ስንሻው የቤቱን በር ከፍቶ ሲገባ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት አለፍ ብሎ ነበር፡፡ ከሚሰራበት ቦታ በጊዜ ቢወጣም ወደ ቤቱ የሚገባው ግን አረፋፍዶ ነው። መብራት ሳያበራ ሄዶ አልጋው ላይ ዘፍ አለ። ጆሮዎቹን ወደ ውጪ ወረወራቸው ከዝምታ በቀር ምንም አላዳመጠም። ትናንትና የመንደሩ ሰዎች ሰፈሩን ይልቀቅልን ሲሉ የቀበሌው አስተዳዳሪ ጋር ሄደው ነበር። በእሱ ያልተማረረ አንድም ሰው ሰፈሩ ውስጥ የለም። ለምን ካላችሁኝ እንዲህ እላችኋለው ∙ ∙ ∙ ስንሻው ውሸታም ነው ∙ ∙ ∙ ከውሸቱ በላይ ብድር በመጠየቅ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በዚህ መንታ ድርጊቱ የሰፈሩ ሰው ጠላው፡፡ “ከሀገር ይውጣልን” ሲሉም አመጹበት። ከመንደሩ ሰው ለመሸሽ ሲልም አምሽቶ ወደ ቤት መግባትን ልማድ አደረገው፡፡
ስንሻው የሀጢያት ጠቢብ ነው ∙ ∙ ∙ እውቀቱን ለእኩይ ነገር የተጠቀመ አንድ ሰው ቢኖር ስንሻው ብቻ ነው፡፡ ከአንድ ሰው የሆነ ነገር ከፈለገ መጀመሪያ ያን ሰው በማሞገስና በማድነቅ ነው የሚጀምረው፡፡ ሰፈሩ ውስጥ የተበደራቸውን ሰዎች ሁሉ በአድናቆትና በሙገሳ ጀምሮ ኪሳቸውን ያራቆታቸው ናቸው፡፡ እሱ ሲናገርና ቅዱስ ጳውሎስ ሲሰብክ አንድ ነው፡፡ አፉ የጅብ ጥላ ነው ∙ ∙ ∙ አፍዝ፣ አደንግዝ፡፡ ብድር ወስዶ ከከለከላቸው የመንደሩ ሰዎች መካከል እማሆይ ምንትዋብ አንዷ ናቸው፡፡ ደጀ ሰላም ድረስ ሄዶ ነበር “ነገ እመልሳለሁ፤ አዛኝቷ ምስክር ትሁነኝ” ብሎ የተቀበላቸው፡፡ አንድም ቀን መልሶላቸው አያውቅም።
እሳቸውም አንድም ቀን ከልክለውት አያውቁም፡፡ ተበድሮ ካስቀረባቸው ሰዎች መካከል እማማ ባንቺ ይርጉም አንዷ ናቸው። ሽሮና በርበሬ ወደሚሸጡበት የጉልት ገበያ ይሄድና “እናት አለሜ” ይላቸዋል ከአዳፋ ሻሻቸው ያመለጠ ነጭ ሽበታቸውን ወደ ማደሪያው እያጎረ፡፡ ከዛም አሳዛኝ አይኑን በእርጅና የሞጨሞጨ አይናቸው ላይ ያስለመልመዋል፡፡ ያኔ ወላድ ሆዳቸው ቦጭ … ቦጭ ይላል፡፡ ለምን እንደሚመጣ እያወቁም “ምነው∙ ∙ ∙ ምን እግር ጣለህ ይሉታል ∙ ∙ ∙፡፡ እንደ ሻሻቸው ያደፈ አሮጌ ጃንጥላቸውን ከጸሀዩ ሊከልሉት ወደ እሱ እያዩ፡፡
“ድሀ ምን ማረፊያ አለው ∙ ∙ ∙ ይሄው እባክናለሁ።”
