሌላም ለነገ ዓላማው ጽናት ሆኖታል። የጉዞ መስመሩ ሻካራው ቢበዛም ይቅር ብሎ አልተወውም። ሕክምናውን ተቀብሎ ግዴታውን ሊወጣ ራሱን አዘጋጀ።
በአጋጣሚ አዲስ አበባ የደረሰ እንግዳ ጉዳዩ ብዙ ነው። ሀገሩን ተላምዶ ማረፊያና ምግብ ማግኘት ቀላል አይደለም። ውጣውረዱ፣ ትራንስፖርቱ፣ ሰው መግባባቱ ይፈትናል። በተለይ ታማሚ ላለበት እንግዳ ነገሮች የዋዛ አይሆኑም። ጎዶሎን የሚሞላ፣ ሃሳብን የሚካፈል ወዳጅ ዘመድ ያስፈልጋል።
ቤት ለእንግዳ . . .
በአዲስ አበባ የአለኸኝ ወላጆች አንድ ሁለት ብለው የሚቆጥሩት ቤተሰብ የለም። ‹‹እከሌ›› የሚሉት ሁነኛ ዘመድን አያውቁም። ልጃቸውን ይዘው አዲስ አበባ የገቡት አባት የሰው ሀገር ሰው ናቸው። ከቀናት በአንዱ ግን ከአንድ ሰው ዘንድ ስልክ አስደውሉ።
ይህ ሰው አዲስ አበባ እንደሚኖር የተነገራቸው ዘመድ ነበር። ለሰውየው ችግራቸውን ዘርዝረው ማረፊያ እንደሚሹ ነገሩት። ታሪኩን የሰማው ሰው ከልቡ አዘነ። በዝምታ አልጨከነባቸውም። ገንዘብ መርዳት፣ ማገዝ ባይችል ማረፊያና ምግብ እንደማይነፍጋቸው ነግሮ ‹‹ቤት ለእንግዳ›› አላቸው።
አለኸኝና አባቱ ከሕክምና መልስ በቤቱ እያረፉ ጊዜያትን ቆጠሩ። ማረፊያና ምግብ በወጉ የተቸራቸው አባትና ልጅ ስድስት ወራትን በሕክምናው ቆዩ። ትንሹ አለኸኝ ውስጡ ከኖረው ድብቅ ዕጢ ይበልጥ ሕክምናው በአካል ፈተነው። የልጅነት አካሉ በኬሞቴራፒው ውጣ ውረድ ሲርድ፣ ሲሸነፍ ታወቀው። ይህ ቆይታ ከብዙ ክፉ ደግ አጋጣሚዎች አገናኘው። ከማይረሱ፣ አንዳንዴ ሲያስታውሷቸው ቶሎ ከማይፈዙ ድርጊቶች አመላለሰው።
ከቀናት በአንዱ . . .
ሁሌም ከኬሞ ሕክምና በኋላ አካል ይደክማል፤ የቀመሱት ምግብ፣ ፉት ያሉት ሁሉ ልውጣ እያለ ይፈትናል። ሽታ፣ ጠረን ያስጠላል። ሕክምናው ግድ ነውና ደርሶ ልተው፤ ላቋርጠው ማለት አይቻልም። ይህ እውነት በልጆች ላይ በሆነ ጊዜ ሕመም፣ መከራው በእጥፍ ነው።
አንድ ቀን አለኸኝ በኬሞ ቴራፒ ሕክምና ሆስፒታል ቆይቶ ወደቤት ሊመለስ የሰፈሩን አውቶቡስ መጠበቅ ያዘ። እንደ ሁልጊዜው በእጅጉ ደክሞታል። በእግሩ መሄድ አልቻለምና አውቶቡስ መጠበቅ ምርጫው ሆነ።
