የጎዳና ተዳዳሪዎችን በዘላቂነት የማቋቋም በጎ ተግባር

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከሚፈጥሯቸው ማኅበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የጎዳና ተዳዳሪነት ነው፡፡ ይህ ችግር በኢትዮጵያም በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታይ ማኅበራዊ ቀውስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በ11 ዋና ዋና ከተሞች ከ89ሺ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ ከ55ሺ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ ከአራት ዓመታት በፊት ይፋ የተደረገ የጥናት መረጃ ያሳያል፡፡

በችግሩ ምክንያት የሚፈጠሩ ቀውሶች ቤተሰብን፣ ሕብረተሰብንና ሀገርን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ናቸው፡፡ ይህ አደገኛ ችግር ያሳሰባቸው በጎ አሳቢ ዜጎች፣ ችግሩ ከዚህ የበለጠ ቀውስ እንዳያስከትል በየጊዜው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ቢስተዋልም፣ ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ግን ስር ነቀል ለውጦችን ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡ የ‹‹ቤተ-ሳይዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በቀለ በ1998 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ የጀመሩት ተግባርም ይህን ችግር የማቃለል ጥረት ማሳያ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በወቅቱ ሐዋሳ ገብርኤል አካባቢ ለጎዳና ሕይወት የተጋለጡ ሁለት ልጆችን ይመለከታሉ፤ በቻሉት አቅም ልጆቹን ለመርዳትም ይወስናሉ፡፡

‹‹ስራው የተጀመረው ሁለት የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን በመርዳት ነበር፡፡ ሕፃናቱ ወላጆች ቢኖራቸውም ለጎዳና ሕይወት የተዳረጉ ናቸው፡፡ በወቅቱ ልጆቹን እየጎበኘሁ አንዳንድ ድጋፎችን ማድረግ ስጀምር ሌሎች ልጆችም ተጨመሩ፡፡ ምግብን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን እናደርግላቸው ነበር፡፡ ሌሎች በጎ ፈቃደኞችም ለልጆቹ እገዛ ያደርጉ ነበር፡፡ በሐምሌ ወር 1999 ዓ.ም ድጋፍ የሚደረግላቸው ልጆች ቁጥር 22 ደረሰ፤ ሕፃናቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው በሚኖሩበት ስፍራ ላይ ነበር። ስለመልካም ስነ ምግባር ምንነት እናስተምራቸውም ነበር›› በማለት ስለምግባረ ሰናይ ተግባራቸው አጀማመር ይገልጻሉ፡፡ በመቀጠልም ከበጎ ፈቃደኞች በተገኘ ድጋፍ ሕፃናቱ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡

ወይዘሮ ዓለምፀሐይ እንደሚሉት፣ ለሕፃናቱ ከሚደረጉት ድጋፎች በተጨማሪ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ቤተሰቦቻቸውም ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር። በነሐሴ 1999 ዓ.ም ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፈቃድ በማውጣት ስራቸውን አጠናክረው ገፉበት፡፡ ድጋፍ የሚደረግላቸው 22 ሕፃናትም ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በመቀጠልም ድርጅቱ ስራውን ሰፋ አድርጎ ለመስራት በማሰብ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መስራት ጀመረ፡፡

‹‹ከትልልቅ መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች ጋር በትብብር የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ተቋማት ከፌዴራል መንግሥት የስራ ፈቃድ ማውጣት ይኖርባቸዋል ስለተባለ፣ በ2004 ዓ.ም ከሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ መጥተን ‹ቤተ-ሳይዳ የሕፃናትና ወጣቶች መርጃ ማኅበር› በሚል ስም ከፌዴራል መንግሥት የበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ ፈቃድ አወጣን›› የሚሉት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ፣ ከኤጀንሲው ያገኙት እውቅና ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድጅቶች ጋር በትብብር እንዲሰሩ ትልቅ እገዛ እንዳደረገላቸው ይገልፃሉ፡፡