“አይዞህ! ሁሉም ያልፋል፤ መበርታት ነው” ይሉታል እውነት፣ እምነት፣ ደግነት በሚያውቁ አዛውንት አይናቸው እያስተዋሉት፡፡ ‹እርሶ እኮ ገነቴ ኖት፤ እርሶ ባይኖሩ ኖሮ ውሻም በጨው አይቀምሰኝ ነበር፡፡ ሳይደግስ አይጣላ፣ እርሶን ጥሎልኛል› ሲል ወደ ሰማይ ይመለከታል። ቀጥሎም ‹እንዳው ∙ ∙ ∙ ነገ የምመልሰው ጥቂት ገንዘብ ካሎት› ይላቸዋል ፊቱን፣ ነፍሱን አሳዝኖ፣ ባዘነ ∙ ∙ ∙ በተራቆተ ባዶ ሰውነት፡፡
መቀነታቸውን ፈትተው “እንካ፣ ይቺ ናት ያለችኝ . . ዛሬ ምንም አልሸጥኩም፡፡” ይሉታል ከእሱ ባልተናነሰ እዝን ውስጥ ወድቀው፡፡ በመጣ ቁጥር እንደሰጡት ነው፡፡ ካላቸው ከመቀነታቸው ላይ ፈትተው፣ ከሌላቸው ደግሞ አጠገባቸው ከምትሸጠው ወጣት ሴት ላይ ተበድረው ይሰጡታል፡፡ እማማ ባንቺ ይርጉ ነገን አያውቁትም ∙ ∙ ∙፤ እርጅና ነው መሰለኝ ነገ መቼ እንደሆነ ዘንግተውታል፡፡ ስንሻውም ይሄን ደካማ ጎናቸውን ሰበብ አድርጎ ሁሌ ማታ ማታ “ነገ እመልሳለሁ” እያለ ገንዘብ ይወስድባቸዋል።
እሳቸው ነገን አያውቁትም ∙ ∙ ∙ አጠገባቸው መጥቶ ገንዘብ ሲላቸው ትናንት የወሰደውን መልሶ የሚጠይቃቸው ነው የሚመስላቸው፡፡ ብዙ ቀን “ነገ እመልሳለሁ” ብሎ የሸጡትን ሁሉ ወስዶባቸው ያውቃል፡፡ ብዙ ቀን ነገን ስለማያውቁ በእርጅናቸው ተጫውቶ ያውቃል። ብዙ ቀን በእውነታቸው ላይ ተረማምዶ ዋሽቷቸው ያውቃል፡፡ እማማ ባንቺ ይርጉ ቀን ሙሉ የሸጡትን ለእሱ አበድረው ቤታቸው ባዶ እጃቸውን ገብተው ያውቃሉ፡፡ “ነገ እመልሳለሁ፤ አበድሩኝ” ብለው ጎረቤት ሄደው ያውቃሉ፡፡
አሁንም ሰጡት ∙ ∙ ∙ በእውነት፣ በእምነት፡፡ ሰላላ እጃቸውን ወደ መቀነታቸው ሲሰዱ የተረፈ አንዳችም ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ ከመቀነታቸው ላይ ቀና ሲሉ ስንሻውን ካጠገባቸው አጡት፡፡ በርቀት እሱን የሚመስል ሰው አዩ፡፡ በምን ፍጥነት ከዚህ እስከዛ እንደሄደ አላውቅ አሉ፡፡ ሁሌ ሳያዩት ነው የሚሄደው፣ ሁሌ እንዲህ እንደ አሁኑ ገንዘብ ሊሰጡት የፈቱትን መቀነታቸውን ለማጥበቅ ጎንበስ ባሉበት ነው ትቷቸው የሚሄደው፡፡ ሲመጣ እንጂ ሲሄድ አይተውት አያውቁም፡፡ ሲመጣ፣ አጠገባቸው ሲቆም መላዕክ ሆኖ ነው፣ ሲሄድ ግን እንደ ሰይጣን ነው .. ሳያዩት፣ ሳይሰሙት ብን ብሎ። ደግሞ አንድም ቀን አመስግኗቸው አያውቅም፡፡
የስንሻውን እግር ተከትሎ አንድ ችግረኛ ‹ስለ ለማርያም ∙ ∙ ∙› ሲል ተጠጋቸው፡፡ ምን ይስጡት? መቀነታቸው ባዶ ነው፡፡ ሻሼ ላይ ካለ ብለው አዳፋ ሻሻቸውን ፈተሹ፤ ለምስኪኑ የሚሆን አንዳች አላገኙም። ወደ ድሀው አዩ ∙ ∙ ∙ እጁን ዘርግቶ እየጠበቃቸው ነው። ከበርበሬው አራት ማንኪያ፣ ከሽሮው አራት ማንኪያ አድርገው በፌስታል ጠቅልለው እንካ አሉት፡፡