ቆይታ ከፈጀ ጥበቃ በኋላ የሚጠበቀው አውቶቡስ ከስፍራው ደረሰ። አየነው እየተንገዳገደ ወደ ውስጥ ለማለፍ የአቅሙን ሞከረ። ሰዎች ተጠቅጥቀዋል፤ መቀመጫዎቹ ሞልተዋል። ልጅ ነውና እሱን ለማስቀመጥ ያሰበው አልተገኘም። አለኸኝ የኬሞው ድካም እያዞረ፣ እያጥወለወለው ነው። በዚህ መሀል እግሩን ዘርግቶ ከተቀመጠ አንድ ሰው ጋር በአካል ተነካኩ።
ሰውየው ብስጭቱ አይሎ ሊመታው ተጋበዘ። አቅም ያጣው ብላቴና ሊመልስለት አልቻለም። ለማስረዳት አፉን ከማላወሱ ይባስ ብሎ ገፍትሮ ጣለው። አለኸኝ ሆድ ባሰው፤ ዕንባ አነቀው። አጋጣሚ ሆኖ ጉዳዩን በቅርበት ያስተዋለ ሌላ ሰው ከወደቀበት አንስቶ ‹‹አይዞህ›› ሲል አጽናናው። ከወንበር አስቀምጦም በወጉ ተንከባከበው።
በወቅቱ አለኸኝ በሆነው ሁሉ ከልቡ አዝኖ በራሱ አማሯል። የዛን ዕለትን አጋጣሚ ዛሬ ሲያስታውሰው ሆዱ ይጎሻል። በአንዳንድ ሰዎች ድርጊት ይከፋል። እንደ ሁለተኛው ዓይነት ሰው ደግ ልቦና ባላቸው መልካም ሰዎች ደግሞ ይጽናናል፤ ይበረታታል።
አለኸኝ ዕድሜው መጨመር ሲይዝ ራሱን ችሎ ሕክምናውን መከታተል ጀመረ። ሕክምናው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ በመሆኑ በየጊዜው ከጎጃም አዲስ አበባ መመላለስ ግድ ይለዋል። ቤተሰቦቹ እሱን ለማዳን ብዙ ደክመው አቅም ጉልበታቸውን፣ ገንዘብ ጊዜያቸውን ሰጥተውታል።
አንዳንዴ ወላጆቹ ስለልጃቸው ሕመም መልስ ባጡ ጊዜ ሁሉን ትቶት እንዲቀመጥ ይመክሩታል። ዓመታት በቆጠረው ሕክምና ተማረውም ይበሳጫሉ። ለእነሱ በመድኃኒት ቆይታ ጊዚያትን መግፋቱ ትርጉም የለሽ ነው። አንድ ቀን “ድኛለሁ” ብሎ እንዲያውጅ ይሻሉ። ይህ አለመሆኑ ውስጣቸውን አድክሞታል።
የልጃቸውን መጨረሻ የሚናፍቁት ወላጆች አሁን ላይ ሕክምናውን ሊረሱት እየፈለጉ ነው። አለኸኝ በምልልስ የሚፈጀውን ግዜ ከብክነት ቆጥረውታል። ከዚህ ይልቅ እንደ ልጅነቱ ውለታ እንዲመልስ፣ ጉልበት እንዲከፍል ይፈልጋሉ። እሱም ቢሆን ልፋት ድካማቸውን አይዘነጋም።
አለኸኝ ወላጆቹ ይህን የሚያስቡት ስለ ካንሰር ግንዛቤው ስለሌላቸው መሆኑን አሳምሮ ያወቃል። አሁን ወጣትነት ዕድሜ ላይ ነው። ትናንት ጤናውን ሊመልስ፣ ከመድኃኒቱ ለመገናኘት ሲል ያለፈበትን መንገድ አይዘነጋውም። ሕክምና ከጀመረ ወዲህ የሚሰማው ሕመም የለም። ለዚህም ፈጣሪውን ከልቡ ያመስግናል።
ቁርጥ ውሳኔ . . .