ድርጅቱ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሚያደርገው ትብብር ቀጥሎ፣ ትብብሩ ከእነዚህ ድርጅቶች መጠነኛ የገንዘብ ድጋፎችን እንዲያገኝ አስቻለው፡፡ በዚህም በሐዋሳ ከተማ ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጡ ሴቶችና ሕፃናት ልዩ ልዩ ድጋፎችን ማድረግ ችሏል፡፡ ‹‹ቤተ-ሳይዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በአዲስ አበባ፣ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ የሕፃናትና ሴቶች ማቆያ ማዕከል አለው፡፡ ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ወደ ማዕከሉ ገብተው ልዩ ልዩ ድጋፎች ይደረግላቸዋል፡፡ ድርጅቱ ቀደም ሲል ድጋፍ የሚያደርገው ድጋፍ የሚደረግላቸው አካላት ወዳሉበት ቦታ በመሄድ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድጋፍ ፈላጊዎቹ ወደ ድርጅቱ ቢሮ ሄደው አንዳንድ ድጋፎችን ያገኙም ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ድጋፍ የሚደረገው ደግሞ በመጠለያ ውስጥ ነው፡፡

‹‹ለጎዳና የተጋለጡ ሴቶችና ሕፃናት ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ወደሚገኝ መጠለያ (ማቆያ) ገብተው ለአራት ወራት ያህል ድጋፍ ሲደረግላቸውና ስልጠናዎችን ሲወስዱ ቆይተው፣ ወደመጡባቸው አካባቢዎች ተመልሰዋል፡፡ በዚያም ቤት ተከራይተንላቸው ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉና እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡ አሁን ደግሞ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 29 ሴት ሕፃናትን ወደ መጠለያ አስገብተን ድጋፍ እያደረግንላቸው እንገኛለን፡፡ መጠለያ ውስጥ በሚቆዩባቸው ወራት የተለያዩ ድጋፎችን እናደርግላቸዋለን፤ ሙያዎችን ይማራሉ፡፡ ስለጎዳና ሕይወት አስከፊነት እና ስለገቢ ማስገኛ ስራዎች ግንዛቤ ካስጨበጥናቸው በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ እንመልሳቸዋለን፡፡ ሕፃናቱም ወደ ኅብረተሰቡ ተመልሰው ትምህርት እንዲጀምሩ እናደርጋለን›› በማለት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በመጠለያው ውስጥ ስለሚደረገው ድጋፍም ያብራራሉ፡፡

‹‹ቤተ-ሳይዳ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሕፃናት የምግብ፣ የትምህርትና የጤና ድጋፎችን ከማድረግ በተጨማሪ በመልካም ስነምግባር፣ በሴቶች ጥቃት፣ በጎዳና ሕይወት፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ በገቢ ማስገኛና በሌሎች ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችንና ስልጠናዎችንም ይሰጣል፡፡ ድርጅቱ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባገኘው ድጋፍ ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ በግጭቶች ምክንያት ለተፈናቀሉ 200 ሴቶችና 250 ሕፃናት የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ለ30 ሴቶች የገቢ ማስገኛ ስልጠናዎችን በመስጠት ፍየልና በግ ገዝቶ ሰጥቷል፡፡ ይህም ሴቶቹ ከዕለታዊ ድጋፍ ጠባቂነት ወጥተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙና የኑሮ መሰረት እንዲኖራቸው እገዛ ያደርጋል፡፡

‹‹ቤተ-ሳይዳ››የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚያከናውነው ፕሮጀክትም ሴቶችና ሕፃናት ከጎዳና ሕይወት እንዲላቀቁ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ዘንድሮ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የምንሰራው ስራ አለ፡፡ ይህም ለጎዳና ሕይወት የተጋለጡ ሴቶችንና ሕፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ከመንግሥት አካላት ጋር በትብብር መስራት ስራውን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል›› ይላሉ፡፡ ‹‹ቤተ-ሳይዳ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት እስካሁን ድረስ ከሁለት ሺ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የስነ ምግባር ትምህርት የተሰጣቸውና ቋሚ ባልሆነ መልኩ አልፎ አልፎ ድጋፍ ያገኙ ወገኖች ደግሞ ከ22ሺ በላይ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ለስራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኘው ከበጎ አድራጊዎች ከሚሰበሰቡ ድጋፎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ከሚደረጉ ትብብሮች እንዲሁም ከፕሮጀክቶች ከሚገኙ ድጋፎች ነው፡፡

‹‹ቤተ-ሳይዳ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ያከናወናቸው ተግባራት የበርካቶችን ሕይወት የለወጡና ለማኅበራዊ መረጋጋትም ትልቅ አዎንታዊ አስተዋፅዖዎችን ያበረከቱ እንደሆኑ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ድርጅቱ እገዛ ያደረገላቸው ሕፃናት ተምረው ስራ ይዘዋል፡፡ አንዳንዶቹ በድርጅቱ ውስጥ ሶሻል ወርከርና የሂሳብ ሰራተኛ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በድርጅቱ ድጋፍ አድገውና ተምረው ዛሬ በሐዋሳ ከተማ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡ ‹ቤተ-ሳይዳ› ድጋፍ ያደረገላቸው ልጆች አዲስ አበባ ላይም የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ ራሳቸውን እየቻሉ ነው፡፡ ድጋፍ ያደረግንላቸው ሴቶችም በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ልብስ በመስፋት፣ በንግድ ስራ ውጤታማ የሆኑ ሴቶች አሉ፡፡ ከሐዋሳ ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ፍየልና በግ እንዲያረቡ የሰጠናቸው ሴቶች በርትተው ሰርተው ጥሩ ውጤቶችን አሳይተውናል›› በማለት የድርጅቱ ምግባረ ሰናይ ተግባራት ስላስገኟቸው ውጤቶች ያስረዳሉ፡፡

‹‹ስራውን የጀመርነው ሰው እንዲያውቅልንና እንዲያወራልን ሳይሆን የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ብቻ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ፣ ይህ እምነታቸው ለብዙ ዓመታት ከመንግሥት ተቋማት ጋር ጠንካራ የሚባል ትስስር ሳይፈጥሩ እንዲቆዩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለብዙ ዓመታት መንግሥት ሳይደግፈን በሐዋሳ ከተማ በቤት ለቤት አገልግሎት ብዙ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ መንግሥት ያወቀን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። ራሳችንን አለማስተዋወቃችን ገንዘብ ለማግኘትም ሆነ ከሌሎች ተቋማት ጋር ትብብር ለመፍጠር ሳያስችለን ቆይቷል፡፡ አሁን ከሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ተቋማት ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡ የመንግሥት ተቋማት ጥሩ ድጋፍ ያደርጋሉ›› በማለት ከመንግሥት አካላት ጋር በትብብር መስራት ስራውን አስፋቶና የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ስራውን ሲጀምሩ በሐዋሳ የራሳቸውን መኖሪያ ግቢ ለበጎ አድራጎት ስራው ቢሮ አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹የሰው መብላት፣ መጠጣትና መደሰት ለእኔ ትልቁ ደስታዬ ነው፡፡ ባለቤቴም በጣም ጥሩ ሰው ስለሆነ ለስራው መሳካት እገዛ ያደርግ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ያለው የቤት ኪራይ ግን በጣም ውድ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ያለው ምልከታም አወንታዊ ባለመሆኑ ቤት ማግኘት ትልቅ ፈተና ነው›› በማለት የቤት ኪራይ በስራቸው ላይ መሰናክል የፈጠረ ፈተና እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ዳዊት ዳና በ‹‹ቤተ-ሳይዳ›› ድጋፍ ተምሮ ሹፌርና የኤሌክትሪክ ጥገና ባለሙያ ለመሆን የበቃ ወጣት ነው፡፡ ‹‹በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነበርን። የምንመገበውና የምንለብሰው አልነበረንም። ወይዘሮ ዓለምፀሐይ አግኝታን ድጋፍ ስታደርግልን የሕይወታችን አቅጣጫ ተቀየረ፡፡ የትምህርት ቁሳቁስ፣ አልባሳትና ሌሎች ድጋፎች ይደረጉልን ነበር፡፡ ትምህርታችንን የተማርነው በ‹ቤተ-ሳይዳ› ድጋፍ ነው። ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ‹የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሁሉ ጠይቁኝ› ትለን ነበር፤ እንደልጆቿ ትንከባከበናለች። የ‹ቤተ-ሳይዳ›ን ውለታ ስናገር ስሜቴን መቆጣጠር ይከብደኛል፤ ውለታቸውን እንዴት አድርገን እንደምንከፍል አላውቅም›› በማለት ስለቀድሞ ሕይወቱና ‹‹ቤተ-ሳይዳ›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ስላደረገለት ድጋፍ ያስታውሳል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም የ‹‹ቤተ-ሳይዳ›› ድጋፍ ያልተለየው ዳዊት፣ በሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአውቶ ኤሌክትሪክ የትምህርት መስክ ተመርቆ በሹፌርነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ እናቱንና ታናሽ ወንድሙን እያገዘ ይገኛል፡፡ ከእርሱ ጋር በ‹‹ቤተ- ሳይዳ›› ድጋፍ ይደረግላቸው የነበሩ ጓደኞቹም በተለያዩ ሙያዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እየደገፉ እንደሚገኝ ይገልፃል፡፡

ቸርነት ዓለማየሁ ሌላው የ‹‹ቤተ-ሳይዳ›› ፍሬ ነው፡ ወይዘሮ ዓለምፀሐይን ከማወቁ በፊት የጎዳና ተዳዳሪ እንደነበር የሚናገረው ቸርነት፣ ምግብና አልባሳትን ጨምሮ ሁሉንም ድጋፍ የሚያደርግላቸው ‹‹ቤተ- ሳይዳ›› እንደነበር ይገልፃል፡፡ ቸርነት ትምህርትን ‹ሀ› ብሎ የጀመረውና እስከ ሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ድረስ ዘልቆ ለምርቃት የበቃው በ‹‹ቤተ-ሳይዳ›› ድጋፍ ነው፡፡ ‹‹ምን እንደምሆን አላውቅም ነበር፡፡ ወላጆቼ ቢወልዱኝም ለዚህ ደረጃ ያበቃችኝ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ናት፡፡ ‹ቤተ-ሳይዳ› ለእኛ ብዙ ዋጋ ከፍሏል›› ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሹፌርነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ቸርነት፣ ትዳር መስርቶ የአንዲት ልጅ አባት ለመሆን በቅቷል፡፡

‹‹ቤተ-ሳይዳ የበጎ አድራጎት ማኅበር ሰዎች፣ በተለይ ወጣቶች፣ ድጋፍ ተደርጎላቸው ስራ እንዲሰሩ ማድረግ እንጂ ተረጂ ሆነው እንዲቀጥሉ አይፈልግም›› የሚሉት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ፣ ድርጅቱ የወደፊት እቅድም በዚሁ መርህ የተቃኘ እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹መንግሥት ቦታ መስጠትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ካደረገልን፣ ለጎዳና ሕይወት የተጋለጡ ሕፃናት በዘላቂነት እንዲቋቋሙና ከችግሩ እንዲወጡ የመስራት ትልቅ እቅድ አለን፡፡ ቦታ ከተሰጠን ብዙ ልጆችን መርዳት እንችላለን፡፡ ብዙ ሴቶች በየመንገዱ ወድቀዋል፤ እነዚህ ሴቶች ትንሽ ድጋፍ ከተደረገላቸው ግን ራሳቸውን መቀየርና ወደተሻለ የሕይወት መስመር መግባት ይችላሉ፡፡ ዋናው ዓላማችንና ፍላጎታችን የተቸገሩ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም ነው›› በማለት ስለድርጅቱ እቅድ ይገልፃሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ጥር 10/2016

Recommended For You