“ይቅርታ እናቴ! የምገዛበት ምንም ፍራንክ የለኝም ∙ ∙ ∙ ልለምን ነው ፊትዎ የቆምኩት ∙ ∙ ∙ በልገሳ የሚሰጡኝ ከሆነ ልቀበሎት” አፐለ ∙ ∙ ∙፤ ስጦታ መሆኑን ባለማመን፡፡ ‹እጄ ላይ የምሰጥህ ሳጣ ነው ሽሮና በርበሬ የሰጠሁህ። የሚያስከፋህ ከሆነ ትንሽ ቆይተህ ናና በገንዘብ እቀይርልሀለው› አሉት፡፡
እጃቸውን ስሞ ተቀበላቸው፡፡ ከእናት አንደበት ያን ያክል ትህትና ሰምቶ አያውቅም፡፡ በዘመኑ ለምኖ ካገኘው ሁሉ ያን እለት በለጠበት። በዘመኑ ከተቀበለው ሁሉ በዛን ቀን ከነዛ አሮጊት የተቀበለው ላቀበት፡፡ ሰው ለካ እያለው ከሚሰጥ ከሌለው ላይ ቢሰጥ ይበልጥ ኖሯል…። ብዙዎች ካላቸው ላይ ነው የሚሰጡት ካላቸው ላይ ካልሆነ ከሌላቸው ላይ ተቀብሎ አያውቅም፡፡ ያላቸው ካልሆኑ የሌላቸው ሰጥተውት አያውቁም።
ሰው ገንዘብ ኪሱ ከሌለ የሚሰጠው ያለ አይመስለውም። እኛ ኪሳችንን ብቻ ስለምንፈትሽ እንጂ ልባችንን መፈተሸ ብንችል የምንሰጠው ብዙ ነገር ነበር፡፡ እኚህ እናትም ያስተማሩት ይሄን ነው፡፡ መቀነታቸው ሲነጥፍ ወደ አዳፋ ሻሻቸው ማተሩ። በዛም አንዳች ሲያጡ እንሆ ካላቸው ላይ አካፈሉት። እሳቸው ለእሱ መስጠት ከሰሰቱ ባለጸጋና ከበርቴ መሀል ከመቀነቷ ላይ ፈትታ ያላትን አንድ ሳንቲም ለጌታ እንደሰጠችው ድሀ ሴት ናቸው፡፡
እማማ ባንቺ ይርጉ “ማርያም” ተብለው አጥተው አያውቁም፡፡ ደሀ ፊታቸው ቆሞ “የለኝም” ብለው አያውቁም፡፡ መስጠት የማይሰለቸው እጅ፣ ማዘን የማይሰለቸው ልብ፣ ጸጋና በረከት የተሞላ ሴትነት። ሁሉን የሚያውቁት ቤት ሲደርሱ ነው …። ሌማቱ ባዶ እንደሆነ፣ ቦሀቃው ሊጥ እንደሌለው የሚያውቁት ማታ ነው . . ቤት ሲደርሱ ∙ ∙ ∙ ግን ሁሉ እንዳለው ባለጸጋ ናቸው፡፡
……….
ያን ቀን ስንሻው ወደ ቤቱ አልተመለሰም ∙ ∙ ∙ ከእማማ ባንቺ ይርጉ እንደ ተለየ ከየት መጣ የማይባል መኪና አግኝቶ ገደለው፡፡ ደባና ፍርድ፡፡
ጠዋት ጉልት ሲደርሱ አጠገባቸው ካለችው ወጣት በመኪና አደጋ ህይወቱ ማለፉን ነገረቻቸው። ግራ የሚያጋባ ወሬ ሰሙ ∙ ∙ ∙ ከእርሶ ላይ እየመጣ ገንዘብ የሚበደረው፤ ተበድሮ የሄደው።
“ማነው እርሱ ∙ ∙ ∙?”
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 10/2016