ዛሬ ሕመም ላይ ባይሆንም ክትትሉን ማቋረጥ አይሻም። ቀጠሮ ባለው ጊዜ ከጎጃም አዲስ አበባ እየመጣ ይታከማል። አለኸኝ ኬሞቴራፒ ከወሰደ ከአስር ዓመት በላይ ሆኖታል። ክትትሉ በቀሪ ሕክምናው ላይ ነው። አስተውሎ ላየው ገጽታው ያም ራል፣ አቋሙ ጥ ሩ ነው።
ሁሌም ይህን ለውጥ የሚያዩ ወላጆች ታዲያ ፍጹም የዳነ መስሏቸው የእጃቸውን ነፈጉት፤ ከኪሳቸው መክፈል ከልክለውም ‹‹ከእንግዲህ በቃን፤ አንችልም›› ሲሉ ድካማቸውን አሳዩት።
አለኸኝ በውሳኔያቸው አልተከፋም። ይህን ባወቀ ጊዜ ወደማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ደውሎ ጉዳዩን አስረዳቸው። ውስጡን ያደመጠው ማዕከል ሃሳቡን ተቀብሎ ለማገዝ አልዘገየም። ሕክምና በኖረው ጊዜ ሙሉ የትራንስፖርት ወጪውን ችሎ ማረፊያውን ሊሰጠው ቃል ገባለት።
አለኸኝ ምላሹን በምስጋና ተቀበለ። ቀጠሮ ባለው ጊዜ ትራንስፖርቱ ሞልቶሎት፣ ማረፊያው ተመቻችቶለት መመላለሱን ቀጠለ። ዛሬ ሃያ አንደኛ ዓመቱን የያዘው ወጣት ከዓላማው አልተናጠበም። በሕመም ሲወድቅ ሲነሳ የወጠነውን ትምህርት ቀጥሎ ዘጠነኛ ክፍል ደርሷል።
አሁን አለኸኝ ፍጹም ጤነኛ ወጣት ነው። በጠዋቱ የተደረሰበትን የካንሰር ሕመም አሸንፎ በድል መራመድ ይዟል። ዛሬ ከፊቱ ብሩህ ተስፋ ይነበባል። ስለነገ የሰነቀው ደግሞ የእሱንና መሰሎቹን ሕይወት የሚታደግ ነው። ነገን ዶክተር ሆኖ ወገኖቹን ማከም፣ ሕመምን መፈወስ ህልሙ ነው።
ይህን ለመወሰን ምክንያቱ የራሱ ሕይወትና ያለፈባቸው ፈታኝ መንገዶች ናቸው። አለኸኝ ባሳለፈው የሕክምና ሂደት በርካቶች በሕመም ሲሰቃዩ፣ ለእንግልትም ሲደረጉ አስተውሏል። ለዚህ መሰል አጋጣሚ እማኝ የሆነው ወጣት ይህን ታሪክ ለመለወጥ በሕክምና ሙያ ማሸነፍ ምኞቱ ነው።
ዛሬን . . .
አለኸኝን ያገኘሁት በማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ግቢ ውስጥ ነበር። ዛሬን በሥፍራው የተገኘበት በሕክምናው ቀጠሮ ምክንያት ነው። ለቤቱ ቤተኛ የሆነው አለኸኝ አዲስ አበባ መምጣት በፈለገ ጊዜ ሶሳይቲው ከጎኑ ለመሆን ተባባሪው ነው። ለመንገዱ የትራንስፖርት ገንዘብ፣ ለማረፊያው ቤትና መኝታ ነፍጎት አያውቅም።
አለኸኝ ከሕክምናው ቆይታ በኋላ ቤተሰቦቹን በእርሻ ያግዛል። እንደ ልጅነቱ ዝቅ ብሎ ይታዘዛል። እነሱ ዛሬም ድረስ የሚወስደው የምልልስ ሕክምና ተመችቷቸው አያውቅም። ሁሉን ትቶ ቢቀመጥ፣ ከጎናቸው ሆኖ የልባቸውን ቢሞላ ይወዳሉ።
እርሻና ጉልጓሉ በኖረ ጊዜ የአለኸኝ ጉልበት የሚፈለገው እንደ ሌሎች ሰዎች ነው። ቢያመው፣ ቢደክመው እንዲያርፍ አይፈቅዱለትም። እሱን ያመዋል፣ ይደክመዋል የሚል አሳቢም ከጎኑ የለም። ቤተሰቦቹ እንዲህ በማድረጋቸው ተቀይሞ አያውቅም። በቻለው አቅም ሁሉን ሊያስረዳ፣ ሊያሳምናቸው ይሞክራል።
አለኸኝ አለማወቅ በፈጠረው የግንዛቤ ክፍተት ያለ አጋርና ደጋፊ ራሱን እያሳከመ እዚህ ደርሷል። ከተወለደባት ትንሽዋ የሊባኖስ ቀበሌ እንደ ባህር ከሰፋው አዲስ አበባ ድረስ ስለሕይወቱ ብዙ ከፍሏል። ነገ ግን ለእሱ ብሩህና ደማቅ ነው። ለመከራዎች እጅ አይሰጥም፤ ለክፉ አጋጣሚዎች አይሸነፍም። ጠንካራውና ብርቱ ወጣት አለኸኝ ቢተው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም